የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2024 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከመስከረም 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 79–81
ለይሖዋ ታላቅ ስም ያላችሁን ፍቅር አሳዩ
ቤዛው—ከአባታችን የተገኘ “ፍጹም ገጸ በረከት”
5 እኛስ የይሖዋን ስም እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በአኗኗራችን ይህን ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ ቅዱስ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16ን አንብብ።) ይህም ሲባል እሱን ብቻ እንድናመልክና በሙሉ ልባችን እንድንታዘዘው ይፈልጋል ማለት ነው። ስደት ቢደርስብንም እንኳ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶችና ሕጎች ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። የይሖዋን መመሪያዎች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ በማዋል ብርሃናችን በሰው ፊት እንዲበራ እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣል። (ማቴ. 5:14-16) የአምላክ ቅዱስ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን፣ የይሖዋ ሕጎች ትክክለኛ መሆናቸውንና የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን በአኗኗራችን እናሳያለን። እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ስህተት መሥራታችን አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ ከልባችን ንስሐ በመግባት ይሖዋን ከሚያስነቅፉ ድርጊቶች እንርቃለን።—መዝ. 79:9
ሮም 10:13—“የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል”
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የይሖዋን ስም መጥራት’ የሚለው አገላለጽ የአምላክን ስም ከማወቅና በአምልኮ ወቅት ስሙን ከመጥራት ያለፈ ነገርን ያመለክታል። (መዝሙር 116:12-14) በአምላክ መታመንንና የእሱን እርዳታ መፈለግን ይጨምራል።—መዝሙር 20:7፤ 99:6
ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ስም ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ የጠቀሳቸው የመጀመሪያዎቹ ቃላት “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” የሚሉ ናቸው። (ማቴዎስ 6:9) በተጨማሪም ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ስሙ የሚወክለውን አካል ማወቅ፣ መታዘዝና መውደድ እንዳለብን አስተምሯል።—ዮሐንስ 17:3, 6, 26
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 111
ዮሴፍ
የዮሴፍ ስም የተሰጠው ቦታ። ዮሴፍ ከያዕቆብ ልጆች መካከል ከነበረው ትልቅ ቦታ አንጻር ስሙ አንዳንድ ጊዜ ሁሉንም የእስራኤል ነገዶች (መዝ 80:1) ወይም በሰሜናዊው መንግሥት ውስጥ የተካተቱትን ነገዶች ለማመልከት ማገልገሉ ተገቢ ነው። (መዝ 78:67፤ አሞጽ 5:6, 15፤ 6:6) ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥም ተጠቅሷል። የሕዝቅኤል ትንቢታዊ ራእይ ዮሴፍ ሁለት ድርሻ እንደሚኖረው (ሕዝ 47:13) እንዲሁም “ይሖዋ በዚያ አለ” የተባለችው ከተማ አንዱ በር በዮሴፍ ስም እንደሚጠራ ይገልጻል (ሕዝ 48:32, 35)፤ የይሖዋ ሕዝቦች መልሰው አንድ እንደሚሆኑ ከሚገልጸው ትንቢት ጋር በተያያዘ ደግሞ የብሔሩ አንዱ ክፍል መሪ ዮሴፍ፣ የሌላኛው ክፍል መሪ ደግሞ ይሁዳ እንደሆነ ተገልጿል። (ሕዝ 37:15-26) የአብድዩ ትንቢት ‘የዮሴፍ ቤት’ ‘የኤሳውን ቤት’ በማጥፋት ረገድ ሚና እንደሚኖረው ይጠቁማል (አብ 18)፤ የዘካርያስ ትንቢት ደግሞ ይሖዋ ‘የዮሴፍን ቤት’ እንደሚያድን ይገልጻል። (ዘካ 10:6) ከመንፈሳዊ እስራኤል ነገዶች አንዱ ተደርጎ የተጠቀሰው ኤፍሬም ሳይሆን ዮሴፍ ነው።—ራእይ 7:8
በራእይ 7:8 ላይ ዮሴፍ መጠቀሱ ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት የተናገረው ትንቢት ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር በተያያዘ እንደሚሠራ ይጠቁማል። በመሆኑም የያዕቆብ ኃያል አምላክ የሆነው ይሖዋ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን “ለበጎቹ” ሲል ሕይወቱን የሚሰጥ ጥሩ እረኛ አድርጎ የሾመው መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዮሐ 10:11-16) በተጨማሪም ክርስቶስ ኢየሱስ መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ያቀፈው የአምላክ ቤተ መቅደስ የሚያርፍበት የመሠረት ድንጋይ ነው። (ኤፌ 2:20-22፤ 1ጴጥ 2:4-6) ይህ እረኛ እና ዓለት ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ነው።—ዮሐ 1:1-3፤ ሥራ 7:56፤ ዕብ 10:12፤ ከዘፍ 49:24, 25 ጋር አወዳድር።
ከመስከረም 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 82–84
ላሏችሁ መብቶች አድናቆት ይኑራችሁ
ከሰማይ ወፎች የምናገኘው ትምህርት
የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ወንጭፊት የምትባለውን፣ ብዙውን ጊዜ በሕንጻዎች ጣሪያ ሥር ጎጆዋን የምትሠራውን ወፍ በሚገባ ያውቋት ነበር። ከእነዚህ ወፎች አንዳንዶቹ ሰለሞን በገነባው ቤተ መቅደስ ጣሪያ ሥር ጎጇቸውን ሠርተው ነበር። በቤተ መቅደሱ አካባቢ ጎጇቸውን የሚሠሩት እነዚህ ወፎች ይህ ቦታ በየዓመቱ ጫጩቶቻቸውን ያለ ችግር ማሳደግ የሚችሉበት አስተማማኝ ስፍራ ሳይሆንላቸው አልቀረም።
በየስድስት ወሩ ለአንድ ሳምንት ያህል በቤተ መቅደሱ ያገለግል የነበረውና ከቆሬ ልጆች አንዱ የሆነው የመዝሙር 84 ጸሐፊ፣ በቤተ መቅደሱ አካባቢ የሚገኙትን የወፍ ጎጆዎች አስተውሎ ነበር። በይሖዋ ቤት ቋሚ መኖሪያ እንዳገኘችው ወንጭፊት ለመሆን ተመኝቶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ታላቁ የማደሪያ ድንኳንህ ምንኛ ያማረ ነው! ሁለንተናዬ የይሖዋን ቅጥር ግቢዎች እጅግ ናፈቀ፤ አዎ፣ በጣም ከመጓጓቴ የተነሳ ዛልኩ። . . . ንጉሤና አምላኬ የሆንከው የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ታላቁ መሠዊያህ ባለበት አቅራቢያ፣ ወፍ እንኳ በዚያ ቤት ታገኛለች፤ ወንጭፊትም ጫጩቶቿን የምታሳድግበት ጎጆ ለራሷ ትሠራለች።” (መዝሙር 84:1-3) ታዲያ እኛስ ከልጆቻችን ጋር ሆነን ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በጉባኤ ለመሰብሰብ እንዲህ ያለ ጉጉት አለን?—መዝሙር 26:8, 12
ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ በመሆን ደስታ ማግኘት
የዕድሜ መግፋት ወይም የጤና እክል በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ሊገድብብን ይችላል። ወላጅ ከሆንክ፣ አብዛኛውን ጊዜህንና ኃይልህን ትንንሽ ልጆችህን ለመንከባከብ ስለምታውለው የግል ጥናት ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነብህ ወይም ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ብዙም ጥቅም እንደማታገኝ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ባሉብህ የአቅም ገደቦች ላይ ትኩረት ማድረግህ ልታከናውናቸው የምትችላቸውን ነገሮች እንዳታስተውል አድርጎህ ይሆን?
በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የኖረ አንድ ሌዋዊ ሊያገኘው የማይችለውን ነገር ተመኝቶ ነበር። ይህ ሌዋዊ በየዓመቱ ለሁለት ሳምንታት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የማገልገል መብት ነበረው። ይሁንና ሁልጊዜ በመሠዊያው አጠገብ ለመኖር እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ነገር መመኘቱ የሚደነቅ ነው። (መዝ. 84:1-3) ታዲያ ይህ ታማኝ ሰው ባለው መብት እንዲረካ የረዳው ምን ነበር? ይህ ሌዋዊ በቤተ መቅደሱ አደባባይ አንዲት ቀን እንኳ መዋል ልዩ መብት እንደሆነ ተገንዝቧል። (መዝ. 84:4, 5, 10) እኛም በተመሳሳይ ከአቅማችን በላይ የሆኑትን ነገሮች በማሰብ ከመብሰልሰል ይልቅ ልናከናውናቸው የምንችላቸውን ነገሮች ማስተዋልና እነዚህንም ማድረግ በመቻላችን አመስጋኞች መሆን ይገባናል።
በአምላክህ በይሖዋ ፊት ውድ ነህ!
12 የጤና እክል አጋጥሞህ ከሆነ ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ አትጠራጠር። ስለ ሁኔታው ትክክለኛ አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳህ ይሖዋን ለምነው። ከዚያም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስቀመጠልህን መልካም ቃላት ለማግኘት ጥረት አድርግ። ይሖዋ አገልጋዮቹን ምን ያህል ውድ አድርጎ እንደሚመለከታቸው በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ ትኩረት አድርግ። ይህን ስታደርግ ይሖዋ በታማኝነት ለሚያገለግሉት ሁሉ መልካም እንደሆነ ማስተዋልህ አይቀርም።—መዝ. 84:11
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 816
አባት የሌለው ልጅ
ቤተሰባቸውን ያጡትና ተሟጋች የሌላቸው እነዚህ ሰዎች በቀላሉ ችላ ሊባሉ ስለሚችሉ ይሖዋ እስራኤላውያን በጽድቅ ጎዳና ላይ መጓዛቸውን ወይም ከዚያ መራቃቸውን ለመግለጽ ‘አባት የሌለው ልጅ’ የሚለውን አገላለጽ ይጠቀማል። ብሔሩ ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት ላይ ሲሆን አባት የሌላቸው ልጆች ጥሩ እንክብካቤ ያገኛሉ። በምድሪቱ ላይ ፍትሕ ሲጣመም ደግሞ አባት የሌላቸው ልጆች ችላ ይባላሉ፤ ይህ ደግሞ የብሔሩን ብልሹነት የሚያሳይ ምልክት ነው። (መዝ 82:3፤ 94:6፤ ኢሳ 1:17, 23፤ ኤር 7:5-7፤ 22:3፤ ሕዝ 22:7፤ ዘካ 7:9-11፤ ሚል 3:5) አባት የሌለውን ልጅ የሚጨቁኑ ሰዎች የይሖዋ እርግማን ይወርድባቸዋል። (ዘዳ 27:19፤ ኢሳ 10:1, 2) ይሖዋ የእነዚህ ልጆች ተከራካሪ (ምሳሌ 23:10, 11)፣ ረዳት (መዝ 10:14) እና አባት (መዝ 68:5) እንደሆነ ገልጿል። ለእነሱ የሚፈርድላቸው (ዘዳ 10:17, 18)፣ ምሕረት የሚያደርግላቸው (ሆሴዕ 14:3)፣ የሚደግፋቸው (መዝ 146:9) እና በሕይወት የሚያኖራቸው እሱ ነው።—ኤር 49:11
ከእውነተኛ ክርስትና መለያዎች አንዱ፣ ባላቸውን ወይም ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ ሰዎች የሚያሳየው አሳቢነት ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ለክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው።”—ያዕ 1:27
ከመስከረም 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 85–87
ጸሎት ለመጽናት ይረዳናል
የይሖዋን ክብር እያንጸባረቃችሁ ነው?
10 የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ‘በጽናት መጸለይ’ ነው። (ሮም 12:12) ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ለማገልገል የእሱን እርዳታ በጸሎት መጠየቅ እንችላለን፤ ይህን ማድረግም ይኖርብናል። በመሆኑም ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን፣ እምነታችንን እንዲያሳድግልን፣ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠን እንዲሁም “የእውነትን ቃል በአግባቡ [የመጠቀም]” ችሎታ እንዲኖረን እሱን በጸሎት መጠየቃችን ተገቢ ነው። (2 ጢሞ. 2:15፤ ማቴ. 6:13፤ ሉቃስ 11:13፤ 17:5) አንድ ልጅ በአባቱ እንደሚመካ ሁሉ እኛም በሰማይ በሚገኘው አባታችን በይሖዋ መተማመን ይኖርብናል። አምላክ፣ እሱን በተሻለ መንገድ ለማገልገል እንዲረዳን ብንጠይቀው ፈጽሞ እንደማያሳፍረን እርግጠኞች ነን። ይሖዋን እንዳስቸገርነው ሆኖ በፍጹም ሊሰማን አይገባም! ከዚህ ይልቅ በጸሎት አማካኝነት እሱን ማወደስና ማመስገን ይኖርብናል። እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ በተለይ ደግሞ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የአምላክን አመራር እንፈልግ፤ በተጨማሪም ለቅዱስ ስሙ ክብር በሚያመጣ መንገድ እንድናገለግለው ይረዳን ዘንድ እንለምነው።—መዝ. 86:12፤ ያዕ. 1:5-7
ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ነው?
17 መዝሙር 86:6, 7ን አንብብ። መዝሙራዊው ዳዊት፣ ይሖዋ ጸሎቱን እንደሰማውና እንደመለሰለት እርግጠኛ ነበር። አንተም ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማና እንደሚመልስልህ መተማመን ትችላለህ። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተመለከትናቸው ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ይሖዋ ጥበብና ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። መንፈሳዊ ቤተሰባችንን አልፎ ተርፎም በአሁኑ ወቅት እሱን የማያመልኩ ሰዎችን በመጠቀም በሆነ መንገድ ሊረዳን ይችላል።
18 ይሖዋ ጸሎታችንን በጠበቅነው መንገድ ላይመልስልን ቢችልም ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። የሚያስፈልገንን ነገር ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ይሰጠናል። እንግዲያው ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እንደሚንከባከብህ፣ በመጪው አዲስ ዓለም ደግሞ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ እርግጠኛ በመሆን በእምነት መጸለይህን ቀጥል።—መዝ. 145:16
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1058 አን. 5
ልብ
“በሙሉ ልብ” ማገልገል። ሥጋዊው ልብ ሥራውን በትክክል እንዲያከናውን ሙሉ መሆን አለበት፤ ምሳሌያዊው ልብ ግን ሊከፋፈል ይችላል። ዳዊት “ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ” በማለት መጸለዩ የአንድ ሰው ልብ ከሚወዳቸውና ከሚፈራቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ሊከፋፈል እንደሚችል ይጠቁማል። (መዝ 86:11) እንዲህ ያለው ሰው “ግማሽ ልብ” ሊኖረው ማለትም በይሖዋ አምልኮ ረገድ ለብ ያለ ሊሆን ይችላል። (መዝ 119:113፤ ራእይ 3:16) አንድ ሰው “መንታ ልብ” (ቃል በቃል ልብና ልብ) ሊኖረውም ይችላል፤ እንዲህ ያለው ሰው ሁለት ጌቶችን ለማገልገል ሊሞክር ወይም አንድ ነገር እያሰበ ሌላ ነገር በመናገር ሊያጭበረብር ይችላል። (1ዜና 12:33 ግርጌ፤ መዝ 12:2 ግርጌ) ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ግብዝነት አጥብቆ አውግዟል።—ማቴ 15:7, 8
ከመስከረም 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 88–89
የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ ነው
የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፉ!
5 ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት አለው የምንልበት ሌላም ምክንያት አለ። ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ፍጹም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው። ይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በምድር ላይ ታማኝ ፍቅር የማሳየው፣ ደግሞም ፍትሕና ጽድቅ የማሰፍነው እኔ ይሖዋ [ነኝ፤] . . . በእነዚህ ነገሮች ደስ እሰኛለሁና።” (ኤር. 9:24) ይሖዋ ትክክልና ፍትሐዊ የሆነውን ነገር ለመለየት ሰዎች ያወጡትን ሕግ መመልከት አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር ለማወቅ የሚያስችል መሥፈርት ያወጣው እሱ ራሱ ነው። በመሆኑም ፍጹም በሆነው የፍትሕ መሥፈርቱ ላይ የተመሠረተ ሕግ ለሰው ልጆች ሰጥቷል። “ጽድቅና ፍትሕ [የዙፋኑ] መሠረት ናቸው፤” ስለሆነም ሕጎቹ፣ መሠረታዊ ሥርዓቶቹና ውሳኔዎቹ በሙሉ ትክክል እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 89:14፤ 119:128) ሰይጣን ‘የይሖዋ አገዛዝ ፍትሐዊ አይደለም’ የሚል ክስ ቢሰነዝርም እሱ ራሱ በዓለም ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ አልቻለም።
የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፉ!
10 የይሖዋ አገዛዝ ጭቆና ያለበት ወይም የማያፈናፍን አይደለም። አገዛዙ ለሰዎች ነፃነት የሚሰጥና ደስታ የሚያስገኝ ነው። (2 ቆሮ. 3:17) ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ሞገስና ግርማ [በአምላክ ፊት] ናቸው፤ ብርታትና ደስታ እሱ በሚኖርበት ስፍራ ይገኛሉ።” (1 ዜና 16:7, 27) በተመሳሳይም መዝሙራዊው ኤታን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እልልታ የሚያውቁ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። ይሖዋ ሆይ፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች በፊትህ ብርሃን ይመላለሳሉ። በስምህ ቀኑን ሙሉ ሐሴት ያደርጋሉ፤ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ።”—መዝ. 89:15, 16
11 በይሖዋ ጥሩነት ላይ አዘውትረን ማሰላሰላችን የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። “በሌላ ቦታ አንድ ሺህ ቀን ከመኖር በቅጥር ግቢዎችህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል!” በማለት የተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ይሰማናል። (መዝ. 84:10) ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል፤ ይህንንም አትረፍርፎ ይሰጠናል። ይሖዋ ያወጣቸው መሥፈርቶች በሙሉ እኛን የሚጠቅሙ ናቸው። ይሖዋ የሚጠብቅብንን ነገር ማድረግ አንዳንድ መሥዋዕትነት መክፈል ቢጠይቅብንም እንኳ እሱን መታዘዛችን ደስታ ያስገኝልናል።—ኢሳይያስ 48:17ን አንብብ።
በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑራችሁ
14 የዳዊትን ቃል ኪዳን ይኸውም ይሖዋ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት የገባለትን ቃል እንመልከት። (2 ሳሙኤል 7:12, 16ን አንብብ።) ይሖዋ ከዳዊት ጋር ይህን ቃል ኪዳን ያደረገው ዳዊት በኢየሩሳሌም ንጉሥ በነበረበት ወቅት ሲሆን መሲሑ በእሱ ዘር በኩል እንደሚመጣ ቃል ገብቶለታል። (ሉቃስ 1:30-33) በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ ዘሩ የሚመጣበትን መስመር ይበልጥ ግልጽ አደረገ፤ በተጨማሪም የዳዊት ወራሽ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ ለመሆን “የሚገባው ባለ መብት” ይሆናል። (ሕዝ. 21:25-27) በኢየሱስ አማካኝነት የዳዊት ንግሥና “ለዘላለም የጸና ይሆናል።” በእርግጥም የዳዊት ዘር “ለዘላለም፣ ዙፋኑም . . . እንደ ፀሓይ ጸንቶ ይኖራል።” (መዝ. 89:34-37) አዎን፣ የመሲሑ አገዛዝ መቼም ቢሆን ምግባረ ብልሹ አይሆንም፤ ያከናወናቸው ነገሮችም ቢሆኑ ዘላለማዊ ይሆናሉ!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“አንተ ብቻ ታማኝ ነህ”
4 “ታማኝነት” የሚለውን ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ካለው አገባብ አንጻር ስንመለከተው አንድን አካል በፍቅር የሙጥኝ በማለትና ከዚህ አካል ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ ዳር እስኪደርስ ድረስ ከእሱ ጎን በመቆም የሚገለጽ ደግነት ነው። ታማኝ ሰው ይህን የሚያደርገው እንዲሁ ግዴታን ለመወጣት ያህል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስቶ ነው። በመሆኑም ታማኝ መሆን እምነት የሚጣልበት ወይም አስተማማኝ ሆኖ ከመገኘት የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙራዊው ጨረቃ ሁልጊዜ በምሽት የምትወጣ በመሆኗ “በሰማያት ታማኝ ምሥክር” ሆና እንደምትኖር ተናግሯል። (መዝሙር 89:37) እዚህ ላይ ጨረቃ ታማኝ ተብላ የተጠራችው አስተማማኝ በመሆኗ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ማሰብ የሚችሉ አካላት ከሚያሳዩት ታማኝነት የተለየ ነው። ለምን? ምክንያቱም ታማኝነት የፍቅር መገለጫ ነው፤ ግዑዝ ፍጥረታት ደግሞ ፍቅር ማሳየት አይችሉም።
5 ታማኝነት የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ባለው አገባብ መሠረት ወዳጃዊ መንፈስ የሚንጸባረቅበት ባሕርይ ነው። አንድ ሰው ለሌላው ታማኝ የሚሆነው በሁለቱ መካከል የጠበቀ ወዳጅነት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ታማኝነት ጊዜያዊ አይደለም። በነፋስ እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ተለዋዋጭ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ታማኝነት ወይም ታማኝ ፍቅር በጣም አስቸጋሪ የሆኑ መሰናክሎችን ሁሉ ማለፍ የሚያስችል ጥንካሬና ጽናት ያለው ባሕርይ ነው።
ከመስከረም 30–ጥቅምት 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 90–91
ዕድሜያችሁ እንዲረዝም በይሖዋ ታመኑ
ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚደረግ ጥረት
ብዙ ሳይንቲስቶች፣ እርጅናን ለማስቀረት የሚደረጉት ሕክምናዎች የሰውን ዕድሜ አሁን ካለው ይበልጥ ሊያስረዝሙ እንደሚችሉ አይሰማቸውም። እርግጥ ነው፣ ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ የሰዎች የዕድሜ ጣሪያ እየጨመረ መጥቷል። ሆኖም ይህ በዋነኝነት የሆነው ከንጽሕና አጠባበቅና ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከል ጋር በተያያዘ መሻሻል ስለታየ እንዲሁም አንቲባዮቲኮችና ክትባቶች ስለተስፋፉ ነው። አንዳንድ የጄኔቲክስ ተመራማሪዎች የሰውን ልጅ ዕድሜ አሁን ከደረሰበት እምብዛም ማስረዘም እንደማይቻል ይናገራሉ።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ሙሴ ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የዕድሜያችን ርዝማኔ 70 ዓመት ነው፤ ለየት ያለ ጥንካሬ ካለን ደግሞ 80 ዓመት ቢሆን ነው። ይህም በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው፤ ፈጥኖ ይነጉዳል፤ እኛም እናልፋለን።” (መዝሙር 90:10) የሰው ልጆች ዕድሜያቸውን ለማርዘም ብዙ ጥረት ቢያደርጉም የሰዎች ዕድሜ አሁንም ጥቅሱ ከሚገልጸው የዘለለ አይደለም።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የኤሊ ዝርያዎች ከ150 ዓመት በላይ መኖር ይችላሉ፤ እንደ አርዘ ሊባኖስ ያሉ ዛፎች ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይኖራሉ። የእኛን ዕድሜ እንዲህ ካሉ ፍጥረታት ጋር ስናወዳድር “ሕይወት በቃ 70 ወይም 80 ዓመት ብቻ ነው?” ብለን መጠየቃችን አይቀርም።
wp19.1 5 ሣጥን
የአምላክ ስም ማን ነው?
ይህ ብዙ ሰዎችን ሲያሳስብ የኖረ ጥያቄ ነው። ምናልባት አንተም ይህ ጥያቄ ተፈጥሮብህ ያውቅ ይሆናል። ይህን ጥያቄ በሌላ አባባል እንዲህ ብለን ልናስቀምጠው እንችላለን፦ ጽንፈ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና ያመጣው አምላክ ከሆነ አምላክ ራሱ ከየት መጣ?
በጥቅሉ ሲታይ ሳይንቲስቶች፣ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለው ይስማማሉ። ከዚህ መሠረታዊ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል።—ዘፍጥረት 1:1
ጽንፈ ዓለም፣ ራሱን በራሱ ሊፈጥር አይችልም። ምክንያቱም ጽንፈ ዓለም ራሱን ፈጠረ ማለት ከሌለ ነገር መጣ ማለት ነው። ሆኖም የሌለ ነገር፣ ለአንድ ነገር መገኘት ምክንያት ሊሆን አይችልም። ጽንፈ ዓለም ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት ምንም ነገር ካልነበረ ዛሬ ጽንፈ ዓለም ራሱ ሊኖር አይችልም ነበር። ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ መረዳት ቢከብደንም ጽንፈ ዓለም ወደ ሕልውና እንዲመጣ ከተፈለገ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የሌለው ብሎም ግዑዝ ከሆነው ጽንፈ ዓለም ውጭ የሆነ አካል የግድ መኖር አለበት። ይህ አካል ገደብ የለሽ ኃይልና ጥበብ ያለው እንዲሁም መንፈስ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው።—ዮሐንስ 4:24
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ በፊት፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም አንተ አምላክ ነህ” ይላል። (መዝሙር 90:2) ስለዚህ አምላክ ምንጊዜም ነበረ ማለት ነው። ከዚያም “በመጀመሪያ” ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ፈጠረ።—ራእይ 4:11
ፍቅር ፍርሃትን እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
16 ሰይጣን ሕይወታችንን እንደምንወድ ያውቃል። በመሆኑም ዕድሜያችንን ለማራዘም ስንል ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጨምሮ ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል ተናግሯል። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን ምንኛ ተሳስቷል! ያም ቢሆን “ለሞት የመዳረግ አቅም ያለው” ሰይጣን፣ ለሞት ያለንን ተፈጥሯዊ ፍራቻ ተጠቅሞ ይሖዋን እንድንተው ለማድረግ ይሞክራል። (ዕብ. 2:14, 15) አንዳንድ ጊዜ የሰይጣን ወኪሎች፣ የይሖዋ አገልጋዮች እምነታቸውን ካልካዱ እንደሚገድሏቸው ይዝቱባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰይጣን፣ ያለብንን ከባድ የጤና እክል ተጠቅሞ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ ይሞክራል። ሐኪሞች ወይም የማያምኑ ቤተሰቦቻችን ደም እንድንወስድ ይገፋፉን ይሆናል፤ ደም መውሰድ ደግሞ የአምላክን ሕግ መጣስ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ሕክምና እንድንከታተል ሊያግባቡን ይሞክሩ ይሆናል።
17 መሞት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም ብንሞትም እንኳ ይሖዋ እኛን መውደዱን እንደማያቆም ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 8:37-39ን አንብብ።) ይሖዋ ወዳጆቹ ቢሞቱም እንኳ በሕይወት ያሉ ያህል ያስታውሳቸዋል። (ሉቃስ 20:37, 38) በትንሣኤ ሊያስነሳቸው ይናፍቃል። (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ‘የዘላለም ሕይወት እንዲኖረን’ ሲል ውድ ዋጋ ከፍሏል። (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ በጣም እንደሚወደንና እንደሚያስብልን እናውቃለን። ስለዚህ ስንታመም ወይም ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ይሖዋን ከመተው ይልቅ ማጽናኛ፣ ጥበብና ብርታት እንዲሰጠን ወደ እሱ መቅረብ ይኖርብናል። ቫሌሪ እና ባለቤቷ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።—መዝ. 41:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ጠባቂ መልአክ አለህ?
መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ ጠባቂ መልአክ አለው ብሎ አያስተምርም። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በአንድ ወቅት “በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው በሰማይ ባለው አባቴ ፊት ዘወትር ስለሚቀርቡ ከእነዚህ ከትናንሾቹ [የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት] መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ” ብሏል። (ማቴዎስ 18:10) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን የተናገረው፣ መላእክት የእሱን ደቀ መዛሙርት በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ሰጥተው እንደሚከታተሏቸው ለማመልከት እንጂ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ጠባቂ መልአክ አለው ለማለት አይደለም። በመሆኑም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች መላእክት እንደሚጠብቋቸው በማሰብ ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ የሞኝነት ወይም የግድየለሽነት ድርጊት አይፈጽሙም።
ታዲያ መላእክት ሰዎችን አይረዱም ማለት ነው? በፍጹም። (መዝሙር 91:11) አንዳንዶች አምላክ በመላእክት አማካኝነት ጥበቃ እንዳደረገላቸውና አመራር እንደሰጣቸው በእርግጠኝነት ያምናሉ። በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ኬነት እንዲህ ከሚሰማቸው ሰዎች አንዱ ነው። በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ኬነት ልክ ሊሆን ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ሥራቸው ሲካፈሉ የመላእክት እገዛ መኖሩን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በተደጋጋሚ ይመለከታሉ። ይሁን እንጂ መላእክት በዓይን ስለማይታዩ አምላክ ሰዎችን ለመርዳት ምን ያህል እንደሚጠቀምባቸው በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ያም ሆኖ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለሚያደርግልን ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ ብናመሰግነው ስህተት አይሆንም።—ቆላስይስ 3:15፤ ያዕቆብ 1:17, 18
ከጥቅምት 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 92–95
ይሖዋን ማገልገል ከሁሉ የተሻለ የሕይወት ጎዳና ነው!
እናንት ወጣቶች፣ ትኩረታችሁ ያረፈው በመንፈሳዊ ግቦች ላይ ነው?
5 መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት፣ ይሖዋ ላሳየን ፍቅርና ላደረገልን ነገሮች አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ያለን ፍላጎት ነው። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋ ምስጋና ማቅረብ ጥሩ ነው፤ . . . ይሖዋ ሆይ፣ ባከናወንካቸው ነገሮች እንድደሰት አድርገኸኛልና፤ ከእጅህ ሥራዎች የተነሳ እልል እላለሁ።” (መዝ. 92:1, 4) ይሖዋ ያደረገልህን ነገሮች ሁሉ እስቲ መለስ ብለህ አስብ። ሕይወትህ፣ ይሖዋን ማወቅና ስለ እሱ እውነቱን መማር መቻልህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጉባኤው እንዲሁም በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋህ ከእነዚህ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትህ ከአምላክ ላገኘሃቸው ለእነዚህ በረከቶች አመስጋኝነትህን ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጥሃል፤ ይህ ደግሞ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ይረዳሃል።
አስተሳሰባችሁን የሚቀርጸው ማን ነው?
8 ይሖዋም ልክ እንደ አንድ ጥሩ ወላጅ፣ ልጆቹ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል። (ኢሳ. 48:17, 18) ስለዚህ ከሥነ ምግባርና ከሌሎች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር በተያያዘ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ረገድ የእሱን አመለካከት እንድናዳብርና በዚያ መሠረት እንድንኖር ግብዣ አቅርቦልናል። ይህ መፈናፈኛ የሚያሳጣ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የማሰብ ችሎታችን እንዲሰፋ፣ እንዲዳብርና የላቀ እንዲሆን ያደርጋል። (መዝ. 92:5፤ ምሳሌ 2:1-5፤ ኢሳ. 55:9) በግለሰብ ደረጃ ማንነታችንን ሳናጣ ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ ምርጫዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። (መዝ. 1:2, 3) በእርግጥም በይሖዋ አስተሳሰብ መመራት ጠቃሚና አስደሳች ነው!
በአምላክህ በይሖዋ ፊት ውድ ነህ!
18 ዕድሜያችን እየገፋ ቢሄድም ይሖዋ ሊጠቀምብን እንደሚችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 92:12-15) ያን ያህል ችሎታ እንደሌለን ወይም የምናከናውነው ሥራ በጣም ውስን እንደሆነ ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ በእሱ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ኢየሱስ አስተምሮናል። (ሉቃስ 21:2-4) ስለዚህ ማከናወን በምትችለው ነገር ላይ ትኩረት አድርግ። ለምሳሌ ስለ ይሖዋ ለሰዎች መናገር፣ ለወንድሞችህ መጸለይ እንዲሁም በታማኝነት እንዲጸኑ ሌሎችን ማበረታታት ትችላለህ። ይሖዋ የሥራ አጋሩ አድርጎ የሚመለከትህ ብዙ ነገር ማከናወን ስለቻልክ ሳይሆን በደስታ ስለምትታዘዘው ነው።—1 ቆሮ. 3:5-9
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
18 ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋ ጥበብ አቻ የማይገኝለት መሆኑን ሲገልጽ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!” (ሮም 11:33) ጳውሎስ “እንዴት” የሚለውን ቃል በመጠቀም ለይሖዋ ጥበብ ያለውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጿል። “ጥልቅ” የሚለውን ቃል መጠቀሙም በአእምሯችን የሚፈጥረው ምስል አለ። ስለ ይሖዋ ጥበብ ስናሰላስል መጨረሻው የማይታይን ገደል ቁልቁል የመመልከት ያህል ጥልቅና ሰፊ ሊሆንብን ይችላል። በዝርዝር ልንገልጸው ቀርቶ ልንገምተው እንኳ አንችልም። (መዝሙር 92:5) ይህ ራሳችንን በትሕትና ዝቅ እንድናደርግ አይገፋፋንም?
ከጥቅምት 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 96–99
‘ምሥራቹን አውጁ’!
የመንግሥቱ ምሥራች ምንድን ነው?
ክርስቲያኖች፣ ስለ አምላክ መንግሥት በመናገር ማለትም ይህ መንግሥት ወደፊት ምድርን በጽድቅ የሚያስተዳድር ዓለም አቀፋዊ አገዛዝ እንደሆነ ለሌሎች በመግለጽ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ መስበክ አለባቸው። ሆኖም “ምሥራች” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላም መንገድ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ‘ስለ ማዳን የሚገልጸው ምሥራች’ (መዝሙር 96:2 NW)፣ ‘የአምላክ ምሥራች’ (ሮም 15:16) እና “ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸው ምሥራች” የሚሉ አገላለጾችን እናገኛለን።—ማርቆስ 1:1
በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል ኢየሱስ የተናገረውና ደቀ መዛሙርቱ የጻፉት እውነት በሙሉ በምሥራቹ ውስጥ ይካተታል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) በመሆኑም የእውነተኛ ክርስቲያኖች ሥራ ስለ መንግሥቱ ለሌሎች በመናገር ብቻ መወሰን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ መጣርም ይኖርባቸዋል።
በፍርድ ቀን ምን ነገሮች ይከናወናሉ?
በቀኝ በኩል ካለው ሥዕል መመልከት እንደሚቻለው ብዙ ሰዎች፣ በፍርድ ቀን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ነፍሳት በአምላክ ዙፋን ፊት ቀርበው ከዚያ ቀደም በሠሩት ነገር መሠረት እንደሚፈረድባቸው ያስባሉ፤ በዚህ ወቅት አንዳንዶች በሰማይ ሕይወት እንደሚያገኙ ሌሎች ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደሚሠቃዩ ያምናሉ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ የፍርድ ቀን የሚመጣው የፍትሕ መጓደልን ለማስወገድ እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 96:13) አምላክ ፈራጅ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች እንደገና ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል።—ኢሳይያስ 11:1-5ን እና የሐዋርያት ሥራ 17:31ን አንብብ።
ለሺህ ዓመትና ከዚያም በኋላ የሚዘልቅ ሰላም!
18 የሰው ልጆች በሰይጣን ተጽዕኖ በመሸነፍ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ሲያምፁ ግን ይህ ቤተሰባዊ አንድነት ተናጋ። ይሁንና ከ1914 ጀምሮ መሲሐዊው መንግሥት ይህንን አንድነትና ኅብረት እንደገና ለመመለስ ደረጃ በደረጃ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። (ኤፌ. 1:9, 10) በአሁኑ ጊዜ ‘የማይታዩት’ አስደናቂ ነገሮች በሺህ ዓመቱ የግዛት ዘመን እውን ይሆናሉ። ከዚያም የክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት “ፍጻሜ” ይሆናል። ከዚያስ በኋላ ምን ይሆናል? ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የተሰጠው ቢሆንም ለሥልጣን የሚጓጓ አይደለም። የይሖዋን ቦታ የመንጠቅ ፍላጎት የለውም። ከዚህ ይልቅ በትሕትና “መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ” ያስረክባል። ኢየሱስ ያለውን ልዩ ቦታና ሥልጣን ‘አምላክን ለማክበር’ ይጠቀምበታል።—ማቴ. 28:18፤ ፊልጵ. 2:9-11
19 በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ የመንግሥቱ ምድራዊ ተገዥዎች ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የይሖዋን ሉዓላዊነት በፈቃደኝነትና በትሕትና ይቀበላሉ። እነዚህ ሰዎች የመጨረሻውን ፈተና በተሳካ ሁኔታ በማለፍ እንዲህ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያሉ። (ራእይ 20:7-10) ከዚያ በኋላ የሚያምፅ ማንኛውም ፍጡር፣ የሰው ልጅም ይሁን መንፈሳዊ አካል ለዘላለም ይወገዳል። ይህ ወቅት እንዴት የሚያስደስት ይሆን? የአጽናፈ ዓለሙ ቤተሰብ በሙሉ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” የሚሆነውን ይሖዋን በደስታ ያወድሳል።—መዝሙር 99:1-3ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 994
መዝሙር
“አዲስ መዝሙር” የሚለው አገላለጽ በመዝሙር መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ኢሳይያስና ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፏቸው መጻሕፍት ላይም ይገኛል። (መዝ 33:3፤ 40:3፤ 96:1፤ 98:1፤ 144:9፤ 149:1፤ ኢሳ 42:10፤ ራእይ 5:9፤ 14:3) “አዲስ መዝሙር” የሚለው አገላለጽ የሚገኝባቸውን የአብዛኞቹን ጥቅሶች አውድ ስንመረምር እንዲህ ያለው መዝሙር የሚዘመረው ይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ከሚጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ አዲስ ክንውን ሲኖር እንደሆነ እንገነዘባለን። መዝሙር 96:10 “ይሖዋ ነገሠ!” የሚል አስደሳች መግለጫ ይዟል። ይህ “አዲስ መዝሙር” ይሖዋ ንግሥናውን ከሚጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ስለተከናወነው አዲስ ክንውን እንዲሁም ይህ ክንውን በሰማይና በምድር ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ የሚገልጽ ይመስላል።—መዝ 96:11-13፤ 98:9፤ ኢሳ 42:10, 13
ከጥቅምት 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 100–102
ለይሖዋ ታማኝ ፍቅር ምላሽ ስጡ
ለጥምቀት ዝግጁ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
18 ሊኖሩህ ከሚችሉት ባሕርያት ሁሉ እጅግ የላቀው ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ነው። (ምሳሌ 3:3-6ን አንብብ።) ለአምላክ ያለህ ጥልቅ ፍቅር በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በተሳካ መንገድ እንድትወጣ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስላለው ታማኝ ፍቅር በተደጋጋሚ ይናገራል። ታማኝ ፍቅር ከሚወዱት አካል ጋር እስከ መጨረሻው መጣበቅን የሚጠይቅ ጠንካራ ባሕርይ ነው። (መዝ. 100:5) የተፈጠርከው በአምላክ መልክ ነው። (ዘፍ. 1:26) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማንጸባረቅ የምትችለው እንዴት ነው?
19 በቅድሚያ አመስጋኝ ልትሆን ይገባል። (1 ተሰ. 5:18) በየዕለቱ ‘ይሖዋ ፍቅር ያሳየኝ እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከዚያም ይሖዋ ያደረገልህን ነገር ለይተህ በመጥቀስ በጸሎትህ ላይ እሱን ማመስገንህን አትርሳ። የይሖዋን የፍቅር መግለጫዎች ለአንተ በግለሰብ ደረጃ እንደተደረጉልህ አድርገህ ተመልከታቸው፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ይሖዋ እንዲህ እንዳደረገለት ተገንዝቧል። (ገላትያ 2:20ን አንብብ።) ከዚያም ‘እኔስ በምላሹ ለይሖዋ ፍቅሬን ማሳየት እፈልጋለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ፈተናዎችን እንድትቋቋምና ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ እንድትወጣ ይረዳሃል። መንፈሳዊ ልማዶችህን ይዘህ በመቀጠል ለአባትህ ያለህን ፍቅር በየዕለቱ እንድታሳይ ይገፋፋሃል።
“የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ!”
10 ልንርቃቸው ከሚገቡ አደጋዎች መካከል ማሽኮርመም፣ ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት እንዲሁም ጎጂ ንግግር ይገኙበታል፤ ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን መዝናኛዎች፣ የብልግና ምስሎችንና የመሳሰሉትን ማየትም በዚህ ውስጥ ይካተታል። (መዝ. 101:3) ጠላታችን ዲያብሎስ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች በንቃት ይከታተላል። (1 ጴጥ. 5:8) ንቁ ካልሆንን ሰይጣን በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ የምቀኝነት፣ የውሸት፣ የስግብግብነት፣ የጥላቻ፣ የኩራትና የምሬት ዘር ሊዘራ ይችላል። (ገላ. 5:19-21) መጀመሪያ ላይ እነዚህ ስሜቶች ያን ያህል አደገኛ እንዳልሆኑ ሊሰማን ይችላል። ከሥራቸው ነቅለን ለመጣል አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰድን ግን እንደ መርዛማ ተክል ማደጋቸውን ሊቀጥሉና ችግር ላይ ሊጥሉን ይችላሉ።—ያዕ. 1:14, 15
የይሖዋን ግልጽ ማስጠንቀቂያዎች ሰምተህ እርምጃ ትወስዳለህ?
7 ከሐሰተኛ አስተማሪዎች መራቅ ሲባል ምን ማለት ነው? በቤታችን አንቀበላቸውም ወይም ሰላም አንላቸውም። ከዚህም ሌላ ጽሑፎቻቸውን አናነብም፣ እነሱ የሚቀርቡባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አንመለከትም፣ ድረ ገጻቸውን አንቃኝም ወይም በእነሱ ድረ ገጽ (ብሎግ) ላይ አስተያየታችንን አናሰፍርም። እንዲህ ያለ ጠንካራ አቋም የምንወስደው ለምንድን ነው? ፍቅር ስላለን ነው። “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ስለምንወድ እውነት ከሆነው ቃሉ ጋር የሚጋጩ የተጣመሙ ትምህርቶችን ለመስማት ፈቃደኞች አንሆንም። (መዝ. 31:5፤ ዮሐ. 17:17) በተጨማሪም አስደናቂ እውነቶችን ያስተማረንን የይሖዋን ድርጅት እንወደዋለን፤ የይሖዋ ድርጅት ካስተማረን እውነቶች መካከል የይሖዋ ስምና ትርጉሙ፣ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ፣ ሙታን ያሉበት ሁኔታ እንዲሁም የትንሣኤ ተስፋ ይገኙበታል። እነዚህንና ሌሎች ውድ እውነቶችን መጀመሪያ ባወቅህበት ጊዜ ምን ተሰምቶህ እንደነበር ታስታውሳለህ? ታዲያ የይሖዋን ድርጅት የሚያጥላላ ነገር የሚናገር ሰው እነዚህን እውነቶች እንድታውቅ በረዳህ ድርጅት ላይ ቅሬታ እንዲያድርብህ እንዲያደርግ ለምን ትፈቅዳለህ?—ዮሐ. 6:66-69
8 ሐሰተኛ አስተማሪዎች ምንም አሉ ምን እኛ እነሱን አንከተልም! እንደነዚህ ወዳሉ የደረቁ የውኃ ጉድጓዶች በመሄድ የምንታለልበት ምን ምክንያት አለ? ይህን ብናደርግ የጠበቅነው ሳይሆን በመቅረቱ ከማዘን ሌላ ምንም የምናተርፈው ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኞች ሆነን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ የይሖዋ ድርጅት በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ንጹሕና መንፈስን የሚያድስ የእውነት ውኃ አማካኝነት ለረጅም ጊዜ ጥማችንን ሲያረካልን ቆይቷል።—ኢሳ. 55:1-3፤ ማቴ. 24:45-47
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 596
ሻላ
ሻላ ብዙውን ጊዜ ምግብ በልቶ ከጠገበ በኋላ ገለልተኛ ወደሆነ አካባቢ በርሮ ይሄድና አንገቱን ትከሻው ውስጥ በመቅበር በአሳዛኝ አኳኋን ይቆማል፤ ምንም እንቅስቃሴ ስለማያደርግ ከሩቅ ሲታይ ነጭ ድንጋይ ሊመስል ይችላል። ይህ ወፍ በዚህ መልኩ ለሰዓታት ይቆማል፤ በመሆኑም መዝሙራዊው ያለበትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመግለጽ “የምድረ በዳ ሻላ መሰልኩ” በማለት ያለምንም እንቅስቃሴ በአሳዛኝ አኳኋን ከሚቆመው ሻላ ጋር ራሱን ማመሳሰሉ ተገቢ ነው። (መዝ 102:6) እዚህ ላይ “ምድረ በዳ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በረሃን ላይሆን ይችላል፤ ከዚህ ይልቅ ሰው የማይኖርበትን ቦታ ምናልባትም ረግረጋማ አካባቢን ሊያመለክት ይችላል። አሁንም በአንዳንድ ወቅቶች በሰሜናዊ ዮርዳኖስ ሸለቆ ያሉ አንዳንድ ረግረጋማ አካባቢዎች የሻላ መኖሪያዎች ናቸው። እስራኤል ውስጥ ሦስት የሻላ ዝርያዎች ይገኛሉ። በብዛት የሚገኘው የምሥራቁ ነጭ ሻላ (Pelecanus onocrotalus) ነው፤ የድልማጥያ ሻላ (Pelecanus crispus) እና ባለሮዝ ጀርባው ሻላ (Pelecanus rufescens) የነጩን ሻላ ያህል በብዛት አይገኙም።
ሻላዎች በሰዎች በማይረበሹበት ያልለማ አካባቢ መሆን ይመርጣሉ። በዚያ ጎጆ ሠርተው ጫጩቶቻቸውን ይፈለፍላሉ፤ እንዲሁም ዓሣ ከያዙ በኋላ በዚያ ያርፋሉ። ሻላዎች ገለልተኛና ባድማ የሆኑ ቦታዎችን ስለሚመርጡ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ባድማ መሆንን ለማመልከት እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። ኢሳይያስ ስለ መጪው የኤዶም ጥፋት ሲናገር ሻላ ምድሪቱን እንደሚወርሳት ገልጿል። (ኢሳ 34:11) ሶፎንያስ፣ ሻላ በነነዌ የፈራረሱ ዓምዶች መካከል እንደሚያድር ትንቢት ተናግሯል፤ ይህም ሙሉ በሙሉ እንደምትጠፋና ሰው አልባ እንደምትሆን ያመለክታል።—ሶፎ 2:13, 14
ከጥቅምት 28–ኅዳር 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 103–104
“አፈር መሆናችንን ያስታውሳል”
ይሖዋን ምሰሉ—ምክንያታዊ ሁኑ
5 ይሖዋ ምክንያታዊ እንዲሆን የሚያነሳሳው ትሕትናውና ርኅራኄው ነው። ለምሳሌ፣ ክፉ የሆኑትን የሰዶም ነዋሪዎች ለማጥፋት በወሰነበት ወቅት ትሕትናው በግልጽ ታይቷል። ይሖዋ መላእክቱን ልኮ፣ ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ ለጻድቁ ሎጥ መመሪያ ሰጠው። ሎጥ ግን እዚያ መሄድ ፈራ። በመሆኑም ከቤተሰቡ ጋር ወደ ዞአር ለመሸሽ እንዲፈቀድለት ለመነ፤ ዞአር ይሖዋ ለጥፋት ካሰባቸው ከተሞች አንዷ ነበረች። ይሖዋ ሎጥን ‘አንዴ ብያለሁ፣ የተባልከውን አድርግ’ ማለት ይችል ነበር። ሆኖም ልመናውን ሰማው፤ ቀድሞ ያሰበው ባይሆንም ዞአርን ላለማጥፋት ወሰነ። (ዘፍ. 19:18-22) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሖዋ ለነነዌ ነዋሪዎች ርኅራኄ አሳይቷል። በከተማዋና ክፉ በሆኑት ነዋሪዎቿ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዲያውጅ ነቢዩ ዮናስን ላከው። ነዋሪዎቿ ንስሐ ሲገቡ ግን ይሖዋ አዘነላቸው፤ ከተማዋንም ሳያጠፋት ቀረ።—ዮናስ 3:1, 10፤ 4:10, 11
እንደ ሳምሶን በይሖዋ ታመኑ
16 ሳምሶን የሠራው ስህተት ከባድ መዘዝ ቢያስከትልበትም የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ መሞከሩን አላቆመም። እኛም በሠራነው ስህተት የተነሳ ወቀሳ ቢሰጠን ወይም ያለንን መብት ብናጣም እንኳ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። ይሖዋ ተስፋ እንደማይቆርጥብን ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 103:8-10) እንደ ሳምሶን ሁሉ እኛም ስህተት ብንሠራም እንኳ ይሖዋ ሊጠቀምብን ይችላል።
17 ማይክል የተባለ ወጣት ወንድም ያጋጠመውን እንመልከት። የጉባኤ አገልጋይና የዘወትር አቅኚ በመሆኑ በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ይካፈል ነበር። የሚያሳዝነው ግን ስህተት በመሥራቱ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን መብቶች አጣ። እንዲህ ብሏል፦ “እስከዚህ ወቅት ድረስ ሕይወቴ በይሖዋ አገልግሎት የተሞላ ነበር። አሁን ግን በይሖዋ አገልግሎት ምንም ነገር ማድረግ እንደማልችል ተሰማኝ። ይሖዋ ትቶኛል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ ሆኖም ከእሱ ጋር ያለኝ ዝምድና እንደ በፊቱ መሆን መቻሉን ወይም እንደ ቀድሞው ጉባኤውን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል መቻሌን ተጠራጥሬ ነበር።”
18 ደስ የሚለው፣ ማይክል ተስፋ አልቆረጠም። እንዲህ ብሏል፦ “አዘውትሬ ልቤን በጸሎት ለይሖዋ በማፍሰስ፣ በማጥናትና በማሰላሰል ከእሱ ጋር ያለኝን ዝምድና ለማደስ ጥረት አደረግኩ።” ውሎ አድሮ ማይክል በጉባኤ ውስጥ የነበሩትን መብቶች መልሶ አገኘ። አሁን የጉባኤ ሽማግሌና የዘወትር አቅኚ ሆኖ እያገለገለ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በተለይ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ያገኘሁት ድጋፍና ማበረታቻ ይሖዋ አሁንም እንደሚወደኝ አስገንዝቦኛል። ንጹሕ ሕሊና ኖሮኝ ጉባኤ ውስጥ በድጋሚ ማገልገል ችያለሁ። ያጋጠመኝ ነገር፣ ይሖዋ ማንኛውም ሰው ከልቡ ንስሐ እስከገባ ድረስ ይቅር እንደሚለው አስተምሮኛል።” እኛም ስህተት ብንሠራም እንኳ አካሄዳችንን ለማስተካከል የቻልነውን ሁሉ እስካደረግንና በይሖዋ መታመናችንን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ በእኛ መጠቀሙን እንደሚቀጥልና እንደሚባርከን መተማመን እንችላለን።—መዝ. 86:5፤ ምሳሌ 28:13
መንፈሳዊ ግቦቻችሁ ላይ መድረስ ትችላላችሁ
2 አንድ መንፈሳዊ ግብ ላይ ለመድረስ ከተቸገርክ ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም። ቀላል ግብ ላይ መድረስ እንኳ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። አሁንም ግብህ ላይ ለመድረስ መፈለግህ በራሱ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተውና ለእሱ ምርጥህን መስጠት እንደምትፈልግ ያሳያል። ይሖዋ ጥረትህን በእጅጉ ያደንቃል። ደግሞም ከአቅምህ በላይ እንድትሰጠው አይጠብቅብህም። (መዝ. 103:14፤ ሚክ. 6:8) ስለዚህ ግብህ ምክንያታዊና ሁኔታህን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። ታዲያ እንዲህ ያለ ግብ ካወጣህ በኋላ እዚያ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ ትችላለህ? አንዳንድ ምክሮችን እስቲ እንመልከት።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’—ለመፍጠር የሚጠቀምበት ኃይል
18 ይሖዋ መፍጠር የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ምን ያስተምረናል? ስለፈጠራቸው ነገሮች ብዛትና ዓይነት ስናስብ በግርምት ፈዘን እንቀራለን። አንድ መዝሙራዊ “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! . . . ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። (መዝሙር 104:24) ይህ ሊታበል የማይችል ሐቅ ነው! የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በምድር ላይ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የሕያዋን ፍጥረታት ዝርያዎች እንዳሉ ደርሰውበታል። ይሁን እንጂ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዝርያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚገምቱም አሉ። አንድ የሥነ ጥበብ ሰው አእምሮው አዲስ የፈጠራ ሥራ ማመንጨት የሚሳነው ጊዜ አለ። በተቃራኒው ግን ይሖዋ አዲስ ነገር ለመፍጠር ያለው ችሎታ መቼም ቢሆን ሊነጥፍ አይችልም።