ኧርንስት ግሉክ ያከናወነው አድካሚ ሥራ
ከዛሬ 300 ዓመታት በፊት ኧርንስት ግሉክ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጥቂቶች ብቻ ለመሥራት የደፈሩትን አንድ ሥራ ማከናወን ጀመረ። ግሉክ መጽሐፍ ቅዱስን በማያውቀው ቋንቋ ለመተርጎም ቆርጦ ተነሳ።
ግሉክ የተወለደው በ1654 ገደማ ጀርመን ውስጥ፣ ሃለ አቅራቢያ በምትገኘው ቬቲን በተባለች አነስተኛ ከተማ ነው። አባቱ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ቄስ ነበሩ። ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ማደጉ ገና በልጅነቱ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዲያድርበት አድርጓል። ግሉክ በጀርመን ሲከታተል የቆየውን የሃይማኖት ትምህርት በ21 ዓመቱ ካጠናቀቀ በኋላ አሁን ላትቪያ በመባል ወደምትታወቀው አገር አቀና። በዚያን ዘመን አብዛኞቹ የላትቪያ ነዋሪዎች መደበኛ ትምህርት ያልተማሩ ሲሆን በቋንቋቸው የሚገኙ መጻሕፍትም በጣም ጥቂት ነበሩ። ግሉክ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በወጣትነት ዕድሜዬ እዚህ አገር ስመጣ በመጀመሪያ ያስተዋልኩት ችግር ቢኖር የላትቪያ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ያልነበረው መሆኑን ነው። . . . ይህ ሁኔታ ቋንቋቸውን ለማጥናትና ጠንቅቄ ለማወቅ በአምላክ ፊት ቃል እንድገባ አነሳሳኝ።” ስለሆነም ግሉክ ለላትቪያ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋቸው ለማዘጋጀት ቁርጥ ውሳኔ አደረገ።
ለትርጉም ሥራ መዘጋጀት
ግሉክ የኖረበት አካባቢ በዚያን ዘመን ሊቮንያ ይባል የነበረ ሲሆን በስዊድን ቅኝ ግዛት ሥር ነበር። በላትቪያ የሚገኘው የስዊድን ንጉሥ እንደራሴ ዮሐነስ ፊሸር፣ የአገሪቱን የትምህርት ደረጃ ከፍ የማድረግና ትርፍ የማካበት ፍላጎት ነበረው። ግሉክ መጽሐፍ ቅዱስን በላትቪያ ቋንቋ ለመተርጎም ማሰቡን ለፊሸር ነገረው። ፊሸር በዋና ከተማዋ በሪገ የግል ማተሚያ ቤት ነበረው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በላትቪያ ቋንቋ በማተም ትምህርትን በበለጠ ማስፋፋትና ዳጎስ ያለ ትርፍ ማካበት ይችላል። ፊሸር የትርጉም ሥራው እንዲጀመር ከንጉሥ ቻርልስ 14ኛ ፈቃድ ጠየቀ። ንጉሡም ፕሮጀክቱ እንዲካሄድ ፈቃድ የሰጡ ከመሆኑም በላይ የገንዘብ ወጪውን ለመሸፈን ቃል ገቡ። ንጉሡ በነሐሴ 31, 1681 በፊርማቸው ያጸደቁት ውሳኔ የትርጉም ሥራው እንዲጀመር መንገድ ከፈተ።
በዚህ ጊዜ ሁሉ ግሉክ ለትርጉም ሥራው ራሱን እያዘጋጀ ነበር። ግሉክ ጀርመናዊ እንደመሆኑ መጠን መጽሐፍ ቅዱስን በላትቪያ ቋንቋ ለማዘጋጀት የማርቲን ሉተርን ትርጉም መሠረት ማድረግ ይችል ነበር። ሆኖም ግሉክ በተቻለው አቅም የተሻለ ትርጉም ለማዘጋጀት ስለፈለገ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ከተጻፈባቸው ቋንቋዎች ማለትም ከዕብራይስጥና ከግሪክ ቢተረጉም የተሻለ እንደሆነ ተሰማው። ግሉክ የዕብራይስጥኛና የግሪክኛ ቋንቋ እውቀቱ አነስተኛ ስለነበር እነዚህን ቋንቋዎች ለማጥናት ወደ ሃምቡርግ፣ ጀርመን ሄደ። እዚያ በነበረበት ጊዜ ከሊቮንያ የመጡ ያኒስ ራተርስ የተባሉ ቄስ የላትቪያን ቋንቋና መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ግሪክኛ እንዲያውቅ ሳይረዱት አልቀሩም።
ለዓመታት መሥራት፣ ለዓመታት መታገሥ
