የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ለ25 ዓመታት መነኩሴ የነበረች ሴት በመጨረሻ እውነትን አወቀች
ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይሖዋን በመንፈሳዊ ቤተመቅደሱ ለማምለክ እንደሚመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ቀደም ሲል ተንብዮ ነበር። (ራዕይ 7:9) ይህም ትንቢት በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ መሆኑን ስንመለከት በጣም ደስ ይለናል። ከአምላክ እውነት ባገኙት እርዳታ ብዙዎች የሐሰት ሃይማኖትን ሰንሰለት በመበጠስ ላይ ናቸው። የሚከተሉት ተሞክሮዎች ለዚህ ማስረጃ ይሆኑናል፦
◻ በኢጣልያ አገር በሮማ የምትኖር ሴት እንዲህ በማለት ታሪኳን ትተርካለች፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ አምላክን በሙሉ ልቤ የማገልገል ፍላጎት ስለነበረኝ ትልቁ ምኞቴ ድንግል ሆኖ ማገልገል ነበር። ታህሣስ 8 ቀን 1960 32 ዓመት ሲሞላኝ በታዛዥነት፣ በድህነትና በንጽሕና የመኖር ቃለ መሐላ ስፈጽም ይህ ምኞቴ ተሳካ። የተሰጠኝ ሥራ 30 ለሚያክሉ እናት አባት የሌላቸው፣ ወላጆቻቸው የካዱአቸውና ወላጆቻቸው የታሰሩባቸው ልጆች ቀን ከሌሊት እንክብካቤ ማድረግ ነበር። ከሥራዬ እርካታ አገኝ ነበር።
“በዚህ ዓይነት ለአሥር ዓመታት ከሰራሁ በኋላ በተቋሙ ውስጥ ትልቅ ግጭት በመፈጠሩ እምነቴ ተናጋ። የሚመራን አምላክ ከሆነ በራሱ ቤት ውስጥ ይህን የመሰለ ብጥብጥና መለያየት እንዲኖር እንዴት ይፈቅዳል? ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።”
ይህች ድንግል በፈረንሣይ አገር የምትኖር የይሖዋ ምስክር የሆነች እህት ነበረቻት። ይህች እህትዋ በደብዳቤ ትመሰክርላትና የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ትልክላታለች። መነኩሲቷ ታሪኳን በመቀጠል እንዲህ ትላለች፣ “ከ23 ዓመት ወዲህ ከአምላክ ቃል ጋር ስገናኝ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር።” ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረችው በዚህ ጊዜ ነበር። “በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ ይሖዋ አምላክንና እርሱ የሚፈልጋቸውን ነገሮች እንዲሁም አስደናቂ የሆኑትን ባሕርያቱን አወቅኩ። በሥዕልና ምስል መጠቀምን እንደሚጠላ ሳውቅ በጣም አዘንኩ። ምክንያቱም የነበርኩበት ተቋም የተለያየ መልክና መጠን ያላቸው ምስሎች የሞሉበት ነበር። ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግኩ በዚያ ቦታ መቆየት እንደማልችል አወቅኩ። ለ25 ዓመታት ከሙሉ ልቤ በድንግልና ካገለገልኩ በኋላ በመጨረሻ እውነቱን አገኘሁ። በዚህም ምክንያት ጥቅምት 1 ቀን 1985 ለመውጣት መወሰኔን አስታወቅኩ። ይህም የበላዮቼን በጣም አስደነገጣቸው።
