በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ማሳየት
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ የእያንዳንዱን ሰው ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር፤ እንዲሁም በፍቅር ተነሳስቶ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ያሳያቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ደንቆሮ የሆነን አንድ ሰው በፈወሰበት ወቅት ሰውየው እንደተሸማቀቀ ሳያስተውል አልቀረም፤ በመሆኑም ከሕዝቡ ነጥሎ ከወሰደው በኋላ ለብቻው ሆኖ ፈወሰው። (ማር. 7:31-35) በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ ያለባቸውን የአቅም ገደብ በመገንዘብና ከአቅማቸው በላይ ብዙ መረጃ ባለማዥጎድጎድ ለእነሱ ያለውን አሳቢነት አሳይቷል። (ዮሐ. 16:12) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላም ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ያሳይ ነበር። (2 ጢሞ. 4:17) እኛም የክርስቶስ ተከታዮች እንደ መሆናችን መጠን እሱን መምሰል እንፈልጋለን። (1 ጴጥ. 2:21፤ 1 ዮሐ. 3:16, 18) ከዚህም በተጨማሪ በአገልግሎታችን ውጤታማ የምንሆነው ለምናነጋግረው ሰው አሳቢነት የምናሳይ እንዲሁም ያለበትን ሁኔታ፣ ፍላጎቱንና የሚያሳስቡትን ነገሮች ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ ነው። የምናነጋግረው ሰው፣ ቤቱ የመጣነው እንዲሁ አንድ መልእክት ለማድረስ ወይም ጽሑፍ ትተን ለመሄድ ብቻ ሳይሆን ለእሱ በግለሰብ ደረጃ ስለምናስብ እንደሆነ ከተገነዘበ እኛን ለማዳመጥ ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ወር እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦
የምታነጋግሩት ሰው የሚያነሳውን ሐሳብ ግምት ውስጥ በማስገባት አቀራረባችሁን እንዴት ማስተካከል እንደምትችሉ የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ወቅት ወይም በአገልግሎት ላይ እያላችሁ ተለማመዱ።
ወንድሞች፣ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ሲመሩ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ማሳየት ስለሚቻልባቸው መንገዶች በውይይት መልክ ማቅረብ ወይም ይህን የሚያሳይ ሠርቶ ማሳያ እንዲቀርብ ማድረግ ይችላሉ።