“አልፈልግም”
1 በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ለመልእክታችን እንደዚህ ዓይነት ምላሽ መስጠታቸው የተለመደ ነው። ታዲያ በክልላችን ውስጥ ግዴለሽ ሰዎች ሲያጋጥሙን ተስፋ እንዳንቆርጥ ምን ሊረዳን ይችላል? ሰዎች ምሥራቹን ለመስማት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ምን ልናደርግ እንችላለን?
2 ደስተኛ ሆኖ መቀጠል:- ብዙ ሰዎች ለመልእክቱ ግዴለሽ የሆኑበትን ምክንያት ማስታወሳችን ደስተኛ ሆነን ለመቀጠል ይረዳናል። አብዛኛውን ጊዜ የምናነጋግራቸው ግለሰቦች ከሃይማኖት መሪዎች ወይም ከሌሎች ሰዎች በሚሰሙት ነገር የተነሳ ጭፍን ጥላቻ ሊያድርባቸው ይችላል። የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ የተማሩ ወይም አምላክ የለሽ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ ያደጉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቀሜታ አይገነዘቡ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ በሃይማኖት ውስጥ በሚመለከቱት ግብዝነት የተነሳ ግራ ተጋብተው ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ግዴለሽ የሆኑት በሁኔታዎች ተበሳጭተው ወይም ተስፋ ቆርጠው ይሆናል። (ኤፌ. 2:12) የኑሮ ጭንቀቶች ስለከበዷቸው ‘ምን እንደሚመጣ ማወቅ’ ወይም ማስተዋል የተሳናቸውም አሉ።—ማቴ. 24:37-39
3 አንዳንዶች ምንም ዓይነት አሉታዊ ምላሽ ቢሰጡንም ጥረታችን ይሖዋን እንደሚያስከብር ማወቃችን በአገልግሎታችን ደስተኞች ሆነን ለመቀጠል ያስችለናል። (1 ጴጥ. 4:11) ከዚህም በተጨማሪ የመልእክታችንን ጥቅም ለማይገነዘቡት ሰዎችም ጭምር ስለ እውነት መናገራችን የራሳችንን እምነት ያጠናክርልናል። በክልላችን ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር እንጣር። ይሖዋ “ቀኝና ግራቸውን ለይተው” ላላወቁት የነነዌ ሰዎች በጣም አዝኖላቸው ነበር። (ዮናስ 4:11) በክልላችን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹ ያስፈልጋቸዋል! ስለዚህ ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረግ የምንችልባቸውን መንገዶች መፈላለግ እንጂ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም።
4 በአካባቢው አሳሳቢ ስለሆነ ጉዳይ መወያየት:- ምናልባት በመግቢያህ ላይ በአካባቢው አሳሳቢ ስለሆነ ጉዳይ አንስተህ የቤቱ ባለቤት ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት መጠየቅ ትችል ይሆናል። በሚናገርበት ጊዜ አዳምጠው፤ ከዚያም ባሳሰበው ጉዳይ ላይ ተመርኩዘህ የመጽሐፍ ቅዱስን አጽናኝ መልእክት አሳየው። በአንድ አካባቢ አሳዛኝ ሁኔታ ከተከሰተ በኋላ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ላገኛቸው ሰዎች በሙሉ በሁኔታው የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጽ ነበር። ስለ ሁኔታው እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ሰዎቹ ወዲያውኑ መናገር ጀመሩ። . . . ሕይወታቸውን በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረጌ በዚያን ዕለት ብዙ አስደሳች ውይይቶች ማድረግ ችያለሁ።”
5 የሰው ልጆች የሚያጋጥማቸው ማንኛውም ችግር በአምላክ መንግሥት መፍትሔ ያገኛል። የምታነጋግረው ሰው ይበልጥ የሚያሳስቡትን ችግሮች ለመረዳት ሞክር። ምናልባት የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ እንድታብራራለት አጋጣሚ ይሰጥህ ይሆናል። አለዚያ ደግሞ በሌላ ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ “ዳግመኛ ለመስማት” ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።—ሥራ 17:32