በመከር ጊዜ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠሁ
ዊኒፍሬድ ሬሚ እንደተናገረችው
“መከሩ ብዙ ነው ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው።” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ቃላት የተናገረው እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለው የነበሩትን ሰዎች ተመልክቶ ስሜቱ ስለተነካና ስላዘነላቸው ነው። እኔም እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። ባለፉትም 40 ዓመታት ጌታ በመከሩ ሥራ እንድካፈል ላቀረበው ጥሪ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ሳደርግ ቆይቼአለሁ።—ማቴዎስ 9:36, 37
የተወለድኩት በምዕራብ አፍሪካ ሲሆን ቤተሰቦቼ ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩአቸው። ወላጆቻችን ሩኅሩሆች ቢሆኑም ጥብቅ ነበሩ። ሃይማኖተኞች ስለ ነበሩ በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን መሄድና የሰንበት ትምህርት መከታተል የማይቀሩ ነገሮች ነበሩ። መንፈሳዊ ነገሮችን እወድ ስለ ነበር ይህ ለኔ አስቸጋሪ ነገር አልነበረም። እንዲያውም በ12 ዓመቴ የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪ እንድሆን ተሹሜ ነበር።
ጋብቻና የኑሮ ውጣ ውረድ
በ1941 በ23 ዓመቴ የቅኝ ግዛት አስተዳደር ጽ/ቤት ሂሳብ ሹም የነበረውን ሊችፊልድ ሬሚን አገባሁ። በቁሳዊ ነገሮች የተደላደልን ብንሆንም አዳዲስ ነገሮችን ለማየትና ቁሳዊ ሀብት ለማከማቸት ያለን ፍላጎት በ1944 ወደ ላይቤሪያ እንድንሄድ አደረገን። በ1950 ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክሮች ሚሲዮናዊ የነበረውን ሆይል ኢርቪንን ሲያገኘው በባለቤቴ ሕይወት፣ በኋላም በኔ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ መጣ። ከሦስት ሳምንታት ጥናት በኋላ ባለቤቴ በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመረ።
ባለቤቴ ቤተ ክርስቲያን መሄዱን ሲያቆም በጣም ተበሳጨሁ። ጾም እንኳን የማይገድፍ አጥባቂ ፕሮቴስታንት ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ቦርሳውን በእጁ ይዞ ሊሰብክ ሲወጣ ሳየው በጣም ተናደድኩ። “ምን ሆነሃል? እንዳንተ ያለ የተከበረ ሰው ከነዚህ ሞኝ ሰዎች ጋር ሊሰብክ ይወጣል?” አልኩት። ይህን ሁሉ ስነግረው እርጋታና ጸጥታ አልተለየውም ነበር።
በሚቀጥለው ቀን ወንድም ኤርቪን ከሊንችፊልድ ጋር ለማጥናት እቤት መጣ። እንደተለመደው በጥናቱ ጊዜ ፈንጠር ብዬ በዝምታ ስመለከት ቆየሁ። ወንድም ኤርቪን መሃይም ነሽ? ብሎ የጠየቀኝ በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ምን? እኔ መሃይም? እንዴት ያለ ስድብ ነው! ቆይ፣ ምን ያህል የተማርኩ እንደሆንኩ አሳየዋለሁ! ይህን የሐሰት ትምህርት አጋልጣለሁ! አልኩ።
እውነትን ተቀበልኩ
ከዚህ ብዙም ሳይቆይ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን የሚለውን መጽሐፍ ሳሎን ጠረጴዛ ላይ ተመለከትኩ። ‘ምን ዓይነት የሞኝ ርዕስ ነው’ ብዬ አሰብኩ። ‘ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር እውነተኛ አይደለም እንዴ?’ አልኩ። መጽሐፉን ስመለካከተው ወዲያው ሌላ ቅር ያሰኘኝ ነገር አገኘሁ። ሰው ነፍስ የለውም፤ ራሱ ነፍስ ነው፤ ውሾችና ድመቶች ሳይቀሩ ነፍሳት ናቸው! ይላል። ይህም በጣም አናደደኝ። ‘ምን ዓይነት ጅል ትምህርት ነው!’ ብዬ አሰብኩ።
