የጥናት ርዕስ 32
መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል
ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?
“የጸጋ ሁሉ አምላክ . . . ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።”—1 ጴጥ. 5:10
ዓላማ
ይሖዋ እንድንጸና ለመርዳት ሲል የትኞቹን ዝግጅቶች አድርጎልናል? ከእነዚህ ዝግጅቶች መጠቀም የምንችለውስ እንዴት ነው?
1. ጽናት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? እርዳታ የምናገኘውስ ከየት ነው? (1 ጴጥሮስ 5:10)
አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ሕዝቦች ጽናት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች ከማይድን በሽታ ጋር እየታገሉ ነው። ሌሎች ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት አጥተዋል። ከቤተሰባቸው አባላት ወይም ከመንግሥት ባለሥልጣናት ተቃውሞ የሚደርስባቸውም አሉ። (ማቴ. 10:18, 36, 37) አንተም እያጋጠመህ ያለው ፈተና ምንም ይሁን ምን ይሖዋ እንድትጸና ሊረዳህ እንደሚችል እርግጠኛ ሁን።—1 ጴጥሮስ 5:10ን አንብብ።
2. ክርስቲያኖች መጽናት የቻሉት ለምንድን ነው?
2 ጽናት እንቅፋት፣ ስደት፣ መከራ ወይም ፈተና ሲያጋጥም ታማኝነትን የመጠበቅና ተስፋን አጥብቆ የመያዝ ችሎታ ነው። እኛ ክርስቲያኖች የምንጸናው በራሳችን ብርታት አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ የምንጸናው ይሖዋ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ ስለሚሰጠን ነው። (2 ቆሮ. 4:7) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይሖዋ እንድንጸና ለመርዳት ሲል ያደረገልንን አራት ዝግጅቶች እንመለከታለን። እያንዳንዱን ዝግጅት ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነም እናያለን።
ጸሎት
3. ጸሎት ተአምር ነው የምንለው ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ ለመጽናት የሚረዳንን አንድ ተአምራዊ ዝግጅት አድርጎልናል። ኃጢአተኛ ብንሆንም እንኳ ከእሱ ጋር መነጋገር እንድንችል አጋጣሚውን ከፍቶልናል። (ዕብ. 4:16) እስቲ አስበው፣ በማንኛውም ጊዜ ስለ የትኛውም ጉዳይ ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን። ማንኛውንም ቋንቋ ብንጠቀም ወይም ከየትም ቦታ ሆነን ብንጸልይ ይሰማናል፤ ከሰዎች ተገልለን ወይም ወህኒ ቤት ታስረን ብንጸልይ እንኳ ይሰማናል። (ዮናስ 2:1, 2፤ ሥራ 16:25, 26) በጣም ከመጨነቃችን የተነሳ ሐሳባችንን በቃላት መግለጽ ቢያቅተንም እንኳ ይሖዋ ምን ማለት እንደፈለግን ይረዳል። (ሮም 8:26, 27) በእርግጥም ጸሎት ተአምር ነው!
4. ለመጽናት የምናቀርበው ጸሎት ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ [እንደሚሰማን]” በቃሉ አማካኝነት አረጋግጦልናል። (1 ዮሐ. 5:14) ይሖዋ ለመጽናት እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን? በሚገባ! ለመጽናት የምናቀርበው ጸሎት ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ይስማማል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ፈተናዎችን በጽናት ስንቋቋም ይሖዋ ለሚነቅፈው ለሰይጣን ዲያብሎስ መልስ መስጠት ይችላል። (ምሳሌ 27:11) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን [ለማሳየት]” እንደሚጓጓ ይገልጻል። (2 ዜና 16:9) በመሆኑም ይሖዋ እኛ እንድንጸና ለመርዳት ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው መተማመን እንችላለን።—ኢሳ. 30:18፤ 41:10፤ ሉቃስ 11:13
5. ጸሎት የአእምሮ ሰላም ሊሰጠን የሚችለው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 26:3)
5 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለሚያስጨንቀን ነገር አጥብቀን ከጸለይን ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅልን’ ይናገራል። (ፊልጵ. 4:7) ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው የአእምሮ ሰላም ለማግኘት የተለያዩ ዘዴዎችን ይሞክሩ ይሆናል። ለምሳሌ አንዳንዶች ያስጨነቃቸውን ነገር ጨምሮ አእምሯቸውን ከማንኛውም ዓይነት ሐሳብ ለማጽዳት አንዳንድ ማሰላሰያ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ሆኖም አእምሮን ባዶ ማድረግ ለመንፈሳዊ አደጋ ያጋልጣል። (ከማቴዎስ 12:43-45 ጋር አወዳድር።) በዚያ ላይ ደግሞ ይሖዋ ስንጸልይ የሚሰጠን ሰላም አንድ ሰው እንዲህ ባለው የማሰላሰል ዘዴ ከሚያገኘው ሰላም በእጅጉ የላቀ ነው። ወደ ይሖዋ ስንጸልይ በእሱ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን እናሳያለን፤ እሱም “ዘላቂ ሰላም” ይሰጠናል። (ኢሳይያስ 26:3ን አንብብ።) ይሖዋ ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ከቃሉ የተማርናቸውን የሚያጽናኑ እውነቶች እንድናስታውስ በመርዳት ነው። እነዚህ እውነቶች ልባችንንና አእምሯችንን ያረጋጉልናል፤ ምክንያቱም ይሖዋ እንደሚያስብልንና እንዲሳካልን እንደሚፈልግ ያስገነዝቡናል።—መዝ. 62:1, 2
