የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 4/15 ገጽ 23-27
  • ኮሌጂያንቶች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኮሌጂያንቶች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው መሠረተ ትምህርት ያስከተለው ውዝግብ
  • የኮሌጂያንቶች ልደትና እድገት
  • የኮሌጂያንቶቹ እምነቶች
  • ሳምንታዊ ስብሰባዎች
  • ብሔራዊ ስብሰባዎች
  • የኮሌጂያንቶች እንቅስቃሴ የተዳከመው ለምን ነበር?
  • ክፍል 17:- ከ1530 እዘአ ወዲህ የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ በእርግጥ ተሐድሶ ነበርን?
    ንቁ!—1996
  • አምላክ ዕድላችንን አስቀድሞ ወስኖታልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት ማሳየት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ካልቪኒዝም በ500 ዓመት ውስጥ ምን ማከናወን ችሏል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 4/15 ገጽ 23-27

ኮሌጂያንቶች

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የተለዩ አድርጓቸዋል

ስለ ኮሌጂያንቶች ሰምተህ ታውቃለህ? ይህ በ17ኛው መቶ ዘመን የነበረ አናሳ የደች ሃይማኖታዊ ቡድን በጊዜው ከነበሩት ዋና ዋና አብያተ ክርስቲያናት የተለየ ነበር። የተለየ የነበረው እንዴት ነው? ከእነሱስ ምን ልንማር እንችላለን? ይህን ለማወቅ ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪክን እንመርምር።

በ1587 ያኮቢዩስ አርሚኒየስ (ወይም ያኮፕ ሃርመንሰን) አምስተርዳም ከተማ ደረሰ። የትምህርት ማስረጃው አጥጋቢ ስለነበር ሥራ ለማግኘት ምንም አልተቸገረም። በ21 ዓመቱ ከሆላንዱ የሌይደን ዩኒቨርሲቲ ተመረቀ። ከዚያ በኋላ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጅ የነበረውን ጆን ካልቪንን በተካው በቴዎዶር ደ ቤዝ አስተማሪነት መንፈሳዊ ትምህርት በመከታተል ለስድስት ዓመት በስዊዘርላንድ ተቀመጠ። በአምስተርዳም የሚገኙ ፕሮቴስታንቶች የ27 ዓመቱን አርሚኒየስ ፓስተራቸው አድርገው መሾማቸው ምንም አያስደንቅም! ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን በርካታ የቤተ ክርስቲያን አባላት ባደረጉት ምርጫ ተጸጽተዋል። ለምን?

ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው መሠረተ ትምህርት ያስከተለው ውዝግብ

አርሚኒየስ ፓስተራቸው ከሆነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአምስተርዳም ፕሮቴስታንቶች መካከል ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው መሠረተ ትምህርት አለመግባባት ፈጥሮ ነበር። ይህ መሠረተ ትምህርት የካልቪናውያን እምነት አቢይ ክፍል ቢሆንም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላት አምላክ አንዳንዶች እንዲድኑ ሌሎች ደግሞ እንዲጠፉ አስቀድሞ ዕድልን የሚወስን ከሆነ ጨካኝና ፍትሕ የጎደለው ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። ካልቪናውያኑ አርሚኒየስ የቤዝ ተማሪ ስለነበረ እነዚህን ተቃዋሚዎች ፈር ያስይዛቸዋል ብለው ጠብቀው ነበር። ይሁን እንጂ ካልቪናውያኑ ይግረማቸው ብሎ አርሚኒየስ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ወገነ። በ1593 ክርክሩ ተጋግሎ የከተማውን ፕሮቴስታንቶች በሁለት ቡድን ከፈላቸው። አንደኛው ቡድን መሠረተ ትምህርቱን የሚደግፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ መሠረተ ትምህርቱን ያጣጣሉ ለዘብተኞችን ያቀፈ ነበር።

በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህ ተራ ክርክር በአገር አቀፍ ደረጃ በፕሮቴስታንቶች መካከል ክፍፍል ፈጠረ። በመጨረሻ በኅዳር 1618 ጉዳዩ እልባት የሚያገኝበት መንገድ ተፈጠረ። በሠራዊቱና በሕዝብ የሚደገፉት ካልቪናውያን እነዚያን ተቃዋሚዎች (በወቅቱ ሪሞንስትራንቶችa ተብለው ይጠሩ ነበር) ወደ ፕሮቴስታንቱ የዶርድሬክት ሲኖዶስ ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲቀርቡ አደረጉ። በስብሰባው ማብቂያ ላይ የሪሞንስትራንት ቄሶች ከአሁን በኋላ ላለመስበክ ቃል በመግባት የመፈረም ወይም ከአገር የመባረር ሁለት ምርጫ ቀረበላቸው። አብዛኞቹ በስደት ከአገር መውጣትን መረጡ። በሪሞንስትራንት ቄሶች እግር ወግ አጥባቂ ካልቪናውያን ተተኩ። ሲኖዶሱ ለጊዜውም ቢሆን ካልቪናዊነት ድል የተቀዳጀ መስሎት ነበር።

የኮሌጂያንቶች ልደትና እድገት

በሌላ ቦታ እንደሆነው ሁሉ በሌይደን አቅራቢያ በቫርሞንት የሚገኘው የሪሞንስትራንቶች ጉባኤ ፓስተሩን አጣ። ይሁን እንጂ በሲኖዶሱ የጸደቀው ለውጥ በሌሎች ቦታዎች ተቀባይነት ቢያገኝም በሪሞንስትራንቶች ጉባኤ ተቀባይነት አላገኘም። ከዚህም በላይ አንድ የሪሞንስትራንት አገልጋይ በሕይወቱ ቆርጦ ጉባኤውን ለመንከባከብ በ1620 ወደ ቫርሞንት ቢመለስም አንዳንድ የጉባኤ አባላት አልተቀበሉትም። እነዚህ አባላት ያለ ቀሳውስት እርዳታ በድብቅ ሃይማኖታዊ ስብሰባቸውን ማካሄድ ጀምረው ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ስብሰባዎች ኮሌጆች ሲባሉ የስብሰባው ተካፋዮች ደግሞ ኮሌጂያንቶች ተብለው ተጠሩ።

ኮሌጂያንቶች ገና ከጅምሩ የሃይማኖት መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዘው የተነሡ ሳይሆኑ ጊዜና አጋጣሚ የወለዳቸው ቢሆኑም ሁኔታዎች ወዲያው መልካቸውን ቀይረዋል። ካይስበርት ቫን ደር ኮድ የተባሉት የጉባኤ አባል ይህ ቡድን የቀሳውስት የበላይ ተቆጣጣሪነት ሳያሻው ስብሰባውን ማካሄዱ ከዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለውና የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ይመላለሱበት ከነበረው መንገድ ጋር ይበልጥ እየተስማማ ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ ተከራክረዋል። የቀሳውስት ክፍል የተፈጠረው ከሐዋርያት ሞት በኋላ ሲሆን እሱም የሆነ የእጅ ሙያ ተምረው ራሳቸውን ለማስተዳደር ፈቃደኛ ላልሆኑ ሰዎች የሥራ መስክ ለመክፈት ሲባል ነው ብለዋል።

