የአንባብያን ጥያቄዎች
የይሖዋ ምሥክሮች የተሰረቁ እቃዎችን ስለመግዛት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?
ክርስቲያኖች በምንም ዓይነት የተሰረቁ ሸቀጣ ሸቀጦችን ወይም እቃዎችን እያወቁ አይገዙም።
መስረቅ ስህተት ነው። ለእስራኤላውያን የተሰጠው የአምላክ ሕግ ቁርጥ ባለ አነጋገር “አትስረቅ” ይላል። (ዘጸአት 20:15፤ ዘሌዋውያን 19:11) አንድ ሌባ ሲሰርቅ ቢያዝ እንደ ሁኔታው ሁለት ዕጥፍ፣ አራት ዕጥፍ ወይም አምስት እጥፍ እንዲከፍል ይደረግ ነበር።
ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሌቦች እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጥፋተኞች እንዳይሆኑና ፈጣን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የሰረቋቸውን እቃዎች ቶሎ ብለው ለመሸጥ ይሞክራሉ። በዚህም ምክንያት የሰረቁትን እቃ ለብዙ ገዥዎች በሚያጓጓ ቀላል ዋጋ ይሸጣሉ። በዘጸአት 22:1 ላይ የተገለጸው እንዲህ ያለ ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም። “ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅ፣ ቢያርደው ወይም ቢሸጠው በበሬው ፈንታ አምስት በሬዎች፣ በበጉም ፋንታ አራት በጎች ይክፈል” ይላል።
ራባይ አብርሃም ቺል እንደነዚህ ያሉ ሕጎች ሊኖራቸው የሚችለውን ትርጉም በመረዳት እንዲህ ብለዋል፦ አንድን የተሰረቀ ንብረት የተሰረቀ መሆኑ ባይታወቅም እንኳን መግዛትም ሆነ መቀበል የተከለከለ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው አንድን ፍየል ከእረኛ እጅ መግዛት የለበትም። ምክንያቱም እረኛው የሚሸጠው አሰሪው ሳያውቅ ገንዘቡን ለራሱ ለማድረግ አስቦ ሊሆን ይችላል።”—ሚትዝቮት—ትዕዛዛቶችና ማብራሪያቸው
የአምላክ ቃል አንድ እረኛ የአሠሪውን ፍየል ሠርቆ በመሸጥ የማይገባውን ገንዘብ ለራሱ ሊያደርግ ስለሚችል ከእረኛ ፍየል አትግዛ በማለት በቀጥታ አይከለክልም። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች ሻጩ የራሱ ንብረት ያልሆነውን ወይም የሰረቀውን የሚሸጥ ከመሰላቸው እያወቁ የሽያጩ ተባባሪዎች መሆን አይገባቸውም። አምላክ የግልን ንብረት የባለቤትነት መብት እንደሚያከብር የአምላክ ሕግ ያሳያል። ሌብነት ደግሞ ይህንን የባለቤትነት መብት የሚያሳጣ ነው። አንድ የተሠረቀ ዕቃ የሚገዛ ሰው ሌባ ላይባል ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ የተሰረቀውን እቃ መግዛቱ የእቃው ባለቤት ንብረቱን እንደገና የማግኘቱን አጋጣሚ ያመነምንበታል።—ምሳሌ 16:19፤ ከ1 ተሰሎንቄ 4:6 ጋር አወዳድር።
ሸማቾች፣ የቤት እመቤቶችም ይሁኑ የኩባንያ የዕቃ ግዥ ሠራተኞች ሸቀጦችን በተቻለ መጠን በርካሽ ዋጋ ለመግዛት እንደሚፈልጉ ሁላችንም እናውቃለን። በዓለም በሙሉ የሚገኙ ሴቶች ርካሽ ሸቀጦች የሚሸጡባቸውን ቦታዎች ይፈልጋሉ፣ የሸቀጦች ዋጋ የሚቀንስባቸው ወራት እስኪደርሱ ድረስ ሽመታቸውን ያዘገያሉ፣ የዋጋ ቅናሽ ለማግኘት ሲሉም ሸቀጦች በጅምላ ከሚሸጡባቸው ቦታዎች ይገዛሉ። (ምሳሌ 31:14) ይሁን እንጂ ርካሽ ሸቀጥ ለማግኘት የሚደረገው ይህን የመሰለ ሙከራ የሥነ ምግባር ገደብ ሊደረግለት ይገባል። በነህምያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ታማኝ ሰዎች በርካሽ ዋጋ ለመግዛት ቢችሉም እንኳን በሰንበት ቀን ሸቀጥ ከመግዛት ይርቁ ነበር። (ነህምያ 10:31፤ ከአሞጽ 8:4-6 ጋር አወዳድር።) ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለስርቆት ያላቸው ጥላቻ እንደተሠረቁ በግልጽ የሚታወቁ ዕቃዎችን በርካሽ ዋጋ ከመግዛት ሊጠብቃቸው ይገባል።