ባለቤቴ ወደ ቤት ሲመጣ በቁጣ አፋጠጥኩት። “እነዚህ አታላዮች ሰው ነፍስ የለውም ይላሉ። ሐሰተኛ ነቢያት ናቸው!” አልኩት። ባለቤቴ አልተጨቃጨቀም። ከዚህ ይልቅ “ዊኒ ሁሉም ነገር እኮ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ” ብሎ በእርጋታ መለሰልኝ። ቆይቶም ወንድም ኤርቪን እኛ ራሳችን ነፍስ እንደሆንንና ነፍስ ደግሞ ሟች እንደሆነች በትዕግስት ከራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያሳየኝ እጅግ ተገረምኩ። (ሕዝቅኤል 18:4) በይበልጥ የነካኝ ጥቅስ በዘፍጥረት 2:7 ላይ የሚገኘው፦ “ሰውም [አዳም] ሕያው ነፍስ ሆነ” የሚለው ነበር። አዓት
እንዴት ተሳስቼ ኖሯል! በቀሳውስት እንደ ተታለልኩ ስለተሰማኝ ከዚያ ቀን ጀምሮ ወደ ቤተ ክርስቲያን አልሄድኩም። በዚህ ምትክ በይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በመካከላቸው የሚታየው ፍቅር በጣም አስደነቀኝ። ይህ እውነተኛ ሃይማኖት መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ።
በኬፕ ፓልማስ በመከሩ የመሰብሰብ ሥራ መሳተፍ
ከሦስት ወራት በኋላ ባለቤቴ ከሚሠራበት ኩባንያ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ለመስረቅ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ግን አላደረገውም። ጓደኞቹ “ሬሚ፣ ድሀ እንደሆንህ ትሞታለህ” ብለው ተሳለቁበት።
ይሁን እንጂ በታማኝነቱ ምክንያት ዕድገት አገኘና አዲስ ቢሮ እንዲያቋቁም ወደ ኬፕ ፓልማስ ተላከ። በቅንዓት በመስበካችን ከሁለት ወራት በኋላ ለመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የሚገኙበት አንድ አነስተኛ ቡድን ለማግኘት ቻልን። በኋላም ሊችፊልድ ለአዲሱ ቢሮ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ለመግዛት ወደ ዋና ከተማው ወደ ሞንሮቭያ ሄዶ ስለ ነበር እዚያው ተጠመቀ። በኬፕ ፓልማስ ለእውነት ፍላጎት ላሳዩት ሰዎች እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችል እርዳታ እንዲደረግ ለማኅበሩ ጥያቄ አቀረበ።
ማኅበሩም ወንድምና እህት ፋውስትን ወደ ኬፕ ፓልማስ በመላክ ለጥያቄያችን ምላሽ ሰጠ። እህት ፋውስት ተወዳዳሪ የሌላት ረዳቴ ነበረች። እኔም በታኅሣስ 1951 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ። አሁን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ‘የዘላለምን ሕይወት ፍሬ’ ለመሰብሰብ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። (ዮሐንስ 4:35, 36) በ1952 በሚያዝያ ወር አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ።
ይሖዋም ድካሜን ወዲያው ባረከልኝና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አምስት ሰዎችን ራስን ወደ መወሰንና ወደ ጥምቀት ደረጃ እንዲደርሱ ረዳኋቸው። ከነሱም መካከል በጊዜው የላይቤሪያ ፕሬዚደንት የነበሩት የደብልዩ ቪ ኤስ ታብማን ያጎት ልጅ የነበረችው ሉዊሳ ማኪንቶሽ ትገኛለች። እሷም ተጠመቀችና የሙሉ ጊዜ አቅኚ በመሆን በ1984 እስከ ሞተችበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት አምላክን አገልግላለች። በተለያዩ አጋጣሚዎችም ለፕሬዚደንቱ መስክራላቸዋለች።
