የጥናት ርዕስ 33
መዝሙር 4 “ይሖዋ እረኛዬ ነው”
ይሖዋ እንደሚወድህ አምነህ ተቀበል
“በታማኝ ፍቅር ወደ እኔ ሳብኩሽ።”—ኤር. 31:3
ዓላማ
ይሖዋ እንደሚወደን አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው? እሱ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለውስ እንዴት ነው?
1. ራስህን ለይሖዋ የወሰንከው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
ራስህን ለይሖዋ የወሰንክበት ጊዜ ትዝ ይልሃል? ይህን ውሳኔ ያደረግከው እሱን ስላወቅከውና ስለወደድከው ነው። በሕይወትህ ውስጥ የእሱን ፈቃድ እንደምታስቀድም እንዲሁም ምንጊዜም በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህ፣ አእምሮህና ኃይልህ እሱን እንደምትወደው ቃል ገባህ። (ማር. 12:30) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለእሱ ያለህ ፍቅር እየተጠናከረ መጥቷል። ታዲያ አንድ ሰው “ይሖዋን እንደምትወደው እርግጠኛ ነህ?” ብሎ ቢጠይቅህ ምን ብለህ ትመልሳለህ? ያለምንም ማመንታት “የእሱን ያህል የምወደው ማንም የለም” ብለህ እንደምትመልስ ምንም ጥያቄ የለውም።
ራስህን ወስነህ በተጠመቅክበት ወቅት ለይሖዋ የነበረህ ፍቅር ትዝ ይልሃል? (አንቀጽ 1ን ተመልከት)
2-3. ይሖዋ ምን አምነን እንድንቀበል ይፈልጋል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (ኤርምያስ 31:3)
2 ይሁንና አንድ ሰው “ይሖዋ እንደሚወድህ እርግጠኛ ነህ?” ብሎ ቢጠይቅህ ምን ብለህ ትመልሳለህ? የይሖዋ ፍቅር የሚገባህ ሰው እንዳልሆንክ በማሰብ መልስ ለመስጠት ታመነታለህ? በልጅነቷ ብዙ መጥፎ ነገር ያጋጠማት አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን እንደምወደው አውቃለሁ። ይህን ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። ይሖዋ የሚወደኝ መሆኑን ግን ብዙ ጊዜ እጠራጠራለሁ።” ታዲያ ይሖዋ በእርግጥ እንደሚወድህ እንዴት ማወቅ ትችላለህ?
3 ይሖዋ እሱ እንደሚወድህ እርግጠኛ እንድትሆን ይፈልጋል። (ኤርምያስ 31:3ን አንብብ።) ወደ ራሱ ስቦሃል። ራስህን ለእሱ ወስነህ በተጠመቅክበት ጊዜ ደግሞ ልዩ የሆነ ስጦታ ሰጥቶሃል፤ ይህ ስጦታ ታማኝ ፍቅሩ ነው። በመሆኑም በጥልቅ ይወድሃል፤ እንዲሁም መቼም ቢሆን አይተውህም። ታማኝ ፍቅሩ አንተን ጨምሮ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደ ‘ውድ ንብረቱ’ አድርጎ እንዲመለከታቸው ያነሳሳዋል። (ሚል. 3:17 ግርጌ) ይሖዋ የእሱን ፍቅር በተመለከተ የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት እንዲሰማህ ይፈልጋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል በልበ ሙሉነት ጽፏል፦ “ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን [ከአምላክ] ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።” (ሮም 8:38, 39) ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከር የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳን እንደሚችል እናያለን።
ይሖዋ እንደሚወደን አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?
4. ከሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች አንዱን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ እንደሚወደን አምነን መቀበላችን ከሰይጣን “መሠሪ ዘዴዎች” አንዱን ለማሸነፍ ያስችለናል። (ኤፌ. 6:11) ሰይጣን ይሖዋን እንዳናገለግል ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው መሠሪ ዘዴዎች አንዱ ‘ይሖዋ አይወድህም’ የሚለውን ውሸት ማስፋፋት ነው። ሰይጣን አጋጣሚዎችን በንቃት እንደሚከታተል አስታውስ። ብዙውን ጊዜ ጥቃት የሚሰነዝርብን የደከምንበትን ጊዜ ጠብቆ ነው። ቀደም ሲል ባጋጠሙን ነገሮች፣ አሁን እያጋጠሙን ባሉት ችግሮች ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚሰማን ስጋት የተነሳ ስሜታችን ሲደቆስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ጥቃት ይሰነዝርብናል። (ምሳሌ 24:10) ሰይጣን ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ምስኪን ሰለባዎቹን ለማደን እንደሚፈልግ አንበሳ ነው። የሚሰማንን ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተጠቅሞ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ለማድረግ ይሞክራል። ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ሁልጊዜ የምናጠናክር ከሆነ ግን ሰይጣንን እና መሠሪ ዘዴዎቹን ‘ለመቃወም’ የተሻለ ብቃት ይኖረናል።—1 ጴጥ. 5:8, 9፤ ያዕ. 4:7
5. ይሖዋ እንደሚወደንና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን የሚሰማን መሆኑ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ እንደሚወደን አምነን መቀበላችን ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ የፈጠረን የመውደድና የመወደድ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። ሌሎች ሲወዱን እኛም እነሱን ለመውደድ እንነሳሳለን። ይሖዋ እንደሚወደንና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ይበልጥ በተሰማን መጠን እኛም ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። (1 ዮሐ. 4:19) ለእሱ ያለን ፍቅር ሲያድግ ደግሞ እሱም ለእኛ ያለው ፍቅር ያድጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ያዕ. 4:8) ይሁንና ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ እንደሚወደን አምነን እንድንቀበል ምን ሊረዳን ይችላል?
6. ይሖዋ እንደሚወደን አምነን ለመቀበል ምን ብለን መጸለይ እንችላለን?
6 ይሖዋ ፍቅሩን ለማስተዋል እንዲረዳህ አዘውትረህ ጸልይ። (ሉቃስ 18:1፤ ሮም 12:12) ይሖዋ፣ እሱ በሚያይህ መንገድ ራስህን ለማየት እንዲረዳህ ጠይቀው። ካስፈለገም በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ እንዲህ ያለውን ጸሎት ማቅረብ ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ ልብህ የሚኮንንህ ከሆነ ይሖዋ እንደሚወድህ አምነህ መቀበል ሊከብድህ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ከልብህ ይበልጥ ታላቅ እንደሆነ አስታውስ። (1 ዮሐ. 3:19, 20) ራስህን ከምታውቀው በላይ ያውቅሃል፤ አንተ በውስጥህ ያላየኸውን ነገር ያያል። (1 ሳሙ. 16:7፤ 2 ዜና 6:30) እንግዲያው ልብህን በፊቱ ‘በማፍሰስ’ እሱ እንደሚወድህ አምነህ ለመቀበል እንዲረዳህ ለምነው። (መዝ. 62:8) ከዚያም ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች በሥራ ላይ በማዋል ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ።
7-8. የመዝሙር መጽሐፍ ይሖዋ እንደሚወደን የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?
7 ይሖዋ የሚናገረውን እመን። ይሖዋ እውነተኛ ማንነቱን እንዲገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ መርቷቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት ይሖዋን እንዴት ግሩም በሆነ መንገድ እንደገለጸው ልብ በል፦ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ ተስፋ የቆረጡትንም ያድናል።” (መዝ. 34:18 ግርጌ) ተስፋ በምትቆርጥበት ጊዜ ብቻህን እንደተተውክ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ እንዲህ ባሉት ጊዜያት የእሱ እርዳታ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንደሚያስፈልግህ ስለሚያውቅ ቅርብህ እንደሚሆን ቃል ገብቶልሃል። በሌላ መዝሙር ላይ ደግሞ ዳዊት “እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም” ሲል ጽፏል። (መዝ. 56:8) ይሖዋ የሚደርስብህን መከራ ያያል። ስለ አንተ በጥልቅ ያስባል፤ ያጋጠመህ ችግርም ያሳስበዋል። አንድ መንገደኛ በአቁማዳው ውስጥ ያለውን ውኃ ውድ አድርጎ እንደሚመለከተው ሁሉ ይሖዋም እንባህን ያጠራቅማል፤ እንዲሁም እንደ ውድ ነገር ይመለከተዋል። መዝሙር 139:3 ስለ ይሖዋ ሲናገር “መንገዶቼን ሁሉ ታውቃለህ” ይላል። ይሖዋ መንገዶችህን ሁሉ ያያል፤ ሆኖም የሚያተኩረው በምታከናውነው መልካም ነገር ላይ ነው። (ዕብ. 6:10) ለምን? እሱን ለማስደሰት ስትል የምታደርገውን እያንዳንዱን ጥረት ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት ነው።a
8 ይሖዋ በመንፈስ መሪነት ባጻፈው ቃሉ ውስጥ ባሉት እንዲህ ያሉ የሚያጽናኑ ጥቅሶች አማካኝነት እንዲህ እያለህ ነው ሊባል ይችላል፦ “ምን ያህል እንደምወድህና እንደማስብልህ እንድታውቅ እፈልጋለሁ።” ሆኖም ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሰይጣን ‘ይሖዋ አይወድህም’ የሚለውን ውሸት ለማስፋፋት ይሞክራል። እንግዲያው ይሖዋ የሚወድህ መሆኑን አልፎ አልፎ የምትጠራጠር ከሆነ ቆም ብለህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የማምነው ማንን ነው? “የውሸት አባት” የሆነውን ሰይጣንን ወይስ “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን?’—ዮሐ. 8:44፤ መዝ. 31:5
9. ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ምን ዋስትና ሰጥቷል? (ዘፀአት 20:5, 6)
9 ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ምን አመለካከት እንዳለው አሰላስል። ይሖዋ ለሙሴና ለእስራኤላውያን ምን እንዳላቸው አስታውስ። (ዘፀአት 20:5, 6ን አንብብ።) ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ሰዎች ታማኝ ፍቅር ማሳየቱን እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል። እነዚህ ቃላት፣ ታማኝ የሆነው አምላካችን ለሚወዱት አገልጋዮቹ ፈጽሞ ፍቅሩን እንደማይነፍጋቸው ያረጋግጡልናል። (ነህ. 1:5) እንግዲያው አልፎ አልፎ ይሖዋ እንደሚወድህ ማረጋገጫ የሚያስፈልግህ ከሆነ ቆም ብለህ ‘ይሖዋን እወደዋለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ከዚያም ይህን አስብ፦ ይሖዋን የምትወደው ከሆነና እሱን ለማስደሰት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ እያደረግክ ከሆነ እሱ በጣም እንደሚወድህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ዳን. 9:4፤ 1 ቆሮ. 8:3) በሌላ አባባል፣ ይሖዋን እንደምትወደው የማትጠራጠር ከሆነ እሱ እንደሚወድህ የምትጠራጠርበት ምን ምክንያት ይኖራል? የእሱ ፍቅርና ታማኝነት ምንጊዜም አስተማማኝ ነው።
10-11. ይሖዋ ለቤዛው ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖርህ ይፈልጋል? (ገላትያ 2:20)
10 በቤዛው ላይ አሰላስል። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ይሖዋ ለሰው ልጆች የሰጠው ትልቁ ስጦታ ነው። (ዮሐ. 3:16) ይሁንና ቤዛው ለአንተ በግለሰብ ደረጃ የተሰጠ ስጦታ ነው? አዎ! የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ከባባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል፤ ክርስቲያን ከሆነ በኋላም ከአለፍጽምናው ጋር መታገል አስፈልጎታል። (ሮም 7:24, 25፤ 1 ጢሞ. 1:12-14) ያም ቢሆን፣ ቤዛው ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሰጠው ስጦታ እንደሆነ ተሰምቶታል። (ገላትያ 2:20ን አንብብ።) ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው በይሖዋ መንፈስ ተመርቶ እንደሆነ አስታውስ። ደግሞም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ የተጻፈው ለእኛ ትምህርት ነው። (ሮም 15:4) ጳውሎስ የጻፈው ሐሳብ፣ ይሖዋ ቤዛውን እንዴት አድርገህ እንድትመለከተው እንደሚፈልግ ያሳያል፤ ቤዛውን እሱ ለአንተ በግለሰብ ደረጃ የሰጠህ ስጦታ አድርገህ እንድትመለከተው ይፈልጋል። ለቤዛው እንዲህ ያለ አመለካከት ስታዳብር ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወድህ ያለህ እምነት ይጠናከራል።
11 ይሖዋ፣ ኢየሱስ እንዲሞትልን ወደ ምድር ስለላከው በጣም እናመሰግነዋለን። ሆኖም ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ሌላው ምክንያት ስለ አምላክ እውነትን ለማስተማር ነው። (ዮሐ. 18:37) ይህ እውነት ይሖዋ ለልጆቹ ያለውን ስሜት ያካትታል።
ኢየሱስ ይሖዋ እንደሚወደን አምነን እንድንቀበል የሚረዳን እንዴት ነው?
