ይሖዋን በመፍራት ደስታ ማግኘትን መማር
“ልጆቼ ኑ፣ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።”—መዝሙር 34:11
1. ፍርሃት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የሚወገደው እንዴት ነው? ይህ ማለት ግን ሁሉም ዓይነት ፍርሃት ይጠፋል ማለት ነው?
በየትኛውም ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች ከፍርሃት ለመገላገል ይፈልጋሉ። ከወንጀልና ከዓመፅ ፍርሃት፣ ከሥራ አጥነት ፍርሃትና ከከባድ በሽታ ፍርሃት ነፃ ለመሆን በጣም ይናፍቃሉ። ይህ ነጻነት በአምላክ መንግሥት ሥር እውን ሲሆን ያ ጊዜ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! (ኢሳይያስ 33:24፤ 65:21–23፤ ሚክያስ 4:4) ሆኖም በዚያን ጊዜ የሚጠፋው ሁሉም ዓይነት ፍርሃት አይደለም፤ እኛም ብንሆን በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ዓይነት ፍርሃት እንዲወገድልን መፈለግ አይኖርብንም። ጥሩ ፍርሃት አለ፤ መጥፎ የሆነ ፍርሃትም አለ።
2. (ሀ) መጥፎው ፍርሃት የትኛው ነው? አስፈላጊው ፍርሃትስ የትኛው ነው? (ለ) አምላካዊ ፍርሃት ምንድን ነው? የተጠቀሱት ጥቅሶች ይህን የሚያመለክቱትስ እንዴት ነው?
2 ፍርሃት የአንድን ሰው የማመዛዘን ችሎታ የሚያሽመደምድ የአእምሮ መርዝ ሊሆን ይችላል። ድፍረትን ሊቦረቡርና ተስፋን ሊያመነምን ይችላል። እንዲህ ያለው ፍርሃት ከጠላቱ አካላዊ ጉዳት እንደሚደርስበት በተዛተበት ሰው ላይ ሊታይ ይችላል። (ኤርምያስ 51:30) ሥልጣን አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን ድጋፍና ተወዳጅነት ማግኘት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስብና በዚህ ረገድ የተዛባ አመለካከት ያለው ሰውም ይህን የመሰለ ፍርሃት ሊያድርበት ይችላል። (ምሳሌ 29:25) ይሁን እንጂ ጉዳት ላይ የሚጥል የግድየለሽነት ድርጊት ከመፈጸም የሚያግድ ጤናማ ዓይነት ፍርሃት አለ። አምላካዊ ፍርሃት ግን እነዚህን ነገሮች ብቻ ያካተተ አይደለም። አምላካዊ ፍርሃት ይሖዋን ቅር እንዳናሰኝ በመፍራትና የይሖዋን ግርማና ቅድስና በማድነቅ ላይ የተመሠረተ ጤናማ ፍርሃት ነው። (መዝሙር 89:7) ይህ ፍርሃት የሚመነጨው ፍቅራዊ ደግነቱንና ጥሩነቱን ከማወቅና ከማድነቅ ነው። (መዝሙር 5:7፤ ሆሴዕ 3:5) በተጨማሪም ይሖዋ ትእዛዙን የማይፈጽሙትን እስከ ሞት ለመቅጣት ሥልጣን ያለው የመጨረሻ ከፍተኛ ዳኛና ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን መገንዘብን ያካትታል።—ሮሜ 14:10–12
3. ለይሖዋ የምናሳየው ፍርሃት ሰዎች ለአንዳንድ አረማውያን አማልክት ከሚያሳዩት ፍርሃት የሚለየው እንዴት ነው?
