ይሖዋን በቤተሰብ ደረጃ ማምለክ
1 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ሆነው ብዙ ነገሮችን ያከናውኑ ነበር። የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን የሚያከናውኑት በተለይም ደግሞ ይሖዋን የሚያመልኩት በቤተሰብ ደረጃ ነበር። (ዘሌ. 10:12-14፤ ዘዳ. 31:12) በዛሬው ጊዜ፣ በብዙ አካባቢዎች የቤተሰብ አባላት በኅብረት ሆነው የሚሠሩት ሥራ በጣም ጥቂት ነው። ይሁንና ክርስቲያኖች በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆነው መሥራታቸው በተለይም ደግሞ ከአምልኮ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ማከናወናቸው ጥቅም እንዳለው ይገነዘባሉ። የቤተሰብ መሥራች የሆነው ይሖዋ፣ ቤተሰቦች በአንድነት እሱን ሲያመልኩ መመልከት እጅግ ያስደስተዋል!
2 አብራችሁ አገልግሉ:- ምሥራቹን አንድ ላይ ሆኖ መስበክ የቤተሰብን አንድነት ያጠናክራል። በመሆኑም አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች አስፋፊዎች ጋር አብሮ የሚያገለግል ከመሆኑም በተጨማሪ ከባለቤቱና ከልጆቹም ጋር አዘውትሮ ያገለግላል። (1 ጢሞ. 3:4, 5) ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም ፕሮግራማቸው የተጣበበ ቢሆንም ከሚስቶቻቸው ጋር አብረው ለማገልግል ዝግጅት ያደርጋሉ።
3 ከልጆቻቸው ጋር የሚያገለግሉ ወላጆች ልጆቻቸው በወንጌላዊነቱ ሥራ እድገት እንዲያደርጉ መርዳት ይችላሉ። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በአገልግሎት ሲካፈሉ፣ ወላጆቻቸው የሚያገኙትን ደስታና እርካታ ብቻ ሳይሆን ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸውንም ፍቅር በተግባር ሲገልጹ ይመለከታሉ። (ዘዳ. 6:5-7) ልጆች እያደጉ መሄዳቸው ከወላጆቻቸው ጋር የማገልገሉን ጠቀሜታ አይቀንስም። ከ15 እስከ 21 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወንዶች ልጆች ያሏቸው አንድ ባልና ሚስት ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው ያገለግላሉ። አባትየው “ልጆቻችንን ሁልጊዜ አንድ ነገር እናስተምራቸዋለን። እንዲሁም አገልግሎታቸው አስደሳችና የሚያበረታታ እንዲሆን የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን” ብሏል።
4 አብራችሁ ተዘጋጁ:- በርካታ ቤተሰቦች ለአገልግሎት አብሮ መዘጋጀቱን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ልጆች ከቤተሰቡ አባላት ጋር ተራ በተራ የቤት ባለቤት በመሆን ልምምድ ማድረጋቸው ያስደስታቸዋል። አንዳንዶች ከቤተሰብ ጥናት በኋላ ጥቂት ደቂቃ ወስደው ይህን የልምምድ ፕሮግራም ያካሂዳሉ።
5 ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ጠቃሚና አስደሳች በሆኑ ሥራዎች ላይ መካፈላችን ደስታችንን ይጨምርልናል። የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ በመሆን ከቤት ወደ ቤት ማገልገላቸው፣ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረጋቸውና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራታቸው ታላቅ ደስታ ያስገኝላቸዋል! እናንተም በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን ስታመልኩ “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” በማለት በደስታ መናገር ትችላላችሁ።—ኢያሱ 24:15