መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ትችላላችሁ!
1. (ሀ) መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኛችሁት መካከል መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተመሥክሮላችሁ እውነትን የሰማችሁት ስንቶቻችሁ ናችሁ?
1 በጉባኤያችሁ ውስጥ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተመሥክሮላቸው እውነትን የሰሙ ምን ያህል ሰዎች አሉ? የዚህን ጥያቄ መልስ ስታውቁ ትገረሙ ይሆናል። መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ሲባል በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ማለትም በጉዞ ላይ እያለን፣ ዘመዶቻችንን ወይም ጎረቤቶቻችንን ለመጠየቅ ስንሄድ፣ ገበያ ስንወጣ፣ በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ እንዲሁም እነዚህን በመሳሰሉት ቦታዎች ለምናገኛቸው ሰዎች ምሥራቹን መስበክ ማለት ነው። ከ200 በሚበልጡ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው 40 በመቶ የሚያህሉት እውነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተመሥክሮላቸው ነው! ይህ ሁኔታ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር በጣም ውጤታማ እንደሆነ ያሳያል።
2. መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከርን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ምሳሌዎች እናገኛለን?
2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ወንጌላውያን ብዙ ጊዜ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይመሠክሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ወደ ሰማርያ እየተጓዘ ሳለ ከያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ ውኃ ለመቅዳት ለመጣች አንዲት ሴት መሥክሮላታል። (ዮሐ. 4:6-26) ፊልጶስ የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ለነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ከእሱ ጋር መወያየት ጀምሯል። (ሥራ 8:26-38) ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ታስሮ በነበረበት ወቅት ለእስር ቤቱ ጠባቂ መሥክሮለታል። (ሥራ 16:23-34) በኋላም ጳውሎስ በቁም እስር ላይ እያለ “ወደ እሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደግነት ይቀበላቸው ነበር፤ . . . ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምራቸው ነበር።” (ሥራ 28:30, 31) አንድ ሰው ዓይናፋር ቢሆን እንኳ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ይችላል። እንዴት?
3. ዓይናፋርነትን ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል?
3 ውይይት መጀመር፦ ብዙዎቻችን ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ውይይት መጀመር ይከብደናል። ለምናውቃቸው ሰዎችም እንኳ ቢሆን ስለ እምነታችን አንስቶ ማውራት ከባድ ሊመስለን ይችላል። ይሁን እንጂ ስለ ይሖዋ ጥሩነት፣ ለአገልጋዮቹ ስለሰጣቸው መንፈሳዊ ሀብትና በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ስላሉበት አሳዛኝ ሁኔታ ካሰላሰልን ለእነሱ ለመመሥከር እንነሳሳለን። (ዮናስ 4:11፤ መዝ. 40:5፤ ማቴ. 13:52) በተጨማሪም ለመመሥከር የሚያስችል ‘ድፍረት እንድናገኝ’ ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ እንችላለን። (1 ተሰ. 2:2) አንድ የጊልያድ ተማሪ “ሰዎችን ለማነጋገር ሲከብደኝ ብዙውን ጊዜ መጸለይ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” በማለት ተናግሯል። እናንተም ውይይት ለመጀመር ከፈራችሁ በልባችሁ አጭር ጸሎት አቅርቡ።—ነህ. 2:4
4. ምን ዓይነት ግብ ልናወጣ እንችላለን? ለምንስ?
4 ከስሙ ለመመልከት እንደሚቻለው፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር መግቢያ መጠቀም አሊያም ጥቅስ በማንበብ ውይይት መጀመር አያስፈልገንም። ወዲያውኑ ምሥክርነት የመስጠት ሐሳብ ሳይኖረን መጀመሪያ ላይ ሌሎች ጉዳዮችን አንስተን የመጨዋወት ግብ ማውጣታችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ብዙ አስፋፊዎች እንዲህ ማድረጋቸው በኋላ ላይ ምሥራቹን ለመመሥከር ድፍረት እንዲያገኙ እንደረዳቸው ተናግረዋል። ግለሰቡ ከእናንተ ጋር መጨዋወት ካልፈለገ ውይይቱን ለመቀጠል መታገል አያስፈልግም። ከዚህ ይልቅ ውይይቱን በትሕትና መንፈስ ቋጭታችሁ የራሳችሁን ጉዳይ መቀጠል ትችላላችሁ።
5. አንዲት ዓይናፋር እህት መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንድትመሠክር የረዳት ምንድን ነው?