ግሉክ የቋንቋ ትምህርቱን በ1680 ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ላትቪያ ተመልሶ በቅስና ማገልገል ጀመረ። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ የትርጉም ሥራውን ተያያዘው። በ1683 ደግሞ አሉክስኔ በሚገኘው ትልቅ ደብር ውስጥ እንዲያገለግል ተሾመ። አሉክስኔ፣ ግሉክ የትርጉም ሥራውን ያከናወነባት ከተማ በመሆን ትታወቃለች።
በወቅቱ የላትቪያ ቋንቋ ለብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትና መሠረተ ሐሳቦች ተስማሚ ቃላት አልነበሩትም። በመሆኑም ግሉክ በትርጉሙ ውስጥ አንዳንድ የጀርመንኛ ቃላትን አካትቷል። እንደዚያም ሆኖ የአምላክን ቃል በላትቪያ ቋንቋ ለመተርጎም የተቻለውን ሁሉ የጣረ ሲሆን ምሁራንም ከፍተኛ ጥራት ያለው የትርጉም ሥራ ስለመሆኑ መሥክረዋል። ሌላው ቀርቶ ግሉክ አዳዲስ ቃላትን ፈጥሯል፤ ከእነዚህ ቃላት መካከል አብዛኞቹ በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በላትቪያ ቋንቋ በስፋት ይሠራባቸዋል። ከእነዚህ መካከል “ምሳሌ፣” “ድግስ፣” “ግዙፍ፣” “መሰለል” እና “መመሥከር” የሚሉት የላትቪያ ቃላት ይገኙበታል።
ዮሐነስ ፊሸር የትርጉም ሥራውን ሂደት ለስዊድኑ ንጉሥ በየጊዜው ያሳውቅ ነበር። በወቅቱ ከተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች መረዳት እንደሚቻለው ግሉክ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በ1683 ተርጉሞ ጨርሷል። መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ተርጉሞ ያጠናቀቀው ደግሞ በ1689 ሲሆን አድካሚ የሆነውን ይህን ሥራ ለመጨረስ የወሰደበት ጊዜ ስምንት ዓመት ብቻ ነው።a የትርጉም ሥራው ለኅትመት ከመብቃቱ በፊት ረጅም ጊዜ ያለፈ ቢሆንም መንግሥት በ1694 በላትቪያ ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ለሕዝብ እንዲሠራጭ ሲፈቅድ የግሉክ ምኞት ተሳካ።
አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ግሉክ መጽሐፍ ቅዱሱን የተረጎመው ለብቻው ስለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው። ግሉክ የሉተርን ትርጉም እንዳመሳከረና በጊዜው በላትቪያ ቋንቋ ይገኙ የነበሩትን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማስተካከያዎች በማድረግ በትርጉም ሥራው እንደተጠቀመባቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በጣም ጥቂት ነበሩ። ሌሎች ተርጓሚዎችስ በሥራው ላይ ተካፍለዋል? ግሉክ በሚተረጉምበት ጊዜ አንድ ረዳት የነበረው ሲሆን ማጣሪያ ንባብ የሚያደርጉና የትርጉሙን የጥራት ደረጃ የሚቆጣጠሩ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በትርጉም ሥራው ላይ በቀጥታ የተካፈሉ አይመስልም። በመሆኑም ግሉክ መጽሐፍ ቅዱሱን የተረጎመው ለብቻው መሆን አለበት።
የግሉክ ትርጉም የላትቪያን የጽሑፍ ቋንቋ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቢሆንም ከዚህ የላቀ ጠቀሜታም አለው። የላትቪያ ሕዝቦች የአምላክን ቃል በገዛ ቋንቋቸው ለማንበብና ሕይወት ሰጪ ትምህርቶቹን ለመቅሰም በቅተዋል። በመሆኑም ኧርንስት ግሉክ የዋለላቸውን ውለታ ፈጽሞ አይረሱም። የአሉክስኔ ነዋሪዎች ግሊካ ኦዞሊ ወይም የግሉክ ዛፎች ብለው የሚጠሯቸውን ሁለት የባሉጥ ዛፎች ከ300 ለሚበልጡ ዓመታት ሲንከባከቡ ኖረዋል። ግሉክ እነዚህን ዛፎች የተከለው በላትቪያ ቋንቋ ለተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ መታሰቢያ እንዲሆኑ ነው። በአሉክስኔ ባለ አንድ አነስተኛ ሙዚየም ውስጥ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የግሉክ ትርጉም የመጀመሪያ እትም አንዱ ነው። በአሉክስኔ ከተማ አርማ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስልና ግሉክ የትርጉም ሥራውን ያጠናቀቀበት ዓመት ይኸውም 1689 ተጽፎ ይገኛል።
