የሚያስፈልጋቸውን አመራር ስጧቸው
ልጆቻችሁ ራሳቸውን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከሚሄደው የዚህ ዓለም የሥነ ምግባር ብልግና እንዴት ሊጠብቁ ይችላሉ? ከዚህ ሊጠበቁ የሚችሉበትን መንገድ የሚያገኙት አንድ የወጣቶች ቡድን በአራተኛ ደረጃ የሚገኝ ስለ ወሲብ መረጃ የምናገኝበት ዋነኛ ምንጭ ነው ካሉት ከቴሌቪዥን አይደለም። አስተማሪዎች የሚያስተምሯቸው ትምህርቶች የዚህን ዓለም ተለዋዋጭ ሥነ ምግባራዊ ደረጃዎችና እሴቶች ከሚያንጸባርቁት ትምህርት ቤቶችም ማግኘት አይችሉም። እንዲሁም የልጆቻችሁ የትምህርት ቤት ጓደኞች ከሚያወሩላቸው ወሬ ሊያገኙ እንደማይችሉ የተረጋገጠ ነው።
ስለ ሥነ ምግባርና ስለ ቤተሰብ አኗኗር የሚሰጡ ትምህርቶች የተሳካ ውጤት እንዲያስገኙ ከተፈለገ ትምህርቱ ከቤት መጀመር ይኖርበታል። ጉዳዩ ያሳሰባቸው አንድ የሁለተኛ ደረጃ መምህር እንደተናገሩት “‘ልጆች፣ ብትቆዩ ምንም የምትጎዱበት ነገር አይኖርም!’ ለማለት የሚደፍር ሰው ያስፈልጋል።”
ይህን ነገር ለልጆቻችሁ አስተምራችኋል? በወሲባዊ ጽሑፎችና ፊልሞች በተጥለቀለቅንበት በዚህ ጊዜ ምንና እንዴት እንደምታስተምሩ ግራ የምትጋቡበት ጊዜ ይኖራልን?
ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚያስገኘው ውጤት
የወላጆቻችሁ አኗኗር በእናንተ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳደረ ሁሉ የእናንተም ምሳሌነት የልጆቻችሁን አኗኗር በብዙ መንገድ ይነካል። ምን ያህል እንደምትወዷቸውና ምን ዓይነት ሰዎች እንዲሆኑ እንደምትፈልጉ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።
ራሳችሁ በድንግልና ቆይታችሁ ያገባችሁ ከሆነ ይህ ምን ያህል አስደስቷችሁ እንደነበረ ለልጆቻችሁ ማሳወቅ ትችላላችሁ። አንድ አያት (ወንድ) ከ60 ዓመት በፊት የገዛ ራሳቸው አባት በጋብቻቸው ላይ ጥቁር ነጥብ ሊጥል የሚችል የሥነ ምግባር ብልግና ሳይፈጽሙ ማግባታቸው ምን ያህል እንዳስደሰታቸው የነገሯቸውን ቀን ያስታውሳሉ። እኚህ አያት ከአባታቸው ጋር ያደረጉት ይህ ጭውውት በአኗኗራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። የእርሳቸውም ምሳሌነት በልጆቻቸው አኗኗር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳደረ ያምናሉ።
ልጆቻችሁ የወጣትነት አኗኗራችሁ በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ እንዳልነበረ የሚያውቁ ከሆነ ግን አኗኗራችሁን የለወጣችሁበትን ምክንያት እንዲያውቁ ማድረግ ይኖርባችኋል። የተለወጣችሁት በዕድሜ በመብሰላችሁ ብቻ ሳይሆን ከዚያ የተሻለ አኗኗርና የሥነ ምግባር ደረጃ ስላገኛችሁ እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል።
ጥሩ አድማጭ መሆን
የተሳካላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ለማዳመጥ በርከት ያለ ጊዜ እንደሚመድቡ ይናገራሉ። በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ በመፈጸም ላይ ያሉትን ነገሮች ያውቃሉ። ካረን ሁልጊዜ ከሰዓት በኋላ በወጥ ቤት ውስጥ እየሠራች ለመቆየት እቅድ ታወጣ ነበር። ይህን በማድረግዋ ሴት ልጆችዋ ወደ ቤት ሲመጡ በቀኑ ውስጥ በትምህርት ቤታቸው ምን እንዳጋጠማቸው ለመነጋገር ይችሉ ነበር።
