የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 4—ዘኁልቁ
ጸሐፊው፦ ሙሴ
የተጻፈበት ቦታ፦ ምድረ በዳ እና የሞዓብ ሜዳ
ተጽፎ ያለቀው፦ 1473 ከዘአበ
የሚሸፍነው ጊዜ፦ 1512-1473 ከዘአበ
በእስራኤላውያን የምድረ በዳ ጉዞ ወቅት የተከናወኑ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መመዝገባቸው በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው ሰዎች ጥቅም ሲባል ነው።a ሐዋርያው ጳውሎስ “ክፉ . . . እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 10:6) በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ የሰፈረው ግልጽ ዘገባ በሕይወት መትረፋችን የተመካው የይሖዋን ስም በመቀደሳችን፣ በማንኛውም ሁኔታ ሥር እሱን በመታዘዛችንና እርሱ ለወከላቸው ሰዎች አክብሮት በማሳየታችን ላይ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጽልናል። ለሕዝቡ ሞገሱ እንዲያሳይ የሚያነሳሳው ታላቅ ምህረቱና ይገባናል የማንለው ደግነቱ እንጂ የእነርሱ ጥሩነት ወይም መልካም ሥራ አይደለም።
2 ከምዕራፍ 1-4 እና 26 ላይ ተዘግቦ በሚገኘው መሠረት ዘኁልቁ [በእንግሊዝኛ ነምበርስ] የሚለው የመጽሐፉ ስም በመጀመሪያ በሲና ተራራ ከጊዜ በኋላ ደግሞ በሞዓብ ሜዳ የተደረገውን የሕዝብ ቆጠራ የሚያመለክት ነው። ይህ ስም ኑመራይ ከሚለው የላቲን ቩልጌት ትርጉም የተወሰደና በግሪክኛው የሴፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ ካለው አሪትሞይ ከሚለው ቃል የተገኘ ነው። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን መጽሐፉን በሚድ ባር የሚል ተስማሚ ስም የሰጡት ሲሆን “በምድረ በዳ“ የሚል ትርጉም አለው። ሚድ ባር የሚለው ዕብራይስጥ ቃል ከተማም ሆነ መንደር የሌለውን ባዶ ቦታ ያመለክታል። በዘኁልቁ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡት ክንውኖች የተፈጸሙት ከከነዓን በስተ ደቡብና በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ምድረ በዳ ነበር።
3 ዘኁልቁ ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትን አምስት መጻሕፍት የያዘው ጥንታዊ ጥራዝ ክፍል እንደነበር የተረጋገጠ ነው። የመጀመሪያው ቁጥር “ም“ የሚለውን መስተፃምር በመጠቀም ከዚያ በፊት ካለው ታሪክ ጋር ያያይዘዋል። በመሆኑም መጽሐፉን የጻፈው ከዚያ በፊት ያሉትን ዘገባዎች የጻፈው ሙሴ መሆን አለበት። በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኘው “ሙሴም . . . ጻፈ“ ከሚለው ሐረግና በመጽሐፉ ማብቂያ ላይ ከሚገኘው “እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የእስራኤልን ልጆች . . . ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው” ከሚለው የመደምደሚያ ሐሳብ የጸሐፊውን ማንነት ግልጽ ያደርጉልናል።—ዘኁ. 33:2፤ 36:13
4 እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ ገና ከአንድ ዓመት ብዙም አልበለጣቸውም ነበር። የዘኁልቁ ዘገባ የሚጀምረው እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ከወጡ በኋላ ያለውን ታሪክ በመተረክ ሲሆን ከ1512 እስከ 1473 ከዘአበ ድረስ ያለውን የ38 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጊዜ የሚሸፍን ነው። (ዘኁ. 1:1፤ ዘዳ. 1:3) በዘኁልቁ 7:1-88 እና 9:1-15 ላይ የሚገኙት ክንውኖች በዚህ ወቅት የተፈጸሙ ባይሆኑም ተጨማሪ መረጃ ሆነው ቀርበዋል። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍል ክንውኖቹ በተፈጸሙበት ጊዜ የተጻፉ መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም፤ ሆኖም ሙሴ የ40 ዓመቱ የምድረ በዳ ጉዞ እስካበቃበት ይኸውም እስከ 1473 ከዘአበ መግቢያ ድረስ የዘኁልቁን መጽሐፍ ጽፎ ሊጨርስ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው።
