የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 1/15 ገጽ 24-29
  • አምላክን ከሚፈሩ ጋር መሰብሰብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክን ከሚፈሩ ጋር መሰብሰብ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘አምላክን ፍሩ ትእዛዛቱንም ጠብቁ’
  • ‘በአምላካዊ ፍርሃት ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ’
  • “አምላክን ፍሩ ክብርንም ስጡት”
  • ይሖዋን በመፍራት ደስታ ማግኘትን መማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ይሖዋን የሚፈራ ልብ ይኑርህ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ይሖዋን ፍሩ ቅዱስ ስሙንም አክብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • እውነተኛውን አምላክ መፍራት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 1/15 ገጽ 24-29

አምላክን ከሚፈሩ ጋር መሰብሰብ

“ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በየትም ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች ከፍርሃት ነፃ የሚሆኑበትን ማለትም ዓመፅን፣ ሥራ አጥነትንና ከባድ ሕመምን ከመፍራት የሚገላገሉበትን ጊዜ ሲናፍቁ ኖረዋል። እኛም ይህን ጊዜ እንናፍቃለን። . . . ታዲያ ፍርሃትን እንዴት እንደምንኮተኩት የምንወያየው ለምንድን ነው?” በ1994 ሰኔ ላይ በጀመረው በእያንዳንዱ “አምላካዊ ፍርሃት” የወረዳ ስብስባ ላይ የስብሰባውን አጠቃላይ መልእክት የሚገልጸውን ንግግር ያቀረበው እያንዳንዱ ተናጋሪ ይህን ስሜት ቀስቃሽ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

በመጀመሪያ በሰሜን አሜሪካ፣ ቀጥሎም በአውሮፓ፣ በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በእስያና በባሕር ደሴቶች በስብሰባው ላይ የተገኙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ፍርሃት መኮትኮት የሚችሉበትን መንገድ ለመማር ጓጉተው ነበር። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ አምላክ ለሕዝቦቹ ከሚሰጣቸው በረከቶች መካፈላችን የተመካው አምላካዊ ፍርሃት ያለን በመሆናችን ላይ ስለሆነ ነው። ተሰብሳቢዎቹ አንድ ላይ የተሰባሰቡት ስለ አምላካዊ ፍርሃት ለመማር ሲሆን በሦስቱ ቀናት ፕሮግራምም ስለዚህ አስፈላጊ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ብዙ ተምረዋል።

‘አምላክን ፍሩ ትእዛዛቱንም ጠብቁ’

በመክብብ 12:13 ላይ የተመሠረተው የመጀመሪያው ቀን ስብስባ አጠቃላይ መልእክት ይህ ነበር። አምላክን መፍራት ማለት ምን ማለት ነው? በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ክፍል ላይ የስብሰባው ሊቀመንበር አምላካዊ ፍርሃት ለይሖዋ ያለንን ፍርሃት የተቀላቀለበት ታላቅ አክብሮትም ሆነ እሱን ላለማሳዘን የምናሳየውን ጤናማ ፍርሃት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገለጸ። ይህ ዓይነቱ አምላካዊ ፍርሃት የሚያርበደብድ አይደለም፤ ጤናማና ተገቢ የሆነ ፍርሃት ነው።

ይህ ጤናማ ፍርሃት የሚጠቅመን እንዴት ነው? “ዝላችሁ ጉዞአችሁን አታቁሙ” የሚል ርዕስ ያለው ተከታዩ ንግግር አምላካዊ ፍርሃት የአምላክን ትእዛዛት በደስታ እንድንጠብቅ እንደሚያነሳሳን ገለጸ። ለአምላክና ለሰዎች ካለን ፍቅር ጋር ተዳምሮ ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ሲኖረን መንፈሳዊ ኃይል ይሞላብናል። አዎን፣ አምላካዊ ፍርሃት ለዘላለም ሕይወት በሚደረገው ሩጫ ወደ ኋላ እንዳንቀር ይረዳናል።