3 አምላካዊ ፍርሃት ጤናማ እንጂ የሚያርበተብት አይደለም። አንድ ሰው ትክክል ለሆነ ነገር የጸና አቋም እንዲኖረው ይገፋፋዋል፤ ስህተት በመሥራት አቋሙን እንዳይለውጥ ያደርገዋል። ሰዎችን በፍርሃት የሚያርበተብት ክፉ አምላክ ነው ለሚባለው ለጥንቱ ፎቦስ ለተባለ የግሪካውያን አምላክ ሰዎች ያድርባቸው ከነበረው ፍርሃት የተለየ ዓይነት ፍርሃት ነው። አስከሬኖችን፣ እባቦችንና የሰዎችን የራስ ቅል እንደ ጌጥ አድርጎ ይጠቀማል የሚባለው ካሊ የተባለ የሂንዱዎች ደም የተጠማ አምላክ በሰዎች ላይ ያሳድራል ከሚባለው ዓይነት ፍርሃትም ፈጽሞ የተለየ ነው። አምላካዊ ፍርሃት ያቀራርባል እንጂ አያርቅም። ከፍቅርና ከአድናቆት ጋር የተሳሰረ ነው። ስለዚህ አምላካዊ ፍርሃት ወደ ይሖዋ እንድንሳብ ያደርጋል።—ዘዳግም 10:12, 13፤ መዝሙር 2:11
አንዳንዶች ይህ ፍርሃት ሲኖራቸው ሌሎች የሌላቸው ለምንድን ነው?
4. ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው የሰው ልጅ ወደ ምን ሁኔታ አሽቆልቁሏል? ለዚህስ ምክንያቱ ምንድን ነው?
4 የሰው ልጅ በአጠቃላይ በውስጡ ይህን የአምላካዊ ፍርሃት ባሕርይ እንዲያሳይ የሚገፋፋው ስሜት የለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 3:9–18 ላይ የሰው ልጅ ሲፈጠር ከነበረበት የፍጽምና ደረጃ ምን ያህል እንዳሽቆለቆለ ይገልጻል። ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ከኃጢአት ሥር የወደቁ መሆናቸውን ከተናገረ በኋላ ከመዝሙር መጽሐፍ በመጥቀስ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ” ብሏል። (መዝሙር 14:1ን ተመልከት።) ከዚያም በመቀጠል የሰው ልጆች አምላክን በመፈለግ ረገድ እንዴት ቸልተኛ እንደሆኑ፣ ደግነት እንደጎደላቸው፣ በንግግራቸው አታላዮች እንደሆኑ፣ ተራጋሚዎችና ደም አፍሳሾች እንደሆኑ በዝርዝር ገልጿል። ዛሬ የምንኖርበትን ዓለም ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ጥሩ መግለጫ ነው! አብዛኞቹ ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ደንታ ቢሶች ናቸው። ደግ መስለው የሚታዩበት ጊዜ ቢኖር እንኳን የይስሙላ ደግነት ነው፤ ያውም ጥቅም የሚያስገኝላቸው ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ውሸትና ቀፋፊ ንግግሮች የተለመዱ ሆነዋል። ደም መፋሰስ በዜና ላይ ብቻ ሳይሆን በመዝናኛ ፕሮግራምም ላይ ይቀርባል። እንዲህ ላለው ሁኔታ መፈጠር ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው? ሁላችንም የኃጢአተኛው አዳም ዘሮች መሆናችን የሚካድ ባይሆንም ሰዎች ጳውሎስ የዘረዘራቸውን እነዚህን ባሕርያት የኑሯቸው ክፍል አድርገው የተቀበሉበት ሌላ ምክንያት መኖር አለበት። ቁጥር 18 “በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም” በማለት ምክንያቱን ይገልጽልናል።—መዝሙር 36:1ን ተመልከት።
5. አንዳንድ ሰዎች አምላካዊ ፍርሃት ሲኖራቸው ሌሎቹ የሌላቸው ለምንድን ነው?
