የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 4/15 ገጽ 4-6
  • አምላክ የምታቀርበውን ጸሎት ይሰማልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ የምታቀርበውን ጸሎት ይሰማልን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተሰሚነት ያገኙ ጸሎቶች
  • ለጸሎት የሚሰጠው መልስ
  • አምላክ እንደሚሰማህ እርግጠኛ ሁን
  • መልስ የሚያገኙት የእነማን ጸሎቶች ናቸው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • መግቢያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2021
  • ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 4/15 ገጽ 4-6

አምላክ የምታቀርበውን ጸሎት ይሰማልን?

አንድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንድን ጉዳይ ሌላ ሰው ወክሎ ለማስፈጸም ወይም ራሱ ለመፈጸም ሊወስን ይችላል። በተመሳሳይም የጽንፈ ዓለሙ ልዑል ገዢ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ምን ያህል ተካፋይ መሆን እንዳለበት ለመወሰን መብት አለው። ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ጸሎታችንን በመስማት በግል ጉዳዮቻችን ተካፋይ ለመሆን እንደመረጠ በመንገር ጸሎታችንን ለእርሱ እንድናቀርብ ያዙናል።​—መዝሙር 66:19፤ 69:13

በዚህ ጉዳይ ላይ አምላክ ያደረገው ምርጫ ሰብአዊ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡአቸው ጸሎቶች ያለውን የግል ስሜት ያሳያል። ሕዝቦቹ ለሚያሳስባቸውና ለሚያስጨንቃቸው ጉዳይ ሁሉ ወደ እርሱ እንዳይቀርቡ በማባረር ፈንታ “ሳታቋርጡ ጸልዩ”፣ “በጸሎት ጽኑ”፣ “ትካዜህን በይሖዋ ላይ ጣል”፣ “የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉት” በማለት አጥብቆ ያሳስባቸዋል።​—1 ተሰሎንቄ 5:17፤ ሮሜ 12:12፤ መዝሙር 55:22፤ 1 ጴጥሮስ 5:7

አምላክ ለአገልጋዮቹ ጸሎት ትኩረት የማይሰጥ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነቱን ወደ እርሱ የመቅረብ ሁኔታ ባላመቻቸና በዚህም መብት በነፃ እንዲጠቀሙበት ባላበረታታ ነበር። እንግዲያውስ አምላክ ራሱን ለሕዝቦቹ ይህን ያህል ተቀራቢ ለማድረግ መምረጡ በእርግጥ ጸሎትን እንደሚሰማ ለመተማመን የሚያስችል አንድ ምክንያት ነው። አዎ፣ አምላክ እያንዳንዱን የአገልጋዮቹን ጸሎት በትኩረት ያዳምጣል።

አምላክ ጸሎትን እንደሚሰማ በግልጽ የሚያመለክተው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሊዘነጋ የማይገባው ነው። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ዮሐንስ “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል” በማለት ጽፎአል። (1 ዮሐንስ 5:14) ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ አምላክ “ጸሎት ሰሚ” መሆኑን በመጥቀስ በእርግጠኛነት “ቃሌንም ይሰማኛል” ብሏል።​—መዝሙር 55:17፤ 65:2

ስለዚህ መጸለይ ራሱ የሚሰጣቸው ጥቅሞች እንዳሉ ባያጠራጥርም አንድ ጻድቅ ሰው በሚጸልይበት ጊዜ ከእነዚህ ሥነ ልቦናዊ ጥቅሞች የበለጠ ነገር ያገኛል። ምክንያቱም እርሱ በሚጸልይበት ጊዜ የሚያዳምጠው አንድ አካል አለ። እርሱም አምላክ ነው።​—ያዕቆብ 5:16-18

ተሰሚነት ያገኙ ጸሎቶች

መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎቶቻቸው በተሰሙላቸውና መልስም ባገኙ ሰዎች ታሪክ የተሞላ ነው። የእነዚህ ሰዎች ተሞክሮ የጸሎት ጥቅም አንድ ሰው ሐሳቡን በየፈርጁ ለያይቶ በቃላት ለመግለጽ በመቻሉ ከሚያገኘው የፈዋሽነት ውጤት አልፎ የሚሄድ መሆኑን ያረጋግጣሉ። የጸሎት ጥቅም አንድ ሰው ከጸሎቱ ጋር በመስማማት በሚያደርጋቸው የግል ጥረቶች የተወሰነ አይደለም።