ቀጥሎ በፕሮግራሙ ላይ የቀረቡት አምላካዊ ፍርሃት እንደሚደግፈን የሚያረጋግጡ ሕያው ማስረጃዎች የታዩባቸው ቃለ ምልልሶች ነበሩ። ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየታቸው የሰዎች ፍላጎት ማጣት፣ ግድ የለሽነት ወይም ስደት ቢያጋጥማቸውም በአገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ እንዴት እንደገፋፋቸውና በግል ከባድ ፈተና ቢደርስባቸውም እንዲጸኑ እንደረዳቸው ተናገሩ።

ታዲያ አንዳንድ ሰዎች አምላካዊ ፍርሃት ሲኖራቸው ሌሎች የሌላቸው ለምንድን ነው? “አምላካዊ ፍርሃትን መኮትኮትና ጥቅሙን ማግኘት” በተባለው ንግግር ላይ የስብሰባውን አጠቃላይ መልእክት የሚገልጸውን ንግግር ያቀረበው ተናጋሪ በኤርምያስ 32:37–39 ላይ አምላክን የሚፈራ ልብ እሰጣችኋለሁ ብሎ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ቃል እንደገባ ገለጸ። ይሖዋ በልባችን ውስጥ አምላካዊ ፍርሃትን ይተክላል። እንዴት? ይህን የሚያደርገው በቅዱስ መንፈሱና በመንፈስ አነሳሽነት ባስጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል ለማጥናትና ካዘጋጀልን የተትረፈረፉ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ልባዊ ጥረት ልናደርግ እንደሚገባ ግልጽ ነው። ከእነዚህም መካከል እሱን መፍራትን እንድንማር የሚረዱን ትልልቅ ስብሰባዎቻችንና የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ይገኙበታል።

የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የተከፈተው በይሖዋና በቃሉ መተማመን እንደሚገባ በሚያሳስብ ምክር ነበር። ከዚያ በመቀጠልም ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን መንግሥቱ በምን ዋና ዋና መንገዶች ሕይወታችንን ሊነካ እንደሚገባ ማብራሪያ ተሰጠ።

ከዚያም በስብሰባው ላይ ከቀረቡት ሦስት ሲምፖዝየሞች መካከል የመጀመሪያው ቀረበ። በቤተሰብ ላይ የሚያተኩረው የዚህ ሲምፖዚየም አጠቃላይ መልእክት “አምላካዊ ፍርሃት መለኮታዊ ግዴታዎችን እንድንታዘዝ ይገፋፋናል” የሚል ነበር። ከቀረበው ቅዱስ ጽሑፋዊና ተግባራዊ ምክር ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦

□ ለባሎች፦ አምላካዊ ፍርሃት አንድን ወንድ ሚስቱን እንደ ራሱ አካል አድርጎ እንዲወዳት ሊገፋፋው ይገባል። (ኤፌሶን 5:28, 29) አንድ ሰው ሆነ ብሎ የራሱን አካል አይጎዳም፣ በጓደኞቹ ፊት ራሱን አያዋርድም ወይም ስለ ራሱ ድክመቶች እያነሣ ራሱን አይተችም። ስለሆነም ሚስቱንም ልክ ራሱን በሚይዝበት መንገድ በአክብሮት መያዝ አለበት።

□ ለሚስቶች፦ ኢየሱስ የነበረው አምላካዊ ፍርሃት ‘ዘወትር አምላክን እንዲያስደስት’ ገፋፍቶታል። (ዮሐንስ 8:29) ይህ ሚስቶች ባሎቻቸውን በተመለከተ ሊኮርጁት የሚገባ ጥሩ መንፈስ ነው።

□ ለወላጆች፦ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ከይሖዋ እንደተገኙ ውርሻዎች በመቁጠር የወላጅነት ኃላፊነቶችን በቁም ነገር ሲወጡ አምላካዊ ፍርሃትን ሊያሳዩ ይችላሉ። (መዝሙር 127:3) የወላጆች የመጀመሪያ ግብ ልጆቻቸውን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ መሆን አለበት።

