ለአገልግሎታችን የሚጠቅም ዓምድ
1. “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት” የተባለው ዓምድ ምን ሁለት ዓላማዎች አሉት?
1 ለሕዝብ የሚሰራጨው የመጠበቂያ ግንብ እትም “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት” የሚል ዓምድ ይዞ የሚወጣበት ጊዜ አለ። ይህ ዓምድ ሁለት ዓላማዎች አሉት፦ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ማራኪ በሆነ መንገድ ማቅረብ ሲሆን ሌላው ደግሞ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮችን ጥሩ አድርገን ማብራራት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እኛን ማሠልጠን ነው። (1 ጴጥ. 3:15) ታዲያ ይህን ዓምድ በጥሩ ሁኔታ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
2. ይህን ዓምድ በአገልግሎታችን ላይ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
2 በአገልግሎት ተጠቀሙበት፦ ይህ ዓምድ የወጣባቸውን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች የተወሰነ ቅጂ ማስቀመጥ ትችላላችሁ። ከዚያም ከቤት ወደ ቤት ያገኛችሁት ሰው ወይም ፍላጎት ያለው ግለሰብ አሊያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ በዚህ ዓምድ ውስጥ የተጠቀሰ ጥያቄ ሲጠይቃችሁ አሊያም የተቃውሞ ሐሳብ ሲያነሳ መጽሔቱን በመስጠት በዚያ ላይ ለመወያየት ግብዣ ልታቀርቡለት ትችላላችሁ። ይህ ዓምድ የወጣበት መጽሔት በእጃችሁ ከሌለ jw.org ከተባለው ድረ ገጽ ላይ ማውረድ ትችላላችሁ።
3. በዚህ ዓምድ ሥር የሚወጡትን ርዕሶች ከምናነጋግረው ሰው ጋር መወያየት የምንችለው እንዴት ነው?
3 በዚህ ዓምድ ሥር ያሉትን ርዕሶችን እንዴት ልንወያይባቸው እንችላለን? አንዳንዶች እነሱ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ሰው የተናገረውን ሐሳብ ሲያነብቡ የሚያወያዩት ግለሰብ ደግሞ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ሰው የሚናገረውን ሐሳብ ጮክ ብሎ እንዲያነብብ ያደርጋሉ። ሌሎች ሰዎች ያደረጉትን ጭውውት ተጠቅሞ መወያየቱ ውጤታማ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ውይይት ግለሰቡ እሱ እየተናገረ እንደሆነ ስለማያስብ ሳይሸማቀቅ የምናስተምረውን ነገር እንዲመረምር ሊያነሳሳው ይችላል።—ዘዳ. 32:2
4. እነዚህን ርዕሶች ራሳችንን ለማሠልጠን ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት ነው?
4 ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን አሠልጥኑ፦ እነዚህን ርዕሶች ስታነብቡ የሚጠቀሱትን ጥቅሶች፣ ምሳሌዎች እንዲሁም የማሳመኛ መንገዶች አስተውሉ። እንዲሁም በምን ዓይነት ስሜት እንደቀረበ ልብ በሉ። ከዚያም በአገልግሎታችሁ ላይ ተመሳሳይ አቀራረብ ለመጠቀም ሞክሩ። (ምሳሌ 1:5፤ 9:9) አንዲት እህት “እነዚህን ርዕሶች ማንበብ ምንጊዜም ምን መልስ መስጠት እንዳለበት ከሚያውቅ ጎበዝ አቅኚ ትምህርት እንደመቅሰም ነው” ብላለች።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ለአገልግሎት ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
5 እነዚህን በድራማ መልክ የቀረቡ ውይይቶች ጥናቶቻችንን ለአገልግሎት ለማሠልጠን ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ለጥናታችሁ የአስፋፊውን ሚና በመስጠት ርዕሱን አብራችሁ አንብቡ። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እምነታቸውን ጥበብ በተሞላበት መንገድ እንዲገልጹ ማለማመድ ይቻላል። (ቆላ. 4:6) በእርግጥም እነዚህ ርዕሶች ይሖዋ ‘አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ እንድንፈጽም’ እኛን ለመርዳት ካደረጋቸው በርካታ ዝግጅቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።—2 ጢሞ. 4:5