ለወንዶች ለመመሥከር ጥረት አድርጉ
1. ከመንግሥቱ ሥራ ጋር በተያያዘ አንገብጋቢ የሆነው ነገር ምንድን ነው?
1 በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ እየተስፋፋ በሄደ መጠን ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ማግኘት ይበልጥ አንገብጋቢ እየሆነ መጥቷል። (ማር. 4:30-32፤ ሥራ 20:28፤ 1 ጢሞ. 3:1-13) ይሁንና በአንዳንድ ቦታዎች የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉ ወንዶች ቁጥር ከሴቶቹ አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው። በአንዳንድ አገሮች ካለው ባሕል የተነሳ ወንዶች፣ ለልጆች መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት የመስጠቱ ኃላፊነት ለሚስቶች የተተወ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በርካታ ወንዶች ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ እንዲሆኑና በእውነተኛው አምልኮ ከጎናችን እንዲሰለፉ ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?
2. ጳውሎስና ጴጥሮስ ለወንዶች ለመመሥከር ያደረጉት ጥረት ጥሩ ውጤት ያስገኘው እንዴት ነው?
2 ለወንዶች ለመመሥከር ይበልጥ ትኩረት ስጡ፦ ብዙውን ጊዜ አንድ የቤተሰብ ራስ እውነትን ሲቀበል ሌሎች የቤተሰቡ አባላት በንጹሕ አምልኮ ከእሱ ጋር እንዲተባበሩ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስና ሲላስ በስብከቱ ሥራቸው ምክንያት ታስረው በነበረበት ወቅት ለእስር ቤቱ ጠባቂ መሥክረውለት ነበር። በመሆኑም ይህ ሰውም ሆነ መላው ቤተሰቡ ተጠምቀዋል። (ሥራ 16:25-34) በተጨማሪም ጳውሎስ በቆሮንቶስ በመስበኩ “የምኩራብ አለቃው ቀርስጶስ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ።” (ሥራ 18:8) “ለአምላክ ያደረና ፈሪሃ አምላክ ያለው” ተብሎ ለተጠራው ለመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እንዲመሠክር ይሖዋ ጴጥሮስን ልኮት ነበር። በዚህም የተነሳ ቆርኔሌዎስ ከዘመዶቹና ከቅርብ ወዳጆቹ ጋር ተጠምቋል።—ሥራ 10:1-48
3. የፊልጶስን ምሳሌ በመከተል እናንተስ ለየትኛው “ባለሥልጣን” መመሥከር ትችላላችሁ?
3 ‘በሥልጣን ላይ ላሉ’ ወንዶች መመሥከር ብዙ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። (1 ጢሞ. 2:1, 2) ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ መልአክ በኢትዮጵያ ንግሥት ገንዘብ ሁሉ ላይ ኃላፊ ሆኖ የተሾመን አንድ “ባለሥልጣን” እንዲያነጋግር ፊልጶስን ልኮት ነበር። ፊልጶስ፣ ሰውየው “የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ” ሲያነብ ሰማና ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች አብራራለት። ከዚያም ይህ ኢትዮጵያዊ ደቀ መዝሙር ሆነ፤ ይህ ሰው ወደ አገሩ ሲመለስ በጉዞው ላይ ምሥራቹን እንደሰበከ መገመት ይቻላል። በተጨማሪም ለንግሥቲቱና በቤተ መንግሥቷ ለሚገኙ ሰዎች መሥክሮ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች ምሥራቹን መስማት የሚችሉበት አጋጣሚ በጣም የጠበበ ነበር።—ሥራ 8:26-39
4. ወንዶች ምሥራቹን የሚሰሙበት ተጨማሪ አጋጣሚ እንዲያገኙ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ብዙ ወንዶችን ለማነጋገር ጣሩ፦ ብዙውን ጊዜ ወንዶች ቀን ላይ ሥራ ስለሚውሉ ምሽት ላይ፣ ቅዳሜና እሁድ ወይም በበዓል ቀናት በአገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ፕሮግራማችሁን ማስተካከል ትችላላችሁ? በሥራ ቦታዎች አካባቢ አዘውትራችሁ ማገልገላችሁ ብዙውን ጊዜ ቤታቸው ለማይገኙ ወንዶች ለመመሥከር የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ይፈጥርላችኋል። በተጨማሪም ወንድሞች፣ ወንዶች ለሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ልዩ ጥረት ማድረግ ይችላሉ። ወንድሞች በተለይ በተደጋጋሚ በተሸፈኑ ክልሎች ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ አንዳንድ ጊዜ የቤቱን አባወራ ማግኘት ይችሉ እንደሆነ መጠየቅ ይችላሉ።
5. አንዲት እህት የመንግሥቱን መልእክት የነገረችው ሰው ፍላጎት በሚያሳይበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርባታል?