□ ለልጆች፦ ይሖዋ ልጆች ‘ለወላጆቻቸው በጌታ’ እንዲታዘዙ ያስተምራቸዋል። (ኤፌሶን 6:1) ስለዚህ ወላጆቻቸውን መታዘዝ አምላክን መታዘዝ ማለት ነው።

የቀኑ የመጨረሻ ንግግር ሁላችንም የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ የሚሰማንን ጥልቅ ስሜት የሚዳስስ ስለነበር ስሜትን በጣም የሚነካ ነበር። ይሁንና ንግግሩ ሊጋመስ ሲል ድንገት አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ተናጋሪው የምትወደው ሰው ሲሞት የተባለው አዲስ ብሮሹር እንደወጣ በማስታወቅ አድማጮችን አስደሰታቸው። ይህ 32 ገጽ ያለው ባለ ሙሉ ቀለም ጽሑፍ በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎች የሚወዱት ሰው ሲሞት የሚከሰተውን ስሜት እንዲረዱና እንዲቋቋሙ ሊረዳ የሚችል ብዙ ሐሳብ ይዟል። ዘመዱ ወይም ወዳጁ የሞተበትን ሰው ለማጽናናት የምትለው ጠፍቶብህ ያውቃልን? የዚህ ብሮሹር አንዱ ክፍል በሐዘን ላይ ያሉትን እንዴት ልንረዳቸው እንደምንችል ያብራራል። ብዙ አድማጮች ተናጋሪው ሲናገር እየሰሙ በዚህ አዲስ ብሮሹር ማንን ሊጠቅሙ እንደሚችሉ ያስቡ ነበር።

‘በአምላካዊ ፍርሃት ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ’

በዕብራውያን 12:28 ላይ የተመሠረተው የሁለተኛው ቀን አጠቃላይ መልእክት ይህ ነበር። በጠዋቱ ፕሮግራም ወቅት “ይሖዋን በመፍራት የሚመላለሱ ጉባኤዎች” የሚል ርዕስ ያለው ሁለተኛው ሲምፖዝየም ቀረበ። የመጀመሪያው ክፍል ያተኮረው በስብሰባ ላይ ስለ መገኘት ነበር። በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ለአምላክና ለመንፈሳዊ ዝግጅቶቹ ያለንን አክብሮት ያሳያል። በስብሰባ ላይ በመገኘት ስሙን እንደምንፈራና ከፈቃዱ ጋር ለመስማማት እንደምንጓጓ እናሳያለን። (ዕብራውያን 10:24, 25) ሁለተኛው ተናጋሪ ጉባኤው ባጠቃላይ ይሖዋን በመፍራት እንዲመላለስ እያንዳንዱ ግለሰብ ዘወትር መልካም ጠባይ ይዞ በመኖር የበኩሉን ማድረግ እንዳለበት ገለጸ። የመጨረሻው ተናጋሪ የሁሉም ክርስቲያኖች መብትና ግዴታ ስለሆነው ነገር ማለትም ያለማሰለስ ምሥራቹን ማወጅን በተመለከተ ንግግር አደረገ። መስበካችንን የምንቀጥለው እስከ መቼ ነው? ይሖዋ ይበቃል እስኪል ድረስ።—ኢሳይያስ 6:11

አሁን በዚህ መጽሔት ላይ በወጡት በጉባኤ የሚጠኑ ርዕሶች ላይ የተሸፈነው “የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ ነው” የሚለው ርዕስ የቀጣዩ ንግግር አጠቃላይ መልእክት ነበር። (ነህምያ 8:10) የይሖዋ ሕዝቦች ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው? ተናጋሪው በአጭር በአጭሩ ብዙ ምክንያቶችን ገለጸ። በምድር ላይ ካሉት ሰዎች በሙሉ ይበልጥ ደስተኞች የሚያደርገን አንዱና ዋነኛው ነገር ከአምላክ ጋር ያለን የተቀራረበ ዝምድና ነው። እስቲ አስቡት፤ ይሖዋ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ካቀረባቸው ሰዎች መካከል የመሆን መብት አግኝተናል በማለት ተናጋሪው አድማጮቹን አሳሰባቸው። (ዮሐንስ 6:44) ይህ እንድንደሰት የሚያነሳሳን እንዴት ያለ ኃይለኛ ምክንያት ነው!

