ስብሰባዎች ለመልካም ሥራ ያነቃቃሉ
1 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በመስክ አገልግሎት መካፈል ዋነኞቹ የአምልኮታችን ገጽታዎች ናቸው። እነዚህ ሁለቱ ጎን ለጎን ይሄዳሉ። አንዱ በሌላው ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመልካም ሥራዎች ያነቃቃሉ፤ ከሁሉ የሚበልጠው መልካም ሥራ ደግሞ የመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ነው። (ዕብ. 10:24) በስብሰባዎች ላይ መገኘታችንን ብናቋርጥ ለመስበክ የሚገፋፋ ምንም ማነቃቂያ ስለማናገኝ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መስበካችንን እናቆማለን።
2 ለመስበክ እንዲያነቃቁን ታቅደው የተዘጋጁ መንፈሳዊ መመሪያዎችን በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ እናገኛለን። የጊዜው አጣዳፊነት ሁልጊዜ ጎላ ተደርጎ ስለሚገለጽልን የመጽሐፍ ቅዱስን ሕይወት ሰጪ መልእክት ለሌሎች ለመውሰድ እንገፋፋለን። በመስበኩ ሥራ እንድንጸና ማበረታቻና ማጠናከሪያ እናገኛለን። (ማቴ. 24:13, 14) በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በመጠቀም በሌሎች ፊት እምነታችንን በመግለጽ ረገድ የበለጠ ልምድ እያገኘን እንሄዳለን። (ዕብ. 10:23) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግበን የበለጠ ውጤታማ አገልጋዮች እንድንሆንና የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል የሚያስችለንን ማሰልጠኛ እናገኛለን።—2 ጢሞ. 4:2
3 የአገልግሎት ስብሰባዎች ለመስበክ የሚያነቃቁን እንዴት ነው? ሁላችንም በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ትምህርቶች ቀደም ብለን እንድንመለከታቸው ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ከዚያም በአገልግሎት ስብሰባ ስንገኝና መድረክ ላይ የሚቀርቡ ሠርቶ ማሳያዎችን ስንመለከት እነዚህ ሐሳቦች በአእምሯችን ውስጥ ይቀረጻሉ። በመስክ አገልግሎት ስንሰማራ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ መለስ ብለን በማሰብና የቀረቡትን ሠርቶ ማሳያዎች በማስታወስ የበለጠ ውጤታማ የሆነ ምሥክርነት ልንሰጥ እንችላለን። ይህን ብዙ አስፋፊዎች እውነት ሆኖ አግኝተውታል።
4 አንዳንዶች ከአገልግሎት ስብሰባው ያገኙትን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሉ ከሌሎች ጋር አብረው ለማገልገል ቀጠሮ ይይዛሉ። እነዚህ ስብሰባዎች በእያንዳንዱ ሳምንት በስብከቱ ሥራ መካፈልን ስለሚያበረታቱ አስፋፊዎቹ ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅሙትን ነጥቦች ሳይረሱ ተግባራዊ ለማድረግ ይነሳሳሉ።
5 ከመሰል አምላኪዎች ጋር የሚያገናኙንና ለመልካም ሥራ የሚያነቃቁንን ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሊተካ የሚችል ምንም ነገር የለም። አገልግሎታችን ስኬታማ እንዲሆን ከፈለግን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውታሪ ተሰብሳቢዎች ልንሆን ይገባናል። ‘መሰብሰባችንን ባለመተው’ ግሩም ለሆነው ለዚህ የይሖዋ ዝግጅት አድናቆታችንን እናሳይ።—ዕብ. 10:25