5 አንዲት እህት ለእውነት ፍላጎት ላሳየ ወንድ ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ ብቻዋን መሄድ አይኖርባትም። ከዚህ ይልቅ ባለቤቷን ወይም ሌላ አስፋፊ ይዛ መሄድ ትችላለች። ፍላጎት ያሳየው ሰው እድገት ማድረጉን ከቀጠለ ብቃት ያለው አንድ ወንድም እንዲረዳው ዝግጅት ማድረጉ የተሻለ ነው።
6. ‘ብዙዎችን ለመማረክ’ በምናደርገው ጥረት የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
6 የወንዶችን ትኩረት የሚስቡ ርዕሰ ጉዳዮችን ተጠቀሙ፦ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ብዙዎችን ለመማረክ’ ሲል አድማጮቹን ግምት ውስጥ ያስገባ የነበረ ከመሆኑም በላይ አቀራረቡን እንደሁኔታው ይለዋውጥ ነበር። (1 ቆሮ. 9:19-23) እኛም በተመሳሳይ የምናገኛቸውን ወንዶች ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን መምረጥና ለእነሱ እንደሚስማማ አድርገን ለማቅረብ መዘጋጀት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል ወንዶች ብዙውን ጊዜ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ እንዲሁም ከቤተሰባቸው ደኅንነት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ያሳስቧቸዋል። ከዚህም በላይ ስለ ሕይወት ዓላማ፣ ስለ ምድር የወደፊት ሁኔታና አምላክ መከራን ስለፈቀደበት ምክንያት መወያየት ሊያስደስታቸው ይችላል። አስተዋዮች በመሆን አቀራረባችንን በዚህ መንገድ የምናስተካክል ከሆነ የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ይበልጥ ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል።—ምሳሌ 16:23
7. የማያምኑ ባሎች በስብሰባ ላይ በሚገኙበት ጊዜ ሁሉም የጉባኤው አባላት በጎ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉት እንዴት ነው?
7 የማያምኑ ባሎችን ለመርዳት ጥረት አድርጉ፦ አብዛኛውን ጊዜ በማያምኑ ባሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ትልቁን ሚና የሚጫወተው ክርስቲያን እህቶቻችን የሚያሳዩት መልካም ምግባር ቢሆንም ሌሎች የጉባኤ አባላትም በዚህ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 3:1-4) አንድ የማያምን ባል ከሚስቱ ጋር ወደ ስብሰባ በሚመጣበት ወቅት የጉባኤው አባላት የሚያደርጉለት ሞቅ ያለ አቀባበል ትልቅ ምሥክርነት ሊሰጥ ይችላል። በስብሰባ ላይ መገኘቱ በራሱ ለእውነት መጠነኛ ፍላጎት እንዳለው የሚጠቁም ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር የሚቀርብለትን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።
8. ወንድሞች ለእውነት እምብዛም ፍላጎት የሌላቸውን የማያምኑ ባሎች ለመርዳት ምን ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ?
8 በሌላ በኩል አንዳንድ ባሎች መጀመሪያ ላይ ለመንፈሳዊ ነገሮች ብዙም ፍላጎት ባያሳዩም እንኳ ውሎ አድሮ ይበልጥ ከሚግባቧቸው ወንድሞች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለመጀመር ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። በአንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች የማያምን ባል ያላትን እህትና ቤተሰቧን ለመጠየቅ በሚሄዱበት ጊዜ ባልየውን የሚያስደስቱ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሱ ያጫውቱት ነበር። ውሎ አድሮ እንዲህ ያለው ጭውውት በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የሚያስችል በር የከፈተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ባልየው የተጠመቀ ወንድም ሆኗል። አንድ ወንድም ደግሞ አንድ የማያምን ባል አጥር በሚሠራበት ጊዜ ሄዶ ረዳው። ወንድም በዚህ መንገድ አሳቢነቱን በተግባር ማሳየቱ ባልየው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊጀምር ችሏል። (ገላ. 6:10፤ ፊልጵ. 2:4) ክርስቲያን ወንድሞች ከሆናችሁ የማያምኑ ባሎችን ለመርዳት ለምን ጥረት አታደርጉም?
9. ክርስቲያን ወንዶችን ማሠልጠን ምን ውጤት ያስገኛል?
9 ክርስቲያን ወንዶችን ማሠልጠን፦ ወንዶች የመንግሥቱን መልእክት ከተቀበሉ በኋላ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመቀበልና ይሖዋን ለማገልገል ሲጣጣሩ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ይኸውም ችሎታቸውንና ጉልበታቸውን መሥዋዕት በማድረግ የይሖዋን ሕዝብ ጉባኤዎች የሚያገለግሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሊሆኑ ይችላሉ። (ኤፌ. 4:8፤ መዝ. 68:18) እንዲህ ያሉ ወንዶች ለማገልገል ካላቸው ጉጉት የተነሳ እረኛ ሆነው ጉባኤውን በፈቃደኝነት ይጠብቃሉ። (1 ጴጥ. 5:2, 3) እነዚህ ወንዶች ለመላው የወንድማማች ኅብረት ትልቅ በረከት ናቸው!
10. ሐናንያ ጳውሎስን ለመርዳት ባደረገው ጥረት ብዙዎች የተጠቀሙት እንዴት ነው?
10 ለምሳሌ ያህል፣ ሳኦል በአንድ ወቅት ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ “የአሕዛብ ሐዋርያ” ሆኗል። (ሮም 11:13) ደቀ መዝሙሩ ሐናንያ መጀመሪያ ላይ ለሳኦል ለመመሥከር አመንትቶ ነበር። ያም ሆኖ ሐናንያ ጌታ የሰጠውን መመሪያ በመከተል የመሠከረለት ሲሆን ይህ ሰው ውሎ አድሮ ሐዋርያው ጳውሎስ ሆኗል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የጳውሎስን ምሥክርነት የሰሙ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እሱ ባከናወነው አገልግሎት ተጠቅመዋል። ከዚህም በላይ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ደብዳቤዎች በአሁኑ ጊዜም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እየጠቀሙ ነው።—ሥራ 9:3-19፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17
11. ለወንዶች ለመመሥከር አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን ሁሉ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
11 እንግዲያው ለወንዶች ለመመሥከር በምናደርገው ጥረት አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን ሁሉ እናድርግ። ይህን ግብ ለማሳካት ስንጣጣር ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለመፈጸምና የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማከናወን የምናደርገውን ከፍተኛ ጥረት እንደሚባርክልን እርግጠኞች ነን።