ማንበብ የሚቸግራቸውን ሰዎች መርዳት
1. ማንበብ የሚቸግራቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ፈታኝ የሚሆነው ለምንድን ነው?
1 በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ማንበብ የሚቸግራቸው ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፤ ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በሌሎች መጻሕፍት አማካኝነት ስናነጋግራቸው ሊሸማቀቁ ይችላሉ። እንዲህ ላሉ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ መስጠት ያን ያህል ጥሩ ውጤት ላያስገኝ ይችላል። ታዲያ በመንፈሳዊ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ከ20 በላይ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎችን በዚህ ረገድ ምን እንደሚያደርጉ ጠይቀናቸው ነበር። አስፋፊዎቹ የሰጡት ሐሳብ ከዚህ በታች ቀርቧል።
2. ማንበብ የሚቸግራቸውን ሰዎች ለመርዳት የትኞቹ መሣሪያዎች ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል?
2 አንድ ሰው ማንበብ የማይችል ወይም የማንበብ ችሎታው ውስን ከሆነ አምላክን ስማ ወይም አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለውን ብሮሹር ተጠቅሞ ጥናት ማስጀመር ይቻላል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ አቅኚ ለግለሰቡ ሁለቱንም ብሮሹሮች ካሳየው በኋላ የትኛውን እንደሚመርጥ ይጠይቀዋል። በኬንያ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እነዚህ ብሮሹሮች በክልሉ በጣም ውጤታማ እንደሆኑ ገልጿል፤ ምክንያቱም በአፍሪካውያን ባሕል መሠረት ሰዎች የሚማሩት በተረት መልክ እንጂ ጥያቄና መልስ ያለው ውይይት በማድረግ አይደለም። በሌላ በኩል አንድ የተማረ ሰው እያነበቡ መጠያየቅ ሊቀልለው ይችላል፤ ነገር ግን ይህ የማስተማር ዘዴ በመደበኛ ትምህርት ላልገፉ ሰዎች ከባድ ሊሆን ይችላል። በርካታ አስፋፊዎች የተወሰነ የማንበብ ችሎታ ያለው ፍላጎት ያሳየ ሰው ሲያገኙ ከአምላክ የተላከ ምሥራች! ወይም የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ! የተባሉትን ብሮሹሮች፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመው ጥናት ያስጀምራሉ።
3. ማንበብ የማይችሉ ሰዎችን በማስተማር ረገድ ውጤታማ ለመሆን ከፈለግን የትኞቹን ነገሮች ማስታወስ ይኖርብናል?
3 አድናቆታችሁን ግለጹ፦ ማንበብ የማይችሉ ሰዎች በሁኔታቸው ሊያፍሩ ወይም ለራሳቸው ዝቅ ያለ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። ለእነዚህ ሰዎች እውነትን ለማስተማር ከመነሳታችን በፊት መጀመሪያ ልንወስደው የሚገባ እርምጃ ዘና ያለ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ነው። አብዛኞቹ ማንበብ የማይችሉ ሰዎች ብሩሕ አእምሮ ስላላቸው መማር ይችላሉ። እነዚህን ሰዎች ዝቅ አድርጋችሁ እንደምትመለከቷቸው የሚያሳይ ነገር ማድረግ የለባችሁም፤ ከዚህ ይልቅ በአክብሮት ልትይዟቸው ይገባል። (1 ጴጥ. 3:15) የሚያደርጉት ጥረት ከንቱ እንዳልሆነና መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ እንደሆነ ከተገነዘቡ ጥናቱን ለመቀጠል ይነሳሳሉ። በመሆኑም አድናቆታችሁን ከመግለጽ ወደኋላ አትበሉ።
ማንበብ የማይችሉ ሰዎች በሁኔታቸው ሊያፍሩ ወይም ለራሳቸው ዝቅ ያለ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። ለእነዚህ ሰዎች እውነትን ለማስተማር ከመነሳታችን በፊት መጀመሪያ ልንወስደው የሚገባ እርምጃ ዘና ያለ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ነው
