መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ ናችሁ?
1. መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል የትኛው ምሳሌ ያሳያል?
1 መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን ይዟል። (ዮሐ. 4:7-15) እንዲህ ያለ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ እንድንሆን ምን ማድረግ እንችላለን?
2. አለባበሳችን፣ አበጣጠራችንና አጋጌጣችን ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
2 አለባበስ፣ አበጣጠርና አጋጌጥ፦ ለአለባበሳችን፣ ለአበጣጠራችንና ለአጋጌጣችን በማንኛውም ጊዜ ተገቢውን ትኩረት መስጠታችን ሳንሸማቀቅ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) አለባበሳችንና አጋጌጣችን ጥሩ እንዳልሆነ ከተሰማን ምሥክርነት ለመስጠት አንገፋፋም። በአንጻሩ ደግሞ ልብሳችን ንጹሕና ሥርዓታማ ከሆነ ሰዎች ስለ እኛ ለማወቅ ሊጓጉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥርዓታማ አለባበስ የነበራቸው አንድ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት በጉዞ ላይ ሳሉ ከአንድ ሙስሊም ጎን ተቀምጠው ነበር። ግለሰቡ አለባበሳቸውን ተመልክቶ ክርስቲያን መሆን አለመሆናቸውን ጠየቃቸው። ይህ ደግሞ ከሰውየው ጋር ለሦስት ሰዓት የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንዲያደርጉ መንገድ ከፈተላቸው።
3. የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ውይይት መጀመር የቻላችሁት እንዴት ነው?
3 ውይይት መጀመር፦ ኢየሱስ በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ሳምራዊቷን ሴት ባገኛት ጊዜ ውይይት የጀመረው ውሃ እንድትሰጠው በመጠየቅ ብቻ ነበር። እኛም በተመሳሳይ አጭር ሐሳብ በመናገር ወይም ቀላል ጥያቄ በመጠየቅ ውይይት መጀመር እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ ምሥክርነት ለመስጠት ፈራ ተባ እንል ይሆናል፤ ይሁንና ይሖዋን እንዲረዳን ከጠየቅነው ውይይት ለመጀመር የሚስችለንን ‘ድፍረት እናገኛለን።’—1 ተሰ. 2:2
4. መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ዝግጁ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
4 ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር፦ በርካታ አስፋፊዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ማግኘት ችለዋል። ያላችሁበትን ሁኔታ ገምግሙና በየዕለቱ ልታገኟቸው ስለምትችሏቸው ሰዎች አስቡ። ተስማሚ የሆኑ ጽሑፎችንና ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ያዙ። ሰዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም የእነሱ ጉዳይ እንደሚያሳስባችሁ አሳዩ። በዕለቱ ውስጥ ሊያጋጥሟችሁ ስለሚችሉት ሁኔታዎች አስቀድማችሁ ማሰባችሁ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ እንድትሆኑ ያስችላችኋል።—ፊልጵ. 1:12-14፤ 1 ጴጥ. 3:15
5. መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችለንን አጋጣሚ መፍጠር ያለብን ለምንድን ነው?
5 መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እንዳናልፍ የሚያነሳሱን ሁለት አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን፤ አንደኛው ለአምላክ ያለን ፍቅር ሲሆን ሌላው ደግሞ ለሰዎች ያለን ፍቅር ነው። (ማቴ. 22:37-39) የስብከቱ ሥራ አንገብጋቢ ከመሆኑ አንጻር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመስበክ የሚያስችለንን አጋጣሚ መፍጠር ይገባናል። ጊዜው ከማለፉ በፊት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ለመስበክ የሚያስችለንን እያንዳንዱን አጋጣሚ በሚገባ ለመጠቀም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል።—ሮም 10:13, 14፤ 2 ጢሞ. 4:2