በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት አንዱ ሌላውን ያንጸው
1 በዕብራውያን 10:24 ላይ ‘ለምክርና ለመልካም ሥራ አንዳችን ሌላውን እንድናነቃቃ’ ምክር ተሰጥቶናል። ይህም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያለው ሐሳብ በመስጠት ሌላውን ማነጽን የሚያጠቃልል ነው። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከምንሰጠውስ ሐሳብ እነማን ይጠቀማሉ?
2 ሌሎች ወንድሞች ግንዛቤያችሁን የሚያሰፋላችሁና መንፈሳዊነታችሁን የሚያጎለብትላችሁ ቀላልና ግልጽ መልስ በመስጠታቸው ምን ያህል እንደተጠቀማችሁ እስቲ ለአንድ አፍታ መለስ ብላችሁ አስቡ። እናንተም በአጸፋው ተመሳሳይ ነገር ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ። መልስ በመስጠት ስትካፈሉ በስብሰባ ላይ የተገኙት ሁሉ የሚያበረታታ ‘መንፈሳዊ ስጦታ ለማካፈል’ ፍላጎት እንዳላችሁ ማሳየታችሁ ነው።—ሮሜ 1:11, 12
3 ጥሩ ሐሳብ መስጠት የሚቻልበት መንገድ፦ በአንቀጹ ውስጥ የሰፈሩትን ነጥቦች በሙሉ በማተት ረዥም ሐሳብ አትስጡ። ረዣዥም መልሶች ትክክለኛው መልስ ቁልጭ ብሎ እንዳይታይ ከማድረጋቸውም ሌላ ሌሎች ሐሳብ እንዳይሰጡ ተስፋ ሊያስቆርጣቸው ይችላል። ለአንድ አንቀጽ የሚሰጠው የመጀመሪያው መልስ አጭርና በጽሑፉ ላይ ለሚገኘው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ብቻ መሆን አለበት። ከዚያ ተጨማሪ መልስ ማከል የሚፈልጉ የትምህርቱን ተግባራዊ ጠቀሜታ ሊጠቅሱ ወይም ጥቅሶቹ እንዴት ሥራ ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ሊጠቁሙ ይችላሉ። ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ገጽ 90–2ን ተመልከቱ።
4 በስብሰባ ላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈራህ ከሆነ ቀደም ብለህ አጠር ያለ ሐሳብ ተዘጋጅና እዚያ አንቀጽ ላይ ሲደርስ እንዲጠይቅህ ለሚመራው ወንድም ንገረው። ጥቂት ስብሰባዎች ላይ እንዲህ ካደረግህ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ቀላል እየሆነልህ ይሄዳል። ሙሴ እና ኤርምያስ በሕዝብ ፊት የመናገር ችሎታ የሌላቸው ሆኖ እንደተሰማቸው አስታውስ። (ዘጸ. 4:10፤ ኤር. 1:6 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።) ይሁን እንጂ ይሖዋ እርሱን ወክለው እንዲናገሩ እንደረዳቸው ሁሉ አንተንም ይረዳሃል።
5 ከምትሰጡት ሐሳብ እነማን ይጠቀማሉ? ሐሳብ ስትሰጡ እውነት በአእምሮአችሁና ልባችሁ ውስጥ ሥር እንዲሰድና ትምህርቱንም በሌላ ጊዜ በቀላሉ እንድታስታውሱት ስለሚረዳችሁ አናንተ ራሳችሁ ትጠቀማላችሁ። በተጨማሪም የምትሰጡትን የሚያንጽ መልስ በመስማት ሌሎችም ይጠቀማሉ። ተሞክሮ ያላቸውም ሆኑ ወጣቶች፣ ዓይን አፋሮችም ሆኑ አዲሶች ሁሉም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እምነታቸውን ሲገልጹ ስንሰማ እንበረታታለን።
6 ‘በጊዜው የተነገሩ ቃላት’ በስብሰባዎች ላይ ሌላውን ለማነጽ ሲያገለግሉ ‘ምንኛ መልካም እንደሆኑ’ በትክክል እንረዳለን!—ምሳሌ 15:23