የጥያቄ ሣጥን
◼ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናቶች መደረግ የሚኖርባቸው መቼ መቼ ነው?
ብዙውን ጊዜ ጠቃሚና አመቺ የሚሆነው በጉባኤው ክልል ያሉትን ሁሉንም ሰዎች በመንግሥት አዳራሹ እንዲሰበሰቡ ከማድረግ ይልቅ ተራርቀው በሚገኙ በዛ ባሉ ቦታዎች የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች እንዲኖሩ ማድረጉ ነው። እነዚህ ጥናቶች በቡድኑ እንዲገኙ ለተመደቡት ለአብዛኞቹ ሰዎች በጣም አመቺ በሆነ ሰዓት ላይ መደረግ ይኖርባቸዋል። ብዙውን ጊዜ ይህ የሚደረገው ሌሎች ስብሰባዎች ወይም የአገልግሎት እንቅስቃሴዎች በማይደረጉበት በሳምንቱ ውስጥ ባለ ምሽት ላይ ነው። ሆኖም ሲመሽ ከቤት መውጣት ለማይፈልጉ አረጋውያንና በማታ ለሚሠሩ ሰዎች ሲባል የመጽሐፍ ጥናቱን ቀን ላይ ለማድረግ ማሰቡ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሣ የመጽሐፍ ጥናቱን ቅዳሜ ወይም እሁድ ቀን ላይ ለማድረግ የሚያስገድድ ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
ሽማግሌዎች ‘ለአብዛኞቹ አስፋፊዎችና ፍላጎት ላላቸው አዲሶች የሚመች’ የስብሰባ ጊዜ ለመለየትና ለመወሰን ወንድሞችን በመጠየቅ መረጃ ሊያሰባስቡ ይችላሉ። (አገልግሎታችን ገጽ 62 በአማርኛው ገጽ 33) የተመረጠው ጊዜ ለመስክ አገልግሎት የታቀዱትን ዝግጅቶች በማያደናቅፍ ወይም ከልክ በላይ በማያጣብብ ቀንና ሰዓት ላይ መሆን አለበት።