የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ጥሩ ዝግጅት አድርጉ
የክርስቶስ ተከታዮች፣ በየዓመቱ ለምናከብረው የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚያደርጉት ዝግጅት የሚያስደስታቸው ከመሆኑም ሌላ እንደ መብት ይቆጥሩታል። (ሉቃስ 22:19) ለመታሰቢያው በዓል ለመዘጋጀት ምን ምን ነገሮች መደረግ አለባቸው?
◼ ሰዓትና ቦታ፦ ሁሉም ሰው በዓሉ የሚከበርበትን ትክክለኛ ሰዓትና ቦታ ማወቅ አለበት። ከአንድ በላይ ጉባኤዎች በመንግሥት አዳራሹ የሚጠቀሙ ከሆነ በሁለቱ ስብሰባዎች መካከል ያለው ጊዜ ውስን ስለሚሆን በሰዓቱ ለመጀመርና ግርግር ሳይፈጠር ለሚቀጥለው ጉባኤ ቦታውን ለመልቀቅ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በመግቢያዎች አካባቢ፣ በመንገዱ ላይ እንዲሁም በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች አላስፈላጊ ጭንቅንቅ እንዳይፈጠር ጥሩ ቅንጅት ሊኖር ይገባል።
◼ የግብዣ ወረቀቶች፦ ሁሉም አስፋፊዎች የሚያሰራጩት የግብዣ ወረቀት ደርሷቸዋል? የያዘውን መልእክትስ አንብበውታል? የግብዣ ወረቀቱን በምን መንገድ ለሰዎች እንደምትሰጡ ተለማምዳችኋል? የግብዣ ወረቀቱን ለእነማን ልትሰጡ አስባችኋል? የግብዣ ወረቀቱ ምንም ሳይተርፍ እንዲሠራጭ ጥረት መደረግ ይኖርበታል።
◼ መጓጓዣ፦ ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች እንዲሁም በርካታ ወንድሞችና እህቶች ወደ መታሰቢያው በዓል ለመምጣት በመጓጓዣ ወይም በሌላ ረገድ እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆናል። በዚህ ረገድ ምን ዝግጅት ተደርጓል?
◼ ቂጣውና ወይኑ፦ ቂጣውና ወይኑ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት መዞር እንደሌለባቸው አስታውሱ። አቅመ ደካማ በመሆናቸው በበዓሉ ላይ መገኘት የማይችሉ ቅቡዓን ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል። ተገቢው ዓይነት ቂጣና ወይን ተዘጋጅቶ መቀመጥ አለበት።—የየካቲት 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14-15 አንቀጽ 14 እና 17ን ተመልከቱ።
◼ የመንግሥት አዳራሽ፦ የመንግሥት አዳራሹ ወይም ለበዓሉ የምትጠቀሙበት ሌላ የመሰብሰቢያ ቦታ አስቀድሞ በደንብ መጽዳት ይኖርበታል። ሳህኖችን፣ የወይን ብርጭቆዎችን፣ ለበዓሉ ተስማሚ የሚሆን ጠረጴዛና የጠረጴዛ ልብስ ቀደም ብሎ ወደ አዳራሹ ማምጣትና በቦታው ማስቀመጥ ያስፈልጋል። የመንግሥት አዳራሹን ሳይሆን ሌላ የመሰብሰቢያ ቦታ የምትጠቀሙ ከሆነ ተሰብሳቢዎች በሙሉ ተናጋሪው የሚናገረውን በሚገባ ማዳመጥ እንዲችሉ ተገቢው ዓይነት የድምፅ መሣሪያ ሊኖራችሁ ይገባል። አስተናጋጆችም ሆኑ ቂጣውንና ወይኑን የሚያዞሩት ወንድሞች በቅድሚያ ሊመረጡና የሥራ ድርሻቸው ምን እንደሆነ፣ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንዴት እንደሚያከናውኑ እንዲሁም ሥርዓታማ የሆነ አለባበስና አበጣጠር አስፈላጊ መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል።
ከምንም ነገር በላይ የላቀ ግምት ለሚሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል፣ በግላችንም ሆነ በጉባኤ ደረጃ ጥሩ ዝግጅት ለማድረግ እንፈልጋለን። ይሖዋ፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ለሰው ዘር የሰጠውን ስጦታ ከልብ የሚያደንቁ ሰዎችን አብዝቶ እንደሚባርክ የተረጋገጠ ነው።