ክርስቲያን ሴቶች ከፍተኛ ግምትና አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል
“እናንተ ባሎች ሆይ፣ . . . ለተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ሚስቶቻችሁን በክብር በመያዝ ከእነርሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ።”—1 ጴጥሮስ 3:7 አዓት
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ያደረገው ውይይት ምን ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ፈጠረ? ለምንስ? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት በመስበክ በተግባር ያሳየው ምንድን ነው?
ኢየሱስ በ30 እዘአ መገባደጃ ሲካር በምትባል ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የጥንት የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አንድ ቀትር ላይ ኢየሱስ ሴቶች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የነበረውን ስሜት አሳይቷል። ከጠዋት ጀምሮ በሰማሪያ ኮረብታማ ስፍራዎች ሲጓዝ ስለዋለ በጣም ተዳክሞ፣ ተርቦና ተጠምቶ ይህ ጉድጓድ ወዳለበት ሥፍራ ደረሰ። በውኃው ጉድጓድ አጠገብ እንደ ተቀመጠ አንዲት ሳምራዊት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስ “ውኃ አጠጪኝ” በማለት ጠየቃት። ሴትየዋ በመገረም ትክ ብላ ሳትመለከተው አልቀረችም። “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” በማለት ጠየቀችው። ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ገዝተው ሲመለሱ ኢየሱስ “ከሴት ጋር በመነጋገሩ” ተደነቁ።—ዮሐንስ 4:4–9, 27
2 ይህቺ ሴት ጥያቄ እንድትጠይቅ ያነሣሣትና ደቀ መዛሙርቱ ለሁኔታው ይህን ያህል ትኩረት እንዲሰጡት ያደረጋቸው ምንድን ነው? ሴትየዋ ሳምራዊት ነበረች፤ አይሁዶች ደግሞ ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። (ዮሐንስ 8:48) ይሁን እንጂ ሁኔታው ይህን ያህል ትኩረት እንዲሰጠው ያደረገ ሌላም ምክንያት እንደ ነበረ ግልጽ ነው። በዚያ ወቅት የነበረው የረቢዎች ወግ ከሴት ጋር በአደባባይ መነጋገርን ያወግዝ ነበር።a ሆኖም ኢየሱስ ለዚህች ቅን ሴት በአደባባይ ሰብኮላታል፤ እንዲያውም መሲሕ መሆኑን ገልጾላታል። (ዮሐንስ 4:25, 26) ስለዚህ ኢየሱስ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወጎች ጨምሮ በማናቸውም ወግ እንደማይመራ አሳይቷል። (ማርቆስ 7:9–13) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ባደረገው ነገርና ባስተማረው ትምህርት ሴቶች በክብር መያዝ እንዳለባቸው ጠቁሟል።
ኢየሱስ ለሴቶች የነበረው አመለካከት
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ልብሱን ለነካችው ሴት ምን ስሜት አሳየ? (ለ) ኢየሱስ ለክርስቲያን ወንዶች በተለይም ለሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ ለሰዎች ያለው ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ከሴቶች ጋር በነበረው ግንኙነት ታይቷል። በአንድ ወቅት ለ12 ዓመታት ደም ይፈስሳት የነበረች ሴት ኢየሱስን ከሕዝብ መካከል ፈልጋ አገኘችው። በወቅቱ የነበረችበት ሁኔታ ሕጉ በሚጠይቀው ሥነ ሥርዓት ረገድ ንጹሕ እንዳትሆን አድርጓት