የጥያቄ ሣጥን
◼ በስብሰባዎች ላይ በጣም ጥሩ የሆነ ሐሳብ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች አንድ ላይ የምንሰበሰብበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። እዚያም በምንሰጠው ሐሳብ እምነታችንን የመግለጽና ሌሎችን የማበረታታት አጋጣሚ አለን። (ምሳ. 20:15፤ ዕብ. 10:23, 24) ሐሳብ መስጠት መብት እንደሆነ አድርገን መመልከትና ቋሚ ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት ማድረግ አለብን። ይህንን በተሻለ ሁኔታ ማከናወን የምንችለው እንዴት ነው?
የመጀመሪያው እርምጃ መዘጋጀት ነው። አስቀድሞ ማንበብና በነገሩ ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው። በጽሑፉ ላይ የቀረበው ሐሳብ መንፈሱ ምን እንደሆነ ለማግኘት ጥረት አድርግ። ትምህርቱ ከዚህ በፊት የቀረበ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ በሰፊው የተብራሩ ወይም ተሻሽለው የቀረቡ ነጥቦችን ፈልግ። የትምህርቱን ጭብጥ በአእምሮህ ያዝ። ራእይ ታላቁ መደምደሚያ የተባለውን መጽሐፍ የመሳሰሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ላይ ጥልቅ የሆነ ትምህርት የሚያቀርቡ መጽሐፎችን ስትዘጋጅ አንድ ጥቅስ በጥቅሱ ዙሪያ ካሉት ሐሳቦች ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለመመልከት ሞክር። እነዚህን ምክሮች መከተልህ የማሰብ ችሎታህን እንድትጠቀም ያበረታታሃል። ጥሩ ሐሳቦች ለመስጠት እንድትዘጋጅና ተሳትፎ በማድረግ ደስታ እንድታገኝ ይረዱሃል።
ከሁሉ የተሻሉ መልሶች የሚባሉት እጥር ምጥን ያሉ፣ በቀላል አነጋገር የሚገለጹና እየተጠና ባለው ጽሑፍ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። መጀመሪያ መልስ የሚሰጠው ሰው ሌሎቹን ነጥቦች ተጨማሪ ሐሳብ እንዲሰጥባቸው በመተው ጥያቄውን በቀጥታ መመለስ አለበት። ረጅም ሰዓት የሚወስዱ እንዲሁም ሌሎች በጥያቄና መልሱ እንዳይካፈሉ የሚያደርጉ የተንዛዙና የተምታቱ ሐሳቦችን ከመስጠት ተቆጠብ። መልስ ስትመልስ ቃል በቃል ከጽሑፉ ላይ ከማንበብ ይልቅ ሐሳብህን በራስህ አባባል ግለጽ። ተጨማሪ መልሶች በተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ የሚገኙ ነጥቦችን የሚያካትቱ ሊሆኑ ይችላሉ። አላስፈላጊ ድግግሞሽን ለማስወገድ እንድትችል ሌሎች ምን ብለው እንደሚመልሱ በጥንቃቄ አዳምጥ።
እጅህን ብዙ ጊዜ ማውጣቱ ጥሩ ነው፤ ሆኖም በሁሉም አንቀጾች ላይ እጅህን ማውጣት አያስፈልግህም። ወጣቶች መልስ በመስጠት እንዲካፈሉ ሐሳብ እናቀርብላቸዋለን። መልስ ለመስጠት የምታመነታ ከሆነ በየትኛው አንቀጽ ላይ ሐሳብ መስጠት እንደምትፈልግ አስቀድመህ የሚመራውን ወንድም ብታሳውቀው በጠየቅኸው አንቀጽ ላይ ሐሳብ እንድትሰጥ አጋጣሚ ሊሰጥህ ይችላል።
የአድማጮችን ተሳትፎ በሚጠይቁ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለሌሎች የምናካፍለው ነገር እንዲኖረን ሁላችንም ብርቱ ጥረት ማድረግ አለብን። የእነዚህ ስብሰባዎች መሳካት ይበልጡኑ የተመካው ሐሳብ ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆናችንና ጥሩ መልሶችን በመስጠታችን ላይ መሆኑን አትዘንጉ።— መዝ. 26:12