በ1621 ቫን ደር ኮድና ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው አባላት ስብሰባቸውን በአቅራቢያው ወደሚገኘው የራይንስበርክ መንደር አዛወሩት።b ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሃይማኖታዊ ስደት እየረገበና ተቻችሎ መኖር እየጎለበተ ሲመጣ የኮሌጂያንቶቹ ስብሰባዎች ዝና በአገሪቱ በሙሉ ከመሰማቱም በላይ ታሪክ ጸሐፊው ዜክፍሬት ዚልቨርበርግ እንደተናገሩት “የተለያዩ ሰዎች” በስብሰባዎቹ ተገኝተዋል። ሪሞንስትራንቶች፣ ሜነናይቶች፣ ሶሲኒያውያንና ሌላው ቀርቶ የሃይማኖት ምሁራን ጭምር ነበሩ። አንዳንዶቹ ገበሬዎች ነበሩ። ሌሎቹ ባለ ቅኔዎች፣ አታሚዎች፣ ሐኪሞችና የእጅ ሞያተኞች ነበሩ። ፈላስፋው ስፒኖዛ (ቤኔዲክቱስ ደ ስፒኖዛ) እና መምህሩ ዮሃን አሞስ ከሚኒየስ (ወይም ያን ኮሜንስኪ) እንዲሁም ዝነኛው ሠዓሊ ሬምብራንት ቫን ራይን የእንቅስቃሴው ተባባሪዎች ሆኑ። እነዚህ ለሃይማኖታቸው ያደሩ ሰዎች ይዘዋቸው የመጡት የተለያዩ አስተሳሰቦች በኮሌጂያንቶች እምነት እድገት ላይ ተጽእኖ አሳድረዋል።

ከ1640 በኋላ ይህ በንቃት ይንቀሳቀስ የነበረ ቡድን በፍጥነት እያደገ ሄደ። በሮተርዳም፣ በአምስተርዳም፣ በሌቫርደንና በሌሎችም ከተማዎች ኮሌጆች ተበራከቱ። የታሪክ ፕሮፌሰሩ የሆኑት አንድሩው ሲ ፊክስ ከ1650 እስከ 1700 በነበሩት ዓመታት “ኮሌጂያንቶቹ በአሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ሆላንድ ውስጥ ዋነኞቹና ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ ሃይማኖታዊ ኃይሎች ለመሆን በቅተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኮሌጂያንቶቹ እምነቶች

ማመዛዘን፣ መቻቻልና የንግግር ነፃነት የኮሌጂያንቶች እንቅስቃሴ መለዮዎች ስለነበሩ ግለሰብ ኮሌጂያንቶች የተለያዩ እምነቶችን የመያዝ ነፃነት ነበራቸው። ሆኖም እርስ በርስ የሚያስተሳስሯቸው አንዳንድ የጋራ እምነቶችም ነበሯቸው። ለምሳሌ ያህል ሁሉም ኮሌጂያንቶች በግል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያለውን አስፈላጊነት ከፍ አድርገው ይመለከቱ ነበር። አንድ ኮሌጂያንት እንደጻፈው እያንዳንዱ አባል “አምላክን ራሱ ተመራምሮ ሊደርስበት ይገባል እንጂ ከሌላ ሰው ስለ አምላክ ማወቅ የለበትም።” እነሱም ይህንኑ አድርገዋል። የ19ኛው መቶ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ በነበሩት በያኮበስ ሲ ቫን ስሌ አባባል መሠረት በወቅቱ ከነበሩት ሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ይልቅ በኮሌጂያንቶች ዘንድ የበለጠ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ይገኝ ነበር። ተቃዋሚዎቻቸው እንኳ ሳይቀሩ ኮሌጂያንቶቹ ያላቸውን መጽሐፍ ቅዱስን በጥሩ ሁኔታ የመጠቀም ችሎታ ያደንቁ ነበር።

ይሁንና ኮሌጂያንቶች መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ባጠኑ ቁጥር ዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ካሏቸው የተለዩ እምነቶችን እያዳበሩ መጡ። ከ17ኛው እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ የሚገኙ ምንጮች አንዳንድ እምነቶቻቸውን ይገልጻሉ:-

የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን። የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ዘመን በፖለቲካ ውስጥ እጅዋን ስታስገባ ከክርስቶስ ጋር የገባችውን ቃል ኪዳን አፈረሰች፤ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባች መሆኗንም አጣች በማለት ኮሌጂያዊውና የሃይማኖት ምሁሩ አዳም ቦሬል በ1644 ጽፈዋል። በዚህ ምክንያት የሐሰት ትምህርቶች እንደተበራከቱና እስከሳቸው ዘመን ድረስ መቀጠላቸውን አክለው ተናግረዋል።