5 አንዲት ዓይናፋር እህት ገበያ ወጥታ ዕቃ ስትገዛ መጀመሪያ ላይ ግለሰቡን ዓይን ዓይኑን እያየች በወዳጅነት መንፈስ ፈገግ ትላለች። ግለሰቡ ፈገግ ካለ አጠር ያለ ነገር ትናገራለች። የሰውየው ምላሽ ጥሩ ከሆነ ይህ ሁኔታ ድፍረት ስለሚጨምርላት ውይይቱን ትቀጥላለች። እህት ሰውየው የሚናገረውን ነገር በጥሞና ካዳመጠች በኋላ ከተስፋው መካከል የትኛውን ብትነግረው የበለጠ ትኩረቱ ሊሳብ እንደሚችል ታስባለች። እንዲህ ዓይነቱን አቀራረብ በመጠቀም ብዙ ጽሑፎችን ማበርከት አልፎ ተርፎ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ችላለች።
6. መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ውይይቱን ምን ብለን መጀመር እንችላለን?
6 ምን ሐሳብ ማንሳት ይቻላል? ውይይት ለመጀመር ምን ማለት እንችላለን? ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ያገኛትን ሴት ማነጋገር የጀመረው ውኃ እንድትሰጠው በመጠየቅ ነበር። (ዮሐ. 4:7) እኛም ወዳጃዊ ሰላምታ በመስጠት ወይም አንድ ጥያቄ በማንሳት ውይይት መጀመር እንችላለን። በጭውውታችሁ መሃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን ለማንሳትና የእውነትን ዘር ለመዝራት የሚያስችል አጋጣሚ ታገኙ ይሆናል። (መክ. 11:6) አንዳንዶች የማወቅ ፍላጎት የሚያነሳሳ አስገራሚ ሐሳብ ተናግረው ሰዎች ጥያቄ እንዲጠይቁ በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዶክተር ፊት ለመቅረብ ወረፋ በምትጠብቁበት ጊዜ “ሁለተኛ የማልታመምበት ያ ጊዜ እስኪመጣ እናፍቃለሁ” በማለት ውይይት መጀመር ትችላላችሁ።
7. አስተዋይ መሆናችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚረዳን እንዴት ነው?
7 በተጨማሪም አስተዋዮች መሆናችን ውይይት ለመጀመር በር ይከፍትልናል። ጥሩ ጠባይ ያላቸው ልጆች ያሉት ወላጅ ስናገኝ አድናቆታችንን ከገለጽንለት በኋላ “ልጆችዎን በማሠልጠን ረገድ እንዲሳካልዎት የረዳዎት ምንድን ነው?” በማለት ልንጠይቀው እንችላለን። አንዲት እህት የሥራ ባልደረቦቿ ብዙ ጊዜ አንስተው የሚወያዩበትን ርዕሰ ጉዳይ ካስተዋለች በኋላ በጉዳዩ ላይ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ታካፍላቸዋለች። አንዲት የሥራ ባልደረባዋ በቅርቡ እንደምታገባ ስታውቅ አንድ ሰው ለሠርጉ ሊያደርገው ስለሚገባው ቅድመ ዝግጅት የሚናገር ንቁ! መጽሔት ሰጠቻት። ይህ ሁኔታ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለማድረግ መንገድ ከፍቶላታል።
8. ውይይት ለመጀመር ጽሑፎቻችንን እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?
8 ውይይት ለመጀመር የሚቻልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ጽሑፎቻችንን ሌሎች ሊያዩት በሚችሉበት ሁኔታ ማንበብ ነው። አንድ ወንድም ከመጠበቂያ ግንብ ወይም ከንቁ! መጽሔት ላይ ትኩረት ሊስብ የሚችል ርዕስ ከፍቶ የማንበብ ልማድ አለው። አጠገቡ ያለው ሰው መጽሔቱን መመልከት እንደጀመረ ካስተዋለ ጥያቄ ይጠይቀዋል ወይም ስለ ርዕሰ ጉዳዩ አጠር ያለ ሐሳብ ይነግረዋል። ብዙ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ውይይት ለመጀመር ብሎም ምሥክርነት ለመስጠት ያስችላል። አንዳንድ ጽሑፎቻችንን ሌሎች ሊያዩት በሚችሉበት ቦታ ማስቀመጥ የሥራ ባልደረቦቻችንን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆችን ትኩረት ሊስብ ስለሚችል ስለ ጽሑፎቹ ጥያቄ እንዲጠይቁ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
9, 10. (ሀ) መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) እናንተስ ለመመሥከር የሚያስችሏችሁን አጋጣሚዎች መፍጠር የቻላችሁት እንዴት ነው?