ለምሳሌ ያህል ንጉሥ ዳዊት ልጁ አቤሴሎም የእሥራኤልን ንግሥና ለመንጠቅ ባሴረበት ጊዜ “አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)] የአኪጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጥ እለምንሃለሁ!” በማለት ጸልዮ ነበር። በወቅቱ የአኪጦፌል ምክር “የእግዚአብሔርን ቃል እንደመጠየቅ ስለነበረች” ዳዊት በጸሎቱ ላይ ያቀረበው ልመና ቀላል አልነበረም። ከዚያ በኋላ አቤሴሎም ንጉሥ ዳዊትን ለመገልበጥ አኪጦፌል ያቀረበለትን ብልሃት ሳይቀበል ቀረ። ለምን? “[ይሖዋ (አዓት)] በአቤሴሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የአኪጦፌልን ምክር እንዲበትን አዘዘ።” በግልጽ እንደሚታየው ዳዊት ያቀረበው ጸሎት ተሰምቶለት ነበር።​—2 ሳሙኤል 15:31፤ 16:23፤ 17:14

በተመሳሳይም ሕዝቅያስ ሕይወቱን ሊቀጭበት ከነበረው ሕመሙ እንዲያድነው አምላክን በተማጸነ ጊዜ ተፈውሷል። ይህ ሊሆን የቻለው ሕዝቅያስ ስለጸለየ ባገኘው ሥነ ልቦናዊ ምክንያት ነበርን? በእርግጥ አልነበረም! ለሕዝቅያስ በኢሳይያስ በኩል የተላከለት የይሖዋ መልእክት “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ እፈውስሃለሁ” የሚል ነበር።​—2 ነገሥት 20:1-6

ከጠበቀው ጊዜ በላይ ዘግይቶ ጸሎቱ የተመለሰለትን ዳንኤል የይሖዋ መልአክ “ቃልህ ተሰምቶአል” በማለት አረጋግጦለታል። እንደ ሀና፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ የመሳሰሉት ሌሎች ሰዎች ጸሎቶችም በሰብአዊ ችሎታ እንደተገኙ ሊታሰብ በማይችልባቸው መንገዶች መልስ አግኝተዋል። እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ጸሎቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው፣ እንደሚሰሙና መልስም እንደሚያገኙ በግልጽ ያስተምራል።​—ዳንኤል 10:2-14፤ 1 ሳሙኤል 1:1-20፤ ሥራ 4:24-31፤ 10:1-7

ይሁንና አምላክ በዛሬው ጊዜ ለታማኝ አገልጋዮቹ ጸሎቶች መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው?

ለጸሎት የሚሰጠው መልስ

ከላይ የተጠቀሱት ጸሎቶች በአስደናቂና ተአምራዊ በሆኑ መንገዶች መልስ ያገኙ ናቸው። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እንኳን ለጸሎቶች የሚሰጡ መልሶች ሁልጊዜ በግልጽ የማይታዩ እንደነበሩ አስታውሱ። ይህ የሆነበት ምክንያት የጸሎቶቹ መልሶች የአምላክን አገልጋዮች በጽድቅ መንገድ ላይ እንዲጸኑ የሚያስችል የሞራል ጥንካሬና ማስተዋል ከመስጠት ጋር የተያያዙ ስለነበሩ ነው። በተለይም ክርስቲያኖች ለሚያቀርቡአቸው ጸሎቶች የሚሰጡ መልሶች አስደናቂና ተአምራዊ ሥራዎችን የሚመለከቱ ሳይሆኑ ይበልጥ መንፈሳዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ናቸው።​—ቆላስይስ 1:9

ስለዚህ ጸሎትህ ሁልጊዜ አንተ በምትጠብቀው ወይም በምትመርጠው መንገድ ስላልተመለሰልህ ተስፋ አትቁረጥ። ለምሳሌ ያህል አምላክ አንድን ፈተና ከማስወገድ ይልቅ እንድትጸና “ከተለመደው በላይ የሆነ ኃይሉን” ሊሰጥህ ይመርጥ ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:17) አምላክ የሚሰጠንን የዚህ ዓይነቱን ኃይል ጥቅም አቃልለን መመልከት የለብንም። ወይም ደግሞ ይሖዋ ጸሎታችንን ጭራሽ አልመለሰልንም ብለን መደምደም የለብንም።

የአምላክ ልጅ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ አምላክን እንደሚሳደብ ሰው ተቆጥሮ መሞቱ በጣም ስላሳሰበው “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” በማለት ጸልዮ ነበር። ይህ ጸሎት በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት አግኝቷልን? በዕብራውያን 5:7 ላይ እንደተረጋገጠልን አዎን ተሰምቶለታል። ይሖዋ ልጁን በስቃይ እንጨት ላይ ከመሞት አላዳነውም። በዚህ ፈንታ “ከሰማይ መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው።”​—ሉቃስ 22:42, 43