ተሃድሶ። በሉተር፣ በካልቪንና በሌሎችም የተመራው የ16ኛው መቶ ዘመን የተሃድሶ እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያንን በማደሱ ተግባር ሊሳካለት አልቻለም። ከዚህ ይልቅ ታዋቂው ኮሌጂያንትና ሐኪም ኬሌነስ አብራሃምስዞን (1622-1706) እንዳሉት ተሃድሶው ጠብና ጥላቻ እንዲቀሰቀስ በማድረግ ሃይማኖታዊ ሁኔታው እንዲባባስ አድርጓል። ትክክለኛ ተሃድሶ ልብን መለወጥ መቻል አለበት፤ ይህ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ደግሞ ይህን ሊያደርግ አልቻለም።

ቤተ ክርስቲያንና ቀሳውስት። ዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የተበላሹ፣ ዓለማዊ መንፈስ የተጠናወታቸውና መለኮታዊ ሥልጣን የተነፈጉ ናቸው። ሃይማኖትን በቁም ነገር የሚመለከት ማንኛውም ሰው ቤተ ክርስቲያን በምትሠራቸው ኃጢአቶች ተባባሪ እንዳይሆን ሲል ከሚገኝበት ቤተ ክርስቲያን ከመውጣት የተሻለ ነገር ሊያደርግ አይችልም። የቀሳውስቱ ሥልጣን፣ ይላሉ ኮሌጂያንቶቹ፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች የሚቃረንና “የክርስቲያን ጉባኤን መንፈሳዊ ደኅንነት የሚጎዳ” ነው።

መንግሥትና ገነት። ከአምስተርዳም ኮሌጅ መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ዳኒኤል ደ ብሬን (1594–​1664) የክርስቶስ መንግሥት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ የሚያድር መንፈሳዊ መንግሥት አይደለም ሲሉ ጽፈዋል። መምህር ያኮብ ኦስተንስ የተባሉት በሮተርዳም የሚገኙ ኮሌጂያንት “ፓትሪያርኮቹ ምድራዊ ነገሮችን ተስፋ ያደርጉ ነበር” ብለዋል። በተመሳሳይም ኮሌጂያንቶች ምድር ወደ ገነትነት የምትለወጥበትን ጊዜ ይጠባበቁ ነበር።

ሥላሴ። የሶሲኒያውያን እምነቶች ተጽእኖ ያሳደሩባቸው አንዳንድ ታዋቂ ኮሌጂያንቶች የሥላሴን ትምህርት አልተቀበሉም።c ለማስረጃ ያህል ዳኒኤል ዝዊከር (1621–78) ሥላሴን የመሳሰለው ከምክንያታዊነት የራቀ ማንኛውም መሠረተ ትምህርት “ሊሆን የማይችልና ሐሰት” ነበር ሲል ጽፏል። ኮሌጂያንቱ ሬኒር ሮሌኦ የተረጎመው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በ1694 ታተመ። የዮሐንስ 1:​1ን ጥቅስ ኋለኛ ክፍል የኦርቶዶክሱ ትርጉም እንደሚለው “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ሳይሆን “ቃልም አምላክ ነበረ” በማለት ተርጉሞታል።d

ሳምንታዊ ስብሰባዎች

ኮሌጂያንቶች የእምነት ልዩነት ቢኖራቸውም በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ኮሌጆቻቸው አሠራር ግን ተመሳሳይ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ቫን ስሌ እንደዘገቡት በኮሌጂያንቶቹ እንቅስቃሴ መጀመሪያ ላይ ለስብሰባዎች የቅድሚያ ዝግጅት ይደረግ የነበረው አልፎ አልፎ ነበር። ኮሌጂያንቶች “ትንቢት” ስለ መናገር አስፈላጊነት የሚናገሩትን የጳውሎስ ቃላት መሠረት በማድረግ ወንድ አባላት በሙሉ በኮሌጆቹ ላይ በነፃነት ንግግር መስጠት ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። (1 ቆሮንቶስ 14:​1, 3, 26) በዚህ ምክንያት ስብሰባዎች አብዛኛውን ጊዜ እስከ ሌሊት ድረስ ይራዘሙ የነበረ ሲሆን በስብሰባው ላይ የተገኙ አንዳንዶችም “እንቅልፍ ይወስዳቸው” ነበር።