የተሰረቁ እቃዎችን እንደሚሸጡ የሚታወቁ ሻጮች ሊኖሩ ይችላሉ። ወይም በሹክሹክታ የሚነገረው ዋጋ በጣም ዝቅተኛ ከሆነ ማንኛውም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው የሚሸጠው ዕቃ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ እንደሆነ በቀላሉ ሊገነዘብ ይችላል። የአንዳንድ አገሮች ሕግ እንኳን ይህን የመሰለ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይደነግጋል። አንድ የሕግ ሥነ ሥርዓት መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦
“ተከሳሹ ንብረቱ በማን ወይም ከማን እንደተሠረቀ፣ መቼ ወይም የት እንደተሠረቀ ወይም እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተሠረቀ በዝርዝር ማወቁ አስፈላጊ አይደለም። የተሠረቀ ንብረት መሆኑን ማወቁ ብቻውን በቂ ነው። . . . አንዳንድ ፍርድ ቤቶች ተከሳሹ ዕቃውን ያገኘው ማንም ተራ የማስተዋል ችሎታና ጥንቃቄ ያለው ሰው የተሠረቀ ዕቃ ነው ብሎ ሊያስብ በሚችልበት ሁኔታ ከሆነ የወንጀሉ ተባባሪ ነው ብለው ያስባሉ።”
ይህ ክርስቲያኖች የተሰረቁ እቃዎችን ከመግዛት እንዲርቁ የሚገፋፋቸው ጠንካራ የሆነ ተጨማሪ ምክንያት ነው። አንድ ክርስቲያን እንደነዚህ ያሉትን የተሰረቁ እቃዎች ቢገዛ ሕግ ተላላፊ ይሆናል። ብዙ ሰዎች የማይከሰሱ መስሎ ከታያቸው ሕግ ከማፍረስ ወደ ኋላ አይሉም። “በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች” ለመገዛት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ግን እንዲህ አያደርጉም። ሕግ አክባሪ መሆናቸው በወንጀል ድርጊት ከመከሰስ ይጠብቃቸዋል። በይሖዋም ፊት ጥሩ ሕሊና እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።—ሮሜ 13:1, 4, 5
የአምላክ ወዳጅ የነበረው አብርሃም ሕሊናውን በማክበር ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። በሚኖርበት ዘመን አራት የምስራቅ ነገሥታት ሎጥ ይኖርበት በነበረው ምድር የነበሩትን ነገሥታት በጦርነት አሸንፈው ብዙ ውድ እቃዎችን ዘረፉ። አብርሃም ተከትሎአቸው በመሄድ ጠላቶቹን አሸንፎ የተሰረቁትን እቃዎች አስመለሰ። የሰዶም ንጉሥ ግን ሽልማት እንዲሆነው “ከብቶቹን ግን ለአንተ ውሰድ” አለው። አብርሃም ግን ከመውሰድ ይልቅ ለሕጋዊ ባለቤታቸው መልሶ “አንተ አብርሃምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል . . . ለአንተ ከሆነው ሁሉ” አልወስድም አለ።—ዘፍጥረት 14:1-24
ክርስቲያኖች የተሰረቁ እቃዎችን በመውሰድ ሊገኝ የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት የገንዘብ ጥቅም አይፈልጉም። ኤርምያስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “በማታለል ገንዘብ የሚሰበስብ ሰው ያልጣለችውን እንቁላል ታቅፋ እንደምትፈለፍል ቆቅ ነው።” (ኤርምያስ 17:11 የ1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ስለዚህ ክርስቲያኖች የተሰረቁ እቃዎችን በሚመለከት የቄሳርን ሕጎች ላለማፍረስ ጥበብ ከማሳየታቸውም በላይ በሥርቆት ድርጊቶች በማንኛውም መንገድ ተካፋዮች እንዳይሆኑ በመጠንቀቅ የአምላክን የፍትሕ ሕግ ጠብቀው ለመኖር ይፈልጋሉ። ዳዊት “ለጻድቅ ያለው ጥቂት ከብዙ ከኃጢአተኞች ሀብት ይበልጣል” ማለቱ ትክክል ነው።—መዝሙር 37:16