“የሚወዱኝ ወንድሞቼና እህቶቼ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ረዱኝ። ነሐሴ 30 ቀን 1986 ይሖዋንና ድርጅቱን እያመሰገንኩ ተጠመቅኩ። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውንም መንገድ ጀመርኩ።”
ይሖዋ አንዲት ልጃገረድ አምላክን ለማገልገል ያላትን ፍላጎት ባረከላት
◻ በብራዚል አገር አንዲት የይሖዋ ምሥክር የሆነች አስተማሪ የፈተና ወረቀት ስታርም አንዲት የ14 ዓመት ተማሪ ስለ አምላክ ለማወቅ የምትፈልግ መሆኗን እንደጻፈች አስተዋለች። ከተማሪዋ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች። ልጅቱ በጥናቱ እየገፋች ስትሄድ ካቶሊኮች የሆኑ ቤተሰቦችዋ ጽሑፎችዋን ሁሉ ቀድደው እንዳታጠና ከለከሉአት። ወጣቷ ተማሪ በትምህርት ቤት የእረፍት ሰዓቶች ማጥናት ጀመረች። ቢሆንም ወዲያው ተደረሰባት። በዚህም ምክንያት ጥናቱ በደብዳቤ ብቻ መካሄድ ጀመረ። ቢሆንም ቤተሰቦችዋ ደብዳቤዎቹን አገኙና አቃጠሉአቸው። አባትዋ ቤተክርስቲያን ሄዳ እንድታስቀድስ ሊያስገድዳት ጀመረ። አብራው ቤተክርስቲያን ብትሄድም በቅዳሴው ጊዜ ይዛ የሄደችውን መጠበቂያ ግንብ በቤተክርስቲያኑ ጽሑፍ መሐል ደብቃ ታነብ ነበር። አንድ ቀን ከቤትዋ ተደብቃ ወጥታ ወደ መንግሥት አዳራሽ እስከሄደችበት ጊዜ ድረስ ሁኔታው በዚሁ ዓይነት ለስድስት ወራት ያህል ቀጠለ። አባትዋ ስብሰባ ይካሄድበት ወደነበረው የመንግሥት አዳራሽ ሄዶ ልጁን ቤት ስትመጣ እንደሚመታት እንዲነግሩአት ለወንድሞች ነገራቸው። ወንድሞች ሊያግባቡት ያደረጉት ሙከራ ሁሉ ሳይሳካ ቀረ።
በማግሥቱ በደስታ እየፈነደቀች ወንድሞችን ለማግኘት ሄደች። በአባትዋ ዱላ ምክንያት በሰውነትዋ ላይ የሚታየውን ሰንበር በሙሉ አሳየቻቸው። ታዲያ ደስ የተሰኘችው ለምን ነበር? አባትዋ ከመንግሥት አዳራሹ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ብዙ ሰዎችን የከተማውን ከንቲባ ጭምር ልጁ የይሖዋ ምስክር ብትሆን ስለምታገኘው ጥቅምና ጉዳት እንዲነግሩት ጠይቆ ነበር። ከንቲባው የይሖዋ ምስክሮች እምነት የሚጣልባቸው ጥሩ ሰዎች እንደሆኑ ነገሩት። ጨምረውም በጣም ጥሩ የሥነ ምግባር ደረጃ እንዳላቸውና ይህም ደረጃቸው ከጠቅላላው የወጣቶች ሥነ ምግባር ጋር ሲወዳደር በጣም ከፍተኛ ስለሆነ በዚህ ዓይነት ሥነ ምግባር የምትመራ ልጅ ብትኖረው በጣም ጥሩ እንደሚሆን ነገሩት። ቢሆንም ልጅቱ መገረፍዋ አልቀረም። ይሁን እንጂ አባትዋ የሚገርፋት ሳታስፈቅድ ከቤት ስለወጣች እንደሆነና ወደፊትም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትዋን ብታቆም ወይም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች መገኘትዋን ብትተው እንዲሁ እንደሚገርፋት ነገራት። አሁን ይህች ልጃገረድ ቀናተኛ አስፋፊ ሆናለች። ከቤተሰቦችዋም መካከል አንዳንዶቹ ለእውነት ፍላጎት ማሳየት ጀምረዋል።
በእውነትም ከዚህ ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉትን ወጣቶች ይባርካቸዋል።—መዝሙር 148:12, 13