ከጊዜ በኋላ ስብሰባዎች ይበልጥ እየተደራጁ መጡ። ኮሌጂያንቶች በእሁድ ቀናት ብቻ ሳይሆን በሥራ ቀናት ምሽት ላይም ይገናኙ ነበር። ተናጋሪውና ጉባኤው በዚያ ዓመት ለሚካሄዱት ለሁሉም ስብሰባዎች አስቀድመው እንዲዘጋጁ ለማስቻል የሚጠኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና የተናጋሪዎችን ስሞች የመጀመሪያ ፊደላት ዝርዝር የያዘ ፕሮግራም ይታተም ነበር። ስብሰባው በመዝሙርና በጸሎት ከተጀመረ በኋላ አንድ ተናጋሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶቹን ያብራራል። ተናግሮ ሲጨርስ ቀደም ሲል በተብራራው ርዕስ ላይ ያላቸውን ሐሳብ እንዲገልጹ ወንዶች የሆኑትን ይጠይቃል። ከዚያም ሌላ ተናጋሪ እነዚያው ጥቅሶች እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻል። ስብሰባው በጸሎትና በመዝሙር ይደመደማል።

በፍሪዝላንድ ክፍለ ሃገር በሃርሊንገን መንደር የሚገኙ ኮሌጂያንቶች ስብሰባዎቻቸው በተያዘላቸው ፕሮግራም እንዲከናወኑ ለማድረግ ለየት ያለ አሠራር ነበራቸው። አንድ ተናጋሪ መናገር ከሚገባው ጊዜ ካሳለፈ አነስተኛ የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ይጠየቅ ነበር።

ብሔራዊ ስብሰባዎች

በተጨማሪም ኮሌጂያውንቶች ትላልቅ ስብሰባዎችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ይህም በመሆኑ ከ1640 ጀምሮ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ኮሌጂያንቶች በዓመት ሁለት ጊዜ (በፀደይና በበጋ) ወደ ራይንስበርክ ይጓዙ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ፊክስ እነዚህ ስብሰባዎች “በርቀትና በስፋት ተሰራጭተው ስለሚገኙት ወንድሞቻቸው አስተሳሰብ፣ ስሜቶች፣ እምነቶችና እንቅስቃሴዎች ጋር በሚገባ እንዲተዋወቁ” አስችለዋቸዋል ሲሉ ጽፈዋል።

በእንግድነት የመጡ አንዳንድ ኮሌጂያንቶች ከመንደረተኞቹ ቤቶችን ሲከራዩ ሌሎቹ ደግሞ የኮሌጂያንቶች ንብረት በሆነው ክሮት ሆስ ወይም ትልቁ ቤት በሚባለው ባለ 30 ክፍል ቤት ውስጥ ያርፉ ነበር። በዚያም ከ60 እስከ 70 ለሚሆኑ ሰዎች ምግብ ይቀርብ ነበር። ከእራት በኋላ ጎብኚዎቹ በሰፊው ግቢ ውስጥ እየተዘዋወሩ ‘የአምላክን ሥራዎች ሊያደንቁ፣ በርጋታ ሊወያዩ ወይም ሊያሰላስሉ ይችሉ ነበር።’