5 ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች አምላካዊ ፍርሃት ሲኖራቸው ሌሎቹ የሌላቸው ለምንድን ነው? ባጭሩ አንዳንድ ሰዎች አምላካዊ ፍርሃትን ሲኮተኩቱ ሌሎች ሳይኮተኩቱ በመቅረታቸው ነው። አምላክን መፍራት አብሮን የሚወለድ ባሕርይ ባይሆንም ሁላችንም ይህን ባሕርይ በውስጣችን የመኮትኮትና የማሳደግ ችሎታ አለን። አምላካዊ ፍርሃት በትምህርትና በሥልጠና የምናገኘው ባሕርይ ነው። ስለዚህ ይህ ባሕርይ ሕይወታችንን የሚመራልን ጠንካራ ኃይል እንዲሆን ከፈለግን ኮትኩተን ልናሳድገው ይገባል።
ደስ የሚያሰኝ ግብዣ
6. በመዝሙር 34:11 ላይ ያለውን ግብዣ ያቀረበልን ማን ነው? ይህ ጥቅስ አምላካዊ ፍርሃትን መማር እንደሚገባ የሚያሳየውስ እንዴት ነው?
6 ይሖዋን መፍራት እንድንማር በመዝሙር 34 ላይ አንድ አስደሳች ግብዣ ቀርቦልናል። ይህ መዝሙር የዳዊት መዝሙር ነው። ዳዊት ጥላ የነበረው ለማን ነው? ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ለሌላ ለማንም ሊሆን አይችልም። ሐዋርያው ዮሐንስ ለኢየሱስ የጠቀሰው ትንቢት በዚህኛው መዝሙር ቁጥር 20 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። (ዮሐንስ 19:36) በዘመናችን በቁጥር 11 ላይ በሚገኙት ዓይነት ቃላት “ልጆቼ ኑ፣ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” ብሎ የሚጋብዘን ኢየሱስ ነው። አምላካዊ ፍርሃት ልንማረው የምንችለው ነገር እንደሆነ ይህ በግልጽ ያሳያል። ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ እኛን ለማስተማር ሙሉ ብቃት አለው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
7. በተለይ ከኢየሱስ አምላካዊ ፍርሃትን የምንማረው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላካዊ ፍርሃትን አስፈላጊነት አሳምሮ ያውቃል። ዕብራውያን 5:7 ስለ ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ “እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት።” ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ያለውን የአምላካዊ ፍርሃት ባሕርይ በመከራ እንጨት ላይ ለመገደል ከመቅረቡ በፊትም እንኳ አሳይቷል። በምሳሌ ምዕራፍ 8 ላይ የአምላክ ልጅ በጥበብ እንደተመሰለ አስታውሱ። በምሳሌ 9:10 ላይ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ተብሎ ተነግሮናል። ስለዚህ ይህ አምላካዊ ፍርሃት የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ የነበረው የባሕርያቱ አንደኛና መሠረታዊ ክፍል ነበር።
8. በኢሳይያስ 11:2, 3 ላይ ይሖዋን ስለ መፍራት ምን እንማራለን?
8 ከዚህም በላይ ኢሳይያስ 11:2, 3 መሢሐዊ ንጉሥ ስለሚሆነው ስለ ኢየሱስ ሲናገር፦ “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል” ይላል። እንዴት ያለ ውብ መግለጫ ነው! የይሖዋ ፍርሃት የማያስደስት ነገር አይደለም። አዎንታዊና ገንቢ ነው። ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድርበት ግዛት በሙሉ የሚሰፍን ባሕርይ ነው። በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ በመግዛት ላይ ሲሆን የእርሱ ተገዥዎች ሆነው ለተሰበሰቡ ሰዎች ይሖዋን እንዲፈሩ በማስተማር ላይ ነው። እንዴት?
9. ኢየሱስ ክርስቶስ ይሖዋን መፍራትን እያስተማረን ያለው እንዴት ነው? ይሖዋን ስለ መፍራትስ ምን እንድንማር ይፈልጋል?
