አቅኚ ሆነህ ይሖዋን ልታገለግለው ትችላለህን?
1 በ“ብርሃን አብሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ላይ አንድ ተናጋሪ “አቅኚ መሆን ትችላላችሁን? አቅኚ ትሆናላችሁን?” በማለት ጠይቆ ነበር። አርማጌዶን በጣም በመቅረቡ ምክንያት የስብከቱን ሥራ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አጣዳፊ ስላደረገው እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ተናጋሪው አስገንዝቧል። — 1 ቆሮ. 7:29
2 አቅኚነት ከባድ ሥራ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ራስን መገሠጽና የራስን አኗኗር በደንብ ማደራጀትን ይጠይቃል። ሆኖም ለአገልግሎቱ የምናደርገው ድካም “ከንቱ” አይደለም። (1 ቆሮ. 15:58) ለመሥራት ስለምንመርጣቸው ጊዜያችንንና ጉልበታችንን የሚያጠፉ ሌሎች ሥራዎች እንዲህ ሊባል ይችላልን? ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ክርስቲያኖች በአገልግሎቱ ቀናተኞች እንዲሆኑ ይገፋፋቸዋል። ለይሖዋ አገልግሎት ያላቸው ቅንዓትም ብዙዎችን ወደ አቅኚነት ሥራ መርቷቸዋል። — 1 ዮሐንስ 5:3፤ ራእይ 4:11
3 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቅርቡ የጨረሱ የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑ ብዙ ወጣቶች አቅኚ ሆኖ ስለማገልገል አጥብቀው በማሰብ ላይ ናቸው። ይህም ሙሉ በሙሉ ተገቢ ነው። ከሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ምን ሌላ ሥራ ሊኖር ይችላል? (ማቴ. 6:33) የአምላክ መንግሥት ምሥራች መሰበክ አለበት። ይህ የይሖዋ ሥራ ነው። ከወጣትነት ጀምሮ በዚህ ሥራ በጋለ ስሜት መሳተፍ እንዴት ያለ መብት ነው! — ማቴ. 24:14
4 እናንተስ ወላጆች ልጆቻችሁ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን እንዲጀምሩ ታበረታቷቸዋላችሁን? ትልቅ ዋጋ ባለው በዚህ ሥራ በሙሉ ልባቸው፣ ነፍሳቸው፣ አሳባቸውና ኃይላቸው እንዲሣተፉ የምትፈልጉ መሆናችሁን ልጆቻችሁ በግልጽ ተረድተዋልን? (ማርቆስ 12:30) ብዙ ወጣት አስፋፊዎች በትምህርት ቤት ባሉባቸው ዓመታት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በረዳት አቅኚነት በመካፈል ራሳቸውን ለዘወትር አቅኚነት ያዘጋጃሉ። በእርግጥም ለይሖዋ ሥራ የሚያሳዩት እንዲህ ያለው ፍቅር የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኘዋል! — ምሳሌ 27:11
5 እርግጥ ነው ለአቅኚነት አገልግሎት አመቺ የሆነ ሁኔታ ያላቸው ሁሉም አይደሉም። ይሁን እንጂ ያገባህም ሆንህ ነጠላ፣ ወጣትም ሆንህ በዕድሜ የገፋህ የምሥራቹ አቅኚ አገልጋይ በመሆን ይሖዋን ለማገልገል በቁም ነገርና በጸሎት አስበህበት ታውቃለህን? (ቆላ. 3:23) አግብተው የሚገኙ ብዙ ወጣት ባልና ሚስቶች አንዳቸው ወይም ሁለቱም አቅኚ እንዲሆኑ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ጥረት እያደረጉ ናቸው።
6 በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚ ለመሆን በማያስችል ሁኔታ ውስጥ ከሆንህ ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ትችላለህን? በጉባኤህ ያሉ ብዙ አስፋፊዎች በሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ ለመሆን ዕቅድ እንዳወጡ የታወቀ ነው። አንተም አብረሃቸው ረዳት አቅኚ ልትሆን ትችላለህን? ምንም እንኳን ሁሉም የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ብዙ በረከቶችን የሚያገኙ ቢሆንም በግ መሰል ሰዎችን በመፈለግ በመንግሥቱ አገልግሎት የበለጠ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ያሉትን ደግሞ ተጨማሪ በረከቶች ይጠብቋቸዋል። — ሥራ 20:35