6. ከጸሎት የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 ምን ማድረግ ትችላለህ? የእምነት ፈተና ሲያጋጥምህ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል”፤ እንዲሁም ሰላሙን እንዲሰጥህ ጸልይ። (መዝ. 55:22) በተጨማሪም ያጋጠመህን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት እንድትችል ጥበብ ለማግኘት ጸልይ። (ምሳሌ 2:10, 11) ይሖዋ ለመጽናት እንዲረዳህ ምልጃ ከማቅረብ በተጨማሪ የምስጋና ጸሎት ማቅረብህንም አትርሳ። (ፊልጵ. 4:6) ይሖዋ ፈተናውን ለመቋቋም እየረዳህ እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶችን ፈልግ፤ እንዲሁም ላደረገልህ ድጋፍ አመስግነው። ያጋጠመህ ፈተና ያገኘኸውን በረከት ከማየት እንዲያግድህ አትፍቀድ።—መዝ. 16:5, 6
ስትጸልይ ይሖዋን ታነጋግረዋለህ። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ደግሞ ይሖዋ ያነጋግርሃል (አንቀጽ 6ን ተመልከት)b
የአምላክ ቃል
7. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለመጽናት የሚረዳን እንዴት ነው?
7 ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳንን ቃሉን ሰጥቶናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ እንደሚደግፈን የሚያረጋግጡ በርካታ ጥቅሶችን ይዟል። እስቲ አንድ ምሳሌ ብቻ እንመልከት። ማቴዎስ 6:8 “አባታችሁ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል” ይላል። እነዚህን ቃላት የተናገረው ኢየሱስ ነው፤ ኢየሱስ ደግሞ ይሖዋን ከማንም በተሻለ ያውቀዋል። በመሆኑም መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጠን የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ለመጽናት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠናክሩ እንዲህ ያሉ በርካታ ጥቅሶችን ይዟል።—መዝ. 94:19
8. (ሀ) ለመጽናት ሊረዳን የሚችል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጥቀስ። (ለ) በሚያስፈልገን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማስታወስ ምን ሊረዳን ይችላል?
8 የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንጸና ሊረዱን ይችላሉ። ምክንያቱም ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳ ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጡናል። (ምሳሌ 2:6, 7) ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነገ ከመጨነቅ ይልቅ በዛሬ ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (ማቴ. 6:34) መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብና የማሰላሰል ልማድ ካለን በሚያስፈልገን ጊዜ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ማስታወስ ቀላል ይሆንልናል።
9. የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይሖዋ በሚሰጠን እርዳታ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩልን እንዴት ነው?
9 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ላይ በመተማመናቸው የእሱን ድጋፍ ያገኙ በርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዟል። (ዕብ. 11:32-34፤ ያዕ. 5:17) እንዲህ ባሉ ዘገባዎች ላይ ስናሰላስል ይሖዋ “መጠጊያችንና ብርታታችን፣ በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን” እንደሆነ ይበልጥ እንተማመናለን። (መዝ. 46:1) በጥንት ዘመን የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች የተከተሉትን የታማኝነት ጎዳና ልብ ብለን ስናስተውል እምነታቸውንና ጽናታቸውን ለመኮረጅ እንነሳሳለን።—ያዕ. 5:10, 11
10. ከአምላክ ቃል የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
10 ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብብ፤ እንዲሁም ጠቃሚ ሆነው ያገኘሃቸውን ጥቅሶች መዝግበህ ያዝ። ብዙዎች እያንዳንዱን ቀን አበረታች በሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ለመጀመር የዕለት ጥቅስ ማንበብን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ማሪa የተባለች እህት ሁለቱም ወላጆቿ በካንሰር በተያዙበት ወቅት እንዲህ ማድረጓ ጠቅሟታል። እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ እነሱን ስትንከባከብ ለመጽናት የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “በየቀኑ ጠዋት ላይ ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት የዕለቱን ጥቅስ አነብና አሰላስልበታለሁ። ይህ ልማድ አእምሮዬን በቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ለመሙላት አስችሎኛል፤ ይህም በራሴና ባጋጠመኝ አስጨናቂ ሁኔታ ላይ ከማተኮር ይልቅ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዳስብ ይረዳኛል።”—መዝ. 61:2
የእምነት አጋሮቻችን
11. ፈተና የሚደርስብን እኛ ብቻ እንዳልሆንን ማወቃችን የሚያበረታታን እንዴት ነው?
