ክርስቲያናዊ ሕይወት
ተሞክሮ ካላቸው ክርስቲያኖች ምን ትምህርት እናገኛለን?
በጉባኤዎቻችን ውስጥ ይሖዋን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ያገለገሉ አረጋውያን አሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ከሚያሳዩት ጠንካራ እምነት ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ስለ ይሖዋ ድርጅት ታሪክ እንዲሁም ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በይሖዋ እርዳታ ስለተወጡበት መንገድ ልንጠይቃቸው እንችላለን። እንዲያውም በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችን ላይ ተገኝተው ተሞክሯቸውን እንዲነግሩን መጋበዝ እንችል ይሆናል።
ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ያገለገላችሁ ክርስቲያኖች ከሆናችሁ ለወጣት ወንድሞችና እህቶች ተሞክሯችሁን ለመናገር ነፃነት ሊሰማችሁ ይገባል። ያዕቆብና ዮሴፍ ታሪካቸውን ለልጆቻቸው ተናግረዋል። (ዘፍ 48:21, 22፤ 50:24, 25) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይሖዋ ስለ አስደናቂ ሥራዎቹ ለልጆቻቸው እንዲናገሩ የቤተሰብ ራሶችን አዟል። (ዘዳ 4:9, 10፤ መዝ 78:4-7) በዘመናችን ያሉ ወላጆችና ሌሎች ወንድሞችም ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት ስላከናወናቸው አስደናቂ ሥራዎች ለቀጣዩ ትውልድ መናገር ይችላሉ።
በእገዳ ሥር አንድነትን ጠብቆ መኖር የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
የኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥራችን በታገደባቸው አንዳንድ አገሮች ላሉ ወንድሞች ምን ዓይነት እርዳታ አበርክቷል?
በእነዚህ አገሮች ያሉ ወንድሞች ጠንካራ እምነት ይዘው መቀጠል የቻሉት እንዴት ነው?
በሩማኒያ ያሉ በርካታ አስፋፊዎች ከይሖዋ ድርጅት የራቁት ለምን ነበር?
እነዚህ ተሞክሮዎች እምነታችሁን ያጠናከሩት እንዴት ነው?
ተሞክሮ ካላቸው ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሀብት አግኙ!