አኗኗርህ ምን አደጋ ሊያስከትል ይችላል?
በጤና ረገድ ያሉት አዝማሚያዎች በብዙ መልኩ ሲታዩ ተስፋ ሰጪ ሆነው አልተገኙም። የዓለም የጤና ድርጅት (ደብሊው ኤች ኦ) በ1998 ያወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ዛሬ ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ብዙ ሰዎች ቢያንስ ቢያንስ አነስተኛ የጤና እንክብካቤ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃና የፍሳሽ ማስወገጃዎች ማግኘት ችለዋል።” እርግጥ ነው፣ ከዓለም ሕዝብ መካከል አብዛኛው አሁንም በድህነት የሚማቅቅ ነው። ሆኖም የብሪታንያ የዜና ማሰራጫ አገልግሎት ድርጅት “ድህነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀደም ሲል ከነበሩት 500 ዓመታት በበለጠ ባለፉት 50 ዓመታት በእጅጉ ቀንሷል” ሲል ዘግቧል።
የዓለም የጤና አጠባበቅ ዘዴ ዕድገት ማሳየቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጅ አማካይ ዕድሜ ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ አድርጓል። በ1955 የነበረው አማካዩ የሰው ዕድሜ 48 ዓመት ነበር። በ1995 ዕድገት አሳይቶ 65 ዓመት ደርሷል። ለዚህ አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ልጆችን የሚያጠቁትን በሽታዎች በመከላከል ረገድ መሻሻል መታየቱ ነው።
ከ40 ዓመታት በፊት በዓለም ዙሪያ ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 40 በመቶዎቹ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ነበሩ። በ1998 ግን ብዙዎቹ የዓለማችን ሕፃናት ክትባት በመውሰዳቸው ልጆችን የሚያጠቁ ዋና ዋና በሽታዎችን መቋቋም ችለዋል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የሚሞቱት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ቁጥር ቀንሶ በዓለም ዙሪያ ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 21 በመቶ ሆኗል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ “ይበልጥ ጤናማና ረጅም ዕድሜ መኖር የሚቻልበት አዝማሚያ እንደታየ ምንም ጥርጥር የለውም።”
እርግጥ ነው፣ ደረጃው ምንም ያህል መሻሻል ያልታየበት ረጅም ሕይወት ትርጉም የሌለው ድል ይሆናል። የተሻሉ የኑሮ ሁኔታዎች ለመፍጠር በሚል ብዙ ሰዎች ለቁሳዊ ተድላዎች ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር የራሱ የሆኑ የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።
የተሻለ አኗኗር ሊባል ይችላልን?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታዩት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች በሰዎች አኗኗር ላይ ከፍተኛ ለውጦች አምጥተዋል። በአሁኑ ጊዜ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ቀደም ሲል ባለጠጋዎች ብቻ ሊያገኟቸው የሚችሉትን ነገሮችና ግልጋሎቶች ማግኘት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ከእነዚህ እድገቶች መካከል አንዳንዶቹ ረጅም ሕይወት የመኖር ተስፋን ያሳደጉት ቢሆንም ብዙ ሰዎች መልሶ የራስን ሕይወት በሚጎዳ አኗኗር ተማርከዋል።
ለምሳሌ ያህል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያላቸውን ከፍተኛ የመግዛት አቅም አደገኛ ዕፆችን፣ አልኮልንና ትምባሆን የመሳሰሉ አላስፈላጊ ነገሮች ለመግዛት ይጠቀሙበታል። የዚህ ሁሉ መጨረሻው ምን እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም። “በዓለማችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው የጤና ጠንቅ በሽታ ሳይሆን የምርት ውጤት ነው” ሲል ዎርልድ ዎች የተባለው መጽሔት ገልጿል። አክሎም “በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰው ልጅ ጤና ላይ ስጋት በመፍጠር ረገድ በኢንፌክሽን በሽታዎች ምትክ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የሚይዘው በትምባሆ ሳቢያ የሚመጣ ሕመም ነው” ብሏል። በተጨማሪም ሳይንቲፊክ አሜሪካን እንዲህ ብሏል:- “ሰውን ለሞት ከሚዳርጉት የካንሰር በሽታዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት በሲጋራ ጦስ የሚከሰቱ ሲሆን የአኗኗር ሁኔታም በተለይ ደግሞ የአመጋገብ ልማድና በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ በእኩል ደረጃ ለካንሰር ያጋልጣል።”
የአኗኗር ምርጫችን በጤናችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ ጤናችንን መጠበቅ ወይም ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው? ጥሩ የአመጋገብ ልማድና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቂ ነው? ከዚህ በተጨማሪ አእምሯዊና መንፈሳዊ ነገሮች በጤናማ አኗኗር ረገድ ምን ሚና ይጫወታሉ?