9 ኢየሱስ የጉባኤው የተሾመ ራስና መሲሐዊ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በጉባኤ ስብሰባዎቻችን፣ በወረዳና በልዩ ስብሰባዎቻችን እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎቻችን አማካኝነት አምላካዊ ፍርሃት ምን እንደሆነና በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምን እንደሆነ በግልጽ እንድንገነዘብ ይረዳናል። በዚህ መንገድ ልክ እንደ እርሱ ይሖዋን በመፍራት ደስታ ማግኘትን እንድንማር ስለዚህ ባሕርይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖረን ለማድረግ ይጥራል።
የሚፈለገውን ጥረት ታደርጋላችሁን?
10. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በምንገኝበት ጊዜ ይሖዋን መፍራት በግልጽ እንዲገባን ከተፈለገ ምን ማድረግ አለብን?
10 እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ስላነበብን ወይም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በስብሰባዎች ላይ ስለተገኘን ብቻ አምላካዊ ፍርሃት ላያድርብን ይችላል። ይሖዋን መፍራት በግልጽ እንዲገባን ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብን ልብ በል። ምሳሌ 2:1–5 እንዲህ ይላል፦ “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” ስለዚህ በስብሰባዎች ላይ በምንገኝበት ጊዜ የሚነገረውን ሁሉ በትኩረት ማዳመጥ፣ ቁልፍ ነጥቦችን ለመከታተልና ለማስታወስ ልባዊ ጥረት ማድረግና ስለ ይሖዋ የሚሰማን ስሜት ለሚሰጠን ምክር ያለንን አመለካከት እንዴት ሊነካው እንደሚገባ በጥሞና ማሰብ ይገባናል፤ አዎን፣ ምክሩን ልባችንን ከፍተን መቀበል ያስፈልገናል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ሊገባን ይችላል።
11. አምላካዊ ፍርሃትን ኮትኩተን ለማሳደግ ከልብ በመነጨ ሁኔታ ዘወትር ምን ማድረግ አለብን?
11 መዝሙር 86:11 (አዓት) ሌላውን አስፈላጊ ነገር ይጠቅስልናል፤ እርሱም ጸሎት ነው። “ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ። በእውነትህም እመላለሳለሁ። ስምህን እንድፈራ ልቤን አንድ አድርግልኝ” በማለት መዝሙራዊው ጸልዮአል። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገብ ስላደረገው ይህን ጸሎት ተቀብሎታል። እኛም አምላካዊ ፍርሃትን በውስጣችን ለማዳበር ይሖዋ እንዲረዳን መጸለይ ያስፈልገናል፤ ዘወትር ከልብ በመጸለይም እንጠቀማለን።—ሉቃስ 18:1–8
ልባችሁንም የሚመለከት ነገር ነው
12. ልብ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው? ይህስ ምንን ይጨምራል?
12 በመዝሙር 86:11 ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ሌላ ነገር አለ። መዝሙራዊው ስለ አምላክ ፍርሃት የአእምሮ እውቀት ብቻ እንዲያገኝ አልጸለየም። ስለ ልቡም ጠቅሷል። አምላካዊ ፍርሃትን መኮትኮትና ማሳደግ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባውን ምሳሌያዊውን ልብንም ይመለከታል። ምክንያቱም ልብ ሲባል በሕይወታችን እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሚገለጽ ውስጣዊ ሰው ማለት ነው፤ ይህም አሳባችንን፣ ዝንባሌያችንን፣ ውስጣዊ ፍላጎታችንን፣ ግባችንን በሙሉ ያካትታል።
13. (ሀ) የአንድ ሰው ልብ መከፋፈሉን ሊጠቁም የሚችለው ምንድን ነው? (ለ) አምላካዊ ፍርሃትን ስንኮተኩት ምንን ግብ አድርገን መሥራት አለብን?