9 ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች መፍጠር፦ የስብከቱ ሥራ አንገብጋቢ ከመሆኑ አንጻር መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምንመሠክረው አጋጣሚው ሲመቻች ብቻ እንደሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። ከዚህ ይልቅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ ለሌሎች ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ይኖርብናል። ሊያጋጥምህ የሚችለውን ግለሰብና ከእሱ ጋር እንዴት ተግባብተህ ውይይት መጀመር እንደምትችል ከወዲሁ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የምታበረክታቸው ጽሑፎች ከእጅህ አይለዩህ።—1 ጴጥ. 3:15
10 ብዙ አስፋፊዎች ዘዴኛ በመሆን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ሕንጻ ላይ የምትኖር አንዲት እህት በሕንጻው የመዝናኛ ስፍራ ውስጥ ተቀምጣ ውብ የሆነ መልክአ ምድር ሊወጣቸው የሚችሉ ቁርጥራጮችን እየገጣጠመች ትጫወታለች። በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ቆም ብለው ስለ ሥዕሉ ውበት አስተያየት ሲሰጡ አጋጣሚውን በመጠቀም ውይይት ትጀምርና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አምላክ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ለማምጣት ስለገባው ተስፋ ትነግራቸዋለች። (ራእይ 21:1-4) እናንተስ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሏችሁን መንገዶች መፍጠር ትችላላችሁ?
11. መደበኛ ባልሆነ መንገድ የመሠከርንለትን ሰው ተከታትለን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
11 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተከታትሎ መርዳት፦ ሰሚ ጆሮ ያለው ሰው ካገኛችሁ እሱን ተከታትላችሁ ለመርዳት ጥረት አድርጉ። ተገቢ ሆኖ ካገኛችሁት “ባደረግነው ውይይት በጣም ተደስቻለሁ፤ ታዲያ በሌላ ጊዜም ለመወያየት እንዴት መገናኘት እንችላለን?” ማለት ትችሉ ይሆናል። አንዳንድ አስፋፊዎች ደግሞ “ባደረግነው ውይይት ተደስቻለሁ። አሁን ስለተወያየንባቸው ነገሮች ይበልጥ ማወቅ የሚፈልጉ ከሆነ በዚህ አድራሻ ሊያገኙኝ ይችላሉ” በማለት አድራሻቸውንና የስልክ ቁጥራቸውን ለግለሰቡ ይሰጣሉ። ግለሰቡን ተከታትላችሁ መርዳት የማትችሉ ከሆነ በአካባቢው ያለ ጉባኤ እንዲረዳው ለማድረግ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የሚለውን ቅጽ ወዲያውኑ ሞልታችሁ ለጉባኤያችሁ ጸሐፊ መስጠት ትችላላችሁ።
12. (ሀ) መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከር ያሳለፍነውን ጊዜ በማስታወሻችን ላይ መመዝገብና ሪፖርት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከር ምን ውጤት ተገኝቷል? (“መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ጥሩ ውጤት ያስገኛል!” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
12 መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከር ያሳለፍነውን ጊዜ በሪፖርታችን ውስጥ ማካተት ይኖርብናል። ስለዚህ በዚህ መንገድ በቀን ውስጥ ያገለገላችሁት ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ቢሆን እንኳ ደቂቃውን በማስታወሻችሁ ላይ መመዝገብ እንዳለባችሁ መዘንጋት የለባችሁም። የሚከተለውን አኃዝ ልብ በሉ፦ እያንዳንዱ አስፋፊ በየቀኑ ለአምስት ደቂቃ ያህል መደበኛ ባልሆነ መንገድ ቢመሠክር ይህ ሰዓት ሲደመር በወር ከ17 ሚሊዮን በላይ ሊሆን ይችላል!
13. መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንድንመሠክር የሚገፋፋን ምንድን ነው?
