የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 5/15 ገጽ 29-31
  • የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ነበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ነበር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተልዕኮው አስቀድሞ ተነግሯል
  • በምድረ በዳ የተሰማ ድምፅ
  • ‘ለሰው ሁሉ’ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ
  • መሲሑን አስተዋወቀ
  • እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ታማኝ ሆነ
  • መጥምቁ ዮሐንስ መንገዱን አዘጋጀ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ዮሐንስ ለመሲሑ መንገድ አዘጋጀ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ዮሐንስ መንገዱን አዘጋጀ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 5/15 ገጽ 29-31

የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ነበር

የታጠቀው ሰፊ የቆዳ ቀበቶ በፀሐይ የገረጣ ቆዳውን አጉልቶታል። ከግመል ጠጉር የተሠራ ልብስ ለብሷል፤ በእርግጥም ነቢይ ይመስላል። ብዙ ሰዎች እርሱ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ይመጡ ነበር። እዚያም ይህ ስሜት የሚስብ ሰው ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ሊያጠምቅ እንደተዘጋጀ በድፍረት ይናገር ነበር።

ሰዎች በጣም ተደንቀው ነበር! ይህ ሰው ማን ነበር? ዓላማውስ ምን ነበር?

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን፤ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጠውን። . . . ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም።” (ማቴዎስ 11:9–11) ዮሐንስ እንዲህ ያለ ወደር የሌለው ሰው የሆነው ለምንድን ነው? የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ስለነበረ ነው።

ተልዕኮው አስቀድሞ ተነግሯል

ዮሐንስ ከመወለዱ ከ700 ከሚበልጡ ዓመታት አስቀድሞ ይህ ሰው “የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፣ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሀ አስተካክሉ” ብሎ በምድረ በዳ እንደሚጮህ ይሖዋ አስታውቋል። (ኢሳይያስ 40:3፤ ማቴዎስ 3:3) ከዮሐንስ ልደት ከ400 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።” (ሚልክያስ 4:5) አጥማቂው ዮሐንስ ከኢየሱስ ስድስት ወራት ገደማ ቀደም ብሎ መወለዱ የአጋጣሚ ነገር ወይም ተፈጥሯዊ ሂደት ስለሆነ ብቻ አልነበረም። ልክ ተስፋ የተሰጠበት ልጅ እንደሆነው እንደ ይስሐቅ ልደት የዮሐንስም መወለድ ተዓምር ነበር፤ ምክንያቱም ሁለቱም ወላጆቹ ማለትም ዘካርያስና ኤልሳቤጥ እርሱን ሲወልዱ መደበኛው የመውለጃ ዕድሜያቸው አልፎ ነበር።—ሉቃስ 1:18

ሌላው ቀርቶ ዮሐንስ ከመፀነሱ አስቀድሞ ተልዕኮው፣ ሥራውና አኗኗሩ በመልአኩ ገብርኤል አማካኝነት ተገልጦ ነበር። የኤልያስ ዓይነት ኃይልና መንፈስ በመያዝ ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎችን ከሞት መንገድ እንደሚመልስና ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው እንዲቀበሉት እንደሚያዘጋጃቸው ተነግሮለታል። ዮሐንስ ከተወለደ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደረ ናዝራዊ የነበረና ወይንም ሆነ የአልኮል መጠጥ የማይጠጣ ነበር። በእርግጥም በበረሀ የሚመገበው ‘አንበጣና የበረሀ ማር’ ነበር። (ማርቆስ 1:6፤ ዘኁልቁ 6:2, 3፤ ሉቃስ 1:13–17) ዮሐንስ ልክ እንደ ሳሙኤል ከልጅነቱ ጀምሮ ለልዑሉ አምላክ ክብራማ አገልግሎት የተለየ ነበር።—1 ሳሙኤል 1:11, 24–28

ዮሐንስ የሚለውን ስም እንኳ የመረጠው አምላክ ነበር። “ዮሐንስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ስም “ይሖዋ ሞገስ አሳየኝ፤ ይሖዋ ምሕረቱን ገለጸ” ማለት ነው።

ልጁ በስምንተኛው ቀን ሲገረዝ አባቱ ዘካርያስ “አንተ ሕፃን ሆይ፣ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፣ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጎበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው” ብሎ ለመናገር በመለኮት ተገፋፍቶ ነበር። (ሉቃስ 1:76–78) የዮሐንስ ሕዝባዊ አገልግሎት በሕይወቱ ውስጥ ቀዳሚ ቦታ መያዝ ነበረበት። ከዚህ ጋር ሲወዳደሩ ሌሎቹ ነገሮች ሁሉ ከቁጥር የሚገቡ አልነበሩም። ከዚህም የተነሳ ቅዱሳን ጽሑፎች የዮሐንስን ሕይወት የመጀመሪያ 30 ዓመታት እንዲህ በማለት በአንድ ነጠላ ዓረፍተ ነገር ያስቀምጡታል፦ “ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፣ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።”—ሉቃስ 1:80