13 የአንድ ሰው ልብ ሊከፋፈል እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። ልብ ተንኮለኛ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 12:2፤ ኤርምያስ 17:9) ጤናማ በሆኑ እንቅስቃሴዎች እንድንካፈል፣ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ወይም ወደ መስክ አገልግሎት እንድንሄድ ሊያነሳሳን ይችላል፤ በዚሁም ላይ ግን አንዳንድ የዓለምን የአኗኗር ዘይቤዎች እንድንወድ ሊያደርገን ይችላል። ይህ ደግሞ በሙሉ ልባችን የመንግሥቱን ፍላጎቶች እንዳናስፋፋ ወደ ኋላ ሊጎትተን ይችላል። ከዚያም ይኸው ተንኮለኛ ልብ የምንሠራው ሥራ ከሌሎች እንደማያንስ ሊያሳምነን ይሞክራል። አለበለዚያም በትምህርት ቤታችን ወይም በመሥሪያ ቤታችን ልባችን በሰዎች ፍርሃት ሊነካ ይችላል። በዚህም ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች የይሖዋ ምሥክር መሆናችንን ከማሳወቅ ልናመነታና እንዲያውም ለክርስቲያን የማይገቡ ነገሮችን ልናደርግ እንችላለን። በኋላ ግን ሕሊናችን ይወቅሰናል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ለመሆን አንፈልግም። ስለዚህ እንደ መዝሙራዊው “ስምህን እንድፈራ ልቤን አንድ አድርግልኝ” ብለን ወደ ይሖዋ እንጸልያለን። በሕይወት እንቅስቃሴዎቻችን በሙሉ የሚገለጸው ውስጣዊ ሰውነታችን በሙሉ ‘እውነተኛውን አምላክ የሚፈራና ትእዛዛቱን የሚጠብቅ’ መሆኑን ለማሳየት እንፈልጋለን።—መክብብ 12:13
14, 15. (ሀ) ይሖዋ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ነጻ ወጥተው ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንደሚመለሱ አስቀድሞ ሲናገር ለሕዝቡ ምን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶ ነበር? (ለ) ይሖዋ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ፈሪሃ አምላክን ለመትከል ምን አድርጓል? (ሐ) እስራኤላውያን ከይሖዋ መንገዶች ዘወር ያሉት ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ ለሕዝቦቹ ይህን የመሰለ አምላክን የሚፈራ ልብ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። በኤርምያስ 32:37–39 ላይ እንደምናነበው ስለ እስራኤል መታደስ አስቀድሞ ከተናገረ በኋላ እንዲህ አለ፦ “ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፣ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። ለእነርሱም ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸውም መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘላለም እንዲፈሩኝ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ።” በቁጥር 40 ላይ ደግሞ “ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ” በማለት አምላክ የገባላቸውን የተስፋ ቃል አጠናክሮታል። ይሖዋ በዚህ የተስፋ ቃሉ መሠረት በ537 ከዘአበ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸውን አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም መልሷል። ይሁን እንጂ ‘ዘወትር እንዲፈሩኝ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ’ በማለት የሰጣቸው የተቀረው የዚህ የተስፋ ቃልስ? የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ከባቢሎን ከተመለሰ በኋላ ከይሖዋ ዘወር ያለውና በዚህም ምክንያት ቤተ መቅደሱ በ70 እዘአ ዳግመኛ ላይሠራ ለዘላለም የጠፋው ለምንድን ነው?