ታዲያ ይህ አስደናቂ የሆነና ተአምራዊ መልስ ነበርን? በእኛ በሰዎች አመለካከት ሊሆን ይችላል! የብርቱ ኃይል ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ግን ተአምር አልነበረም። ኢየሱስም ቀድሞ በሰማይ ይኖር ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ መላእክት ለሰዎች ይገለጡ እንደነበር ያውቅ ስለነበር መልአክ ለእርሱ መታየቱ በእኛ ላይ የሚኖረውን ያህል አስደናቂ የሆነ ውጤት አይኖረውም። የሆነ ሆኖ ኢየሱስን ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ጀምሮ ያውቀው የነበረው ይህ መልአክ ኢየሱስን ከፊቱ ይጠብቀው የነበረውን ፈተና እንዲቋቋም አጠንክሮታል።

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉትን አገልጋዮቹን ጸሎት በመመለስ ለመጽናት የሚያስችላቸውን ብርታት ይሰጣቸዋል። ይህ ለመጽናት የሚያስችል ድጋፍ የሚመጣው በግል አብረናቸው ከምንሰበሰብ የአምልኮ ባልደረቦቻችን በሚሰነዘር ማበረታቻ አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ታዲያ የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑ መሰሎቻችን የእኛ ዓይነት ፈተና አጋጥሟቸው ስለማያውቅ እኛን ለማበረታታት አይችሉም ብለን የሚሰጡንን ማበረታቻ እንንቅ ይሆንን? ኢየሱስም ሊያበረታው ስለመጣው መልአክ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይችል ነበር። በዚህ ፈንታ ማበረታቻውን ለይሖዋ ያቀረበው ጸሎት ምላሽ እንደሆነ አድርጎ በመቀበል የአባቱን ፈቃድ በታማኝነት ለመፈጸም ችሏል። እኛም ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ የሚሰጠንን ማበረታቻ በደስታ ለመቀበል እንፈልጋለን። እንዲሁም በትዕግሥት በመጽናት የምናሳልፋቸውን ጊዜዎች አብዛኛውን ጊዜ ከመጠን ያለፈ ብዙ በረከቶችን አስከትለው እንደሚመጡ አስታውሱ።​—መክብብ 11:6፤ ያዕቆብ 5:11

አምላክ እንደሚሰማህ እርግጠኛ ሁን

ለጸሎትህ አፋጣኝ ምላሽ ሳታገኝ ብትቀር ጸሎት ስለሚያስገኘው ውጤት ጥርጣሬ አይግባህ። ከጭንቀት እፎይታ ለማግኘት ወይም ለአምላክ በሚቀርበው አገልግሎት ተጨማሪ ኃላፊነት ለማግኘት የሚቀርቡ አንዳንድ ጸሎቶች በአምላክ አስተያየት ተገቢና ጥሩ የሆነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ መልስ ሳያገኙ ይቆዩ ይሆናል። (ሉቃስ 18:7, 8፤ 1 ጴጥሮስ 5:6) በግልህ በጥልቅ ስለሚያሳስብህ ጉዳይ እየጸለይህ ከሆነ ፍላጎትህ ኃይለኛ እንደሆነና የልብህ ግፊትም ንጹሕና እውነተኛ መሆኑን ለአምላክ ለማሳየት በጸሎትህ ጽና። ያዕቆብ ከአንድ መልአክ ጋር ለረዥም ሰዓቶች ከታገለ በኋላ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” በማለቱ በረከትን ለመቀበል የነበረው ፍላጎት ኃይለኛ መሆኑን አሳይቷል። (ዘፍጥረት 32:24-32) እኛም ባለማቋረጥ ከለመንን በጊዜው በረከትን እንደምንቀበል የያዕቆብ ዓይነት እርግጠኛነት ሊኖረን ይገባል።​—ሉቃስ 11:9

በመጨረሻም ሊታሰብበት የሚገባ አንድ ጉዳይ አለ። በጽንፈ ዓለሙ ልዑል የበላይ ገዢ ዘንድ ተሰሚነት ማግኘት ውድ መብት ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ ይሖዋ አምላክ በቃሉ አማካኝነት ስለ ብቃቶቹ ሲነግረን በጥንቃቄ እናዳምጣለንን? ጸሎቶቻችንን ከፈጣሪያችን ጋር በጣም ወደ መቀራረብ የሚያመጡን እንደመሆናቸው መጠን ለእኛ ሊነግረን ለሚፈልገው ነገር ሁሉ ከፍ ያለ ትኩረት ለመስጠት እንፈልጋለን።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የሚቀርቡለትን ፀሎቶች ይሰማል። እኛስ በቃሉ በኩል የሚነግረንን እንሰማለንን?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