ኧርሊን ልጆችዋ ከትምህርት ቤት የሚመጡበትን ጊዜ ጠብቃ ያደረጉትን ነገር ሁሉ ሲነግሯት ታዳምጥ ነበር። “መታረም የሚያስፈልገው ነገር ከኖረ ለእርማቱ ሌላ ጊዜ እደርስበታለሁ። ባላዳምጥ ኖሮ እንዲህ ያለው ነገር መፈጠሩን እንኳን አላውቅም ነበር” ትላለች። ሴት ልጆችዋ ተማሪዎች በነበሩበት ጊዜም ይሁን ለጋብቻ ለመጠናናት በሚቀጣጠሩበት ጊዜ ይህ የንግግር መስመር እንዳይቋረጥ አድርጋ ቆይታለች። በዚህ መንገድ ከልጆቻችሁ ጋር የምታሳልፉት ጊዜ በኋላ ላይ ከብዙ ችግር ያድናችኋል።
ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ የማይናገሩ ከሆኑስ? እንደዚያ ከሆኑ ራሳችሁን ‘በተፈጥሮአቸው ዝምተኞች ስለሆኑ ነው ወይስ ከዚህ በፊት ባደረግኩት ነገር ምክንያት ያጋጠማቸውንና ያደረጉትን ነገር ለእኔ ለመግለጽ ስለሚፈሩ ነው? አሁን ከልብ እንደማስብላቸው በማሳየት በእኔ ላይ ያላቸውን ትምክህት ለማሳደግ ልዩ ጥረት ለማድረግ እችላለሁን? አሁን ቀለል ያሉ ነገሮችን እንዲነግሩኝና ሲውል ሲያድር ደግሞ ይበልጥ ከባድ የሆኑ ነገሮችን እንዲገልጡልኝ ላደፋፍራቸው እችላለሁን?’ ብላችሁ ጠይቁ።
በጣም አስፈላጊ የሆኑ ማስጠንቀቂያዎች
ልጆቻችሁ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶች ስለሚያስከትሏቸው ውጤቶች ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል የሚያዳምጡት ነገር ከዚህ የተለየ ቢሆንም ማንኛውም ዓይነት የእርግዝና መከላከያ መቶ በመቶ አስተማማኝ እንዳልሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል። የእርግዝና መከላከያ መድኃኒት በሚወሰድበት ጊዜ እንኳን እርግዝና ሊኖርና በሩካቤ ሥጋ የሚተላለፍ በሽታ ሊይዝ ይችላል። ፕላንድ ፓረንትሁድ የተባለው ድርጅት እንዳለው ኮንዶሞች 12 በመቶ እርግዝና ለመከላከል ሳይችሉ ሲቀሩ ከኤድስ ቫይረስ ለመከላከል ያልቻሉበት ጊዜ ግን ከዚህ በእጅጉ ይበልጣል።
ብዙ ወጣቶች በእነርሱ ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንደማይደርስ እርግጠኛ የሆኑ ይመስላል። ይሁን እንጂ በሩካቤ ሥጋ የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ኤድስን ጨምሮ፣ ገና ምንም ዓይነት የበሽታ ምልክት ከማይታይባቸውና ሌሎችን በመበከል ላይ እንዳሉ ከማያውቁ ሰዎች ሊተላለፉ ይችላሉ። በዛሬው ጊዜ በወጣቶች ላይ እንደወረርሽኝ ከተዛመቱት ከእነዚህ በሽታዎች ብዙዎቹ መካንነት፣ አካለ ጎደሎ ልጅ መውለድ፣ ካንሰርና ሞት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ጊዜ 40 ሚልዮን የሚያክሉ አሜሪካውያን የአባለ ዘር ኸርፐስ በተባለውና ምንም ዓይነት መድኃኒት ባልተገኘለት በሽታ እንደተለከፉ ይታመናል። በዚህ በሽታ የተለከፉ እናቶች በሽታውን ለልጆቻቸው ሊያስተላልፉ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት እነዚህ ንጹሐን ሕፃናት የአእምሮ ጉድለት ወይም ሊድን የማይችል የነርቭ ቀውስ ኖሯቸው ይወለዳሉ፣ ወይም የውስጥ አካሎቻቸው በበሽታው በመመረዛቸው ምክንያት ይሞታሉ። ታዲያ ገና ለገና ይገኛል ተብሎ ለሚታሰብ ቅጽበታዊ ደስታ ይህን ያክል አሠቃቂ ኪሣራ መክፈል ምክንያታዊ ነውን?