12. ኢየሱስ ስለ ይሖዋ የተናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
12 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ለሰዎች መናገር ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 10:22) ኢየሱስ ስለ ይሖዋ የተናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። ደግሞም ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለረጅም ዘመናት ከይሖዋ ጋር በሰማይ ላይ ኖሯል። (ቆላ. 1:15) ኢየሱስ፣ ይሖዋ ለእሱ እንዲሁም ለሌሎች ያሳየውን ፍቅር በዓይኑ ስላየ ይሖዋ ታማኝ ልጆቹን ምን ያህል እንደሚወዳቸው በሚገባ ያውቃል። ታዲያ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንደሚወደን አምነን እንድንቀበል የሚረዳን እንዴት ነው?
13. ኢየሱስ ይሖዋን እንዴት እንድናየው ይፈልጋል?
13 ኢየሱስ ይሖዋን እሱ በሚያይበት መንገድ እንድናየው ይፈልጋል። በወንጌሎች ውስጥ ኢየሱስ ከ160 ጊዜ በላይ ይሖዋን “አባት” ወይም “አብ” ብሎ ጠርቶታል። ከተከታዮቹ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜም “አባታችሁ” ወይም “የሰማዩ አባታችሁ” እንደሚሉት ያሉ አገላለጾችን ተጠቅሟል። (ማቴ. 5:16፤ 6:26) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ይሖዋን “ሁሉን ቻይ፣” “ሉዓላዊ” እንዲሁም “ታላቅ ፈጣሪ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ይጠሩት ነበር። ኢየሱስ ግን ይሖዋን “አባት” ብሎ በተደጋጋሚ ጠርቶታል። ይህ አገላለጽ፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ አንድ ልጅ ከአፍቃሪ አባቱ ጋር ያለው ዓይነት ቅርበት ከእሱ ጋር እንዲኖራቸው እንደሚፈልግ ያሳያል። በእርግጥም ኢየሱስ ይሖዋን ልክ እሱ በሚያየው መንገድ ማለትም ልጆቹን እንደሚወድ አፍቃሪ አባት እንድናየው ይፈልጋል። ኢየሱስ “አባት” ወይም “አብ” የሚለውን አገላለጽ የተጠቀመባቸውን ሁለት ቦታዎች እስቲ እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
14. ኢየሱስ እያንዳንዳችን በሰማዩ አባታችን ዓይን ቦታ እንዳለን ያሳየው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 10:29-31) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 በመጀመሪያ ኢየሱስ በማቴዎስ 10:29-31 ላይ ምን እንዳለ እንመልከት። (ጥቅሱን አንብብ።) ድንቢጦች ይሖዋን የመውደድም ሆነ የማምለክ ችሎታ የሌላቸው ትናንሽ ወፎች ናቸው። ያም ቢሆን አባታችን ለአንዲት ድንቢጥ እንኳ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ መሬት ላይ ስትወድቅ ያስተውላል። በፍቅር ተነሳስተው ለሚያመልኩት ታማኝ አገልጋዮቹማ በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደሚሰጣቸው መገመት ይቻላል። በተጨማሪም ኢየሱስ “የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል” ብሏል። ይሖዋ ስለ እኛ እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር የሚያውቅ ከመሆኑ አንጻር በጣም እንደሚያስብልን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። በእርግጥም ኢየሱስ እያንዳንዳችን በሰማዩ አባታችን ዓይን ውድ እንደሆንን አምነን እንድንቀበል ይፈልጋል።
ይሖዋ ለአንዲት ድንቢጥ እንኳ ቦታ ስለሚሰጥ መሬት ላይ ስትወድቅ ያስተውላል። እሱን ለምትወደውና በታማኝነት ለምታገለግለው ለአንተማ ምን ያህል ትልቅ ቦታ ይሰጥህ ይሆን! (አንቀጽ 14ን ተመልከት)
15. ኢየሱስ በዮሐንስ 6:44 ላይ የተናገራቸው ቃላት ስለ ሰማዩ አባትህ ምን ያስተምሩሃል?