ሁሉም ባይሆኑም አብዛኞቹ ኮሌጂያንቶች የጥምቀትን አስፈላጊነት ተገንዝበው ነበር። ይህም በመሆኑ ጥምቀት በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ላቅ ያለ ግምት የሚሰጠው ነገር ሆነ። አብዛኛውን ጊዜ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወነው ቅዳሜ ጠዋት እንደነበረ ታሪክ ጸሐፊው ቫን ስሌ ተናግሯል። ስለ ጥምቀት አስፈላጊነት ንግግር ከተሰጠ በኋላ መዝሙርና ጸሎት ይከተላሉ። ከዚያም ተናጋሪው ለመጠመቅ የሚፈልጉትን አዋቂ ሰዎች እምነታቸውን እንዲገልጹ ማለትም “ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው አምላክ ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” እንደሚሉት ያሉ ነገሮችን እንዲናገሩ ይጋብዛል። ንግግሩ በጸሎት ከተደመደመ በኋላ በቦታው የተገኙት በሙሉ ወደ መጠመቂያው ገንዳ ሄደው እየተመለከቱ ወንዶችና ሴቶች ውኃው ትከሻቸው ላይ እንዲደርስ በገንዳው ውስጥ ይንበረከካሉ። ከዚያም አጥማቂው የአዲሱን አማኝ ራስ በቀስታ በመግፋት ወደ ውኃው ውስጥ ይከተዋል። ሥነ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሌላ ንግግር ለመስማት ሁሉም ወደየቦታቸው ይመለሳሉ።

ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ላይ መደበኛው ስብሰባ በአጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ በመዝሙርና በጸሎት ይጀመራል። ምንጊዜም ተናጋሪ እንዲኖር ሲባል በሮተርዳም፣ በሌይደን፣ በአምስተርዳምና በኖርዝ ሆላንድ የሚገኙ ኮሌጆች ለእያንዳንዱ ስብሰባ የሚሆኑ ተናጋሪዎች በየተራ ያቀርቡ ነበር። እሁድ ጠዋት የጌታን እራት ለማክበር የተመደበ ጊዜ ነበር። ንግግር፣ ጸሎትና መዝሙር ከተደረገ በኋላ ወንዶች ከዚያም ሴቶች ከቂጣውና ከወይኑ ይካፈላሉ። እሁድ ምሽት ላይ ተጨማሪ ንግግሮች ይቀርባሉ፤ ከዚያም ሰኞ ጠዋት ላይ የሚቀርበውን የመደምደሚያ ንግግር ለማዳመጥ ሁሉም ይሰበሰባል። በእነዚህ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡት አብዛኞቹ ንግግሮች፣ ይላሉ ቫን ስሌ፣ በአንድ ትምህርት ላይ ጥልቅ የሆነ ማብራሪያ የሚሰጡ ሳይሆኑ ትምህርቱን በሥራ ላይ ማዋልን ጎላ አድርገው የሚገልጹ ነበሩ።

የራይንስበርክ መንደር ነዋሪዎች እነዚህን ስብሰባዎች ለማስተናገድ ደስተኞች ነበሩ። አንድ የ18ኛው መቶ ዘመን ታዛቢ በብዛት ይጎርፉ የነበሩት እንግዶች ምግብና መጠጥ ይገዙ ስለነበር ለመንደሪቱ ጥሩ ገቢ አስገኝቶላታል ሲሉ ጽፈዋል። ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ትልቅ ስብሰባ ካበቃ በኋላ ኮሌጂያውያንቶቹ በራይንስበርክ ለሚገኙ ድሆች የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ ይለግሱ ነበር። እነዚህ ስብሰባዎች በ1787 ሲቋረጡ መንደሪቱ የገቢ ምንጯን እንዳጣች ምንም አያጠራጥርም። ከዚያ በኋላ የኮሌጂያንቶች እንቅስቃሴ እየተዳከመ መጣ። ለምን?

የኮሌጂያንቶች እንቅስቃሴ የተዳከመው ለምን ነበር?