ወደ ታችኛው ቢዩካነን
በ1957 በክልል የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ወቅት ባለቤቴና እኔ ልዩ አቅኚዎች እንድንሆን ተጋበዝን። ከልባችን ከጸለይንና ከተወያየንበት በኋላ የሥራ ምድባችንን ለመቀበል ወሰንን። ሊችፊልድ በኬፕ ፓልማስ የነበረውን ሥጋዊ ሥራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ጥቂት ወራት ወሰደበት። ስለዚህ እኔ ቀደም ብዬ ከዚህ በፊት ተሠርቶ በማያውቀው በታችኛው ቢዩካነን የስብከቱን ሥራ ለመጀመር ሄድኩ።
እዚያም እንደ ደረስኩ የማክሊን ቤተሰብ ተቀበለኝ። በሚቀጥለው ቀን በባህሉ መሠረት የፔሌ ጎሳ ምክትል አለቃ ወደሆኑት ሰው ተወሰድኩ። አለቃውና ቤተሰቡ የሞቀ አቀባበል አደረጉልኝ። እኔም በቤቱ ውስጥ ለነበሩት ጥቂት ሰዎች መሰከርኩ። በዚያ ቀን ካነጋገርኳቸው ሰዎች ውስጥ ምክትል አለቃውንና ሚስቱን ጨምሮ ከስድስት የማያንሱ ሰዎች ምስክሮች ሆነዋል።
ከትንሽ ጊዜ በኋላ ከ20 ለሚበልጡ ተሰብሳቢዎች የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መምራት ጀመርኩ። በይሖዋ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መመካት ነበረብኝ። እርሱም በጎቹን ለመንከባከብ የሚያስፈልገኝን ጥንካሬና ችሎታ ሰጠኝ። ሲደክመኝ ወይም ብቃት እንዳነሰኝ ሆኖ ሲሰማኝ የጥንቶቹን ታማኞች፣ በተለይም ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ በድፍረት ያከናወኑትን እንደ ዲቦራና ሕልዳና ያሉትን ሴቶች አስታውሳለሁ።—መሳፍንት 4:4-7, 14-16፤ 2 ነገሥት 22:14-20
በታችኛው ቢዩካነን ለሦስት ወራት ያህል ከቆየሁ በኋላ በመጋቢት 1958 የክልል የበላይ ተመልካቹ ጆን ሻሩክ ለጉብኝት እንደሚመጣ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። ብዙ ሕዝብ ሊይዝ የሚችል አንድ ምድር ቤት ተከራየሁ። ከዚያም ወንድም ሻሩክን ለመገናኘት ወደ ላይኛው ቢዩካነን ሄድኩ። እሱ ግን አልመጣም። ለዓይን እስኪይዝ ድረስ ከጠበቅሁት በኋላ ደክሞኝ ወደ ታችኛው ቢዩካነን ተመለስኩ።
እኩለ ሌሊት አካባቢ ላይ በር ሲንኳኳ ሰማሁ። ስከፍት የክልል የበላይ ተመልካቹን ብቻ ሳይሆን ባለቤቱንም ተመለከትኩ። የእርሱ መምጣት ከወንድም ሻሩክ መምጣት ጋር መጋጠሙ በጣም አስደሰተኝ። ያለሁበትን ቤት እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? አንድ አዳኝ አግኝተው ኖሮ አንዲት ለሰዎች ስለ ይሖዋ የምትሰብክ ሴት ያውቅ እንደሆነ ጠየቁት። “አዎን” ብሎ መለሰና እኔ ወዳለሁበት ቦታ መራቸው። ወደ ታችኛው ቢዩካነን ከመጣሁ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ብርሃኔ ይህን ያህል ደምቆ በመታየቱ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ።—ማቴዎስ 5:14-16