4. የማንበብ ችሎታቸው ውስን የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ለጥናታቸው እንዲዘጋጁ ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ተማሪው የማንበብ ችሎታው ውስን ቢሆንም እንኳ ለጥናቱ እንዲዘጋጅ አበረታቱት። በደቡብ አፍሪካ ያሉ አንዳንድ አስፋፊዎች ጥናቶቻቸው፣ ማንበብ የሚችል የቤተሰባቸው አባል ወይም ጓደኛቸው እንዲረዳቸው መጠየቅ እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል። በብሪታንያ የሚገኝ አንድ አስፋፊ ደግሞ ጥናቶቹ የተወሰኑ አንቀጾችን በእሱ መጽሐፍ እንዲከታተሉ ያደርጋል፤ ይህም መልሶቹ ላይ ማስመር ጥናቱን ምን ያህል ቀላል እንደሚያደርግላቸው እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። በሕንድ የሚኖር አንድ ወንድም በቀጣዩ ሳምንት በሚሸፈነው ትምህርት ላይ የሚገኙትን ሥዕላዊ መግለጫዎች አስቀድመው በመመልከት እንዲያሰላስሉባቸው ጥናቶቹን ያበረታታቸዋል።
5. ጥናቱን በምንመራበት ወቅት ትዕግሥት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 ትዕግሥተኛ ሁኑ፦ የምትጠቀሙበት የማስጠኛ ጽሑፍ ምንም ይሁን ምን ትኩረት ማድረግ ያለባችሁ ዋና ዋና ነጥቦቹ ላይ ነው፤ ጥናታችሁም እነዚህን ነጥቦች በሚገባ እንዲገነዘብ እርዱት። መጀመሪያ አካባቢ ውይይታችሁ ከ10 ወይም ከ15 ደቂቃ ባይበልጥ ጥሩ ነው። ብዙ ክፍል ለመሸፈን አትሞክሩ፤ ጥቂት አንቀጾች ላይ ብቻ መወያየታችሁ በቂ ሊሆን ይችላል። ተማሪው የሚያነበው ቀስ እያለ ከሆነ ትዕግሥተኛ ሁኑ። ለይሖዋ ያለው አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ የማንበብ ችሎታውን ለማሻሻል ይነሳሳ ይሆናል። ጥናታችሁ አድናቆቱ እንዲጨምር ለማድረግ ገና ከጅምሩ በስብሰባ ላይ እንዲገኝ አበረታቱት።
6. አንድን ሰው ንባብ ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው?
6 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማንበብ መቻላቸው ፈጣን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል። (መዝ. 1:1-3) ብዙ አስፋፊዎች በጥናቱ መጨረሻ ላይ ጥቂት ደቂቃዎች ወስደው ጥናታቸውን ማንበብና መጻፍ ማስተማራቸው ጠቃሚ እንደሆነ ተመልክተዋል፤ ይህን ለማድረግ አፕላይ ዩርሰልፍ ቱ ሪዲንግ ኤንድ ራይቲንግ (በአማርኛ አይገኝም) የተባለውን ጽሑፍ የሚጠቀሙ አሉ። ተማሪው ተስፋ ከቆረጠ በንባብ ረገድ ያደረገውን መሻሻል ጠቅሳችሁ ብትነግሩት በራስ የመተማመን ስሜቱ ሊገነባ ይችላል። ይሖዋ ጥረቱን እንደሚባርክለት አረጋግጡለት፤ እንዲሁም የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት እንዲጸልይ አበረታቱት። (ምሳሌ 16:3፤ 1 ዮሐ. 5:14, 15) በብሪታንያ የሚገኙ አንዳንድ አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው ሊደርሱባቸው የሚችሉ ምክንያታዊ ግቦችን ደረጃ በደረጃ እንዲያወጡ ያበረታቷቸዋል፤ ለምሳሌ መጀመሪያ ላይ ሆሄያቱን በሙሉ ለማጥናት ግብ እንዲያወጡ ያደርጋሉ። ከዚያም የተወሰኑ ጥቅሶችን ከመረጡ በኋላ እነሱን ፈልገው ማንበብ እንዲማሩ ያደርጋሉ፤ በመጨረሻ ደግሞ ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማንበብ ግብ እንዲያወጡ ያበረታቷቸዋል። አንድን ሰው ንባብ ማስተማር ከፈለግን ማንበብ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በማስተማር ሳንወሰን የማንበብ ፍላጎት እንዲያድርበት ማድረግ ይኖርብናል።
7. ማንበብ ለሚቸግራቸው ሰዎች እውነትን ከማስተማር ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ በትምህርት ያልገፉ ሰዎችን ዝቅ አድርጎ አይመለከትም። (ኢዮብ 34:19) ይሖዋ የሚመለከተው የግለሰቡን ልብ ነው። (1 ዜና 28:9) በመሆኑም ማንበብ ለሚቸግራቸው ሰዎች እውነትን ከማስተማር ወደኋላ አትበሉ። እነዚህን ሰዎች ጥናት ለማስጀመር ሊረዷችሁ የሚችሉ በርካታ ግሩም መሣሪዎች አሉ። በጥናታቸው እየገፉ ሲሄዱ ደግሞ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ልትረዷቸው ትችላላችሁ።