በ17ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ምክንያት በሃይማኖት ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ሚና በተመለከተ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። አንዳንድ ኮሌጂያንቶች ሰብዓዊ አስተሳሰብ ከመለኮታዊው ራእይ ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ሌሎች ግን በዚህ ሐሳብ አልተስማሙም። በመጨረሻ ይህ አለመግባባት አጠቃላዩን የኮሌጂያንቶች እንቅስቃሴ ለሁለት ከፈለው። ኮሌጂያንቶቹ እንደገና የተዋሃዱት በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የነበሩት ዋና ዋናዎቹ አቀንቃኞች ከሞቱ በኋላ ነበር። ያም ሆኖ ግን ከዚህ መከፋፈል በኋላ እንቅስቃሴው “በፍጹም እንደ ቀድሞው አልሆነም” ሲሉ ታሪክ ጸሐፊው ፊክስ ተናግረዋል።

በ18ኛው መቶ ዘመን በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እየጎለበተ የመጣው ተቻችሎ የመኖር ሁኔታ ለኮሌጂያንቶች መመናመን አስተዋጽኦ አድርጓል። የኮሌጂያንቶቹ የምክንያትና የመቻቻል መሠረታዊ ሥርዓቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ በሰፊው ተቀባይነት እያገኙ ሲመጡ “በአንድ ወቅት ብቸኛ የነበረው የኮሌጂያንቶች ብርሃን እየደበዘዘ ሄዶ ለምሁራዊነት እንቅስቃሴ ደማቅ ብርሃን ቦታውን ለቀቀ።” በ18ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ አብዛኞቹ ኮሌጂያንቶች በሜነናይቶችና በሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ተዋጡ።

ኮሌጂያንቶች በእንቅስቃሴያቸው ውስጥ የአስተሳሰብ አንድነት እንዲኖር የማድረግ ዓላማ ስላልነበራቸው በኮሌጂያንቶቹ ብዛት ልክ የተለያዩ አመለካከቶች ነበሩ። ይህን ተገንዝበው ስለነበር ክርስቲያኖች ‘በአንድ አሳብ የተባበሩ’ እንዲሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውንም ማሳሰቢያ ተግባራዊ አድርገናል ሊሉ አልቻሉም። (1 ቆሮንቶስ 1:​10) የዚያኑ ያህል ግን ኮሌጂያንቶች የአስተሳሰብ አንድነትን የመሳሰሉ መሠረታዊ የሆኑ ክርስቲያናዊ እምነቶች እውን የሚሆኑበትን ጊዜ በተስፋ ይጠባበቁ ነበር።

በኮሌጂያንቶች ዘመን ትክክለኛው እውቀት በስፋት አለመዳረሱን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሃይማኖቶች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ምሳሌ ትተዋል። (ከዳንኤል 12:​4 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው መግለጻቸው ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉን ፈትኑ” ሲል ከሰጠው ምክር ጋር የሚስማማ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:​21) የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ያኮበስ አርሚኒየስንና ሌሎችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ልማዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አለመሆናቸውን እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ይህን በተገነዘቡ ጊዜ በደንብ ከተደራጁ ሃይማኖቶች የተለየ አቋም ለመያዝ ደፋሮች ነበሩ። አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ1610 ተቃዋሚዎቹ ለደች ገዥዎች የተቃወሙበትን ምክንያት የሚገልጽ ሰነድ (በእንግሊዝኛ ሪሞንስትረንስ) ልከው ነበር። ሪሞንስትራንቶች ተብለው የተጠሩት ይህን ካደረጉ በኋላ ነበር።

b ኮሌጂያንቶች በሚሰበሰቡበት በዚህ ቦታ ሳቢያ ራይንስበርከራውያን ተብለውም ይጠሩ ነበር።

c የኅዳር 22, 1988 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 19 ላይ የሚገኘውን “ሶሲኒያውያን​—⁠ሥላሴን ያልተቀበሉት ለምን ነበር?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

d Het Nieuwe Testament van onze Heer Jezus Christus, uit het Grieksch vertaald door Reijnier Rooleeuw, M.D. (የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ኪዳን በሬኒር ሮሌኦ ኤም ዲ ከግሪክኛ የተተረጎመ)

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሬምብራንት ቫን ራይን

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኮሌጂያንቶች እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩበት የቫርሞንት መንደርና የጥምቀት ሥነ ሥርዓት የሚከናወንበት ደ ቭሊት ወንዝ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Background: Courtesy of the American Bible Society Library, New York

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