ጥሩ የማንበብ ችሎታ የሌላቸውን ሰዎች አስተምሩ
1. በአገልግሎት ስንካፈል ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥመናል?
1 በአገልግሎት ስንካፈል አንዳንድ ጊዜ ጥሩ የማንበብ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች የሚያጋጥሙን ሲሆን ለእነዚህ ሰዎች እውነትን ማስተማር ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን?
2. ጥሩ የማንበብ ችሎታ ለሌላቸው ሰዎች አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? እንዴትስ?
2 አክብሯቸው፦ ይሖዋ የሚመለከተው የአንድን ሰው የልብ ሁኔታ እንጂ የትምህርት ደረጃውን አይደለም። (1 ሳሙ. 16:7፤ ምሳሌ 21:2) ስለሆነም ጥሩ የማንበብ ችሎታ የሌላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርገን አንመለከታቸውም። አብዛኛውን ጊዜ ማለት ይቻላል እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን በአክብሮትና በትዕግሥት የምንይዛቸው ከሆነ ለምናደርግላቸው እርዳታ በጎ ምላሽ ይሰጣሉ። (1 ጴጥ. 3:15) ግለሰቡን በዚህ መንገድ መያዝ ጥቅስ ወይም አንድ አንቀጽ እንዲያነብ ከመጫን መቆጠብን ይጨምራል። ግለሰቡ ውድ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እየተማረ ሲሄድ የአምላክን ቃል ‘በቀንና በሌሊት ማንበብ’ ደስታ እንደሚያስገኝ እየተገነዘበ ስለሚመጣ ይህን ደስታ ለማጣጣም ካለው ጉጉት የተነሳ የማንበብ ችሎታውን ለማሻሻል ይበልጥ ሊነሳሳ ይችላል።—መዝ. 1:2, 3 NW
3. ጥሩ የማንበብ ችሎታ ለሌላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ስናስተምር የትኞቹን ዘዴዎች መጠቀም እንችላለን?
3 የማስተማሪያ ዘዴዎች፦ ሥዕሎች፣ ሰዎችን ለማስተማርና የተማሩትን ነገር እንዲያስታውሱ ለመርዳት የሚያስችሉ በጣም ግሩም የማስተማሪያ ዘዴዎች ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ፣ በምታጠኑት ጽሑፍ ላይ ከሚገኝ አንድ ሥዕል ላይ ምን እንደተገነዘበ ልትጠይቀው ትችላለህ። ከዚያም ሥዕሉ የሚያስተምረው ነገር ምን እንደሆነ እንዲረዳ ግልጽ የሆኑ ጥያቄዎችን ጠይቀው። እንዲሁም ከሥዕሉ ላይ ለማስተማር የምትፈልገውን ነገር የሚያጎሉ ጥቅሶችን ተጠቀም። ሥዕሎቹን ትምህርቱን ለመከለስም ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። በአንድ ጊዜ ብዙ ትምህርት ለመሸፈን አትሞክር። የትምህርቱን ጭብጥና በውስጡ የተካተቱትን ዋና ዋና ነጥቦች አጉላ፤ በተጨማሪም በትምህርቱ ውስጥ ያልተካተቱ ነጥቦችን አታንሳ። ጥቅሶቹን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንብብ፤ እንዲሁም ተማሪው የተነበበው ጥቅስ የያዘውን መልእክት በእርግጥ ተረድቶት እንደሆነ ለማየት ጥያቄዎችን ጠይቀው። እንዲህ ማድረግህ ግለሰቡ በራሱ ተመራምሮ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለመረዳት እንዲጥር ስለሚያነሳሳው የማንበብ ችሎታውን ለማሻሻል ያለው ፍላጎት ሊጨምር ይችላል።
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን የማንበብ ችሎታውን እንዲያሻሽል እንዴት ልንረዳው እንችላለን?
4 የማንበብ ችሎታን ለማሻሻል የሚረዱ መሣሪያዎች፦ ጥሩ የማንበብ ችሎታ የሌለው ወይም አቀላጥፎ የማንበብ ችሎታን ለማዳበር አጋጣሚውን ያላገኘ ሰው አንድን ሐሳብ በመረዳትና በማስታወስ ረገድ ጎበዝ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለውን ሰው፣ ጥሩ አድርጎ የማንበብ ችሎታ ያለው ግለሰብ ሲያነብ የራሱን ጽሑፍ በመያዝ ቃላቱን አብሮ እያነበበ እንዲከታተል ልታበረታታው ትችላለህ። እንዲህ ማድረጉ የማንበብ ችሎታውን እንዲያሻሽል ሊረዳው ይችላል። አፕላይ ዩርሰልፍ ቱ ሪዲንግ ኤንድ ራይቲንግ (በአማርኛ አይገኝም) የተባለውን ብሮሹር ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። በአንዳንድ አካባቢዎች፣ ሽማግሌዎች የማንበብ ችሎታቸውን ማሻሻል የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት ሲሉ በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። ጥሩ የማንበብ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ለመዳን የሚያበቃቸውን ጥበብ እንዲያገኙ የሚያስችሏቸውን “ቅዱሳን መጻሕፍት” እንዲያውቁ በምናደርገው ጥረት እስከ አሁን የተመለከትናቸው ተግባራዊ ሐሳቦች ሊጠቅሙን ይችላሉ።—2 ጢሞ. 3:15