13 መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንድንመሠክር የሚያነሳሳን ከሁሉ የላቀው ምክንያት ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር ነው። (ማቴ. 22:37-39) ልባችን ለይሖዋ ባሕርያትና ለዓላማው ባለን አድናቆት ከተሞላ ‘የመንግሥቱን ግርማና ክብር ለማሳወቅ’ እንገፋፋለን። (መዝ. 145:7, 10-12) ለሰዎች ያለን ልባዊ አሳቢነት የምናገኘውን እያንዳንዱን አጋጣሚ ተጠቅመን ጊዜው ከማብቃቱ በፊት የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች እንድንሰብክ ያነሳሳናል። (ሮም 10:13, 14) መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር አስቀድመን በማሰብና መጠነኛ ዝግጅት በማድረግ ሁላችንም በዚህ የስብከት ዘዴ መካፈል እንችላለን፤ እንዲህ በማድረግ ልበ ቅን የሆነ አንድ ሰው እውነትን እንዲያውቅ መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም እንችል ይሆናል።
[ከገጽ 4 የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከሰዎች ጋር ሌሎች ጉዳዮችን አንስተን የመጨዋወት ግብ ማውጣት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል
[ከገጽ 5 የተቀነጨበ ሐሳብ]
ብዙ አስፋፊዎች ዘዴኛ በመሆን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ውይይት ለመጀመር የሚረዱ ሐሳቦች
◼ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ
◼ ተግባቢ የሚመስሉትንና የማይቸኩሉ ሰዎችን ምረጥ
◼ ዓይን ዓይናቸውን ተመልከት፣ ፈገግ በልና ሊያግባባችሁ የሚችል አንድ ርዕሰ ጉዳይ አንሳ
◼ ጥሩ አዳማጭ ሁን
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ጥሩ ውጤት ያስገኛል!
• አንድ ወንድም ጋራዥ ውስጥ መኪናው እስክትጠገንለት እየተጠባበቀ ሳለ አጠገቡ ለነበሩ ሰዎች ከመሠከረላቸው በኋላ የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት በመስጠት በሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ ጋበዛቸው። ከአንድ ዓመት በኋላ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ አንድ የማያውቀው ወንድም መጥቶ ሞቅ ባለ ስሜት ይህን ወንድም ሰላም አለው። ይህ ሰው ከዓመት በፊት ጋራዥ ውስጥ የመጋበዣ ወረቀት ከሰጣቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነበር! ሰውየው በዚያ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ንግግሩን ያዳመጠ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራለት ስሙን አስመዝግቦ ነበር። አሁን እሱም ሆነ ሚስቱ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
• እውነትን መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሰማች አንዲት እህት ከልጆቿ ጋር በተያያዘ የምታገኛቸውን ሰዎች እንደ ልዩ የአገልግሎት ክልሏ አድርጋ ትመለከታቸዋለች። በዚህ የአገልግሎት ክልሏ ውስጥ ጎረቤቶቿ፣ በትምህርት ቤትና በወላጆች ስብሰባ ላይ የምታገኛቸው ወላጆች ይገኙበታል። ከሰዎች ጋር ስትተዋወቅ ምንጊዜም መጽሐፍ ቅዱስ ልጆቿን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግላት መጽሐፍ መሆኑን የሚገልጽ ቀለል ያለና ከልብ የመነጨ ሐሳብ ትነግራቸዋለች፤ ከዚያም ርዕስ ቀይራ ስለ ሌላ ጉዳይ ማውራት ትጀምራለች። ይሁንና በዚህ መንገድ ውይይት ስለምትጀምር በውይይቱ መሃል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማንሳት ከባድ አይሆንባትም። ይህን ዘዴ በመጠቀም 12 ሰዎች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ረድታለች።