በምድረ በዳ የተሰማ ድምፅ

በጢባርዮስ ቄሣር 15ኛ ዓመት የግዛት ዘመን፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስ በይሁዳ በሚገዛበት ወቅት አጥማቂው ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚለውን አስገራሚ መልእክት ይዞ በምድረ በዳ ብቅ አለ። (ማቴዎስ 3:2፤ ማርቆስ 1:4፤ ሉቃስ 3:1, 2) በአካባቢው ሁሉ የሚገኙ ሰዎች ስሜታቸው ተቀስቅሶ ነበር። ይህ ድፍረት የተሞላበት አዋጅ ተጨባጭ የሆነ ተስፋ በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩ ሰዎችን ልብ ነክቷል። በተጨማሪም የዮሐንስ ማስታወቂያ ከልብ የመነጨ ንስሐን ይጠይቅ ስለነበር የአንድን ሰው ትሕትና የሚፈታተን ነበር። ቅንነቱና የጸና እምነቱ ብዙዎቹን ሐቀኛና ቅን ሰዎች ከአምላክ የተላከ ሰው እንደሆነ አድርገው እንዲቀበሉት ገፋፍቷቸዋል።

የዮሐንስ ዝና ወዲያውኑ በስፋት ተናኘ። የይሖዋ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን በአለባበሱና ለአምላክ ባለው ልባዊ ፍቅር በቀላሉ ተለይቶ ይታወቅ ነበር። (ማርቆስ 1:6) ካህናትና ሌዋውያን እንኳ ይህንን ሁሉ ትኩረት የሳበው ምን እንደሆነ ለማወቅ ከኢየሩሳሌም ተጉዘዋል። ንስሐ መግባት? ንስሐ የሚገባው ለምንድን ነው? ከምንስ ነው ንስሐ የሚገባው? ይህ ሰው ማነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ፈልገው ነበር። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም . . . እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ። እንኪያስ፦ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለ ራስህ ምን ትላለህ? አሉት። እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢይ ካይደለህ፣ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።”—ዮሐንስ 1:20–25

ወደ መንግሥቲቱ ለሚገቡ ሰዎች ንስሐና ጥምቀት አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው። ስለዚህ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ ‘እኔ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን በውኃ አጠምቃቸዋለሁ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ብርቱው ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። እኔ የጫማውን ጠፍር እንኳ ለመፍታት የምበቃ አይደለሁም። ተጠንቀቁ! መንሹ በእጁ ነው፣ ስንዴውን ወደ ጎተራው ይሰበስባል ገለባውን ግን አቃጥሎ ያጠፋዋል።’ (ሉቃስ 3:15–17፤ ሥራ 1:5) በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በመሲሑ ተከታዮች ላይ ሲወርድ ጠላቶቹ ግን የጥፋትን እሳት ቀምሰው ነበር።

‘ለሰው ሁሉ’ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

ብዙ ልበ ቅን አይሁዳውያን በዮሐንስ ቃላት ተገፋፍተው ለሕጉ ቃል ኪዳን ታማኝ ባለመሆን የሠሯቸውን ኃጢአቶች በግልጽ ተናዘዙ። ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ እንዲያጠምቃቸው በማድረግ ንስሐ መግባታቸውን በግልጽ አሳይተዋል። (ማቴዎስ 3:5, 6) በዚህም ምክንያት ልባቸው መሲሑን መቀበል በሚችልበት ትክክለኛ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር። የአምላክን የጽድቅ ብቃቶች ለማወቅ ያላቸውን ጥማት በማርካት ዮሐንስ እንደ ራሱ ደቀ መዛሙርት አድርጎ በደስታ መመሪያ ሰጥቷቸዋል፤ ሌላው ቀርቶ እንዴት እንደሚጸልዩ ያስተምራቸው ነበር።—ሉቃስ 11:1

ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን የመሲሑን መንገድ ጠራጊ በተመለከተ “በእርሱ ምስክርነት ሰው ሁሉ እንዲያምን ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ መጣ” በማለት ጽፏል። (ዮሐንስ 1:7 የ1980 ትርጉም) ሰው ሁሉ አጥማቂው ዮሐንስ ‘ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሲሰብክ’ ለመስማት ይመጣ ነበር። (ሥራ 13:24) ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ወደ ንጥቂያ እንዳይመለሱ አስጠንቅቋቸዋል። ወታደሮችን በማንም ሰው ላይ ግፍ እንዳይፈጽሙ ወይም ሌሎችን በሐሰት እንዳይከስሱ መክሯቸዋል። ግብዞቹን ሃይማኖተኞች ማለትም ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና፦ ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።”—ማቴዎስ 3:7–9፤ ሉቃስ 3:7–14

