ትርጉም ያለው የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ
1 ኢየሱስ 70ቹን አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ለመስክ አገልግሎት የተዘጋጁ እንዲሆኑ ለመርዳት ሲል ያደረገው ስብሰባ በሉቃስ 10:1–11 ላይ ተመዝግቦ እናገኘዋለን። ኢየሱስ የተደራጁ እንዲሆኑ፣ ስለሚናገሩት ነገር እንዲዘጋጁና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት እንደሚቋቋሙ የሚረዷቸውን ቀጥተኛ መመሪያዎች ሰጥቷቸዋል። ይህን ዘገባ በመመርመር ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።
2 ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ሁሉም 70ዎቹ ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። አንዳንድ ሰዎች በመስክ አግልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ አርፍዶ የመምጣት ልማድ ካላቸው ብዙ ጊዜ ይባክናል። አርፍደው በመመጣታቸው በአብዛኛው እንደገና መመደብ አስፈላጊ ይሆናል። ይህም ሁሉም አገልግሎት ቶሎ እንዳይጀምሩ እንቅፋት ይሆናል። ሁላችንም በሰዓቱ በመድረስ የበኩላችንን ድርሻ ልናበረክትና ወዲያውኑ ወደ አገልግሎት ክልላችን ልንሄድ እንችላለን።
3 ኢየሱስ ለቡድኑ “የእግዚአብሔር መንግሥት” የሚል አንድ የተወሰነ የመወያያ ርዕስ ሰጥቶ ነበር። (ሉቃስ 10:9) እኛም ተመሳሳይ መልእክት እንድናውጅ ተነግሮናል። እንዲሁም ምን ብለን እንደምንናገር በዚህ ስብሰባ ላይ ለሚቀርቡልን አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች አመስጋኞች ነን። ስብሰባውን የሚመራው ወንድም በተለያዩ ጊዜያት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ከ40 የሚበልጡ የተለያዩ መግቢያዎችና ጥቅሶችን ከያዘው ምክንያቱን ማስረዳት ከተባለው መጽሐፍ ሊጠቅስ ይችላል። አጠር ያሉ አንድ ወይም ሁለት አቀራረቦችን መለማመዱ ምን ብለን እንደምንናገር በአእምሮአችን ለመያዝ ያስችለናል። ይህም ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ በበለጠ ድፍረት እንድንናገር ያስችለናል።
4 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ብለው እንደሚናገሩ ብቻ ሳይሆን እንዴት አድርገው እንደሚናገሩም ጭምር ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 10:5, 6) በአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡት ትዕይንቶች ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት መናገር እንደምንችል ያሳያሉ። የሚመራው ወንድም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ቀርቦ የነበረ አንድ ሐሳብ ለአገልግሎት ሲሠማሩ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በመጥቀስ ክለሳ ያደርግ ይሆናል። ዝግጅት የተደረገበትና በጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ቀላል አቀራረብ ሐሳባችንን አሰባስበን መናገር እንድንችል ይረዳናል።
5 በተጨማሪም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በግል ሊያሳዩት ስለሚገባ ጠባይም መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 10:7, 8) ስለዚህ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብስባውን የሚመራው ወንድም ሥራችንን የሚያደናቅፍ ማንኛውንም ነገር እንድናስወግድ የሚረዱንን መመሪያዎች ሊሰጠን ይችላል። በየመንገዱ ማዕዘን ላይ ተኮልኩለን እንዳንታይ ወይም ከተቃዋሚዎች ጋር በመጨቃጨቅ ጊዜ እንዳናጠፋ ሊያስጠነቅቀን ይችላል። ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ትክክለኛ መዝገብ እንዲኖረን ወይም በተለያየ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ያሳስበን ይሆናል።
6 70ዎቹ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን መመሪያዎች ተከትለው ሠሩ። በኋላም ‘ደስ ብሏቸው’ ተመለሱ። (ሉቃስ 10:17) እኛም በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ላይ የተሰጡትን መመሪያዎች ከተከተልን የመንግሥቱን መልእክት በመስበክ የምናገኘው ደስታ እንደሚጨምር ልንጠባበቅ እንችላለን። — ሥራ 13:48, 49, 52