የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 2/15 ገጽ 4-6
  • ከልብና ከአእምሮ ውስጥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከልብና ከአእምሮ ውስጥ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክን ዓይነት አመለካከት መያዝ
  • ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለብን?
  • መንፈሳዊ የጽዳት ዘመቻ
  • ወደፊት በምትኖረው ንጹሕ ምድር ተደሰት!
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ገነት ወይስ የቆሻሻ መጣያ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንጽሕና ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ንጽሕና—ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 2/15 ገጽ 4-6

ከልብና ከአእምሮ ውስጥ ብክለትን ነቅሎ ማውጣት

ይሖዋ የሰው ልጆችን የቆሻሻ ወይም የዝርክርክነት ምኞት አላሳደረባቸውም። ፕላኔቷ መኖሪያቸው ንጽሕና፣ ሥርዓትና ውበት ያላት ገነት እንድትሆን የታቀደች ነበረች። አምላክ እየተበላሸች ሄዳ ለዓይን የምታስቀይም የቆሻሻ መጣያ እንድትሆን ዓላማው አልነበረም። — ዘፍጥረት 2:​8, 9

ይሁን እንጂ ሰዎች መለኮታዊ አመራርን አንቀበለም ካሉ በኋላ የራሳቸውን የዓለም ሥርዓት መገንባት ጀመሩ። አንድ ነገር ላይ ለመድረስ መለኰታዊ ጥበብና የሕይወት ተሞክሮ ስላልነበራቸው ነገሮች ጥሩ ወይም መጥፎ መሆናቸውን በሙከራ ለማወቅ ተገደዱ። የዓለም ታሪክ ሰዎች በተሳካ መንገድ ራሳቸውን ለመምራት እንደማይችሉ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አረጋግጧል። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:​9 አዓት፤ ኤርምያስ 10:​23) በዛሬው ጊዜ በልዩ ልዩ መልክ የሚታየው የብክለት ችግር የሰዎች አግባብ የሌለው አገዛዝ ያስከተለው ውጤት ነው።

የአምላክን ዓይነት አመለካከት መያዝ

አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ፈጣሪ ባወጣቸው የንጽሕና የአቋም ደረጃዎች መሠረት ለመኖር ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። በ1991 አጋማሽ ላይ ቼኮዝሎቫኪያ ውስጥ በፕሬግ ከተማ የይሖዋ ምስክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ለማድረግ ሲያቅዱ በዚህ መንገድ ችግር ገጥሟቸው ነበር።a ስትራሆቭ ስታድየም በበቂ ሁኔታ ሊያስተናግደው የሚችል ወደ 75,000 የሚጠጋ ሕዝብ ይሰበሰባል። ነገር ግን ስታድየሙ ለአምስት ዓመት ማንም ሳይጠቀምበት ቆይቶ ነበር። ባለመጠገኑና በአየር ጠባይ ምክንያት በመጎዳቱ ለዓይን ያስቀይም ነበር። 1,500 የሚሆኑ የይሖዋ ምስክሮች ስታድየሙን በማደስና እንደገና ቀለም በመቀባት ከ65,000 ሰዓታት በላይ አጥፍተዋል። ይህ የጽዳት ዘመቻ በስብሰባው ጊዜ ስታድየሙ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሊመለክ የሚቻልበት ቦታ እንዲሆን አስችሎታል።

ጠቅላላው ዓለም ለንጽሕናና ለሥርዓት አነስተኛ ግምት እየሰጠ ባለበት ጊዜ የይሖዋ ምስክሮች የተለዩ እንዲሆኑ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው? ልዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ክርስቲያኖች እንደ ራስ ወዳድነት፣ ለሌላው አለማሰብ፣ ስስትና የፍቅር ጉድለት ያሉትን አፍራሽ ባሕርያት ማጥፋት እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ስለሚቀበሉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና” በማለት ይናገርና “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል [ትክክለኛ አዓት ] እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው” ተኩበት ይላል። ንጽሕናን፣ ሥርዓታማነትንና ውበትን የያዙ ባሕርይ አካባቢን ለማቆሸሽ ለሚገፋፉ ዝንባሌዎች ምንም ቦታ የለውም። — ቆላስይስ 3:​9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:​1፤ ፊልጵስዩስ 4:​8፤ ቲቶ 2:14