በየትኛውም ትልቅ ስብሰባ በጣም የሚያስደስተው ነገር ጥምቀት ነው። “አምላካዊ ፍርሃት” የተባሉት የወረዳ ስብስባዎችም ከዚህ የተለዩ አልነበሩም። “ይሖዋን በመፍራት የሚከናወን ራስን መወሰንና ጥምቀት” በተሰኘው ንግግር ላይ ተናጋሪው እያንዳንዱ የተጠመቀ ግለሰብ ያሉበት ግዴታዎች አራት መሆናቸውን እንዲህ ሲል ገለጸ፦ (1) የአምላክን ቃል እንድንረዳውና በሥራ ላይ እንድናውለው በሚረዱን ጽሑፎች አማካኝነት ማጥናት አለብን፤ (2) መጸለይ አለብን፤ (3) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከመሰል አማኞች ጋር መገናኘት አለብን፤ (4) ለይሖዋ ስምና መንግሥት መመሥከር አለብን።

የቅዳሜ ከሰዓት በኋላው ፕሮግራም “ይሖዋ የማይተወው ሕዝብ” የሚል አጽናኝ ርዕስ ባለው ንግግር ጀመረ። ከሠላሳ አምስት መቶ ዘመናት በፊት የእስራኤል ሕዝብ አስቸጋሪ ጊዜያት ሲያጋጥሙት ይሖዋ በሙሴ በኩል “አምላክህ እግዚአብሔር . . . አይጥልህም፣ አይተውህም” የሚል ዋስትና ሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም 31:6) ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡና ሲወርሷት እስራኤላውያንን በመጠበቁ ይሖዋ የሰጠው ዋስትና እውነተኛ መሆኑን አስመስክሯል። ዛሬ እኛም ብንሆን አስቸጋሪ ፈተናዎች ሲገጥሙን ከእሱ ጋር እስከተጣበቅንና የቃሉን ምክር እስከሠራንበት ድረስ ይሖዋ እንደማይተወን ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መደሰት የምትችለው እንዴት ነው? “በየቀኑ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብቡ” በተባለው ንግግር ላይ ተናጋሪው የሚመራመር አእምሮ በመያዝና እንደነዚህ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ማንበብ ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ አቅርቧል፦ ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ባሕሪዎችና መንገዶች ምን ያስተምረኛል? በነዚህ ነገሮች ረገድ ይበልጥ ይሖዋን ልመስል የምችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ ማንበብ አስደሳችና አርኪ ነው።

ቀጥሎ “ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎችን ለመርዳት የተደረጉ ዝግጅቶች” የሚል ርዕስ ባለው የፕሮግራሙ ሦስተኛ ሲምፖዚየም ላይ ትኩረት ተደረገ። ይሖዋ በአሁኑ ወቅት ላሉት አገልጋዮቹ ብሎ ተአምር ባይሠራም እሱን የሚፈሩትን እንደሚረዳ እሙን ነው። (2 ጴጥሮስ 2:9) ይህ ሲምፖዚየም በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ይሖዋ እኛን ለመርዳት ያዘጋጀልንን የሚከተሉትን አራት ዝግጅቶች ዳስሷል፦ (1) ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ከአቅማችን በላይ የሆኑ ሥራዎችን እንድንሠራ ኃይል አስታጥቆናል። (2) በቃሉ አማካኝነት ምክርና መመሪያ ይሰጠናል። (3) በቤዛው አማካኝነት ንጹሕ ሕሊና ሰጥቶናል። (4) ሽማግሌዎችን ጨምሮ በድርጅቱ አማካኝነት መመሪያ ይሰጠናል፤ እንዲሁም ጥበቃ ያደርግልናል። (ሉቃስ 11:13፤ ኤፌሶን 1:7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ ዕብራውያን 13:17) በእነዚህ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለመጽናት እንችላለን፤ በዚህ መንገድ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እናገኛለን።