ስለነበር እዚያ መገኘት አልነበረባትም። (ዘሌዋውያን 15:25–27) ይሁን እንጂ በሽታዋ በጣም ተስፋ ስላስቆረጣት በሕዝቡ መካከል ሹልክ ብላ ከኢየሱስ በስተኋላ ቀረበች። ልብሱን ስትነካ ወዲያውኑ ተፈወሰች! ኢየሱስ ምንም እንኳ ሴት ልጁ በጠና ወደ ታመመችበት ወደ ኢያኢሮስ ቤት እየሄደ ቢሆንም ቆመ። ከውስጡ ኃይል እንደወጣ ስለተሰማው ማን እንደነካው ለማወቅ ዙሪያውን ተመለከተ። በመጨረሻ ሴትየዋ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ወደቀች። ኢየሱስ ለምን ከሕዝቡ ጋር ተቀላቀልሽ ወይም ያለ ፈቃዴ ለምን ልብሴን ነካሽ ብሎ ገሠጻትን? አልገሠጻትም፤ ከዚህ ይልቅ ሞቅ ያለ የወዳጅነት ስሜት ያለውና ደግ ሆኖ አገኘችው። ‘ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል’ አላት። ኢየሱስ ሴትን በቀጥታ “ልጄ ሆይ” ያለበት ጊዜ ይህ ብቻ ነበር። ይህ ቃል ምንኛ አጽናንቷት ይሆን!—ማቴዎስ 9:18–22፤ ማርቆስ 5:21–34
4 ኢየሱስ የሕጉን ትርጉም በጥልቀት ተረድቷል። ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን መንፈስ እንዲሁም ምሕረትንና ርኅራኄን የማሳየትን አስፈላጊነት ተገንዝቧል። (ከማቴዎስ 23:23 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ የታመመችውን ሴት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ከመገንዘቡም በላይ እምነቷን ግምት ውስጥ አስገብቷል። በዚህም ለክርስቲያን ወንዶች በተለይም ለበላይ ተመልካቾች ጥሩ ምሳሌ ትቷል። አንዲት ክርስቲያን እህት የግል ችግር በተለይም ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ወይም ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ቢያጋጥማት ሽማግሌዎች የምትናገረውን ወይም የምታደርገውን ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን ሰፋ አድርገው ለመመልከት መጣርና ሁኔታዎቹንና ድርጊቱን እንድትፈጽም የገፋፋትን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ማስተዋል ምክርና እርማት ከመስጠት ይልቅ ትዕግሥት፣ የሰውን ችግር መረዳትና ርኅራኄ ማሳየት እንደሚገባ ሊጠቁም ይችላል።—ምሳሌ 10:19፤ 16:23፤ 19:11
5. (ሀ) ሴቶች በረቢዎች ወግ የታገዱት በምን መንገድ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን በመጀመሪያ ያዩትና ስለ እሱ የመሠከሩት እነማን ነበሩ?
5 ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ይኖሩ የነበሩ ሴቶች በረቢዎች ልማድ ምክንያት የሕግ ምሥክር እንዳይሆኑ ታግደው ነበር።b ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 16 ጠዋት ከሞት ከተነሣ በኋላ ወዲያውኑ የተፈጸመውን ሁኔታ አስብ። ኢየሱስ ከሞት እንደ ተነሣ መጀመሪያ የሚያየውና ጌታቸው መነሣቱን ለሌሎች ደቀ መዛሙርት የሚመሠክረው ማን ይሆን? ኢየሱስ እስኪሞት ድረስ በተሰቀለበት ቦታ የቆዩት ሴቶች ኢየሱስ ከሞት እንደ ተነሣ ለማየት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሆነው ተገኙ።—ማቴዎስ 27:55, 56, 61
6, 7. (ሀ) ኢየሱስ ወደ መቃብሩ ለመጡት ሴቶች የነገራቸው ምን ነበር? (ለ) ወንዶች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሴቶች ለሰጧቸው የምሥክርነት ቃል መጀመሪያ ላይ ያሳዩት ስሜት ምን ነበር? ከዚህ ምን ለመማር ይቻላል?