5 የዘገባውን ትክክለኛነት ለመጠራጠር የሚያበቃ ምንም ምክንያት የለም። የተጓዙበት ምድር በአብዛኛው ደረቅ ሲሆን ሙሴም ’ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ምድረ በዳ’ ሲል ገልጾታል። ይህ እውነት መሆኑን ደግሞ ዛሬም እንኳን ሳይቀር ተበታትነው በሚገኙትና የግጦሽ መሬትና ውኃ ፍለጋ ዘወትር ከቦታ ቦታ ከሚዘዋወሩት ነዋሪዎቹ ሁኔታ መመልከት ይቻላል። (ዘዳ. 1:19) ከዚህም በተጨማሪ የብሔሩን አሰፋፈር፣ በሰልፍ የሚጓዙበትን ሥርዓትና በካምፕ ውስጥ ለሚከናወኑ ጉዳዮች መመሪያ የሚሰጡ የመለከት ድምፆችን የሚመለከቱት ዝርዝር መመሪያዎች ታሪኩ የተጻፈው በ“ምድረ በዳ“ መሆኑን ያረጋግጣሉ።—ዘኁ. 1:1
6 የከነዓንን ምድር ሰልለው የተመለሱት ሰላዮች “ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው” በማለት ያቀረቡት አሸባሪ ሪፖርት እንኳን ሳይቀር የአርኪኦሎጂ ድጋፍ አለው። (13:28) በዚያን ወቅት የነበሩት የከነዓን ነዋሪዎች በሰሜን ከኢይዝራኤል ሸለቆ አንስቶ በደቡብ በኩል እስከሚገኘው እስከ ጌራራ ድረስ በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እርስ በርሳቸው የተያያዙ ምሽጎችን በመሥራት ይዞታቸውን አጠናክረው እንደነበር ዘመናዊ ግኝቶች ያሳያሉ። ከተሞቹ የተጠናከረ ምሽግ የነበራቸው ከመሆኑም በላይ የተገነቡት ከፍ ባሉ ቦታዎችን ላይ ነበር፤ እንዲሁም ከቅጥሮቻቸው ከፍ ብለው የሚገኙ ማማዎች ነበሯቸው። ይህም ለብዙ ዘመን በተንጣለለው የግብጽ ምድር ይኖሩ እንደነበሩት እስራኤላውያን ባሉት ሕዝቦች ዘንድ አስፈሪ አድርጓቸው ነበር።
7 የዓለም መንግሥታት ድክመቶቻቸውን ሸፋፍነው ድላቸውን አጉልተው መናገር የሚቀናቸው ቢሆንም በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ዘገባ ግን ታሪካዊ እውነትን በሚያሳይ ሐቀኝነት አማሌቃውያንና ከነዓናውያን እስራኤላውያንን ፈጽመው እንዳሳደዷቸው ይናገራል። (14:45) ሕዝቡ እምነት የለሾች እንደሆኑና ለአምላክ አክብሮት እንደጎደላቸው በግልጽ ይናገራል። (14:11) የአምላክ ነቢይ የሆነው ሙሴ በፍጹም ግልጽነት የሕዝቡን፣ የወንድሙን ልጆች እንዲሁም የወንድሙንና የእህቱን ኃጢአት አጋልጧል። የራሱንም ድክመት ቢሆን አልሸሸገም። በመሪባ ውኃ እንዲፈልቅ ባደረጉ ጊዜ ይሖዋ እንዲከበር ባለማድረጉ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብቱን ማጣቱን ተናግሯል።—3:4፤ 12:1-15፤ 20:7-13
8 ዘገባው በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ጠቃሚ የሆኑት ቅዱሳን ጽሑፎች እውነተኛ ክፍል መሆኑን የሚያረጋግጠው ዋና ዋናዎቹን ክንውኖች በሙሉ ለማለት ይቻላል ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችንም ጨምሮ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በቀጥታ መጠቀሳቸው ሲሆን አብዛኞቹም ጸሐፊዎች እነዚህ ነጥቦች ያላቸውን ትርጉም ጎላ አድርገው ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል ኢያሱ (ኢያሱ 4:12፤ 14:2)፣ ኤርምያስ (2 ነገ. 18:4)፣ ነህምያ (ነህ. 9:19-22)፣ አሳፍ (መዝ. 78:14-41)፣ ዳዊት (መዝ. 95:7-11)፣ ኢሳይያስ (ኢሳ. 48:21)፣ ሕዝቅኤል (ሕዝ. 20:13-24)፣ ሆሴዕ (ሆሴዕ 9:10)፣ አሞጽ (አሞጽ 5:25)፣ ሚክያስ (ሚክ. 6:5)፣ ሉቃስ ስለ እስጢፋኖስ ንግግር ያቀረበው ዘገባ (ሥራ 7:36)፣ ጳውሎስ (1 ቆሮ. 10:1-11)፣ ጴጥሮስ (2 ጴጥ. 2:15, 16)፣ ይሁዳ (ይሁዳ 11) እና ኢየሱስ ለጴርጋሞን ጉባኤ ስለተናገራቸው ቃላት ዮሐንስ ያቀረበው ዘገባ (ራእይ 2:14) ይገኙበታል። እነዚህ በሙሉ በዘኁልቁ የሚገኘውን ታሪክ የሚጠቅሱ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱም እንዲሁ አድርጎ ነበር።—ዮሐ. 3:14
9 ታዲያ የዘኁልቁ መጽሐፍ ዓላማ ምንድን ነው? ዘገባው ከታሪካዊ ቅርስነት የበለጠ ጠቀሜታ አለው። የዘኁልቁ መጽሐፍ ይሖዋ የሥርዓት አምላክ መሆኑንና ፍጥረታቱ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲሰጡት የሚፈልግ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። አንባቢው ስለ እስራኤላውያን መቆጠር እንዲሁም መፈተንና መጥራት በሚያነብበት ጊዜ በአእምሮው ውስጥ ይህ ሐቅ ይቀረጻል። በተጨማሪም የሕዝቡ ለመታዘዝ እምቢተኛ መሆንና ዓመፀኛ አካሄዳቸው ይሖዋን መታዘዝ ያለውን አስፈላጊነት የሚያጎላ ታሪክ መሆኑን ይገነዘባል።
