ውጤታማ መግቢያዎችን ማዘጋጀት የሚቻለው እንዴት ነው?
1. ጥሩ መግቢያ መጠቀም ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
1 የአንድ ምግብ ግሩም መዓዛ ምግቡን ለመብላት እንድንጓጓ እንደሚያደርገን ሁሉ፣ ጥሩ መግቢያዎችም አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለመጀመር በር ይከፍታሉ። ውጤታማ መግቢያዎች ርዝመታቸው ወይም ይዘታቸው ሊለያይ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ግሩም ጣዕም እንዳለው ምግብ ሁሉ እነዚህ መግቢያዎችም አስቀድሞ ማሰብንና ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃሉ። (ምሳሌ 15:28) ታዲያ አንድ መግቢያ ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
2. ትኩረት የሚስብ መግቢያ ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችን ምረጡ፦ የምንጠቀመው መግቢያ ትኩረት የሚስብ ካልሆነ፣ የቤቱ ባለቤት በውይይቱ እንዳይቀጥል እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መግቢያ ስታዘጋጁ፣ በክልላችሁ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። በአካባቢያችሁ ያሉ ሰዎች ስለ መልካም አስተዳደር፣ ስለ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ወይም ጦርነት ስለሚወገድበት ጊዜ መወያየት ያስደስታቸዋል? ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ስለ አንድ ጉዳይ ያላቸውን አመለካከት መግለጽ ያስደስታቸዋል፤ ስለዚህ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚያበረታቱ ጥያቄዎችን አዘጋጁ። በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ከሚወጡት የመግቢያ ሐሳቦች መካከል አንዱን መርጣችሁ ለክልላችሁ በሚስማማ መልኩ ልትጠቀሙበት ትችሉ ይሆን? አልፎ አልፎ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ወቅት አንዳንድ የመግቢያ ሐሳቦችን ለምን አትለማመዱም?
3. መግቢያችን በክልላችን ውስጥ ካሉ ሰዎች ባሕልና አስተዳደግ ጋር እንዲስማማ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
3 የሰዎችን ባሕልና አስተዳደግ ግምት ውስጥ አስገቡ፦ በአንዳንድ አካባቢዎች፣ የመጣነው ለምን እንደሆነ ወዲያውኑ መናገር ይጠበቅብናል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ወደ ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት ስለ ቤቱ ባለቤት ደኅንነት አለመጠየቅ እንዲሁም ስለ ራሳችን አንዳንድ ነገሮችን አለመግለጽ እንደ ነውር ይቆጠራል። በሌሎች ቦታዎች ሰዎቹ ክርስቲያኖች ስለሆኑ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰን ውይይታችንን መጀመር እንችል ይሆናል። (ሥራ 2:14-17) በአካባቢው ያሉት ሰዎች ክርስቲያን ካልሆኑ ወይም ጨርሶ ሃይማኖት ከሌላቸው ወዲያውኑ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከማንሳት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ተመላልሶ መጠይቅ በምናደርግላቸው ወቅት መጠቀማችን የተሻለ ሊሆን ይችላል።—ሥራ 17:22-31
4. ያዘጋጀነውን መግቢያ ስንናገር መጀመሪያ ላይ የምንጠቀምባቸውን ቃላት በተመለከተ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል?
4 መጀመሪያ ላይ የምንናገራቸው ቃላት፦ መጀመሪያ ላይ የምትናገሯቸውን ቃላት በጥንቃቄ ምረጡ። ብዙውን ጊዜ አጭርና ያልተወሳሰቡ ዓረፍተ ነገሮችን መጠቀም የተሻለ ነው። የመጀመሪያዎቹን ቃላት የምንናገርበት መንገድም ሊታሰብበት ይገባል። በግለት ተናገሩ። ለግለሰቡ እንደምታስቡለት በሚያሳይና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ፈገግ ብላችሁ አናግሩት። እነዚህን ሐሳቦች በሥራ ላይ ማዋላችን በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች “ከይሖዋ ማዕድ” ለመመገብ እንዲነሳሱ የሚያደርግ ጥሩ መግቢያ ለማዘጋጀት ይረዳናል።—1 ቆሮ. 10:21