6 መግደላዊት ማርያምና ሌሎች ሴቶች በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ማለዳ የክርስቶስን አስክሬን ለመቀባት ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ማርያም መቃብሩ ባዶውን ሆኖ ስታገኘው ስለ ሁኔታው ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ለመንገር እየሮጠች ሄደች። ሌሎቹ ሴቶች እዛው ቀሩ። ወዲያውኑ አንድ መልአክ ተገለጠላቸውና ኢየሱስ እንደ ተነሣ አበሰራቸው። መልአኩ ‘ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው’ በማለት አዘዛቸው። እነዚህ ሴቶች የሰሙትን ዜና ለመናገር እየተጣደፉ ሲሄዱ ኢየሱስ ራሱ ተገለጠላቸውና ‘ሄዳችሁ ለወንድሞቼ ንገሯቸው’ ብሎ አዘዛቸው። (ማቴዎስ 28:1–10፤ ማርቆስ 16:1, 2፤ ዮሐንስ 20:1, 2) መግደላዊት ማርያም መልአኩ መገለጡን ስላላወቀች በሐዘን ተውጣ ወደ ባዶው መቃብር ተመለሰች። እዚያ ቦታ ሳለች ኢየሱስ ተገለጠላትና ማንነቱን ከተረዳች በኋላ “ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው” አላት።—ዮሐንስ 20:11–18፤ ከማቴዎስ 28:9, 10
7 ኢየሱስ በመጀመሪያ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስ ወይም ከሌሎቹ ወንድ ደቀ መዛሙርት ለአንዱ ሊገለጥ ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ የትንሣኤው የመጀመሪያዎቹ የዓይን ምሥክሮች እንዲሆኑና ስለዚህ ትንሣኤ ለወንድ ደቀ መዛሙርቱ እንዲመሠክሩ በማድረግ ለእነዚህ ሴቶች ሞገስ ሊያሳያቸው መረጠ። ወንዶቹ ደቀ መዛሙርት መጀመሪያ ላይ ምን ተሰማቸው? የታሪክ መዝገቡ “ይህ ቃል ቅዠት [የማይረባ ነገር አዓት] መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም” በማለት ይገልጻል። (ሉቃስ 24:11) ይህን የምሥክርነት ቃል ለማመን የተቸገሩት ከሴቶች ስለመጣ ነበርን? እንደዛም ተሰምቷቸው ቢሆን እንኳ ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን የሚጠቁሙ ብዙ ማስረጃዎችን አግኝተዋል። (ሉቃስ 24:13–46፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3–8) ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ወንዶች የመንፈሳዊ እህቶቻቸውን አስተያየቶች በቁም ነገር መመልከታቸው ጥበብ ነው።—ከዘፍጥረት 21:12 ጋር አወዳድር።
8. ኢየሱስ ከሴቶች ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየው ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ለሴቶች የነበረውን አመለካከት ማወቅ በእርግጥም በጣም የሚያስደስት ነው። ምን ጊዜም ቢሆን ከሴቶች ጋር በነበረው ግንኙነት ሩኅሩኅና ፍጹም ሚዛናዊ ስለነበር ሴቶችን ከልክ በላይ ከፍ ከፍ አላደረጋቸውም ወይም አላቃለላቸውም። (ዮሐንስ 2:3–5) የሴቶችን ክብር የገፈፉትንና የአምላክን ቃል የሻሩትን የረቢዎች ወግ አልተቀበለም። (ከማቴዎስ 15:3–9 ጋር አወዳድር።) በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ሴቶችን በአክብሮት በመያዝ ይሖዋ አምላክ ሴቶች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚሰማውን ስሜት አሳይቷል። (ዮሐንስ 5:19) በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቲያን ወንዶች ሊከተሉት የሚገባውን አስደናቂ ምሳሌ ትቷል።—1 ጴጥሮስ 2:21
ኢየሱስ ስለ ሴቶች ያስተማራቸው ትምህርቶች
9, 10. ኢየሱስ ሴቶችን በተመለከተ የነበሩት የረቢዎች ወጎች የተሳሳቱ መሆናቸውን ያጋለጠው እንዴት ነው? ፈሪሳውያን ስለ ፍቺ ጥያቄ ካነሡ በኋላ ምን አለ?
9 ኢየሱስ የረቢዎች ወግ የተሳሳተ መሆኑን ያጋለጠውና ሴቶችን ያከበረው በድርጊቶቹ ብቻ ሳይሆን በትምህርቶቹም ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል ፍቺንና ምንዝርን በተመለከተ ያስተማረውን ትምህርት ተመልከት።
10 ፍቺን በተመለከተ ኢየሱስ “ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” የሚል ጥያቄ ተጠይቆ ነበር። በማርቆስ ዘገባ መሠረት ኢየሱስ “[ያለ ዝሙት ምክንያት] ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርሷ ላይ ያመነዝራል፤ እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው። (ማርቆስ 10:10–12፤ ማቴዎስ 19:3, 9) እነዚህ በቀላል አነጋገር የተገለጹ ቃላት ለሴቶች አክብሮትን ያሳያሉ። እንዴት?