15 ኢየሱስ “አብ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበትን ሌላ ጥቅስ እንመልከት። (ዮሐንስ 6:44ን አንብብ።) የሰማዩ አባትህ በግለሰብ ደረጃ በደግነት ወደ እውነት ስቦሃል። የሳበህ ለምንድን ነው? ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዳለህ ስላየ ነው። (ሥራ 13:48) ኢየሱስ በዮሐንስ 6:44 ላይ ያሉትን ቃላት የተናገረው ይሖዋ በኤርምያስ 31:3 ላይ የተናገረውን ሐሳብ አስታውሶ ሊሆን ይችላል። በዚያ ጥቅስ ላይ ይሖዋ “በታማኝ ፍቅር ወደ እኔ ሳብኩሽ [ወይም፣ ለአንቺ ታማኝ ፍቅር ማሳየቴን ቀጠልኩ]” ብሏል። (ኤር. 31:3 ግርጌ፤ ከሆሴዕ 11:4 ጋር አወዳድር።) ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ። አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባትህ አንተም እንኳ እንዳሉህ የማታውቃቸውን መልካም ባሕርያት ማየቱን ይቀጥላል።
16. (ሀ) ኢየሱስ ምን እያለን እንዳለ ሊቆጠር ይችላል? ልናምነው የሚገባውስ ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ከማንም የተሻለ አባት እንደሚሆንልህ ያለህን እምነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? (“ሁላችንም እንደ እሱ ያለ አባት አናገኝም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
16 ኢየሱስ ይሖዋን “አባታችን” ብሎ ሲጠራው እንዲህ እያለህ እንዳለ ሊቆጠር ይችላል፦ “ይሖዋ የእኔ አባት ብቻ አይደለም፤ የአንተም አባት ነው። በግለሰብ ደረጃ እንደሚወድህና በጣም እንደሚያስብልህ ዋስትና እሰጥሃለሁ።” እንግዲያው ይሖዋ የሚወድህ መሆኑን አልፎ አልፎ የምትጠራጠር ከሆነ ቆም ብለህ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘አባታችንን ከማንም በተሻለ የሚያውቀውና ሁልጊዜም እውነትን የሚናገረው ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ማመን የለብኝም?’—1 ጴጥ. 2:22
እምነትህን ማጠናከርህን ቀጥል
17. ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከራችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከራችንን መቀጠል ይኖርብናል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ መሠሪ የሆነው ጠላታችን ሰይጣን ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለዚህም ሲል ይሖዋ የሚወደን መሆኑን እንድንጠራጠር ለማድረግ ሁልጊዜ ይሞክራል። ሰይጣን እንዲያሸንፍ ልንፈቅድለት አይገባም!—ኢዮብ 27:5
18. ይሖዋ እንደሚወድህ ያለህን እምነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?
18 ይሖዋ እንደሚወድህ ያለህን እምነት ለማጠናከር፣ እሱ በሚያይህ መንገድ ራስህን ለማየት እንዲረዳህ ሁልጊዜ ጸልይ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የይሖዋን ፍቅር የገለጹት እንዴት እንደሆነ አሰላስል። ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ምን አመለካከት እንዳለው አስታውስ፤ ለሚወዱት ሰዎች ፈጽሞ ፍቅሩን አይነፍጋቸውም። ቤዛውን በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደተሰጠህ ስጦታ አድርገህ መቁጠር የምትችለው ለምን እንደሆነ አሰላስል። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሰማዩ አባትህ እንደሆነ በሰጠህ ዋስትና ተማመን። እንዲህ ካደረግክ፣ አንድ ሰው “ይሖዋ እንደሚወድህ እርግጠኛ ነህ?” ብሎ ቢጠይቅህ በልበ ሙሉነት እንዲህ የሚል ምላሽ መስጠት ትችላለህ፦ “አዎ፣ ይወደኛል! እኔም ለእሱ ያለኝን ፍቅር ለማሳየት በየዕለቱ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ!”
መዝሙር 154 ፍቅር ለዘላለም ይኖራል
a ይሖዋ እንደሚወደን የሚያረጋግጡ ተጨማሪ አጽናኝ ጥቅሶችን ለማግኘት ጥቅሶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት በተባለው ጽሑፍ ላይ የሚገኘውን “ጥርጣሬ፤ በራስ አለመተማመን” የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ ተመልከት።