የራእይ መጽሐፍ የእውነተኛ ደስታ ቁልፍ ነው
1 በራእይ 1:3 ላይ የሚገኙት የሐዋርያው ዮሐንስ ቃላት ለእኛ ምሥራች ናቸው። ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይገልጹልናል። ዮሐንስ እዚህ ጥቅስ ላይ “የሚያነበው የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን [“ደስተኞች፣” አዓት] ናቸው” በማለት ጽፏል። ራእይ— ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለው መጽሐፍ ብዙ ሰዎች ታላቅ ደስታ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። ይህን መጽሐፍ ለሰዎች የምናበረክትበት ጥሩ ምክንያት አለን።
2 የሚከተለውን ጥያቄ በመጠየቅ ውይይት መጀመር ትችላለህ:-
◼ “የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ሰዎች አንብበው እንዲረዱት ተብሎ የተጻፈ ነው ብለው ያስባሉ ወይስ ምሥጢር እንደሆነ የሚቀር ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ብዙ ሰዎች እንደ እርስዎ ያለ አመለካከት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ 1:3 ላይ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ። [አንብብ።] ስለዚህ የራእይ መጽሐፍ የያዘውን ሐሳብ አንብቦ መረዳት ይቻላል፤ በተጨማሪም በውስጡ ያለው እውቀት ደስታ ያስገኝልናል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?” በገጽ 6 አንቀጽ 2 ላይ ያለውን ሐሳብ ጥቀስና እንዲህ በል:- “ይህ ጽሑፍ የራእይን መጽሐፍ ቁጥር በቁጥር ያብራራል። ጊዜ መድበው ቢያነቡት በጣም ይጠቀማሉ። ይህንን ቅጂ ትቼልዎት ብሄድ ደስ ይለኛል።”
3 ብዙ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላቱ ስለሚያሳስባቸው የሚከተለው አቀራረብ ፍላጎት ሊያሳድርባቸው ይችላል:-
◼ “ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈልገን ነገር ምን ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ብዙ ሰዎች ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮች ያስፈልገኛል ብለው ያምናሉ።” ገጽ 73 አውጣና “ፍቅረ ነዋይና ጥበብ” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡትን ዋና ዋና ነጥቦች ጥቀስ። በመቀጠል እንዲህ በል:- “ይህም ሰዎች በጣም የሚያተኩሩት በቁሳዊ ነገሮች ላይ እንደሆነ ያሳያል። እኛ ይበልጥ መጨነቅ ያለብን ስለሚያስፈልጉን መንፈሳዊ ነገሮች ነው። እውነተኛ እውቀት በጣም ያስፈልገናል። ነገር ግን ማወቅ ያለብን ስለምን ነገር ነው?” ዮሐንስ 17:3ን አንብብና ስለ አምላክ ማወቅ እንዴት ወደ ዘላለም ሕይወት ሊመራ እንደሚችል ተናገር። መጽሐፉን እንዲወስድና አምላክ የሰዎችን ፍላጎት በሙሉ ለማሟላት ስላለው ዓላማ መጽሐፉ የሚሰጠውን ግሩም ሐሳብ ልታሳየው እንደምትፈልግ ንገረው።
4 ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ ያለው መከራ በጣም ስለሚያሳስባቸው የሚከተለውን አቀራረብ መሞከር ትችላለህ:-
◼ “ያነጋገርኳቸው ሰዎች ሁሉ ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን ብለው ይጨነቃሉ። አንዳንድ የዓለም መሪዎች አዲስ የሰላም ዘመን የሚመጣበት ጊዜ በጣም እንደተቃረበ ይሰማቸዋል። ስለዚህ ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ምንም እንኳ ሰዎች ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ዓመፅና መከራ በዓለም ዙሪያ እየጨመሩ መሄዳቸውን ቀጥለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ችግሮች ብቸኛና ዘላቂ መፍትሄው ምን እንደሆነ ይናገራል። [2 ጴጥሮስ 3:13ን አንብብ። በገጽ 302 ላይ ያለውን ሥዕል አውጣና ሰማያዊው የአምላክ መንግሥት ለዚህች ምድር ዘላቂ ሰላምና ደህንነት የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ ንገረው።] ይህ ጽሑፍ በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር የዘላለም ሕይወት የሚያገኘው የዚህ አዲስ ኅብረተሰብ አባል ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ እንዲችሉ ይረዳዎታል።”
5 በሥራ የተወጠረ ሰው አጋጥሞህ መልእክትህን ለማሳጠር ከተገደድክ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ጊዜ ስለሌለዎት . . . [ተስማሚ ትራክት ወይም መጽሔት ምረጥ] የሚል ርዕስ ያለውን ይህንን ትራክት [መጽሔት] ትቼልዎት ብሄድ ደስ ይለኛል። ቢያነቡት ጥሩ ነው። በሚቀጥለው ጊዜ ብቅ ስል ምን ሐሳብ እንዳገኙበት ቢነግሩኝ ደስ ይለኛል።”
6 ሰዎች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት አስደናቂ ትንቢቶች ያላቸውን ትርጉም ሲረዱ ደስታ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ ይህንን መጽሐፍ እናበረክትላቸዋለን።— ምሳሌ 3:13