ንባብህን ልታሻሽል ትችላለህ
እርግጥ ንባብን ለማሻሻል ተዓምራዊ መንገድ የለውም። ይሁን እንጂ ማንበብ የምትችል ከሆነ ከዚያ በተሻለም ሁኔታ ለማንበብ ትችላለህ! አዘውትረን የማናነብ ከሆነ በተሻለ ሁኔታ ማንበብ እንችላለን ብለን ተስፋ ማድረግ አንችልም። ለዚሁ ዓላማ ቢያንስ በቀን ግማሽ ሰዓት ከተቻለም ከዚያ በላይ ሊመደብለት ይገባል።
መራጭ የመሆን አስፈላጊነት
የምታነበውን ነገር በተመለከተ መራጭ ሁን። ለንባብ የምትመርጠው ጽሑፍ አንተ በምታውቃቸው ቃላት የተዘጋጀና ቴክኒካዊ ያልሆነ ርዕሰ ጉዳይ የሚያብራራ ይሁን። ከዚያ ቀስ በቀስ የቃላት ዕውቀትህን የሚያሰፉልህን ጽሑፎች ምረጥ።
ሁሉም ጽሑፎች የሚያንጹና አእምሮን የሚያድሱ ስላልሆኑ በሌላ መልክም መራጭ ሁን። በአንድ ወቅት አንድ ጥበበኛ ሰው እንዲህ ብሏል:– “ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፣ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል።” (መክብብ 12:12) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ጽሑፎች ይገኛሉ፤ ብዙዎቹ ሥነ ምግባርን የማያቆሽሹ ትምህርት ይዘው ይወጣሉ። በይበልጥ በሥነ ምግባር ንጽህናህና በመንፈሳዊነትህ እንድትቀጥል የሚረዱህን ጽሑፎች ምረጥ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ በምዕራፍ 13 ቁጥር 20 ላይ እንዲህ ይላል:- “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” ይህ መሠረታዊ ሥርዓት አንድ ሰው በጓደኛ ረገድ መራጭ መሆን እንዳለበት ለማሳሰብ የሚሠራ ቢሆንም የምናነበውን ነገር መራጮች እንድንሆን ለመምከርም ሊሠራ ይችላል።
በአነባብ ልማድ ላይ ለውጥ ማድረግ
ገና እንደተወለድን ማንበብ እንደማንችል ግልጽ ነው። በሕይወታችን ውስጥ እንደሚያጋጥሙን ሌሎች ነገሮች ሁሉ ንባብም የሚዳብር ችሎታ ነው። አንድ ሰው ፒያኖ መጫወት ሳይለማመድ ጥሩ ችሎታ ያለው ፒያኖ ተጫዋች ሊሆን ይችላልን? ወይስ ብዙ ጊዜ የጠረጴዛ ኳስ ሳይጫወት ጥሩ የጠረጴዛ ኳስ ተጫዋች ይወጣዋልን? አንድ ሰው ፒያኖ ወይም የጠረጴዛ ኳስ ተጫዋች ሲሆን ገና ከመጀመሪያው መጥፎ ልማዶችን ካዳበረ ሊያስወግዳቸው ይገባል አለበለዚያ ግን የእነርሱ እስረኛ ሆኖ ይቀራል።
ይህ ለንባብም ይሠራል። አንድ ተማሪ በልጅነቱ ደካማ የንባብ ልማዶችን ከጀመረ ንባቡ ሰንካላ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ሕይወቱን በሙሉ ባለው የተወሰነ የማንበብ ችሎታ ከጽሑፍ ጋር ሲታገል ይኖራል። ዕድሜው እየገፋ ሲሄድም መጥፎዎቹን የንባብ ልማዶች ማሸነፉ አስቸጋሪ ይሆንበታል። ይሁንና አንድ ሰው ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆነ ሊሳካለት ይችላል! እስቲ ከእነዚህ ልማዶች አንዳንዶቹን እንመልከት።
ንባብን ለማሻሻል የሚያስችለው አካላዊ ሁኔታ በመጀመሪያ የሚያተኩረው በዓይን እንቅስቃሴ ላይ ነው። አንድ መስመር ባነበብክ ቁጥር ዓይኖችህ በርካታ ቆምታዎችን ያደርጋሉ። እነዚህ ቆምታዎች አስፈላጊ ናቸው፤ ምክንያቱም ዓይናችን የሚያየው ምን እንደሆነ የሚያስተውለው ቆምታ ሲኖር ብቻ ነው። ዓይናችን ያየው ነገር በእነዚህ ቆምታዎች ወቅት ወደ አእምሮ ይተላለፋል። አእምሮም የመልእክቱን ምንነት ይተረጉማል። ንባቡን የሚያካሂደው ዓይን ሳይሆን አእምሮ ነው። ዓይኖችህ ከአእምሮ ጋር ተያይዘው የሚሠሩ ቅጥያዎች ናቸው።