• አንዲት እህት የኢንሹራንስ አሻሻጭ የሆነ ሰው ወደ ቤቷ ሲመጣ አጋጣሚውን ምሥክርነት ለመስጠት ተጠቅማበት ነበር። ሰውየውን የተሟላ ጤንነት፣ ደስታና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት አስተማማኝ የሆነ ዋስትና ቢያገኝ ደስ ይለው እንደሆነ ጠየቀችው። እሱም ደስ እንደሚለው ከገለጸላት በኋላ እንዲህ ያለ ዋስትና የሚሰጠው የትኛው ኢንሹራንስ እንደሆነ ጠየቃት። እህት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን ተስፋ አሳይታው ጽሑፍ አበረከተችለት፤ ሰውየውም ጽሑፉን በአንድ ምሽት አንብቦ ጨረሰው። ከዚያም ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ዝግጅት የተደረገለት ሲሆን በስብሰባዎችም ላይ መገኘት ጀመረ። ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ ተጠምቋል።
• አንዲት እህት በአውሮፕላን እየተጓዘች እያለ አጠገቧ ከተቀመጠች ሴት ጋር መነጋገር የጀመረች ከመሆኑም በላይ ለሴትየዋ መሠከረችላት። በጉዟቸው መገባደጃ ላይ እህት አድራሻዋንና የስልክ ቁጥሯን ለሴትየዋ በመስጠት በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷ ሲመጡ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኗት እንድትጠይቅ አበረታታቻት። በማግስቱ ሁለት እህቶች የሴትየዋን በር አንኳኩ። ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረች ሲሆን ፈጣን እድገት በማድረግ ተጠመቀች፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይህች እህት ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጠናት ጀመረች።
• ማየት የተሳናቸውና በመጦሪያ ተቋም ውስጥ የሚኖሩ 100 ዓመት የሆናቸው አንድ ወንድም ብዙ ጊዜ “የአምላክ መንግሥት ያስፈልገናል” ብለው ይናገራሉ። ይህ አባባላቸው ነርሶቹና ሌሎች ሕሙማን ጥያቄ እንዲያነሱ ስላደረጋቸው ወንድም ስለዚህ መንግሥት ለማብራራት አጋጣሚ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። እዚያ ከሚሠሩት ሴቶች መካከል አንዷ በገነት ውስጥ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ጠየቀቻቸው። እሳቸውም “በዚያ ጊዜ ማየትና እንደገና ቆሜ መሄድ ስለምችል ተሽከርካሪ ወንበሬን አቃጥለዋለሁ” በማለት መለሱላት። እኚህ ወንድም ማየት ስለማይችሉ ይህች ሴት መጽሔቶችን እንድታነብላቸው ይጠይቋታል። ልጃቸው ልትጠይቃቸው ስትመጣ ሴትየዋ መጽሔቶቹን ወደ ቤቷ መውሰድ ትችል እንደሆነ ጠየቀቻት። ነርሷ “የመጦሪያ ተቋማችን አዲሱ መሪ ቃል ‘መንግሥቱ ያስፈልገናል’ የሚል ነው” በማለት ለልጃቸው ነግራታለች።
• አንዲት እህት ምግብ ቤት ውስጥ ምግብ ለመውሰድ ተሰልፋ እያለ በአቅራቢያዋ የተቀመጡ አረጋውያን ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሲወያዩ የሚያወሩት ነገር ጆሮዋ ጥልቅ አለ። ከመካከላቸው አንዱ መንግሥት ችግሮቻቸውን ሊፈታላቸው እንደማይችል ተናገሩ። በዚህ ጊዜ እህት ‘ይህን አጋጣሚ መጠቀም አለብኝ’ ስትል አሰበች። አጠር ያለ ጸሎት ካቀረበች በኋላ ወደ ሰዎቹ ጠጋ አለች። ራሷን ካስተዋወቀች በኋላ የሰውን ዘር ችግሮች በሙሉ ስለሚፈታው የአምላክ መንግሥት ነገረቻቸውና የያዘችውን ብሮሹር አበረከተችላቸው። በዚህ ጊዜ የምግብ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ወደ እነሱ ጠጋ አለ። እህት ሥራ አስኪያጁ ምግብ ቤቱን ለቃ እንድትሄድ የሚነግራት መስሏት ነበር። ሆኖም ሰውየው ውይይቱን ሲያዳምጥ እንደነበር ገልጾ እሱም ብሮሹሩን መውሰድ እንደሚፈልግ ነገራት። ውይይቱን ስታዳምጥ የነበረች አንዲት የምግብ ቤቱ ሠራተኛ ደግሞ እያለቀሰች ወደ እነሱ ተጠጋች። ይህቺ ሴት ከዚህ ቀደም መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና የነበረ ሲሆን እንደገና ጥናቷን የመቀጠል ፍላጎት አሳይታለች።