እሁድ ቀን በአገልግሎት መካፈል ትችላላችሁ?
1. ጳውሎስና ጓደኞቹ በፊልጵስዩስ በነበሩበት ወቅት ካደረጉት ነገር ምን እንማራለን?
1 ዕለቱ ሰንበት ስለሆነ በፊልጵስዩስ የሚኖሩት አብዛኞቹ አይሁዳውያን እረፍት ላይ ነበሩ። ጳውሎስና ጓደኞቹ የሚስዮናዊ ጉዟቸውን በሚያደርጉበት ወቅት ወደዚች ከተማ ጎራ ብለው ነበር። እነሱም በዚህ ዕለት አገልግሎት ከመውጣት ይልቅ እረፍት ቢያደርጉ ብዙ ሲሠሩ ከመቆየታቸው አንጻር ማንም ሊወቅሳቸው የሚችል አልነበረም። ይሁንና አይሁዳውያን ከከተማዋ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ስፍራ ለጸሎት እንደሚሰባሰቡ ስላወቁ አጋጣሚውን ተጠቅመው ለሰዎቹ ለመመሥከር ወደዚያ አመሩ። በዚህም የተነሳ ሊዲያ የተባለች ሴት ምሥራቹን የሰማች ሲሆን እሷና በቤቷ የሚኖሩ ሰዎችም ተጠመቁ፤ ጳውሎስና ጓደኞቹ ባገኙት ውጤት ምን ያህል ተደስተው ይሆን! (ሥራ 16:13-15) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች እሁድ ቀን የማረፍ ልማድ አላቸው፤ ታዲያ በዚህ ዕለት የተወሰነውን ጊዜ ለእነዚህ ሰዎች ለመመሥከር ለምን አንጠቀምበትም?
2. እሁድ ቀን ያለ ምንም እንግልት መስበክ የቻልነው የይሖዋ ሕዝቦች ምን መሥዋዕትነት ስለከፈሉ ነው?
2 በእሁድ ቀን ምሥራቹን ለመስበክ የተደረገው ትግል፦ በ1927 የይሖዋ ሕዝቦች በየሳምንቱ እሁድ የተወሰነ ሰዓት በአገልግሎት እንዲያሳልፉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸው ነበር። በእሁድ ቀን መስበክ ሲጀምሩ ግን ወዲያውኑ ተቃውሞ ተነሳ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብዙ የአምላክ አገልጋዮች የእሁድን የሰንበት ሕግ ጥሳችኋል፣ የሰዎችን ሰላም ነስታችኋል እንዲሁም ያለ ፈቃድ ሽያጭ አካሂዳችኋል በሚል ታሰሩ። ይሁንና የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ ተስፋ አልቆረጡም። በ1930ዎቹ ዓመታት ላይ “የቡድን ዘመቻ” በማደራጀት በአንድ አካባቢ ያሉ ጉባኤዎች በኅብረት ሆነው አንድን ክልል መሸፈን ጀመሩ። ባለሥልጣናቱ አስፋፊዎቹን ለማሰር ሙከራ ያደረጉባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ቁጥራቸው በጣም ብዙ ስለነበር ምሥራቹን ከመስበክ ሊያስቆሟቸው አልቻሉም። ታዲያ እሁድ ቀን ምንም ዓይነት እንግልት ሳይደርስብን መስበክ እንድንችል እነዚህ ወንድሞች የከፈሉልንን መሥዋዕትነት ከልብ ታደንቃላችሁ?
3. እሁድ ቀን ለአገልግሎት አመቺ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ለስብከት በጣም አመቺ የሆነ ቀን፦ እሁድ ቀን ብዙ ሰዎች ሥራ ስለማይኖራቸው ቤታቸው ይገኛሉ። በዚያ ላይ በአብዛኛው ዘና ስለሚሉ ተረጋግተው ያዳምጣሉ። ቤተ ክርስቲያን የመሄድ ልማድ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች በዚህ ቀን ስለ አምላክ ለመነጋገር ይበልጥ ፍላጎት ይኖራቸዋል። እሁድ ቀን ስብሰባ ካለን ለዚያ ብለን የምንለብሰው ልብስ ለአገልግሎትም ተስማሚ ስለሚሆን ከስብሰባው በፊት ወይም በኋላ ለማገልገል ለምን እቅድ አናወጣም? አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የሚበላ ነገር በቦርሳችን መያዝ እንችላለን።
4. እሁድ ቀን የተወሰነውን ጊዜ በአገልግሎት ማሳለፋችን ምን በረከት ሊያስገኝልን ይችላል?
4 እሁድ ቀን ለአገልግሎት የምናውለው የተወሰነውን ሰዓት ብቻ ስለሚሆን እረፍት ለማድረግ ብንፈልግ እንኳ በቂ ጊዜ ይኖረናል። በቅዱስ አገልግሎት ከተካፈልን በኋላ የምናደርገው እረፍት ደግሞ ጣፋጭ ይሆንልናል። (ምሳሌ 3:24) እንደ ሊዲያ ያሉ ሰዎችን በማግኘትም ልንባረክ እንችላለን!