በወንድም ሻሩክ ጉብኝት ጊዜ 40 የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች በመገኘታቸው በጣም ተደሰትን። ከጊዜ በኋላ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ተቋቋመና ቆንጆ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ቻልን። ይሁን እንጂ ሕይወታችን ምንም ዓይነት ችግር ያላጋጠመው አልነበረም። ለምሳሌ በ1963 በኮላኹን ሃይማኖታዊ ስደት ፈነዳ። ባለቤቴም ተያዘና ታሰረ። በጣም ተደብድቦ ስለነበረም ሆስፒታል ለመግባት ተገደደ።
ከሆስፒታል ከወጣ ብዙም ሳይቆይ በዚያው ዓመት በባንጋ ትልቅ ስብሰባ አደረግን። በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ወታደሮች ዙሪያችንን ከበቡና ለባንዲራ ሰላምታ እንድንሰጥ አዘዙን። እምቢ ስንላቸው ወታደሮቹ እጃችንን ወደላይ ከፍ አድርገን ፀሐይን በቀጥታ እንድንመለከት አስገደዱን። አንዳንዶቻችንንም በጠመንጃቸው ሠደፍ መቱን። ለአምላክ ያለኝን ፍጹም አቋም ለመጠበቅ እንዲረዳኝ “አትፍሯቸው!” የሚለውን የመንግሥቱን መዝሙር እዘምር ነበር። ከዚያ በኋላ ወታደሮቹ በጣም ቆሻሻ በሆነ እስር ቤት ወረወሩን። ከሦስት ቀናት በኋላ የውጭ አገር ዜጎች የሆኑት ተለቀቁ። ሊችፊልድ እና እኔ ካገር ተባርረን ወደ ሴራልዮን እንድንሄድ ተደረግን። የአገር ተወላጆች የሆኑት ምስክሮችም በማግስቱ ተለቀቁ።
ተጨማሪ መብቶችና ሽልማቶች
በደቡብ ሴራልዮን ከሚገኘው ከቦ ጉባኤ ጋር እንድንሠራ ተመደብን። ወደ ንያላ እስከተዛወርንበት ጊዜ ድረስ እዚያ ለስምንት ዓመት አገለገልን። ንያላ እያለን ባለቤቴ ተተኪ የክልል የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲሠራ በመሾሙ በዚህ አገልግሎቱ አብሬው የመሥራት መብት አግኝቼአለሁ። ከዚያም በ1970ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ከምሥራቅ ፍሪታውን ጉባኤ ጋር እንድንሠራ ተመደብን።
መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናኋቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ እውነትን ሲቀበሉ የመመልከትን በረከት አግኝቻለሁ። ከ60 የሚበልጡ መንፈሳዊ ልጆችና የልጅ ልጆችን አግኝቻለሁ። እነዚህ ለእኔ “የማመስገኛ መልእክት” ሆነውልኛል። (2 ቆሮንቶስ 3:1) ከመካከላቸው ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ የነበረባቸው ይገኛሉ። ከእነዚህም አንዷ የአላዱራ ሃይማኖት ነቢይ የነበረችው ቪክቶሪያ ዲክ ነች። በ1 ዮሐንስ 5:21 ላይ ያለውን ከተገነዘበች በኋላ ብዙዎቹን የአስማት ኃይል አላቸው የምትላቸውንና እንደ ቅዱስ አድርጋ የምታከብራቸውን ዕቃዎች አስወገደች። ከዚያም ራሷን መወሰኗን በጥምቀት ካሳየች በኋላ ልዩ አቅኚ ሆና ከዘመዶቿ መካከል ብዙዎቹ እውነትን እንዲቀበሉ ለመርዳት ቻለች።
በሚያዝያ 1985 44ኛውን የጋብቻ በዓላችንን ልናከብር ጥቂት ወራት ብቻ ሲቀሩን ባለቤቴ በሞት ተለየኝ። ነገር ግን ብቻዬን አልተጣልኩም። ረዳቴ የሆነውን ይሖዋን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ማገልገሌን ቀጠልኩ። እሱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ከረዳኋቸው ሰዎች ጋር ልዩ የሆነ ቅርበት ይሰማኛል። የራሴ ቤተሰብ እንደሆኑ ይሰማኛል። እኔም እወዳቸዋለሁ እነሱም ይወዱኛል። ስታመም እኔን ለመርዳት ይሯሯጣሉ፣ እኔም እረዳቸዋለሁ።
እንደገና አዲስ ሕይወት የመኖር አጋጣሚ ባገኝ በደስታ ማጭዴን ይዤ በመከሩ ሥራ በመካፈል ከይሖዋ ጋር አብሬ እንደምሠራ አያጠያይቅም።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዊኒፍሬድ ሬሚ በዛሬው ጊዜ