የኋለኞቹ ሥራዎቹ
ግሉክ ወደ ላትቪያ እንደመጣ የሩሲያን ቋንቋ መማር ጀምሮ ነበር። በ1699 መጽሐፍ ቅዱስን ወደዚህ ቋንቋ በመተርጎም ሌላውን ራእዩን እያሳካ መሆኑን ጽፏል። በ1702 በጻፈው ደብዳቤ ላይ ደግሞ የላትቪያን መጽሐፍ ቅዱስ አሻሽሎ ለማውጣት ሥራ መጀመሩን ገልጿል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም አመቺ የነበሩት ሁኔታዎች እየተለወጡ መጡ። ለበርካታ ዓመታት ሰላም የሰፈነባት ላትቪያ የጦር አውድማ ሆነች። በ1702 የሩሲያ ጦር ሠራዊት ስዊድናውያንን ድል ካደረገ በኋላ አሉክስኔን በቁጥጥሩ ሥር አዋለ። ግሉክና ቤተሰቡ ወደ ሩሲያ ተወሰዱ።b ሁከት በነገሠባቸው በእነዚህ ጊዜያት ግሉክ እያዘጋጃቸው የነበሩት የላትቪያና የሩሲያ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሶች ጠፉበት። ግሉክ በ1705 ሞስኮ ውስጥ ሕይወቱ አለፈ።
ግሉክ በኋላ ላይ እየሠራቸው የነበሩት የላትቪያና የሩሲያ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሶች መጥፋታቸው ትልቅ ኪሳራ ነበር። ሆኖም እስከ አሁን ድረስ በላትቪያ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነቡ ሁሉ ከግሉክ የመጀመሪያ ትርጉም ተጠቃሚዎች ናቸው።
ኧርንስት ግሉክ መጽሐፍ ቅዱስን የተለያዩ ሕዝቦች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች የመተርጎሙን አድካሚ ሥራ በድል ከተወጡት በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው። እነዚህ ሰዎች ባደረጉት ጥረት በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የአምላክን ቃል በራሱ ቋንቋ ማንበብና ውድ የሆነውን የእውነት ውኃ መጠጣት ችሏል። አዎን፣ ከ2,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች በተተረጎሙት የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞች አማካኝነት ይሖዋ በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰዎች ማንነቱን በማሳወቅ ላይ ይገኛል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በ1611 የወጣውን ኦቶራይዝድ ቨርሽን ወይም ኪንግ ጄምስ ቨርሽን የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት 47 ምሁራን ለሰባት ዓመታት መልፋት አስፈልጓቸዋል።
b ግሉክ ከሞተ በኋላ፣ የማደጎ ልጁ የሩሲያውን ዛር ታላቁ ፒተርን አገባች። ፒተር በሞተበት ዓመት ይኸውም በ1725 ቀዳማዊ ካትሪን በመባል የሩሲያ እቴጌ ሆነች።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የግሉክ ትርጉም
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ግሉክ የትርጉም ሥራውን ባከናወነባት ከተማ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ላይ ይገኛሉ