እንዲያውም ለዚህ በሽታ መተላለፍ ምክንያት የሆነው ሕገ ወጥ ወሲብ ምንም ዓይነት ደስታ ያልተገኘበት ሊሆን ይችላል። ለብዙ ወጣቶች ቃለ መጠይቅ ያደረገ አንድ ተመራማሪ “ሴቶች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ከፈጸሟቸው ወሲባዊ ድርጊቶች መካከል ጠብቀውት የነበረውን ደስታ ያስገኘላቸው ካላስገኘላቸው በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ ተናግሯል።” ወላጆች ፈጣሪያችን ይህች የተዋበች ምድራችን በሰዎች እንድትሞላ ብሎ ያዘጋጀውና አስደናቂ የሆነው ሩካቤ ሥጋ ከጋብቻ ክልል ውጭ በሆነ አሳፋሪ ሁኔታ መጀመር እንደማይኖርበት ለልጆቻቸው አበክረው ማስረዳት ይኖርባቸዋል።
በተለይ የሚያስፈልጋቸው ትምህርት
ልጆቻችሁ ከጋብቻ ውጭ ከሚፈጸም ሩካቤ ሥጋ የሚመጡትን ችግሮች ለማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛውና እርግጠኛው መንገድ ለረዥም ዘመናት ተፈትኖ የተረጋገጠውንና አምላክ የደነገገውን መሠረታዊ ሥርዓት መጠበቅ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? ከጋብቻ በፊት ሩካቤ ሥጋ አለመፈጸም፣ ከዚያም ሌላ ወሲባዊ ጓደኛ ከማያውቅ ተወዳጅ ሰው ጋር ዘላቂና የዕድሜ ልክ ቁርኝት መሥርቶ በታማኝነት መኖር ነው።
ይሁን እንጂ ከዝሙት የምንሸሽበት መሠረታዊ ምክንያት ፈጣሪያችን ስህተት ነው ማለቱ እንጂ ችግር ማስከተሉ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከዝሙት ራቁ’፣ “ከዝሙት ሽሹ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። ለምን? ምክንያቱም እንደነዚህ ያሉትን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ሰዎች “የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”— 1 ተሰሎንቄ 4:3፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10, 18
አምላካዊ ሥርዓቶችን መከተል ይበልጥ ደስተኛና እርካታ ያለው ኑሮ እንድንኖር ያስችለናል። በሩካቤ ሥጋ ከሚተላለፉ በሽታዎች፣ ከማይፈለጉ እርግዝናዎች፣ በነጠላ ወላጆች ምክንያት ከሚመጡ የቤተሰብ ችግሮች፣ ለስስት ዓላማቸው ከተጠቀሙብን በኋላ ከሚተዉን ሰዎች ከሚመጣብን የስሜት ቁስል ይጠብቀናል።
የጥንቱ የአምላክ ነቢይ የጻፋቸው የሚከተሉት ቃላት ከ2,500 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ እውነተኛ መሆናቸው ተረጋግጧል:- “እኔ የሚረባህን የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”— ኢሳይያስ 48:17, 18
ይሁን እንጂ ይህ የሥነ ምግባር ሥርዓት በዘመናችን ከተስፋፋው ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ አብሮ የመዋል ልማድ ጋር የሚስማማው እንዴት ነው? ቀጥሎ ይህ ጥያቄ ይብራራል።