ቅዳሜ ከሰዓት የነበረው የመጨረሻው ንግግር በሚልክያስ ትንቢት ላይ የተመሠረተው “አስፈሪው የይሖዋ ቀን ቀርቧል” የተሰኘው ነበር። ባለፉት የታሪክ ወቅቶች በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ፍርድ ሲፈረድባት እንደነበረው ጊዜ ያሉ አስፈሪ ቀናት ነበሩ። ይሁንና በሰው ታሪክ ሁሉ፣ ከሁሉ የከፋው አስፈሪ ቀን ‘እግዚአብሔርን የማያውቁት፣ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙት’ የበቀል እርምጃ ሲወሰድባቸው የሚመጣው መጪው የይሖዋ ቀን ይሆናል። (2 ተሰሎንቄ 1:6–8) ይህ ጊዜ ምን ያህል ቀርቧል? ተናጋሪው “መጨረሻው ቀርቧል! ይሖዋ ቀኑና ሰዓቱን ያውቃል። ፕሮግራሙን አይለውጥም። በትዕግሥት እንድንጸና ይፈልግብናል” ሲል ገለጸ።

ሁለት ቀናት እንዳለፉ ማመን ያዳግት ነበር። የመጨረሻው ቀን ምን ይዞ ይሆን?

“አምላክን ፍሩ ክብርንም ስጡት”

የሦስተኛው ቀን አጠቃላይ መልእክት በራእይ 14:7 ላይ የተመሠረተ ነበር። በጠዋቱ ፕሮግራም ወቅት የይሖዋ ምሥክሮችን ከሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የሚለዩአቸውን አንዳንድ መሠረታዊ ትምህርቶች የሚያጎሉ ተከታታይ ንግግሮች ቀረቡ።

“ጻድቃን ከሞት ይነሣሉ” በተባለው ንግግር ላይ ተናጋሪው የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ጥያቄ አቀረበ፦ “በነዚህ የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ዓመታት ታማኝነታቸውን ጠብቀው የሞቱ ሰዎች በሺው ዓመት የፍርድ ቀን ውስጥ የሚነሡት መቼ ነው?” መልሱ ምን ነበር? “መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን አይነግረንም” በማለት ተናጋሪው ገለጸ። “ይሁን እንጂ በዘመናችን የሞቱት በፍርድ ቀን ውስጥ የሚሰጠውን ሰፊ የትምህርት ዘመቻ ከአርማጌዶን ከሚተርፉት እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ለማከናወን ቀደም ብለው መነሣታቸው ምክንያታዊ አይደለምን? በእርግጥም ነው!” ተራፊዎች ይኖራሉን? እንዴታ! ይህን የሚያረጋግጡልን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና ምሳሌዎች ከዚያ ቀጥሎ በቀረበው “ታላቁን መከራ በሕይወት ማለፍ” በተባለው ንግግር ላይ በግልጽ ተብራርተዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ተስፋዎችን እንደያዘ ማለትም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩና ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ አብረውት የሚገዙት የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት እንደሚያገኙ ከረጅም ጊዜ በፊት ተረድተዋል። ሰማያዊው ተስፋ ‘አንተ ታናሽ መንጋ . . . አትፍራ’ በተባለው ንግግር ላይ ተብራርቷል። (ሉቃስ 12:32) ከአሁኑ የዓለም ሁኔታ አንፃር ታናሹ መንጋ ደፋር መሆን አለበት፤ እያንዳንዳቸው እስከ መጨረሻው መጽናት አለባቸው። (ሉቃስ 21:19) “ድፍረታቸው” አለ ተናጋሪው “እጅግ ብዙ ሰዎችን ያበረታታቸዋል። እነሱም ጭምር እስካሁን በምድር ላይ ከታዩት ሁሉ ታላቅ ከሆነው መከራ ለመዳን ሲጠባበቁ የድፍረትን ባሕርይ መኮትኮት አለባቸው።”