11. ኢየሱስ “ያለ ዝሙት ምክንያት” ሲል የተናገራቸው ቃላት ስለ ጋብቻ ትስስር ምን ይጠቁማሉ?
11 በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ “ያለ ዝሙት ምክንያት” በሚሉት ቃላት (በማቴዎስ ወንጌል ዘገባ ውስጥ ይገኛሉ) የጋብቻ ሰንሰለት እንደ ቀላል ነገር ወይም በቀላሉ የሚበጠስ ነገር ተደርጎ መታየት እንደሌለበት ጠቁሟል። በወቅቱ ተስፋፍቶ የነበረው የረቢዎች ትምህርት ጥሩ ምግብ አትሠራም ወይም ከሌላ ወንድ ጋር ስትነጋገር ታይታለች በሚሉት ዓይነት ጥቃቅን ምክንያቶች ሚስትን መፍታት ይፈቅድ ነበር። እንዲያውም አንድ ባል ይበልጥ ቆንጆ ናት የሚላትን ሴት ካገኘ ሚስቱን እንዲፈታ ይፈቀድለት ነበር! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር . . . ጋብቻን ሊኖረው ወደሚገባው ትክክለኛ ቦታ ለመመለስ ሲል ለሴቶች ያለውን ድጋፍ መስጠቱ ነበር” በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። በእርግጥም ጋብቻ ሴት ያለ ስጋት የምትኖርበት ዘላቂ ትስስር መሆን አለበት።—ማርቆስ 10:6–9
12. “በእርሷ ላይ ያመነዝራል” በሚሉት ቃላት ኢየሱስ ያስተዋወቀው ሐሳብ ምን ነበር?
12 በሁለተኛ ደረጃ “በእርሷ ላይ ያመነዝራል” በሚሉት ቃላት በሚጠቀምበት ወቅት ኢየሱስ በረቢ ፍርድ ቤቶች የማይታወቅ አንድ አመለካከት ማለትም ባል በሚስቱ ላይ ያመነዝራል የሚል አመለካከት አስተዋውቋል። ዘ ኤክስፖዚተርስ ባይብል ኮሜንታሪ የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን ማብራሪያ ይሰጣል፦ “የአይሁድ እምነት ተከታዮች የነበሩ ረቢዎች አንዲት ሴት ታማኝነቷን በማጉደል በባሏ ላይ ታመነዝራለች፤ አንድ ወንድ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቢያደርግ በራሱ ላይ ምንዝር ይፈጽማል። ይሁን እንጂ አንድ ወንድ የፈለገውን ነገር ቢያደርግ በጭራሽ በሚስቱ ላይ ምንዝር ፈጸመ ሊባል አይችልም ይሉ ነበር። ኢየሱስ ግን ባል የሚስትን ያህል የሥነ ምግባር ግዴታ እንዳለበት ሲገልጽ የሴትን ደረጃና ክብር ከፍ አድርጓል።”
13. ኢየሱስ በክርስትና ሥርዓት ፍቺን በተመለከተ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ያለው የአቋም መመዘኛ አንድ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
13 በሦስተኛ ደረጃ “ባልዋን ፈትታ” በሚለው ሐረግ ኢየሱስ አንዲት ሴት ታማኝ ያልሆነ ባልዋን ለመፍታት ላላት መብት እውቅና ሰጥቷል፤ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ቢኖርም በዘመኑ በነበረው የአይሁድ ሕግ ውስጥ አልተካተተም ነበር።c “አንዲት ሴት በፈቃድዋም ሆነ ያለ ፈቃድዋ ልትፈታ ብትችልም ወንድን መፍታት የሚቻለው ከፈለገ ብቻ ነው” ይባል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው በክርስትና ሥርዓት ለወንድም ሆነ ለሴት የሚሠራው የአቋም መመዘኛ አንድ ነው።
14. ኢየሱስ በትምህርቶቹ ያንጸባረቀው የማንን ባሕርይ ነው?
