ገነት ወይስ የቆሻሻ መጣያ—የቱን ትመርጣለህ?
ገነት በምትመስል ውብ ደሴት ላይ ዕረፍት ለማድረግ በመፈለግና በፀሐይ ብርሃን ለመደሰት በጉጉት ላይ ያለ አንድን አውሮፓዊ ሰው አይቶ ሰውየው አውሮፓዊ ቱሪስት ነው ከማለት በቀር ሌላ ሥራ አለው የሚል ማንም አይኖርም። የባሕሩን ዳርቻ የሚያዋስኑትን ሰፋፊ የአሸዋ ክምሮች አቋርጦ ሲሄድ የተጣሉ ጠርሙሶች፣ ቆርቆሮዎች፣ ከፕላስቲክ የተሠሩ የዕቃ መያዣዎች፣ የማስቲካና የከረሜላ መጠቅለያዎች፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች ባሉበት ቆሻሻ መካከል በጥንቃቄ መንገዱን እየመረጠ ማለፍ ነበረበት። እዚህ ለመምጣት ስል የተጓዝኩበት ገነት ይህ ነውን? ብሎ በማሰብ እንደሚበሳጭ ግልጽ ነው።
ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሞህ ያውቃልን? ሰዎች ገነት መሰል በሆነ ስፍራ የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ አስበው እዚያ ከደረሱ በኋላ ግን ቦታውን ገነት ሳይሆን የቆሻሻ መጣያ ሲያስመስሉት ሕሊናቸው ቅር የማይለው ከሆነ ወደዚህ ቦታ ለመሄድ ለምን ያልማሉ?
“ገነት” በሚመስሉ ቦታዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም
በግልጽ የሚታየው ይህ የውበት፣ የጽዳትና የንጽሕና ችላ መባል ብዙ ቱሪስቶች ለሚጎርፉባቸው “ገነት” መሰል ቦታዎች ብቻ የተወሰነ ነገር አይደለም። ዘመናዊው ኅብረተሰብ በሁሉም ቦታ በአካባቢ መበከል መቅሰፍት እየተሰቃየ ነው ለማለት ይቻላል። ብዙ የንግድ ፋብሪካዎች በብዙ ኩንታል የሚመዘን ቆሻሻዎችን በመጣል በከፍተኛ ሁኔታ ብክለት ያደርሳሉ። በአግባቡ ያልተወገዱ ጎጂ ቆሻሻዎችና ሳይታሰብ ባሕር ላይ ከመርከብ የሚፈሰው ዘይት የምድራችንን ሰፊ ክፍል እንዳያበላሹና ለማንኛውም ዓይነት ሕይወት የማይስማማ እንዳያደርጉት ስጋት ፈጥረዋል።
ጦርነቶችም ብክለት ያደርሳሉ። ዓለም በፍርሃት ሲመለከተው የነበረው የ1991ዱ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት በብክለቱ ላይ አንድ ደረጃ ጨምሮለታል። የኢራቅ የጦር ኃይሎች 600 የሚያህሉ የዘይት ጉድጓዶችን በእሳት አያይዘው ነበር። አንድ የአውሮፓ ጋዜጣ ሁኔታውን ሲገልጽ እርምጃው ኩዌትን “የሲኦል ቃጠሎ ራእይ” የሚታይባት አስመስሏት ነበር ብሏል። ጊኦ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እቶኑን “እስከ ዛሬ በሰው እጅ ከደረሱት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ የአካባቢ መቅሰፍት” በማለት ገልጾታል።
ጦርነቱ እንዳበቃ ወዲያውኑ የማጽዳት ሥራ ተጀመረ። የሚነድዱትን የዘይት ጉድጓዶች ማጥፋቱ እንኳን ብዙ ወራት የፈጀ ከባድ ሥራ ነበር። የዓለም የጤና ድርጅት የደረሰው የብክለት ጭማሪ በኩዌት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር 10 በመቶ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ሪፖርት አድርጓል።
አደገኝነታቸው አነስተኛ ቢሆንም የሚያውኩ ነገሮች
