የጥያቄ ሣጥን
◼ አዲሶች ከመጠመቃቸው በፊት ከእነርሱ ጋር የትኞቹን ጽሑፎች ማጥናት ይገባናል?
አንድ ሰው ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ ከመጠመቁ በፊት ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ይኖርበታል። (ዮሐ. 17:3) አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር እና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ በማጥናት የሚያስፈልገውን እውቀት ማግኘት ይችላል። ብዙውን ጊዜ መጀመሪያ የሚጠናው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር ነው። ይሁን እንጂ ጥናቱ በእውቀት መጽሐፍ ከተጀመረ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር መጽሐፉ ካለቀ በኋላ ማጥናት ይገባዋል። ይህ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ጠቅለል አድርጎ ያቀርባል። መጀመሪያ ከተጠና ተማሪው ይሖዋን ለማስደሰት ስለሚፈለግበት ብቃት መሠረታዊ ግንዛቤ እንዲኖረው ያደርጋል። መጨረሻ ከተጠና ደግሞ በእውቀት መጽሐፍ ላይ ለተሸፈኑት ትምህርቶች ጥሩ ክለሳ ሆኖ ያገለግላል። በሁለቱም ሁኔታ ቢሆን ተማሪው ለማስረጃነት የቀረቡትን ጥቅሶች እንዲያነብና እንዲያሰላስልባቸው አበረታቱት። ሥዕሎቹ ውጤታማ የማስተማሪያ መሣሪያዎች ስለሆኑ የሥዕሎቹን መልእክት ጎላ አድርጋችሁ መግለጽ አትርሱ።—የጥር 15, 1997 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-17ን ተመልከቱ።
ተማሪው ሁለቱንም ጽሑፎች አጥንቶ ከጨረሰ ሽማግሌዎች ከእርሱ ጋር የሚከልሷቸውን ለጥምቀት የሚያዘጋጁ ጥያቄዎች በሙሉ የመመለስ ብቃት ሊኖረው ይችላል። እንዲህ ከሆነ በሌላ ጽሑፍ አማካኝነት መደበኛ የሆነ ጥናት መምራት አያስፈልግም። ቢሆንም ግን አስጠኚው ተማሪው የሚያደርገውን መሻሻል በንቃት ሊከታተል ይገባል።—የጥር 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14, 17ን ተመልከቱ።