አዲሱ ሰውነት ክርስቲያኖች ሆነ ብለው አካባቢያቸውን እንዳይበክሉ ወይም መንግሥታት የደነገጓቸውን ብክለትን የሚከላከሉ ሕግጋት በቸልተኝነት ሳይታዘዙ እንዳይቀሩ በማድረግ ብክለትን በተመለከተ ጠንቃቆች እንዲሆኑ ይጠይቅባቸዋል። ክርስቲያኖች በየመንገዱ ቆሻሻ እንዲጥሉ የሚያደርግ ግድ የለሽነት፣ የራስ ወዳድነትና የስንፍናን ዝንባሌ እንዲያስወግዱ ይረዳቸዋል። ለሌሎች ንብረት አክብሮት ማሳየታቸው በግድግዳ ላይ የተለያዩ ጽሑፎች መጻፍን ወይም መለጠፍን ሀሳብን የመግለጫ መንገድና ክፋት የሌለበት ጨዋታ ወይም ስዕል የመሳል ሌላ አማራጭ መንገድ አድርገው እንዳይጠቀሙበት ያግዳቸዋል። አዲሱ ሰውነት ቤቶችን፣ መኪናዎችን፣ ልብሶችንና ገላቸውን ንጹሕ አድርገው እንዲይዙ ይጠይቅባቸዋል። — ከያዕቆብ 1:​21 ጋር አወዳድር።

ይህንን አዲስ ሰውነት ለመልበስ ፈቃደኛ ያልሆኑት ሰዎች አምላክ በሚያመጣት ገነት ውስጥ ሕይወት እንዳያገኙ ቢከለክላቸው በእርሱ ላይ ሊያማርሩ ይችላሉን? በፍጹም አይችሉም። በልቡ ወይም በአእምሮው ውስጥ የተደበቀ አካባቢን የመበከል ዝንባሌ ያለው ማንኛውም ሰው እንደገና ገነት የሆነችውን ምድር ውበት ያበላሽ ይሆናል። ይህም ገነትን ለመንከባከብ ለሚፈልጉ ሰዎች ትልቅ ሐዘን ያመጣባቸዋል። አምላክ ምድርን የሚያጠፏትን ለማጥፋት ያደረገው ውሳኔ ጻድቅና ፍቅራዊ ነው። — ራእይ 11:​18፤ 21:​8

ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለብን?

ይሁን እንጂ ይህ ማለት ክርስቲያኖች ብክለትን የሚከላከሉ ወይም የቆሸሹትን አካባቢዎች የማጽዳት ዘመቻዎችን እንዲያራምዱ ይፈለግባቸዋል ማለት ነውን?

ብክለት ጤንነትንና የሕዝብን ደኅንነት እጅግ የሚጎዳ መሆኑ ግልጽ ነው። ለእስራኤላውያን ከሰጠው ሕግ ለመመልከት እንደምንችለው ይሖዋ ስለእነዚህ ጉዳዮች ያስባል፤ ተገቢም ነው። (ዘጸአት 21:​28–34፤ ዘዳግም 22:​8፤ 23:​12–14) ነገር ግን ወደ ሌሎች አሕዛብ እየዞሩ የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ አሳምነው አቋማቸውን እንዲያስለውጡ መመሪያ የሰጠበት አንድም ጊዜ አልነበረም። የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም እንዲህ እንዲያደርጉ አልተነገራቸውም።

በዛሬው ጊዜ የአካባቢ ደኅንነት ጉዳዮች በቀላሉ ፖለቲካዊ መከራከሪያ ነጥቦች ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ የአካባቢ ችግሮችን ለማቃለል ተብለው የተቋቋሙ ናቸው። ፖለቲካዊ መሥመር የያዘ ክርስቲያን ደግሞ በፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ አይሆንም። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ደንግጓል። ይህን ደንብ ችላ የሚል ክርስቲያን “ከሚሻሩት የዚህ የነገሮች ሥርዓት ገዦች” ጋር ተባባሪ የመሆን አደጋ ተደቅኖበታል። — ዮሐንስ 17:​16፤ 1 ቆሮንቶስ 2:​6 አዓት

ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት ማኅበራዊ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ ለማስገኘት አልሞከረም፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህንን እንዲያደርጉ አልነገራቸውም። ለነሱ የሰጣቸው ትዕዛዝ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋቸውንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ነበር። የአካባቢ ፖሊሲዎችን በሚመለከት አላዘዛቸውም። — ማቴዎስ 28:​19, 20

በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው ስለሚገባው ነገር ሲያብራራ ክርስቶስ እንዲህ አለ:- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ።” (ማቴዎስ 6:​33) ይሖዋ በመሢሐዊት መንግሥቱ አማካኝነት የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያስከብርበት ጊዜ የአካባቢ ችግሮች ሁሉንም በሚያረካ መንገድ ለዘለቄታው መፍትሔ ያገኛሉ።

ስለዚህ የይሖዋ ምስክሮች ሚዛናዊ አቋም ይይዛሉ። ሮሜ 13:​1–7 ከሚናገረው አንፃር መንግሥታት አካባቢን ለመቆጣጠር የሚያወጧቸውን ሕግጋት በጥንቃቄ ማክበር ግዴታቸው ነው። በተጨማሪም ለጎረቤት ያላቸው አምላካዊ ፍቅር የሌሎችን ንብረት ባለማጥፋትና ቆሻሻን እጃቸው እንዳመጣላቸው ባለመጣል ለሕዝብ ወይም ለግል ንብረት አክብሮት እንዲያሳዩ ይገፋፋቸዋል። ነገር ግን በሚወሰዱት ዓለማዊ የጽዳት እርምጃዎች የመሪነቱን ቦታ አይዙም። ከሁሉ በፊት የሚያስቀድሙት ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት መስበክ ነው። ይህም ተገቢ ነው። ምክንያቱም ዘላቂ ጥቅም ማምጣት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ይህ መሆኑን ያውቃሉ።

መንፈሳዊ የጽዳት ዘመቻ

የጥንት እስራኤላውያን ደምን በማፍሰስ፣ የብልግና አኗኗር በመከተል ወይም ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አክብሮትን ባለማሳየት የምድሪቱ መበከል ስለሚያስከትለው መዘዝ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘኁልቁ 35:​33፤ ኤርምያስ 3:​1, 2፤ ሚልክያስ 1:​7, 8) ምናልባት ጥፋተኞች ሆነውበት ሊሆን ቢችልም የተወገዙት አካላዊ ብክለትን ሳይሆን መንፈሳዊ ብክለትን በተመለከተ እንደሆነ ግልጽ ነው።b

እንግዲያው ዛሬ አንድ ክርስቲያን በመጀመሪያ ደረጃ ለማስወገድ መጣጣር የሚገባው መንፈሳዊ ብክለትን ወይም እድፈትን ነው። ይህንንም ማድረግ የሚችለው የመበከልን ዝንባሌ ከልብና ከአእምሮ ውስጥ ነቅሎ የሚያወጣውን “አዲሱን ሰውነት” በመልበስ ነው። ከአራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምስክሮች በራሳቸው ላይ ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ የጽዳት ዘመቻ በማድረግ ከዚህ መንፈሳዊ ንጽሕና እንዲሁም ጎልቶ ከሚታይ አካላዊ ንጽሕና ጥቅም እያገኙ ነው። — ኤፌሶን 4:​22–24

መንፈሳዊ የጽዳት ዘመቻ የሚደረግበት ጊዜ ዛሬ ነው። ዓለም አቀፋዊ የሆነ አካላዊ የጽዳት ዘመቻ በጊዜው ይከተላል። ለምድር የሚገባትን ከብክለት ነፃ የሆነ የአካባቢ ሁኔታ በመስጠትም ቤታችንን ዓለም አቀፍ የቆሻሻ መጣያ ከመሆን ያድናታል። — መክብብ 3:1

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ ምሥራቅ አውሮፓ ስብሰባዎች ዝርዝር ሪፖርት ለማግኘት የታኅሳስ 22, 1991ን ንቁ! ተመልከት።

b እስራኤላውያን ብረት የማቅለጥን ሥራ ለምደው ነበር። ከመዳብ ማዕድን ማውጫ ቦታዎቻቸው የአንዳንዶቹ ቅሪት ተገኝቷል። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ለማዘጋጀት ሲባል መዳብ ይቀልጥ ነበር። (ከ1 ነገሥት 7:​14–46 ጋር አወዳድር) ይህ የማቅለጥ ሂደት በጭስ፣ በሚነጠርበት ጊዜ ከላይ በሚንሳፈፉ ቆሻሻዎችና በዝቃጮች መልክ የተወሰነ መጠን ያለው ብክለት ሳይፈጥር ይከናወን ነበር ማለት ሊሆን የማይችል ነገር ይመስላል። ሆኖም ይሖዋ አነስተኛ የሕዝብ ብዛት ባለበትና ገለልተኛ በሆነው አካባቢ ሊኖር የሚችለውን ቆሻሻ ችሎ ለማለፍ ፈቃደኛ እንደነበር ግልጽ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