በዮሐንስ ዘመን የነበሩ ሃይማኖታዊ መሪዎች በጥቅሉ ሲታዩ በእርሱ ላይ እምነት ለማሳደር አሻፈረኝ ከማለታቸውም በተጨማሪ አጋንንት ተጠናውተውታል በማለት በሐሰት ወነጀሉት። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን የጽድቅ መንገድ አልተቀበሉም። በሌላ በኩል የዮሐንስን ምሥክርነት ያመኑ ኃጢአተኛ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ጋለሞቶች ንስሐ ገብተው ተጠምቀው ነበር። ወቅቱ ሲደርስ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሕ መሆኑን ተቀብለዋል።—ማቴዎስ 21:25–32፤ ሉቃስ 7:31–33

መሲሑን አስተዋወቀ

በ29 እዘአ ከፀደይ ጀምሮ እስከ በልግ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የአምላክ ታማኝ ምሥክር የሆነው ዮሐንስ አይሁዳውያን በሚመጣው መሲሕ ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል። ይህ ወቅት መሲሐዊው ንጉሥ የሚመጣበት ጊዜ ነበር። በመጣ ጊዜ ግን እርሱም ወደዛው የዮርዳኖስ ውኃ በመሄድ እንዲጠመቅ ጠየቀ። መጀመሪያ ላይ ዮሐንስ ሐሳቡን ባይቀበልም በኋላ ግን ተስማማ። መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ ሲወርድበትና ልጁን እንደተቀበለው የሚገልጸውን የይሖዋን ድምፅ ሲሰማ የተሰማውን ደስታ ገምት።—ማቴዎስ 3:13–17፤ ማርቆስ 1:9–11

ከሁሉም በፊት ኢየሱስን በመሲሕነቱ ያወቀው ዮሐንስ ከመሆኑም በላይ የራሱን ደቀ መዛሙርት ከዚህ ቅቡዕ ጋር አስተዋውቋቸዋል። “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት ዮሐንስ ተናገረ። በተጨማሪም እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፣ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፣ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ።”—ዮሐንስ 1:29–37

ለስድስት ወራት ያክል የዮሐንስ ሥራ ከኢየሱስ አገልግሎት ጋር ጎን ለጎን ቀጥሎ ነበር። ሁለቱም ቢሆኑ አንዳቸው ሌላኛው እየሠራ ያለውን ሥራ ተረድተውታል። ዮሐንስ ራሱ ሚዜ እንደሆነ አድርጎ ከመመልከቱም በተጨማሪ እርሱና የሚሠራው ሥራ እየቀነሰ ሲሄድ ክርስቶስ ግን ሲጨምር በመመልከቱ ተደስቶ ነበር።—ዮሐንስ 3:22–30

በኤልያስ የተመሰለው የእርሱ መንገድ ጠራጊ ዮሐንስ መሆኑን ኢየሱስ ለይቶ አሳይቷል። (ማቴዎስ 11:12–15፤ 17:12) በአንድ አጋጣሚ ላይ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሙሴ ሕግና የነቢያት መጻሕፍት እስከ አጥማቂው ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ቆይተው ነበር፤ ከዚያም ወዲህ የሚነገረው የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ቃል ነው፤ እያንዳንዱም ሰው ወደዚያች መንግሥት ለመግባት ብርቱ ጥረት ያደርጋል።”—ሉቃስ 16:16 የ1980 ትርጉም

እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ታማኝ ሆነ

ዮሐንስ በድፍረት እውነቱን በመናገሩ ምክንያት ተይዞ ታሰረ። የንጉሥ ሄሮድስን ኃጢአት እንኳ ለማጋለጥ ያለበትን ኃላፊነት ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። ይህ ንጉሥ የአምላክን ሕግ ጥሶ የወንድሙ ሚስት ከሆነችው ሄሮድያዳ ጋር ምንዝር ይፈጽም ነበር። ሄሮድስ ንስሐ ገብቶ የአምላክን ምሕረት እንዲያገኝ ዮሐንስ በድፍረት ነግሮታል።

ዮሐንስ እንዴት ያለ የእምነትና የፍቅር ምሳሌ ነው! የግል ነፃነቱን መሥዋዕት በማድረግ ለይሖዋ አምላክ ያለውን ታማኝነትና መሰሎቹ ለሆኑት የሰው ልጆች ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ከአንድ ዓመት እስር በኋላ ‘ተቀይማው’ በነበረችው በክፉዋ ሄሮድያዳ በተወጠነ አጋንንታዊ ደባ ምክንያት አንገቱ ተቆረጠ። (ማርቆስ 6:16–19 የ1980 ትርጉም፤ ማቴዎስ 14:3–12) ቢሆንም የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ለይሖዋ ያለውን ንጹሕ አቋም ጠብቋል፤ እንዲሁም ጽድቅ በሰፈነበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት ለማግኘት በቅርቡ ከሞት ይነሳል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