በሰዎች አእምሮ ውስጥ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲቀረጽ አድርጉ
1 የሰው ልጅ እርጅናን ለማዘግየትና ዕድሜውን ለማራዘም ብርቱ ጥረት ቢያደርግም እርጅናና ሞት የማይቀሩ ክስተቶች ሆነዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች የሚያረጁትና የሚሞቱት ለምን እንደሆነ፣ እርጅና የሚያስከትላቸው አስከፊ ውጤቶች እንዴት እንደሚሻሩና ሞት እንዴት እንደሚወገድ ስለሚገልጽ ምንኛ አመስጋኞች ነን! እነዚህ እውነቶች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ላይ አሳማኝ በሆነ መንገድ ቀርበዋል። ይህ መጽሐፍ ገነት ተመልሳ የምትቋቋምበትን ጊዜ በመጠቆም ሕይወትንና ሞትን በሚመለከት ለሚነሱ ሰዎችን ግራ ለሚያጋቡ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።
2 በመጋቢት ወር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ግብ በማድረግ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ እናበረክታለን። (ማቴ. 28:19, 20) ከዚያም ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ እናደርግላቸዋለን። በዚህ መንገድ የዘላለም ሕይወት ተስፋ በሰዎች አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ ማድረግ እንችላለን። (ቲቶ 1:2) ይህንን ለማድረግ የሚከተሉት ሐሳቦች ሊረዱህ ይችላሉ።
3 በመጀመሪያ ስታነጋግር እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ
◼ “የሰው ልጆች ረዥም ዕድሜ ለመኖር የሚናፍቁት ለምንድን ነው ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ ሂንዱዎች፣ ሙስሊሞችና ሌሎች ሰዎች ከሞት በኋላ ሕይወት አለ የሚል ተስፋ አላቸው።” እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 6 “የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ አውጣና አንቀጽ 3ን አንብብ። በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች አብራራ። ለቤቱ ባለቤት በአንቀጹ መጨረሻ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንብብና መልሶቹን ራሱ ከመጽሐፉ ማየት ይፈልግ እንደሆነ ጠይቀው። መልሶቹን የማወቅ ጉጉት ካደረበት የሚቀጥሉትን ጥቂት አንቀጾች ተወያዩ። በዚህ ሁኔታ ጥናት መጀመር ይቻላል! ያለበለዚያ የቤቱ ባለቤት መጽሐፉን እንዲያነበው ትተህለት ሂድና በመልሶቹ ላይ ለመወያየት በሚቀጥለው ቀን ወይም በሁለተኛው ቀን ለመመለስ ዝግጅት አድርግ።
4 “እውቀት” የተባለውን መጽሐፍ ላበረከትክላቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ተመልሼ የመጣሁት ባለፈው ጊዜ ሞትን አስመልክቶ ባነሳናቸው ሁለት ጥያቄዎች ላይ ለመነጋገር ነው።” ለቤቱ ባለቤት ጥያቄዎቹን አስታውሰው። ከዚያም ምዕራፍ 6 ላይ “መዘዘኛው ደባ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ባለው ሐሳብ ተወያዩ። ሁኔታውን አይተህ ጥናቱን ቀጥል ወይም በአንቀጽ 7 መደምደሚያ ላይ ያለውን የመጨረሻ ጥያቄ ተጠቀምና ለሚቀጥለው ውይይት መሰረት ጥለህ ሂድ። ተመልሰህ ለመሄድ ቀጠሮ ያዝ። ለቤቱ ባለቤት የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት ስጠውና ስብሰባው እንዴት እንደሚካሄድ በደንብ ግለጽለት። በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርብለት።
5 ከቤት ወደ ቤትም ሆነ በአጋጣሚ ምስክርነት እንዲህ በማለት ውይይት መክፈት ትችላለህ:-
◼ “የእኛም ሆነ የምድር የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን ብለው አስበው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ምድር ገነት ትሆናለች በማለት ጠቅለል አድርጎ ይናገራል። በመጀመሪያ አምላክ የተወሰነውን የምድር ክፍል ውብ የአትክልት ስፍራ እንዳደረገውና የፈጠራቸውን ባልና ሚስት በእዚያ እንዳስቀመጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። እነሱም ተባዝተው መላዋን ምድር መሙላትና ቀስ በቀስ ወደ ገነትነት መለወጥ ነበረባቸው። በዚያች ምድር ላይ ሕይወት ምን ሊመስል ይችል እንደነበር ይህንን አገላለጽ ልብ ይበሉት።” እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ገጽ 8ን አውጣና “ሕይወት በገነት ውስጥ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር አንቀጽ 9ን አንብብ። ከዚያም በአንቀጽ 10 ላይ ያለውን ሐሳብ ካወያየኸው በኋላ አንቀጹ ውስጥ የተጠቀሰውን ኢሳይያስ 55:10, 11 አንብብ። ወደፊት በምትቋቋመው ገነት ውስጥ ስለሚኖረው ሕይወት የሚናገረውን ከአንቀጽ 11-16 ያለውን እንድትወያዩበት ጋብዘው። አለበለዚያም ሰውየው ራሱ መጽሐፉን እንዲያነበው አበረታታውና እንደገና ተገናኝታችሁ ለመወያየት ዝግጅት አድርግ።
6 በመጀመሪያ ጉብኝትህ ጥናት ካልተጀመረ ተመልሰህ ስትሄድ እንዲህ በማለት ጥናት ለማስጀመር መሞከር ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ባደረግነው ውይይት ምድር ወደ ገነትነት እንድትለወጥ የአምላክ ዓላማ መሆኑን ተመልክተናል። ይህ ደግሞ “ገነት ምን ሊመስል ይችላል?” የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።” እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 1ን አውጣና “ወደ ፊት በምትቋቋመው ገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ከአንቀጽ 11-16 ያለውን አስጠናው። በመቀጠልም ከገጽ 4-5 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየውና ይህን በሚመስል ውብ አካባቢ መኖር ይፈልግ እንደሆነ ጠይቀው። ከዚያም በገጽ 10 አንቀጽ 17 ላይ ያለውን የመጀመሪያውን ዐረፍተ ነገር አንብብ። ሁኔታውን አይተህ ጥናቱን ቀጥል ወይም በሚቀጥለው ጉብኝትህ አንድ ሰው ወደፊት በምትቋቋመው ገነት ውስጥ መኖር እንዲችል ምን እንደሚፈለግበት ልታብራራለት እንደምትችል ንገረው። የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት ስጠውና የስብሰባውን ፕሮግራም ግለጽ። ሰውየው ስብሰባ እንዲገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርብለት።
7 እውቀት የተባለው መጽሐፍ አምላክ የሰጠውን “የዘላለም ሕይወት” ተስፋ ለሌሎች ሰዎች ለማሳወቅ የሚረዳ በጣም ግሩም መሳሪያ ነው። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትህ ‘ሊዋሽ የማይችለው’ አምላክ የሰጠው ይህ ታላቅ ተስፋ በሰዎች አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ ሊያደርግ ይችላል።