አዝጋሚ አንባቢ በየቃላቱ ላይ ይቆማል። ይህ ደግም ወደ አእምሮ የሚላከውን መልእክት የተቆራረጠ ስለሚያደርገውና ዓይኖቻችን ስለሚደክሙ ከተነበበውም የምናስታውሰው ትንሹን ስለሚሆን ንባቡን አሰልቺ ያደርገዋል። ጥሩ ችሎታ ያላቸው አንባቢዎች ዓይኖቻቸውን በጽሑፉ ላይ አሳርፈው ሲያነቡ ቀላልና አንድ ዓይነት መልክ ያለው የዓይን እንቅስቃሴ ይኖራቸዋል። በየመስመሩ ቆም የሚሉባቸውን ቦታዎች ቁጥር መቀነስን ይማራሉ። በአንድ ጊዜ ሐረጐችን በማንበብ የጽሑፉን ገጽ በፍጥነት ማንበብ ይችላሉ፤ እንዲሁም የመረዳት ችሎታቸው ይጨምራል።
ይህም ወደ ኋላ እየተንሸራተቱ የማንበብን ልማድ ያስታውሰናል። ይህም ማለት ወደ ኋላ ተመልሰን ያነበብናቸውን ነገሮች ደግመን ማንበብ ማለት ነው። ወደ ኋላ እየተንሸራተቱ ማንበብ ብዙ ጊዜ ልማድ ይሆናል። እርግጥ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ የተወሰኑ ሐሳቦች ግልጽ የማይሆኑበት ጊዜ አለ። በዚህ ጊዜ የተባለውን ነገር መለስ ብሎ ማንበቡ አስፈላጊ ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኛው ድግግሞሽ አላስፈላጊና እንዲያውም ንባቡን የሚያጓትት ነው። የሚቻል ሲሆን እየተንሸራተቱ የማንበብን ልማድ አስወግድ።
ጥሩ የንባብ ችሎታን ይገታል ብለው ባለሙያዎች የሚናገሩለት ሌላው ልማድ ደግሞ ቮካላይዜሽን ማለትም ከንፈርን እያንቀሳቀሱ ማንበብ ነው። ይህም ማለት አንባቢው ከንፈሩን እያንቀሳቀሰ እያንዳንዱን ቃል ለራሱ ያነባል ማለት ነው። በተመሳሳይም አንዳንዶች ድምፅ ሳያሰሙ ቃላቱን በአእምሯቸው ውስጥ ይጠሯቸዋል። ይህም ሰብቮካላይዜሽን ተብሎ የሚጠራ ነው። ድምፅ እያሰማንም ሆነ ሳናሰማ የምናደርገው ንባብ በደቂቃ ልናነባቸው የምንችላቸውን ቃላት ቁጥር ይገድብብናል፤ ምክንያቱም የምናነበው በንግግራችን ፍጥነት ብቻ ነው። አማካይ የንግግር ፍጥነት በደቂቃ 125 ቃላት ሲሆን አማካይ የማንበብ ፍጥነት ግን በደቂቃ ከ230–250 ቃላት መሆኑን ተመዝግበው የሚገኙ ማስረጃዎች ያሳያሉ።
ድምፅ እያሰማን ከምናነብበት ፍጥነት በበለጠ ለማንበብ የምንፈልጋቸው ነገሮች ስለሚኖሩ ከንፈርን እያንቀሳቀሱ ማንበብን ልማድ አታድርገው። በዚህ መንገድና ውስጣዊ ድምፅ በማሰማት ስታነብ ከሚኖርህ በተሻለ ፍጥነት ለማንበብ ሞክር። ቃላትን አንድ ላይ ሰብሰብ እያደረግህ ለማንበብ ጣር። እንዲሁም ከንፈር በማንቀሳቀስ ሆነ ቃላቱን በውስጥ በማሰማት የሚደረጉ ንባቦች ነገሩን ለመረዳት እንደሚያግዙ አስተውል።
ይሁን እንጂ ወደ ኋላ እየተመለሱ እንደማንበብ ሁሉ ከንፈርን እያንቀሳቀሱ ማንበብ ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። አንድ ሰው በተለዩ ነጥቦች ላይ በጥልቀት ለማሰላሰል ወይም በአእምሮው ለመቅረጽ ከፈለገ ቃላቱን አሁንም አሁንም መደጋገም ብቻ ሳይሆን በተወሰነ መጠን ድምፅ እያሰማ በውስጡ ማንበብም አስፈላጊ ነው። በአብዛኛው ጊዜ ይህ የሚደረገው “ከንፈርን በማንቀሳቀስ” ወይም ጮክ ብሎ በማንበብ ነው።