14 የኢየሱስ ትምህርቶች ለሴቶች ደኅንነት በጥልቅ እንደሚያስብ በግልጽ ያሳያሉ። ስለዚህ አንዳንድ ሴቶች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት በገዛ ንብረቶቻቸው እስኪያገለግሉት ድረስ ኢየሱስን ያን ያህል የወደዱት ለምን እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም። (ሉቃስ 8:1–3) ኢየሱስ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” ብሏል። (ዮሐንስ 7:16) ኢየሱስ ባስተማረው ነገር ይሖዋ ለሴቶች ያለውን ከአንጀት የመነጨ አሳቢነት አሳይቷል።
‘በክብር ያዟቸው’
15. ሐዋርያው ጴጥሮስ ባሎች ለሚስቶቻቸው ማድረግ ስላለባቸው አያያዝ ምን ብሎ ጻፈ?
15 ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ ሴቶችን እንዴት እንደያዛቸው በቀጥታ ተመልክቷል። ከ30 ዓመት ገደማ በኋላ ጴጥሮስ ለሚስቶች ፍቅራዊ ምክር ሰጣቸውና ቀጥሎ “እናንተ ባሎች ሆይ፣ ጸሎታችሁ እንዳይታገድ ለተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ሚስቶቻችሁን በክብር በመያዝ ከእነርሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ፤ ይገባናል የማንለው የሕይወት ስጦታ አብራችሁ ወራሾች ናችሁና” በማለት ጻፈ። (1 ጴጥሮስ 3:7 አዓት) ጴጥሮስ ‘በክብር ያዟቸው’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
16. (ሀ) “ክብር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ስም ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) በኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ ወቅት ይሖዋ ኢየሱስን ያከበረው እንዴት ነበር? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
16 በአንድ የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ መሠረት በእንግሊዝኛ “ኦነር” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ስም (ቲሚ) “ዋጋ፣ ጠቀሜታ፣ አክብሮት መስጠት” ማለት ነው። የዚህ ግሪክኛ ቃል የተለያዩ አገባቦች “ስጦታዎች” እና “ውድ” ተብለው ተተርጉመዋል። (ሥራ 28:10 አዓት ፤ 1 ጴጥሮስ 2:7 አዓት) ጴጥሮስ በ2 ጴጥሮስ 1:17 ላይ የተጠቀመበትን የዚህኑ ቃል አንድ አገባብ ብንመረምር አንድን ሰው ማክበር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እናስተውላለን። እዚህ ጥቅስ ላይ ጴጥሮስ የኢየሱስን ተአምራዊ ለውጥ ጠቅሶ “ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሏልና” በማለት ጽፏል። ኢየሱስ በተአምር በተለወጠበት ወቅት ይሖዋ ኢየሱስን እንደ ተቀበለው በመግለጽ ልጁን አክብሯል፤ ይህን ያደረገውም ሌሎች እየሰሙት ነበር። (ማቴዎስ 17:1–5) ስለዚህ ሚስቱን የሚያከብር ሰው ሚስቱን በሌሎች ፊት አያዋርዳትም ወይም ደግሞ አያቃልላትም። ከዚህ ይልቅ በቃሉና በድርጊቱ በግልም ሆነ በሰዎች ፊት እንደሚያከብራት ያሳያል።—ምሳሌ 31:28–30
17. (ሀ) ክርስቲያን ሚስቶች መከበር የሚገባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ወንድ በአምላክ ፊት ከሴት የበለጠ ዋጋ እንዳለው ሊሰማው የማይገባው ለምንድን ነው?
