የሰዎች ግዴለሽነት በእናንተ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
1 ግዴለሽነት ማለት ስሜት የለሽ ወይም ደንታ ቢስ መሆን፣ ፍላጎት ማጣት ወይም ትኩረት አለመስጠት ነው። በአገልግሎት ብዙ ጊዜ ከሚያጋጥሙንና ይበልጥ አስቸጋሪ ከሆኑት ዝንባሌዎች መካከል አንዱ ነው። የሰዎች ግዴለሽነት በእናንተ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? አገልግሎታችሁን እንድትቀንሱ አድርጓችኋልን? የመንግሥቱን መልዕክት ለሰዎች ለማዳረስ የሰዎችን ግዴለሽነት ማሸነፍ የምትችሉት እንዴት ነው?
2 በመጀመሪያ ደረጃ በክልላችሁ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ግዴለሽ ያደረጋቸው ነገር ምን እንደሆነ እወቁ። በፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው ቅር መሰኘታቸው ነውን? ለገጠሟቸው ችግሮች ምንም መፍትሔ እንደ ሌለ ይሰማቸዋልን? የተሻለ ነገር ይመጣል የሚሉ ተስፋዎችን ይጠራጠራሉ? ወዲያውኑ ሊጨበጡ የሚችሉ ጥቅሞችን እስካላገኙ ድረስ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ማሰብ ስለማይፈልጉ ነውን?
3 የመንግሥቱን ተስፋ አጉላ፦ የአምላክ መንግሥት ማስወገድ የማይችለው ምንም ዓይነት ችግር የለም። ይህን በምንናገርበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አውጥቶ ማንበብ የማያመች ቢሆንም እንኳ ከቅዱሳን ጽሑፎች ቁልፍ ሐሳቦችን መናገር ይኖርብናል። (ዕብ. 4:12) ሆኖም ጭውውቱ ወደዚህ ነጥብ እንዲያመራ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ሰዎች ቤታቸው ድረስ የመጣንበትን ዓላማ እንዲረዱት ያስፈልጋል። ወደ እነርሱ የምንሄደው ለጎረቤቶቻችን ካለን ፍቅርና ለኅብረተሰቡ ካለን አሳቢነት የተነሳ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያስፈልጋል። በደንብ የታሰበበት ጥያቄ፣ ለምሳሌ “መፍትሔው ምንድን ነው? ብለው ያስባሉ” ብሎ መጠየቅ ይቻላል። አንዱ ዓይነት አቀራረብ ካልተሳካላችሁ ሌላ ሞክሩ። ሆኖም በኅብረተሰቡ ውስጥ ባሉ ፖለቲካዊ ውዝግቦች ለአንዱ የወገናችሁ የሚያስመስሉ ጥያቄዎችንና ሐሳቦችን ለማስወገድ መጣር ይኖርባችኋል።
5 በጣም ሃብታም የሆኑ ሰዎች በሚኖሩበት አንድ ክልል ውስጥ የቤቶቹ ባለቤቶች ለመንግሥቱ መልእክት ግዴለሾች በመሆናቸው በዚያ የሚያገለግሉ አስፋፊዎች ፍላጎት የሚቀሰቅስ መግቢያ ለመጠቀም ጥረት አደረጉ። አንድ ባልና ሚስት እውቀት የተባለውን መጽሐፍ በሚያበረክቱበት ጊዜ የሚከተለውን መግቢያ ሞከሩ:- “በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ስኬታማ ለመሆን ጥሩ ትምህርት አስፈላጊ ነው ብለው ያስባሉ? የተሟላ ትምህርት ማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትንም እንደሚጨምር ይስማማሉ?” አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ሦስት መጻሕፍት ያበረከቱ ሲሆን ከተበረከተላቸው ሰዎች መካከል አንዲት ሴት መላውን የእውቀት መጽሐፍ እንዳነበበችውና መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት መስማማቷን በሌላ ጊዜ ገልጻለች።
6 ግዴለሽነት በሚያጋጥምህ ጊዜ የተለያዩ አቀራረቦች ተጠቀም፣ የሚያመራምሩ ጥያቄዎችን ጠይቅ እንዲሁም የአምላክ ቃል ባለው ኃይልም ተጠቀም። እንዲህ በማድረግ እኛ ያገኘነውን አስደናቂ የሆነ የመንግሥቱን ተስፋ ሌሎችም እንዲቀበሉ ልትረዳቸው ትችላለህ።