11 ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳንን ክርስቲያን የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶናል። ‘በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችን ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ’ መገንዘባችን በራሱ ብቻችንን እንዳልሆንን ያረጋግጥልናል። (1 ጴጥ. 5:9) በእርግጥም፣ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ሌሎች የእምነት አጋሮቻችን ተመሳሳይ ፈተና እንዳጋጠማቸውና በጽናት እንደተወጡት መተማመን እንችላለን። በመሆኑም እኛም መጽናት እንችላለን ማለት ነው።—ሥራ 14:22
12. የእምነት አጋሮቻችን የሚረዱን እንዴት ነው? እኛስ ምን ልናደርግላቸው እንችላለን? (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4)
12 የእምነት አጋሮቻችን እንድንጸና ሊያበረታቱን ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ የዚህን እውነተኝነት አይቷል። በቁም እስር ላይ በነበረበት ጊዜ የረዱትን ክርስቲያኖች በስም እየጠቀሰ አመስግኗቸዋል። እነዚህ ወንድሞች ጳውሎስን አጽናንተውታል፤ ማበረታቻና ተግባራዊ እርዳታም ሰጥተውታል። (ፊልጵ. 2:25, 29, 30፤ ቆላ. 4:10, 11) በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥመን ይችላል። ለመጽናት እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይደርሱልናል፤ እነሱ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው ደግሞ እኛ እንደርስላቸዋለን።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።
13. ማያ የተባለች እህት እንድትጸና የረዳት ምንድን ነው?
13 በሩሲያ የምትኖር ማያ የተባለች እህት ከወንድማማች ማኅበራችን ትልቅ ማበረታቻ አግኝታለች። በ2020 ቤቷ በፖሊሶች ተበርብሮ ነበር፤ በተጨማሪም እምነቷን ለሌሎች በማካፈሏ ፍርድ ቤት ቀረበች። ማያ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም በዛልኩበት ወቅት ወንድሞችና እህቶች እየደወሉና እየጻፉ ምን ያህል እንደሚወዱኝ ይነግሩኝ ነበር። . . . አፍቃሪ የሆነ ትልቅ ቤተሰብ አባል እንደሆንኩ ጠፍቶኝ አያውቅም። ከ2020 አንስቶ ግን ይህን ይበልጥ መረዳት ችያለሁ።”
14. የእምነት አጋሮቻችን ከሚሰጡን ድጋፍ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 ምን ማድረግ ትችላለህ? በፈተና ውስጥ ስትሆን ከክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ጋር ተቀራረብ። የሽማግሌዎችን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ሽማግሌዎች “ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” ሊሆኑልህ ይችላሉ። (ኢሳ. 32:2) ከዚህም ሌላ፣ የእምነት አጋሮችህም የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት እየተቋቋሙ እንደሆነ አትዘንጋ። የተቸገረን ሰው መርዳት ሚዛናዊ ለመሆንና አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳሃል፤ ይህም አንተም ያጋጠመህን መከራ በጽናት እንድትቋቋም ያግዝሃል።—ሥራ 20:35
ከክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ጋር ተቀራረብ (አንቀጽ 14ን ተመልከት)c
ተስፋችን
15. ተስፋ ኢየሱስን ጨምሮ የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች የጠቀማቸው እንዴት ነው? (ዕብራውያን 12:2)
15 ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳን አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቶናል። (ሮም 15:13) ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፈው በጣም አስቸጋሪ ቀን ተስፋ እንዲጸና የረዳው እንዴት እንደሆነ አስታውስ። (ዕብራውያን 12:2ን አንብብ።) ኢየሱስ የእሱ ታማኝ መሆን የይሖዋ ስም ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያውቅ ነበር። ከዚህም ሌላ፣ ኢየሱስ ወደ አባቱ ለመመለስና ከጊዜ በኋላም ከወንድሞቹ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ ውስጥ ለማገልገል ይጓጓ ነበር። እኛም በተመሳሳይ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋችን በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ በጽናት ለመወጣት ይረዳናል።