17 ጴጥሮስ ክርስቲያን ባሎች ለሚስቶቻቸው ይህን አክብሮት ‘መስጠት’ እንዳለባቸው ተናግሯል። ይህ አክብሮት የሚሰጣቸው እንዲያው በደግነት ሳይሆን የሚገባቸው ስለሆነ ነው። ሚስቶች ይህ ዓይነቱ አክብሮት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ጴጥሮስ “ይገባናል የማንለውን የሕይወት ስጦታ አብራችሁ ወራሾች ናችሁና” በማለት ገልጿል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩት ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈላቸው ወንዶችና ሴቶች በሙሉ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ወራሾች እንዲሆኑ ተጠርተው ነበር። (ሮሜ 8:16, 17፤ ገላትያ 3:28) በጉባኤ ውስጥ ተመሳሳይ ኃላፊነቶች ባይኖራቸውም በመጨረሻ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር በመግዛት ተካፋይ ይሆናሉ። (ራእይ 20:6) አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች ምድራዊ ተስፋ በያዙበት በአሁኑ ወቅትም ቢሆን ማንኛውም ክርስቲያን ወንድ በጉባኤ ውስጥ ባሉት መብቶች ምክንያት በአምላክ ፊት ከሴቶች የበለጠ ዋጋ እንዳለው ቢሰማው ከባድ ስሕተት ይሆናል። (ከሉቃስ 17:10 ጋር አወዳድር።) የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የዘላለምን ሕይወት ተስፋ በመዘርጋት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚሆኑበትን አጋጣሚ የከፈተላቸው በመሆኑ ወንዶችና ሴቶች በአምላክ ፊት ያላቸው መንፈሳዊ አቋም እኩል ነው።—ሮሜ 6:23
18. ጴጥሮስ ባል ሚስቱን እንዲያከብራት የሚያስገድደውን ምን ምክንያት አቀረበ?
18 ጴጥሮስ ባል ‘ጸሎቱ እንዳይታገድ’ ሚስቱን ማክበር እንዳለበት በመግለጽ አስገዳጅ ምክንያት አቅርቧል። “እንዳይታገድ” የሚለው ቃል፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “መቋረጥ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ግሥ (ኢንኮፕቶ ) የመጣ ነው። ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ በተባለው በቫይን መጽሐፍ መሠረት ይህ ቃል “ሰዎች እንዳያልፉ ለማድረግ መንገዶችን ማበላሸት ወይም በመንገድ ላይ መሰናክል ማስቀመጥን ለመግለጽ ያገለግላል።” ስለዚህ ለሚስቱ አክብሮት የማያሳይ ባል አምላክ ጸሎቶቹን እንዳይሰማው የሚያግድ ነገር እንዳለ ሊታወቀው ይችላል። ሰውዬው ወደ አምላክ መቅረብ እንደማይገባው ወይም ይሖዋ ጸሎቱን እንደማይሰማው ሊሰማው ይችላል። ይሖዋ ወንዶች ለሴቶች የሚያደርጉት አያያዝ በጣም እንደሚያሳስበው ግልጽ ነው።—ከሰቆቃወ ኤርምያስ 3:44 ጋር አወ ዳድር።
19. በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶችና ሴቶች እርስ በርስ በመከባበር አንድ ላይ መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው?
19 አክብሮት የማሳየት ግዴታ በወንዶች ላይ ብቻ የተጣለ አይደለም። ባል ሚስቱን በፍቅርና በክብር በመያዝ ለሚስቱ ከፍተኛ ግምት መስጠት ቢኖርበትም ሚስትም ለእሱ በመገዛትና ጥልቅ አክብሮት በማሳየት ለባሏ ከፍተኛ ግምት መስጠት አለባት። (1 ጴጥሮስ 3:1–6) ከዚህም በላይ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ‘እርስ በርሳቸው እንዲከባበሩ’ መክሯቸዋል። (ሮሜ 12:10) ይህም ወንዶችና ሴቶች እርስ በርስ በመከባበር በጉባኤ ውስጥ እንዲያገለግሉ ይጠይቅባቸዋል። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ሲሰፍን ክርስቲያን ሴቶች በመሪነት ቦታ ላይ ያሉትን ሥልጣን ዝቅ በሚያደርግ መንገድ አይናገሩም። ከዚህ ይልቅ ሽማግሌዎችን ይደግፏቸዋል፤ ከእነሱም ጋር ይተባበራሉ። (1 ቆሮንቶስ 14:34, 35፤ ዕብራውያን 13:17) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በበኩላቸው “የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች ቆነጃጅትን እንደ እህቶች በፍጹም ንጽሕና” ይይዟቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ሽማግሌዎች ክርስቲያን እህቶች የሚያቀርቡትን ሐሳብ በደግነት ግምት ውስጥ በማስገባት በጥበብ ይመላለሳሉ። ስለዚህ አንዲት እህት ቲኦክራሲያዊ የራስነት ሥርዓትን በመቀበል በአክብሮት ጥያቄ ብትጠይቅ ሌላው ቀርቶ ትኩረት የሚጠይቅ አንድ ነገር ብትጠቁም ሽማግሌዎች ጥያቄዋን ወይም ችግሯን በደስታ ይመለከታሉ።
20. በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ በሰፈረው መዝገብ መሠረት ሴቶች መያዝ ያለባቸው እንዴት ነው?
20 በኤደን ኃጢአት ከተሠራ በኋላ በብዙ ባህሎች ሴቶች ያላቸው ቦታ ዝቅ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሴቶች በመጀመሪያ እንዲያዙ የፈለገበት መንገድ ይህ አልነበረም። በባህል ደረጃ ለሴቶች ያለው አመለካከት ምንም ይሁን ምን በዕብራይስጥም ሆነ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የሰፈረው መዝገብ አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ሴቶች በክብር መያዝ እንዳለባቸው ያሳያል። ይህ አምላክ የሰጣቸው መብት ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዘ ኢንተርናሽናል ስታንደርድ ባይብል ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ሴቶች ከወንዶች እንግዶች ጋር ምግብ አይበሉም ነበር፤ ወንዶች ከሴቶች ጋር መነጋገር የለባቸውም ይባል ነበር። . . . በተለይ በአደባባይ ከሴት ጋር መነጋገር ነውር ነበር።” የረቢዎችን ትምህርቶች የያዘው የአይሁዶች ሚሽና እንዲህ በማለት ይመክራል፦ “ከሴት ጋር ብዙ አታውራ። . . . ከሴት ጋር ብዙ የሚያወራ ሰው በራሱ ላይ ጉዳት ያመጣል፣ የሕጉን ጥናት ችላ ይላል በመጨረሻም ገሃነም ይገባል።”—አቦት 1:5
b ፓለስታይን ኢን ዘ ታይም ኦቭ ክራይስት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በአንዳንድ መንገዶች ሴት ከባሪያ እኩል እንደሆነች ተደርጋ ትታይ ነበር ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ የባሏን መሞት ለመመሥከር ካልሆነ በስተቀር በፍርድ ቤት ቀርባ መመሥከር አትችልም ነበር።” ዘ ሚሽና ዘሌዋውያን 5:1ን ጠቅሶ “ስለ ‘መመሥከር’ [የሚናገረው ሕግ] የሚሠራው ለሴት ሳይሆን ለወንድ ነው” ሲል ገልጿል።—ሺቦት 4:I
c የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ የንጉሥ ሄሮድስ እህት ሰሎሜ ለባሏ “የፍቺ ወረቀት ላከችለት፤ ይህም ከአይሁድ ሕግ ጋር የሚስማማ አልነበረም። ምክንያቱም እኛ እንደዚህ እንዲያደርግ የምንፈቅደው ለወንድ (ብቻ) ነው” ሲል ዘግቧል።—ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ XV, 259 [vii, 10]
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ኢየሱስ ሴቶችን በክብር እንደያዛቸው የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉ?
◻ የኢየሱስ ትምህርቶች ለሴቶች አክብሮት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
◻ ባል ክርስቲያን ሚስቱን በክብር መያዝ ያለበት ለምንድን ነው?
◻ አክብሮት በማሳየት ረገድ ሁሉም ክርስቲያኖች ምን ግዴታ አለባቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ሴቶች ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን በመጀመሪያ በማየታቸውና ለወንድሞቹ በመመሥከራቸው ተደስተዋል