የመንግሥት ዜና ቁጥር 38 በኅዳር ወር ይሰራጫል!
1. ሰዎች ሙታንን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች ያነሳሉ? በኅዳር ወር እነዚህ ጥያቄዎች የሚመለሱላቸው እንዴት ነው?
1 የሰው ልጆች፣ ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን አንድ የጋራ ጠላት አላቸው፤ ይኸውም ሞት ነው። (1 ቆሮ. 15:26) ብዙ ሰዎች ሙታን የት እንዳሉና ከእነሱ ጋር እንደገና መገናኘት ይችሉ እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ጉባኤዎች በሙሉ የሞቱ ሰዎች እንደገና በሕይወት መኖር ይችላሉ? የተባለውን የመንግሥት ዜና ቁጥር 38ን ለአንድ ወር ያህል ያሰራጫሉ። ይህ ልዩ ዘመቻ ኅዳር 1 ይጀምራል። የመንግሥት ዜና ቁጥር 38 በልዩ ዘመቻው ወቅት ከተሰራጨ በኋላ እንደ ማንኛውም ትራክት በአገልግሎት ላይ እንጠቀምበታለን።
2. የመንግሥት ዜና ቁጥር 38 የተዘጋጀው እንዴት ነው?
2 የተዘጋጀው እንዴት ነው? የመንግሥት ዜና ቁጥር 38 የተዘጋጀው በቁመቱ ለሁለት እንዲታጠፍ ተደርጎ ሲሆን በፊት ገጹ ላይ ትኩረት የሚስብ ጥያቄ ይገኛል፤ ከሥሩም “ይችላሉ? አይችሉም? ወይስ ምናልባት?” የሚሉ አማራጭ መልሶች ቀርበዋል። አንባቢው የመንግሥት ዜናውን ሲከፍት በፊተኛው ገጽ ላይ ላለው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ምን መልስ እንደሚሰጥና የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝለት መመልከት ይችላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል የሚችለው ለምን እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ ያገኛል። የመንግሥት ዜናው የኋላ ገጽ የአንባቢውን ስሜት የሚቀሰቅስ ጥያቄ የያዘ ሲሆን የበለጠ ለማወቅ ጥረት እንዲያደርግም ያበረታታዋል።
3. የመንግሥት ዜና ቁጥር 38 የሚሰራጨው እንዴት ነው?
3 የሚሰራጨው እንዴት ነው? ይህ ዘመቻ የሚከናወነው የመታሰቢያው በዓል ወይም የአውራጃ ስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶች በሚሰራጩበት መንገድ ነው። ሽማግሌዎች ከሚያዝያ 1, 2013 ደብዳቤ ጋር በሚስማማ መልኩ ጉባኤው ክልሉን እንዴት መሸፈን እንዳለበት መመሪያ ይሰጣሉ። አነስተኛ ክልል ያላቸው ጉባኤዎች በአቅራቢያቸው ሰፊ ክልል ያላቸው ጉባኤዎች ካሉ እነዚህን ጉባኤዎች ማገዝ ይችላሉ። የመንግሥት ዜና ቁጥር 38ን የምትወስዱት ለአንድ ሳምንት የምትጠቀሙበትን ያህል ብቻ መሆን አለበት። በዘመቻው ወቅት ከቤት ወደ ቤት አሰራጭተን የተረፈንን የመንግሥት ዜና የአደባባይ ምሥክርነት ስንሰጥ ልንጠቀምበት እንችላለን። ወሩ ከማለቁ በፊት ሁሉም የመንግሥት ዜና ተሰራጭቶ ካለቀ ሌሎች ትራክቶችን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ማበርከት ይኖርብናል። በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ ላይ ትኩረት የምናደርገው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ በመጋበዝ ላይ ሳይሆን በልዩ ዘመቻው ላይ ነው። ቅዳሜና እሁድ፣ ሁኔታው አመቺ እንደሆነ ከተሰማን መጽሔቶችንም ማበርከት እንችላለን። ታዲያ በዚህ ልዩ ዘመቻ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅታችኋል?