ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ኪሣራው ምን ያህል ነው?
አንድ የዴንማርክ ምሳሌ “በሽታ የሰው ሁሉ ጌታ ነው” ይላል። ሥር የሰደደ በሽታ የያዘው ማንኛውም ሰው ይህ “ጌታ” በእርግጥም በጣም ጨካኝ መሆኑን ሊመሠክር ይችላል! ይሁን እንጂ በሽታ በአብዛኛው ጌታ ከመሆን ይልቅ ተጋብዞ የሚመጣ እንግዳ መሆኑን ስታውቅ መገረምህ አይቀርም። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል፣ በሽተኞች በሕመምና በአካላዊ ጉዳት ምክንያት በሆስፒታል ከሚያሳልፉት ቀናት ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው ሊወገድ የሚችል ነው። ታዲያ ለበሽታ ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? ጤናማ ያልሆኑና አደገኛ የሆኑ የአኗኗር ልማዶች ናቸው። አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት።
ማጨስ። በ53 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኘው አይራ ኢምፊዚማ የሚባል በሽታ ይዞታል። ይህ ለአርባ ዓመት ያህል የቆየ ትንባሆ የማጨስ ልማዱ ያስከተለበት ጠንቅ ነው። ከበሽታው ፋታ ለማግኘት በብልቃጥ የታሸገ ኦክሲጅን መሳብ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ በየወሩ 2,800 ብር የሚያክል ወጪ ይጠይቅበታል። በ1994 በሆስፒታል ያሳለፈው የዘጠኝ ቀን ቆይታ 126,000 ብር አስወጥቶታል። አይራ በዚያ ዓመት ለሕክምና ያወጣው ወጪ 140,000 ብር ደርሷል። ይህ ሁሉ ችግር ቢደርስበትም ሳይውል ሳያድር ማጨስ ማቆም እንደሚኖርበት አይሰማውም። “ለማጨስ ያለኝ አምሮት ለማመን የሚያዳግት ነው” ይላል።
እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚደርሰው በአይራ ላይ ብቻ አይደለም። ማጨስ አደገኛ መሆኑ በሚገባ የታወቀ ቢሆንም በመላው ዓለም በእያንዳንዱ ቀን 15 ቢልዮን የሚደርሱ ሲጋራዎች ይለኮሳሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ከማጨስ ጋር በተያያዙ በሽታዎች የሚወጣው ወጪ 350 ቢልዮን ብር እንደሚደርስ ይገመታል። ይህ ማለት በ1993 ሽያጭ ላይ የዋለ እያንዳንዱ የሲጋራ ፓኮ 15 ብር የሚያክል የሕክምና ወጪ አስከትሎ ነበር ማለት ነው።
አንድ ሕፃን በሚወለድበት ጊዜ ከማጨስ ጋር ዝምድና ያላቸው የሕክምና ወጪዎች መከመር ይጀምራሉ። አንድ ምሳሌ ብቻ ብንጠቅስ በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ አንድ ጥናት አንደተረጋገጠው ከሚያጨሱ እናቶች የሚወለዱ ልጆች ከንፈራቸው ወይም ላንቃቸው የተሰነቀጠ ሆነው የመወለድ ዕድላቸው ከማያጨሱ እናቶች ከሚወለዱት በሁለት እጥፍ ይበልጣል። ይህ ችግር ሕፃኑ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ድረስ እስከ አራት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ሊጠይቅ ይችላል። በመላ ዕድሜው ለሕክምናና በዚህ በሽታ ምክንያት ከሕክምና ጋር ተዛምዶ ላላቸው ወጪዎች እስከ 700,000 ብር ሊጠይቅ ይችላል። ከዚህም በላይ የተጎዳ አካል ይዞ መወለድ የሚያስከትለው የስሜት ጉዳት በገንዘብ ሊተመን የሚችል አይደለም።
ብዙ አጫሾች የጡረታ ገንዘብ ማግኘት ወደሚችሉበት ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ስለሚሞቱ በማጨሳቸው ምክንያት የሚያወጡት የሕክምና ወጪ በዚህ ይካካሳል የሚሉ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን እንደሚለው “ይህ አባባል አከራካሪ ከመሆኑም በላይ በማጨስ ምክንያት አለ ዕድሜ በመሞት የሕክምና ወጪ ይቀንሳል ብሎ ማሰብ ሰብዓዊነት የጎደለው አስተሳሰብ እንደሆነ ብዙ ሰዎች ይስማማሉ።”
የአልኮል መጠጥ አለ አግባብ መውሰድ። የአልኮል መጠጥ አለ አግባብ መውሰድ የጉበት ሲሮሲስ፣ የልብ በሽታ፣ የጨጓራ በሽታ፣ የአንጀት መቁሰል፣ የቆሽት በሽታና ሌሎች የጤንነት ችግሮች ያስከትላል። ከዚህም በላይ እንደ ሳንባ ምች ላሉ የኢንፌክሽን በሽታዎች ሊያጋልጥ ይችላል። ዶክተር ስታንተን ፒል እንደሚሉት በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየዓመቱ “በመጠጥ ምክንያት የጤና ችግር የገጠማቸውን ሰዎች ለማከም 70 ቢልዮን ብር ይወጣል።”
ብዙ ጊዜ አልኮል ገና በማህጸን ውስጥ ባለ ጽንስ ላይ ጉዳት ያስከትላል። በየዓመቱ በዩናይትድ ስቴትስ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት አናቶቻቸው በእርግዝናቸው ወቅት መጠጥ በመጠጣታቸው ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ሆነው ይወለዳሉ። ከእነዚህ ሕፃናት መካከል አንዳንዶቹ ፊታል አልኮል ሲንድሮም (ኤፍ ኤ ኤስ) የተባለ የጤንነት ቀውስ ይዘው ስለሚወለዱ አካላዊም ሆነ አእምሮአዊ እክል ያስከትልባቸዋል። ኤፍ ኤ ኤስ ላለበት አንድ ሕፃን በመላ ዕድሜው የሚወጣው የሕክምና ወጪ 9.8 ሚልዮን ብር እንደሚደርስ ይገመታል።
አልኮል ስሜት የመቆጣጠር ችሎታን ስለሚቀንስ ከልክ በላይ መጠጣት ብዙ ጊዜ ለአምባጓሮ ያነሳሳል። ይህ ደግሞ ሕክምና የሚጠይቅ አካላዊ ጉዳት ያስከትላል። በተጨማሪም ሰክረው መኪና የሚያሽከረክሩ ሰዎች ይህ ነው የማይባል አደጋ ያስከትላሉ። እናትዋ ሰክሮ ከሚያሽከረክር ሰው ጋር ከተጋጨች በኋላ፣ ከኋላ ወንበር ውስጥ ተፈልቅቃ የወጣችው የስምንት ዓመቷ ሊንድሴ ያጋጠማትን ሁኔታ እንውሰድ። ሊንድሴ ሰባት ሳምንት ያህል በሆስፒታል ቆይታ በርካታ ቀዶ ሕክምናዎች ተደረጉላት። ለሕክምናዋ 2,100,000 ብር ወጥቷል። በሕይወት መትረፏ ራሱ ለርሷ ትልቅ ዕድል ነበር።
አደገኛ ዕፆችን መውሰድ። በአሜሪካ ዕፅ በመውሰድ ምክንያት የሚደርሰው ዓመታዊ ወጪ 469 ቢልዮን ብር እንደሚደርስ አንድ ተመራማሪ ገምተዋል። በኒው ዮርክ በሚገኘው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሱስና አለ አግባብ የሚወሰዱ ቅመሞች ማዕከል ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆሴፍ ኤ ካሊፋኖ ጁንየር ችግሩ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትልበትን ሌላ ገጽታ ጠቁመዋል። “የአእምሮ ችግር ኖሯቸው የሚወለዱ ሕፃናት ከአሥር ዓመት በፊት ብዙም ያልነበሩ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን በየቀኑ 14,000 ብር የሚከፈልባቸውን አዲስ የተወለዱ ሕፃናት የሚታከሙባቸው ክፍሎች አጣበዋል። . . . እያንዳንዱን ሕፃን ሙሉ ሰው እስከመሆን ለማድረስ የ7 ሚልዮን ብር ወጪ ሊጠይቅ ይችላል።” በተጨማሪም ካሊፋኖ እንደገለጹት “በ1994 አደገኛ ዕፆችን ከመውሰድ ጋር ግንኙነት ባላቸው ምክንያቶች ሆስፒታል ተኝተው ለታከሙ በሽተኞች መንግሥት ካወጣው 21 ቢልዮን ብር ውስጥ አብዛኛው የወጣው ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶች ቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል ለማድረግና ዕፅ መውሰዳቸውን ለማቆም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው።”
ይህ አጉል ልማድ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያስከትለው በገንዘብ ሊተመን የማይችል ሥቃይ የሁኔታውን አሳዛኝነት በጣም ከፍ ያደርገዋል። አደገኛ ዕፆችን በመውሰድ ምክንያት ቤተሰቦች ከሚደርሱባቸው ችግሮች መካከል የትዳር መፍረስ፣ ልጆችን በቸልታ መተው፣ የገንዘብ ውድመት ይገኛሉ።
ዘማዊነት። በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ 12 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በአባለ ዘር በሽታ ይለከፋሉ። ይህ አሃዝ ዩናይትድ ስቴትስን ካደጉ አገሮች በሙሉ በአንደኛነት ቦታ ላይ ያስቀምጣታል። የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሐይጂንና የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዴቪድ ሴሌንታኖ ይህንን ሁኔታ “ብሔራዊ ውርደት” ብለውታል። እነዚህ በሽታዎች፣ ኤድስን ሳይጨምር፣ የሚያስከትሉት ቀጥተኛ ወጪ በየዓመቱ 70 ቢልዮን ብር ይደርሳል። በተለይ ወጣቶች ለዚህ አደጋ የተጋለጡ ናቸው። ይህም የሚያስደንቅ አይደለም! አንድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው 12ኛ ክፍል ከደረሱ ወጣቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሩካቤ ሥጋ ፈጽመው የሚያውቁ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ አራት የወሲብ ጓደኞች የነበሯቸው ናቸው።
ኤድስ ራሱ በጤና እንክብካቤ ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል። በ1996 መጀመሪያ ላይ ከሁሉ የተሻለ ሆኖ የተገኘው ፕሮቲየስ ኢንሂቢተርስ የተባሉ መድኃኒቶችን ከሌሎች የቆዩ መድኃኒቶች ጋር በማቀናጀት የሚሰጥ ሕክምና ለአንድ ሰው በዓመት ከ84,000 እስከ 126,000 ብር የሚጠይቅ ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህ ወጪ ኤድስ ከሚያስከትለው ስውር ወጪ አነስተኛው ክፍል ነው። በሽተኛው ፍሬያማ ሥራ ለመሥራት ባለመቻሉና በሽተኛውን ለማስታመም ከሥራ ወይም ከትምህርት ቤት በመቅረት ምክንያት የሚደርሰው ኪሣራ ከፍተኛ ነው። በ2000 ዓመት ላይ ኤች አይ ቪና ኤድስ በመላው ዓለም ከ2,492 ቢልዮን እስከ 3,598 ቢልዮን ብር እንደሚያሟጥጥ ይገመታል። የአውስትራሊያን ወይም የሕንድን ኢኮኖሚ በሙሉ ጥርግርግ አድርጎ የማጥፋት ያህል ይሆናል።
ጠበኝነት። ጆይሰሊን ኤልደርስ የዩናይትድ ስቴትስ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ በ1992 ጠበኝነት ያስከተለው የሕክምና ወጪ 94.5 ቢልዮን ብር እንደነበር ሪፖርት አድርገዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሆኑት ቢል ክሊንተን “አሜሪካ ለጤና የምታወጣው ወጪ ይህን ያህል ከፍተኛ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ የድንገተኛ አደጋ ክፍሎቻችን በጩቤ በተተለተሉና በጥይት በተመቱ ሰዎች የተሞሉ መሆናቸው ነው” ብለዋል። ዘ ጆርናል ኦቭ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን በዩናይትድ ስቴትስ ጠበኝነት “ዋነኛ የጤና ችግር ሆኗል” ያለው ያለበቂ ምክንያት አልነበረም። ሪፖርቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ሰፊ ተቀባይነት ባገኘው ግንዛቤ መሠረት ጠበኝነት የሚያስከትለው ውጤት በሽታ ተብሎ ሊጠራ የማይችል ቢሆንም በግለሰብና በሕዝብ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጫና ግን ከብዙ አካላዊ ሕመሞች የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም።”
በኮሎራዶ የሚገኙ 40 ሆስፒታሎች ያዘጋጁት ሪፖርት በ1993 የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ለእያንዳንዱ የጠብ ድርጊት ተጎጂ የወጣው ወጪ 67,000 ብር እንደደረሰ ያመለክታል። ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ከታከሙት መካከል ከግማሽ የሚበልጡት የሕክምና ኢንሹራንስ የሌላቸው ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ሕክምናቸው የጠየቀውን ወጪ ለመክፈል የማይችሉ ወይም ፈቃደኛ ያልሆኑ ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች ቀረጥ፣ የኢንሹራንስ አረቦንና የሆስፒታል ወጪ ከፍ እንዲል ያስገድዳሉ። የኮሎራዶ ሆስፒታሎች ማህበር “ሁላችንም እንከፍላለን” በማለት ሪፖርቱን አጠናቋል።
የባሕርይ ለውጥ ማድረግ
ከሰብዓዊ ጥረቶች አንጻር ከታየ ጤናማ ያልሆኑ የአኗኗር ልማዶችን ለመቀየር የመቻሉ ተስፋ በጣም የጨለመ ነው። የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ያቀረበው አንድ ሪፖርት “አሜሪካ የኤደን ገነት አይደለችም፤ ጤንነት የሚጎዱ ነገሮችን አለ አግባብ መውሰድን ጨርሰን ለማስወገድ አንችልም” ብሏል። “ይሁን እንጂ እነዚህን ልማዶች ባስወገድን መጠን ይበልጥ ጤናማ የሆኑ ልጆች እናገኛለን፣ ጠበኝነትና ወንጀል ይቀንሳል፣ ቀረጥ ይቀንሳል፣ ለጤና የምናወጣው ወጪ ይቀንሳል፣ የምናገኘው ትርፍ ከፍ ይላል፣ የተሻለ ትምህርት የሚያገኙ ተማሪዎች ይኖሩናል፣ የኤድስ በሽተኞች ቁጥር ይቀንሳል።”
እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ መሣሪያ ሊኖር እንደማይችል የይሖዋ ምሥክሮች ተገንዝበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ተራ መጽሐፍ አይደለም። የሰው ልጆች ፈጣሪ በሆነው በይሖዋ አምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ‘የሚረባንን ነገር የሚያስተምረን፣ በምንሄድበትም መንገድ የሚመራን’ እርሱ ነው። (ኢሳይያስ 48:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለጤና የሚጠቅሙ ናቸው። ምክሩን የሚከተሉ ሰዎችም ከፍተኛ በረከት ያጭዳሉ።
ለምሳሌ ያህል ከባድ አጫሽ የነበረችውን አስቴርን እንውሰድ።a ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመረች በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ታስተምራት የነበረችው ሴት በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በመጎብኘት አንድ ሙሉ ቀን እንድታሳልፍ ጋበዘቻት። በመጀመሪያ ላይ አስቴር ግብዣውን ለመቀበል አመነታች። የይሖዋ ምሥክሮች እንደማያጨሱ ስለምታውቅ አንድ ሙሉ ቀን እንዴት አብራቸው ልትውል እንደምትችል አሰበች። ስለዚህ አስቴር ማጨስ ካማራት ወደ መፀዳጃ ቤት ገባ ብላ የምታጨሰው አንድ ሲጋራ ቦርሳዋ ውስጥ አስቀመጠች። እንዳሰበችውም አንዱን ጉብኝት ከጨረሰች በኋላ ወደ መፀዳጃ ቤት ገባ አለችና ሲጋራዋን ለማጨስ አወጣች። በዚህ ጊዜ ግን አንድ ነገር አስተዋለች። ክፍሉ በጣም ንጹሕና አየሩም ንጹሕ ነበር። “ሲጋራ በማጨስ ያን የመሰለ ንጹሕ ቦታ ላቆሽሽ አልፈለግኩም” በማለት አስቴር ታስታውሳለች። “ስለዚህም ወደ ሽንት ቤቱ ጨመርኩና ውኃ ለቀቅኩበት። ከዚያ ወዲህ ሲጋራ የሚባል ነገር ነክቼ አላውቅም!
በመላው ዓለም በሚልዮን የሚቆጠሩ እንደ አስቴር ያሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖርን እየተማሩ ነው። ይህን በማድረጋቸውም ራሳቸውን ከመጥቀም አልፈው ለሚኖሩባቸው ማኅበረሰቦች ውድ ሀብቶች ሆነዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለፈጣሪያቸው ለይሖዋ አምላክ ታላቅ ክብር አምጥተዋል።—ከምሳሌ 27:11 ጋር አወዳድር።
“የኤደን ገነት” በሰዎች ጥረት ሊገኝ የማይችል ቢሆንም አምላክ እንደሚያመጣው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:13 “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ይላል። (ከኢሳይያስ 51:3 ጋር አወዳድር።) በዚያች አዲስ ምድር የሰው ልጅ አምላክ መጀመሪያውኑ ባወጣው ዓላማ መሠረት ፍጹም የሆነ ጤንነት አግኝቶ ስለሚኖር ጤና አጠባበቅ አሳሳቢ ነገር አይሆንም። (ኢሳይያስ 33:24) አምላክ ስለ ሰጣቸው ተስፋዎች ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ደስተኞች ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እውነተኛ ስሟ አይደለም
[ምንጭ]
© 1985 P. F. Bentley/Black Star