15 ይሖዋ የገባላቸውን ተስፋ ስላጠፈ አልነበረም። ይሖዋ በልባቸው ውስጥ ፈሪሃ አምላክ ለመትከል የሚያስችል እርምጃ ወስዶ ነበር። ከባቢሎን መልሶ በገዛ አገራቸው እንዲሰፍሩ በማስቻል ያሳያቸው ምሕረት እርሱን በታላቅ አክብሮት እንዲመለከቱትና እንዲፈሩት በቂ ምክንያት ሊሆናቸው ይገባ ነበር። አምላክ ይህንን እርዳታውን በነቢያቱ በሐጌ፣ በዘካርያስና በሚልክያስ እንዲሁም እንዲያስተምራቸው በተላከው በዕዝራ፣ በገዥው በነህምያና በገዛ ራሱ ልጅ አማካኝነት በሰጣቸው ማሳሰቢያዎች፣ ምክሮችና ተግሣጾች አጠናክሮታል። አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡ ቃሉን ሰምተው ይታዘዙ ነበር። ይህንንም ያደረጉት ሐጌና ዘካርያስ የሰጧቸውን ማሳሰቢያ ሰምተው የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና በሠሩበት ጊዜና በዕዝራ ዘመን የባዕድ አገር ተወላጆች የሆኑትን ሚስቶቻቸውን ባሰናበቱበት ጊዜ ነበር። (ዕዝራ 5:1, 2፤ 10:1–4) ይሁን እንጂ በአብዛኛው ታዛዦች አልሆኑም። ሁል ጊዜ በትኩረት የሚያዳምጡ አልነበሩም፣ ምክር ተቀባዮች ሆነው አልቀጠሉም፤ ልባቸውንም ዘወትር ክፍት አላደረጉትም። እስራኤላውያን አምላክን መፍራትን በልባቸው ውስጥ እየኮተኮቱ አልነበረም፤ በዚህም ምክንያት ይህ ባሕርይ መላ ሕይወታቸውን የሚቆጣጠርላቸው ኃይል አልሆነላቸውም።—ሚልክያስ 1:6፤ ማቴዎስ 15:7, 8
16. ይሖዋ አምላካዊ ፍርሃትን በእነማን ልብ ውስጥ ተክሏል?
16 ሆኖም አምላክ በሕዝቦቹ ልብ ውስጥ አምላክን መፍራትን ለመትከል የገባው የተስፋ ቃል ከንቱ ሆኖ አልቀረም። ሰማያዊ ተስፋ ከተሰጣቸው ክርስቲያኖች፣ ማለትም ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር አዲስ ቃል ኪዳን ገብቷል። (ኤርምያስ 31:33፤ ገላትያ 6:16) አምላክ እነዚህን መንፈሳዊ እስራኤላውያን በ1919 የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ነፃ አወጣቸው። እርሱን የመፍራት ባሕርይም በልባቸው ውስጥ ጠልቆ እንዲተከል አድርጓል። ይህም ለእነርሱም ሆነ የመንግሥቲቱ ምድራዊ ተገዥዎች በመሆን ሕይወት የማግኘት ተስፋ ላላቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” ብዙ ጥቅሞች አስገኝቷል። (ኤርምያስ 32:39፤ ራእይ 7:9) ይሖዋን መፍራት በእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ልብ ውስጥም ተተክሏል።
አምላካዊ ፍርሃት በልባችን ውስጥ እንዴት እንደሚተከል
17. ይሖዋ አምላካዊ ፍርሃትን በልባችን ውስጥ የተከለው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ ይህንን አምላካዊ ፍርሃት በልባችን ውስጥ የተከለው እንዴት ነው? በመንፈሱ አማካኝነት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ውጤት የሆነ ምን ነገር ተሰጥቶናል? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ተሰጥቶናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይሖዋ ጥንት ባደረጋቸው ነገሮች፣ በአሁኑ ጊዜ ለሕዝቦቹ የገባውን ቃል በመፈጸምና ስለ መጪዎቹ ሁኔታዎች ባስነገራቸው ትንቢቶች አማካኝነት ሁላችንም አምላካዊ ፍርሃትን እንድናዳብር የሚያስችለንን ጠንካራ ምክንያት ሰጥቶናል።—ኢያሱ 24:2–15፤ ዕብራውያን 10:30, 31
18, 19. ትልልቅ ስብሰባዎችና የጉባኤ ስብሰባዎች አምላካዊ ፍርሃት እንዲኖረን የሚረዱን እንዴት ነው?