16. ተስፋ አንዲት እህት እንድትጸና የረዳት እንዴት ነው? እሷ ከሰጠችው ሐሳብ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
16 በሩሲያ የምትኖር አላ የተባለች እህት፣ ባሏ በቁጥጥር ሥር ውሎ ማረፊያ ቤት በገባበት ወቅት የመንግሥቱ ተስፋ የጠቀማት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “መጸለዬና በወደፊት ተስፋችን ላይ ማሰላሰሌ ከመጠን በላይ ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድተውኛል። ይህ መከራ የሚያበቃበት ጊዜ እንዳለ አውቃለሁ። ይሖዋ ድል መንሳቱ አይቀርም፤ እኛም እንደዚያው።”
17. ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋችን ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ምን ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ ስላዘጋጀልን አስደናቂ ተስፋ ጊዜ ወስደህ አሰላስል። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ራስህን ሣል፤ እንዲሁም ያኔ የምናገኛቸውን በረከቶች በዓይነ ሕሊናህ ለማሰብ ሞክር። እንዲህ ስናደርግ፣ ዛሬ ያጋጠመን ማንኛውም ፈተና “ጊዜያዊና ቀላል” ሆኖ ይታየናል። (2 ቆሮ. 4:17) ከዚህም ሌላ፣ እምነትህን ለሌሎች ለማካፈል የቻልከውን ሁሉ አድርግ። አምላክ ለወደፊቱ ጊዜ ያለውን ዓላማ ሳያውቁ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያለውን መከራ መቋቋም ምን ያህል ከባድ ሊሆንባቸው እንደሚችል አስብ። አጭር ውይይት በማድረግ ብቻ እንኳ ስለ መንግሥቱ ተስፋ ለማወቅ እንዲጓጉ ልታደርግ ትችላለህ።
ይሖዋ ስላዘጋጀልን አስደናቂ ተስፋ ጊዜ ወስደህ አሰላስል (አንቀጽ 17ን ተመልከት)d
18. ይሖዋ በሰጠን ተስፋዎች ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው?
18 ኢዮብ በርካታ ፈተናዎችን በጽናት ከተወጣ በኋላ ይሖዋን እንዲህ ብሎታል፦ “አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል፣ ደግሞም ያሰብከውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደማይሳንህ አሁን አወቅኩ።” (ኢዮብ 42:2) ኢዮብ እንደተገነዘበው፣ የይሖዋ ዓላማ እንዳይፈጸም ማገድ የሚችል ምንም ነገር የለም። ይህ እውነታ ለመጽናት ብርታት ይሰጠናል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ብዙ ሐኪሞች ጋር ብትሄድም ለሕመሟ መፍትሔ ባለማግኘቷ ተስፋ የቆረጠችን አንዲት ሴት ለማሰብ ሞክር። ሆኖም ተሞክሮ ያለውና እምነት የሚጣልበት አንድ ሐኪም በሽታዋን ሲያገኝላትና እንዴት እንደሚያክማት ሲነግራት ሕመሟ እስኪድን መጠበቅ ቢያስፈልጋትም ከአሁኑ እፎይታ ይሰማታል። ብሩህ ተስፋ እንዳላት ማለትም ከሕመሟ እንደምትድን ስለምታውቅ መጽናት ትችላለች። እኛም በተመሳሳይ በገነት ውስጥ እንደምንኖር ያለን ተስፋ እንድንጸና ይረዳናል።
19. ለመጽናት ምን ያስፈልገናል?
19 እስካሁን እንደተመለከትነው ይሖዋ በጸሎት፣ በቃሉ፣ በእምነት አጋሮቻችን እንዲሁም በተስፋችን አማካኝነት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። በእነዚህ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ የምንጠቀም ከሆነ ለመከራ የዳረገን የሰይጣን ዓለም እስኪወገድ ድረስ ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም ይረዳናል።—ፊልጵ. 4:13
መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ወቅት አልፎ ወቅት ሲተካ በታማኝነት እየጸና ያለ አረጋዊ ወንድም።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ወቅት አልፎ ወቅት ሲተካ በታማኝነት እየጸና ያለ አረጋዊ ወንድም።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ወቅት አልፎ ወቅት ሲተካ በታማኝነት እየጸና ያለ አረጋዊ ወንድም።