በእያንዳንዱ ታላቅ የአካባቢ ብክለት ቁጥር ልክ በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች አነስተኛ የአካባቢ ብክለቶችን ለመጥቀስ ይቻላል። ቆሻሻን በየቦታው የሚጥሉና በግድግዳዎች ላይ የተለያዩ ጽሑፎች የሚጽፉና የሚለጥፉ “አርቲስቶች” የሚያደርሱት ብክለት አነስተኛ ቢሆንም ፕላኔቷ ምድር ገነት እንዳትሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
በአንዳንድ ቦታዎች በግድግዳ ላይ የተለያዩ ጽሑፎች መጻፍና መለጠፍ በጣም ከመለመዱ የተነሳ ነዋሪዎቹ እነዚህን ነገሮች ትኩረት ሰጥተው ስለማይመለከቷቸው ያሉ መስሎ አይታያቸውም። እንደነዚህ ዓይነት ጽሑፎች በምድር ውስጥ ለውስጥ በሚጓዙ መኪናዎች ላይ፣ በሕንፃ ግድግዳዎች ላይና በሕዝብ ስልክ መደወያ ቤቶች ላይ ይገኛሉ። በሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ላይ ብቻ መጻፋቸው ቀርቷል።
አንዳንድ ከተሞች ባረጁና ዖና በሆኑ ሕንፃዎች የተሞሉ ናቸው። የመኖሪያ አካባቢዎች በቆሸሹ ቤቶችና ግቢዎች መልካቸው ተበላሽቷል። የተሰበሩ መኪናዎች ክምችት፣ የተጣሉ ማሽኖችና የተሰባበሩ ዕቃዎች ክምር በጣም ውብ መሆን ይችሉ የነበሩ የእርሻ ማሳዎችን መልክ አጥፍቷል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ሰውነታቸው ስለማደፉና ስለመቆሸሹ የማይጨነቁ ይመስላል። በአለባበስና በአበጣጠር ዝርክርክ ሆኖ መታየት ተቀባይነት ያለው ብቻ ሳይሆን ፋሽን ሆኗል። ጽዱና ንጹሕ መሆንን የሚወድዱ ሰዎች ምንም የመለወጥ ተስፋ እስከማይኖራቸው ድረስ ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ።
እንዴት ያለ ከፍተኛ ሥራን የሚጠይቅ ነው!
ትልልቅ ከተሞችን፣ ትንንሽ ከተሞችንና እርሻዎችን እንዲሁም ሰዎችን ራሳቸውን የመለወጡን ጉዳይ ሳንጠቅስ የምድራዊ ቤታችንን የባሕር ዳርቻዎች፣ ደኖችና ተራራዎች አንጸባራቂና ለስላሳ በሆኑት የቱሪዝም መጽሔቶች ላይ እንደሚወጡት የገነት ሥዕሎት እንዲመስሉ አድርጎ ለመለወጥ እንዴት ያለ ከፍተኛ የጽዳት ዘመቻ ያስፈልጋል!
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቱሪስት በዚያ ቀን ወደ ኋላ ላይ አንድ የጽዳት ሠራተኞች ቡድን ወደ አካባቢው በመሄድ ትልልቆቹን ቆሻሻዎች ሲያስወግድ በማየቱ ተደስቶ ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል ትንንሽ የመስተዋት ስብርባሪዎችን፣ ቆርኪዎችን፣ በቆርቆሮ የታሸጉ ምግቦች ወይም መጠጦች መክፈቻዎችንና በጣም ብዙ የሲጋራ ቁርጥራጮችን ይተዋሉ። ስለዚህ ከጽዳቱ በኋላም ቢሆን ቦታው ከገነትነት ይልቅ ከቆሻሻ መጣያ ጋር ይበልጥ የሚመሳሰልባቸው በጣም ብዙ ሁኔታዎች ነበሩ።
ፕላኔቷ ምድራችንን ዓለም አቀፍ የቆሻሻ መጣያ ከመሆን ለማዳን የሚደረግ ዓለም አቀፍ የጽዳት ዘመቻ እነዚህን ሁሉ ጠራርጎ ማጥፋትን የሚጠይቅ ነው። እንዲህ ያለ የጽዳት ዘመቻ የሚከናወን ለመሆኑ አንዳች ተስፋ ይኖር ይሆን? ካለስ የሚከናወነው እንዴት ነው? የጽዳቱንስ ዘመቻ የሚያካሂደው ማን ነው? መቼ?