18 በዘዳግም 4:10 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ለሙሴ “ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፣ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ” ማለቱን ልብ እንበል። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ሕዝቡ እርሱን መፍራትን ለመማር እንዲችሉ የሚረዷቸውን በርካታ ነገሮች አዘጋጅቷል። በትልልቅ ስብሰባዎችና በጉባኤ ስብሰባዎች ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱንና ጥሩነቱን የገለጸባቸው መንገዶች ሲዘረዘሩ እንሰማለን። ራእይ ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ እያጠናን ሲሆን በዚህ መጽሐፍ አማካይነት ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና ጥሩነት እየተማርን ነው። ይህን መጽሐፍ ማጥናታችሁ እናንተንም ሆነ ለይሖዋ ያላችሁን አመለካከት የለወጠው እንዴት ነው? አምላክን ላለማሳዘን ያላችሁን ፍላጎት አጠናክሮታልን?
19 በስብሰባዎቻችን ላይ ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹን ለማዳን ስለ ፈጸማቸው ድርጊቶች እናጠናለን። (2 ሳሙኤል 7:23) ራእይ ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የራእይ መጽሐፍ ስናጠና በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ስለተፈጸሙ ትንቢታዊ ራእዮችና ገና ወደፊት ስለሚፈጸሙ በጣም አስፈሪ የሆኑ ክስተቶች እንማራለን። መዝሙር 66:5 (አዓት) እነዚህን የአምላክ ሥራዎች አስመልክቶ ሲናገር “እናንት ሕዝቦች፣ ኑና የአምላክን ሥራ እዩ። ለሰው ልጆች ያደረጋቸው ነገሮች በጣም የሚያስፈሩ ናቸው” ይላል። አዎን፣ እነዚህ የአምላክ ሥራዎች በትክክለኛ አመለካከት ሲታዩ በልባችን ውስጥ ለይሖዋ ታላቅ አክብሮትና ፍርሃት ያሳድሩብናል። በዚህ መንገድ ይሖዋ አምላክ “ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ” በማለት የገባውን የተስፋ ቃል እንዴት እንደሚፈጽመው ለመገንዘብ እንችላለን።—ኤርምያስ 32:40
20. አምላካዊ ፍርሃት በልባችን ውስጥ በደንብ ሥር እንዲሰድ በእኛ በኩል ምን ማድረግ ይገባናል?
20 ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ጥረት ሳናደርግ ይህ ፍርሃት በልባችን ውስጥ ሊያድግ እንደማይችል ግልጽ ነው። በደመ ነፍስ የሚመጣ አይደለም። ይሖዋ የራሱን ድርሻ ያከናውናል። እኛ ደግሞ በውስጣችን አምላካዊ ፍርሃትን ኮትኩተን በማሳደግ የበኩላችንን ማድረግ አለብን። (ዘዳግም 5:29) ሥጋዊ እስራኤላውያን ይህን ሳያደርጉ ቀርተው ነበር። መንፈሳዊ እስራኤላውያንና ተባባሪዎቻቸው ግን ትምክህታቸውን በይሖዋ ላይ በመጣል አምላክን መፍራት የሚያስገኛቸውን ብዙ ጥቅሞች በሕይወታቸው ውስጥ እያዩ ናቸው። ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል አንዳንዶቹን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አምላካዊ ፍርሃት ምንድን ነው?
◻ ይሖዋን በመፍራት ደስታ ማግኘትን እየተማርን ያለነው እንዴት ነው?
◻ አምላካዊ ፍርሃት እንዲኖረን በእኛ በኩል ምን ጥረት ማድረግ ይገባናል?
◻ አምላካዊ ፍርሃት እንዲኖረን ማድረግ ሁሉንም የምሳሌያዊውን ልብ ገጽታዎች የሚያካትተው ለምንድን ነው?
[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ይሖዋን መፍራት በግልጽ እንዲገባን በትጋት ማጥናት ይገባናል