በጠዋቱ ፕሮግራም መደምደሚያ ላይ አድማጮች በፊታችሁ የተደቀኑት ምርጫዎች የተሰኘውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማ በደስታ ተመለከቱ። በኢያሱና በነቢዩ ኤልያስ ዘመን እስራኤላውያን በመንታ መንገዶች ላይ ነበሩ። መምረጥ ነበረባቸው። ኤልያስ “እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ” ብሏቸው ነበር። (1 ነገሥት 18:21) ዛሬም ቢሆን የሰው ልጅ በመንታ መንገዶች ላይ ነው። በሁለት አሳቦች የምናነክስበት ጊዜ አይደለም። ትክክለኛው ምርጫ ምንድን ነው? የጥንቱ ኢያሱ ያደረገው ዓይነት ምርጫ ነው። እሱ “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን” አዓት] እናመልካለን” ብሎ ነበር።—ኢያሱ 24:15

ድንገት ይመስላል፤ እሑድ ከሰዓት ሆነና “አሁኑኑ እውነተኛውን አምላክ መፍራት ያለብን ለምንድን ነው” የተሰኘው የሕዝብ ንግግር የሚቀርብበት ጊዜ ደረሰ። በራእይ 14:6, 7 ላይ የሰው ልጆች በሙሉ “እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” ተብለዋል። በአሁኑ ወቅት አምላክን መፍራት አስቸኳይ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጥቅሱ እንደሚናገረው “የፍርዱ ሰዓት ደርሷል።” አሁን የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ልጁ አማካኝነት ይሖዋ ይህን የረከሰ፣ ዓመፀኛ የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል። ተናጋሪው አምላክን ለሚፈሩት እፎይታ ለማስገኘትም ሆነ ምድራዊ መኖሪያችንን ከጥፋት ለማዳንና ለመጠበቅ ብቸኛው መንገድ ይህ እንደሆነ ገለጸ። አሁን የምንኖረው በዚህ የነገሮች ሥርዓት ማክተሚያ ቀኖች ላይ ስለሆነ አሁኑኑ እውነተኛውን አምላክ መፍራታችን አስቸኳይ ነው!

የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ፍሬ ሐሳብ አጠር ባለ መንገድ ከቀረበ በኋላ የመጨረሻው ተናጋሪ መድረኩን ተረከበ። የስብሰባው ፕሮግራም ተሰብሳቢዎቹ አምላካዊ ፍርሃት ይበልጥ እንዲገባቸው እንዳደረገ ገለጸ። አምላክን የሚፈሩ የሚያገኟቸውን ብዙ በረከቶች አጎላ። ተናጋሪው በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን የተሰኘ አዲስ የቪዲዮ ካሴት መውጣቱን አስታወቀ። ካሴቱ ከ1993–94 በተካሄዱት “መለኮታዊ ትምህርት” ዓለም አቀፍ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የተንጸባረቁትን ልዩ ገጽታዎች ያጎላል። ንግግሩ እየተገባደደ ሲሄድ ብዙዎች ‘በቀጣዩ ዓመት ምን ነገር በጉጉት ልንጠብቅ እንችላለን?’ ብለው ያስቡ ነበር። በብዙ ቦታዎች የሚደረጉ የሦስት ቀናት የወረዳ ስብሰባዎች ልንጠብቅ እንችላለን።

መደምደሚያው ላይ ተናጋሪው “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ” የሚለውን ሚልክያስ 3:16ን ጠቀሰ። ተሰብሳቢዎቹ የይሖዋን ስም ለማሰብና እሱን በአምላካዊ ፍርሃት ለማገልገል ቁርጥ ያለ አቋም እንዲይዙ የሚያደርግ ሐሳብ አስጨብጧቸዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥምቀት እጩዎች አምላካዊ ፍርሃት ማሳየታቸውን መቀጠል አለባቸው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በፊታችሁ የተደቀኑት ምርጫዎች” የተሰኘው ድራማ ይሖዋን በማገልገል ረገድ ቁርጥ ያለ አቋም የመያዝን አስፈላጊነት ለአድማጮች አስገንዝቧል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተሰብሳቢዎቹ “የምትወደው ሰው ሲሞትብህ” የተሰኘውን አዲስ ብሮሹር በማግኘታቸው ተደስተዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