የጥንቱ የእስራኤል መሪ ኢያሱም እንደሚከተለው ተብሎ ታዝዞ ነበር:- “ይህ [የአምላክ] ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ መጽሐፉንም በተመስጦ ከንፈርህን እያንቀሳቀስህ ቀንና ሌሊት አንብበው።” ለምን? “በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ ለመፈጸም ጠንቃቃ ትሆን ዘንድ፤ በዚህ ሁኔታ መንገድህ ይቀናልሃል፣ በጥበብም ትመላለሳለህ።” (ኢያሱ 1:8 አዓት] ‘የሕጉን መጽሐፍ’ ድምፅን እያሰሙ ማንበቡ የተነበበውን በአእምሮ ለመቅረጽና በዚያ ያሉትን ሐሳቦች በጥንቃቄ ለማሰላሰል ይረዳል። በመሆኑም ኢያሱ የአምላክ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን እንዴት መመላለስ እንዳለበት ሕጉ በፊቱ የተቀመጠ ያህል ሁልጊዜ ያሳስበው ነበር። በተመሳሳይም ዛሬ ታማኝ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል ማስታወስና በእርሱ ላይ ማሰላሰል ጥበብ እንደሆነ ይገነዘባሉ። በዚህም ምክንያት ዘወትር ያነቡታል። —መዝሙር 103:17, 18፤ ከምሳሌ 4:5 ጋር አወዳድር።
የተሻለ የመረዳት ችሎታን ማዳበር
ግሌን ማየር ብሌይር የተባሉ ሰው ዲያግኖስቲክ ኤንድ ሪሜዲያል ቲቺንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “የሁሉም የንባብ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ዋነኛ ግብ በተማሪዎች በኩል የመረዳት ችሎታን ለማዳበር ነው። ሌሎች ጉዳዮች በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ናቸው።” በመሠረቱ ያነበብከውን መረዳት ማለት ስሜቱን ማግኘት፣ ማስተዋል ማለት ነው። ንባብንም ዋጋማና ጠቃሚ የሚያደርገው ይኸው ነው።
በኒው ዮርክ ኮሌጅ አስተማሪ የሆኑት ሮበርት ክሪክ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ምንጊዜም ቢሆን የመረዳት ችሎታን ለማገዝ በዓላማ ለማንበብ ጣር። ለማንበብ ከመረጥከው ጽሑፍ ውስጥ ምን ለማግኘት እንደምትፈልግ አስቀድመህ ወስን። አንዳንድ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለማወቅ ስትል ለማንበብ ትፈልግ ይሆናል። በሌላ ጊዜ የምታደርገው ንባብ ደግሞ ለመደሰትና ለመዝናናት ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ምንም ዓይነት ቢሆን ጽሑፉን እንደምታነብበት ዓላማና እንደ ጽሑፉ ክብደት የአነባብህን ዓይነት እንደሁኔታው ለዋውጥ። ስታነብ በጥልቀት አስተውል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- “ጸሐፊው ይህንን ያለው ለምንድን ነው? ዓላማው ምን ነበር? የአንቀጹን ዋና ነጥብ ወይም ሐሳብ ለይተህ አውጣ። እኔን እንዴት ይነካኛል? ብለህ ራስህን ጠይቅ። አዎን፤ በዓላማ ማንበብን ልማድህ አድርግ፣ ደስታ ታገኝበታለህ።
በደንብ ለማንበብ መቻል ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል
ተማሪዎችም ሆናችሁ በአንድ ሙያ ሰልጥናችሁ የምትሠሩ፣ የቤት እመቤቶች ወይም የቢሮ ወይም ፋብሪካ ሠራተኞች ጥሩ የንባብ ልማዶች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ጥሩ የማንበብ ልማድ ላላቸው ሰዎች ብዙ በሮች ክፍት ይሆኑላቸዋል።
ጥሩ አንባቢ የሆነ ተማሪ በትምህርቱ ብቃት ያለው ይሆናል፤ እንዲሁም ከትምህርት ቤት ብዙ እንደሚጠቀም ምንም ጥርጥር የለውም። የተሰጠውን የቤት ሥራ ደግሞ ደጋግሞ በማንበብ የሚጠፋውን ጊዜ ያድናል።
በተመሳሳይም ጥሩ የማንበብ ልምድ ያለው በንግድ ወይም በአንድ የተለየ ሙያ የተሰማራ ሰው ረጅም የሆኑ ሪፖርቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አንብቦ ይጨርሳል። ይህም ደግሞ ከታካሚዎቹ፣ ወይም ከደንበኞቹ ጋር የግል ግንኙነት እንዲያደርግ ጊዜ ይሰጠዋል። የተሻለ የንባብ ልማድ ሰፋ ያለ ይዘት ያለው ጽሑፍ ለማንበብ ያስችለዋል። ይህም ሌሎች ከሠሯቸው ሥራዎች፣ ካካሄዷቸው ጥናቶችና ምርምሮች ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቅ ያስችለዋል።
በተሻሻለ የንባብ ችሎታ አማካኝነት በተገኘ ተጨማሪ እውቀት የቤተሰብ ራሶች ብዙውን ጊዜ የሥራና የቤተሰብ ኃላፊነት የመወጣት ችሎታቸውን ማሻሻል ይችላሉ። በብዙ አገሮች መመሪያዎችን፣ ሕጎችንና ተመሳሳይ ሥርዓቶችን ማንበብ መቻል የቤት ውስጥ ኑሮን በተሻለ ሁኔታ ለማካሄድ ያስችላል። የንባብ ችሎታ የቤተሰብን የገንዘብ አጠቃቀምም በተመለከተ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
በማንበብ ብዙ እውቀት ያገኙ የቤት እመቤቶች ቤተሰቡን ጥሩ ምግብ መመገብን፣ ንፅህናን፣ ሕመምን መከላከል ወይም የታመሙትንም መንከባከብን በተመለከተ በተሻለ ሁኔታ መሥራት ይችላሉ። ጥሩ አንባቢ የሆኑ እናቶች ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት ማንበብ እንዲችሉ በማስተማር ሊሳካላቸው ይችላል።—በእንግሊዝኛው የንቁ መጽሔት በሚያዝያ 22, 1968 ገጽ 20–22 ላይ ያለውን ተመልከት።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥሩ አድርጎ የሚያነብ ሰው ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ዘልቆ የሚያልፍ ሕይወት ለማግኘት የሚያበቃ ዕውቀት እንኳ ሊያገኝ ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዚህን የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ በተመለከተ የተነገሩት ትንቢቶች ዛሬ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው። በምድር ላይ በገነት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ የፈጣሪያችንንና የዓላማዎቹን እውቀት ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ በዮሐንስ 17:3 ላይ እንዲህ ብሏል:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላከኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”
እንግዲያው ለመግባት ፈቃደኛ ለሆነ ለማንኛውም ሰው ወደ ዕውቀትና የደስታ ዓለም የሚወስደው በር ያለምንም ጥርጥር ክፍት ነው። ቁልፉ ንባብ ነው። አዎን፣ በደንብ ማንበብን ቻል፤ ይህም በር ሁልግዜ ክፍት ይሆንልሃል!
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምታነበውን መጽሐፍ መራጭ ሁን