10 ዘገባው ተጠብቆ የቆየው ለሚመጡት ትውልዶች ጥቅም ሲባል መሆኑን አሳፍ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፣ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፣ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፤ እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ፣ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፣ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፣ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች።” (መዝ. 78:7, 8) በዘኁልቁ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹ ክንውኖች በተደጋጋሚ ጊዜያት በመዝሙራት ውስጥ የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህም መዝሙሮች አይሁዳውያኑ ቅዱስ አድርገው የሚመለከቷቸውና ለብሔሩ ጠቃሚ በመሆናቸውም በተደጋጋሚ የሚያነቧቸው ክፍሎች ነበሩ።—መዝ. 78, 95, 105, 106, 135, 136
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
32 ኢየሱስ በተለያዩ ጊዜያት ከዘኁልቁ መጽሐፍ የጠቀሰ ሲሆን ሐዋርያቱም ሆኑ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ዘገባ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለና በጣም ጠቃሚ መሆኑን በግልጽ አሳይተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስን የታማኝነት አገልግሎት ታሪኩ በአብዛኛው በዘኁልቁ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኘው ከሙሴ ጋር በቀጥታ አነጻጽሮታል። (ዕብ. 3:1-6) የእንስሳት መሥዋዕቱና በዘኁልቁ 19:2-9 ላይ የምትገኘው የቀይ ጊደር አመድ መረጨት በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ከኃጢአት የመንጻት የላቀ ዝግጅት በሥዕላዊ ሁኔታ ለመመልከት እንችላለን።—ዕብ. 9:13, 14
33 በተመሳሳይም ጳውሎስ በምድረ በዳ ከነበረው ዓለት ውኃ መፍለቁ ለእኛ ትርጉም ያለው ነገር እንደሆነ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፣ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።” (1 ቆሮ. 10:4፤ ዘኁ. 20:7-11) ክርስቶስ ራሱ ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፣ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል።”—ዮሐ. 4:14
34 በተጨማሪም ኢየሱስ ራሱ አምላክ በእርሱ በኩል ላደረገው ድንቅ ዝግጅት ጥላ የሆነና በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ አንድ ክንውን በቀጥታ ጠቅሷል። “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” ብሏል።—ዮሐ. 3:14, 15፤ ዘኁ. 21:8, 9
35 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት ይህል እንዲቅበዘበዙ የተደረጉት ለምንድን ነው? በእምነት ማጣት ምክንያት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፦ “ወንድሞች ሆይ፣ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፣ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፣ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ። “ ለመታዘዝ እምቢተኞችና እምነት የለሾች በመሆናቸው እነዚያ እስራኤላውያን በምድረ በዳ አልቀዋል። “እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ [የአምላክ] ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።” (ዕብ. 3:7–4:11፤ ዘኁ. 13:25–14:38) ይሁዳ ቅዱስ የሆኑ ነገሮችን ስለሚሳደቡ አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች ሲያስጠነቅቅ በለዓም ሽልማት ለማግኘት ሲል በስስት ያደረገውንና ቆሬ የይሖዋ አገልጋይ በሆነው በሙሴ ላይ በማመፅ የተናገረውን ነገር ጠቅሷል። (ይሁዳ 11፤ ዘኁ. 22:7, 8, 22፤ 26:9, 10) በተጨማሪም ጴጥሮስ በለዓምን “የዓመፃን ደመወዝ [ወደደ]”በማለት የገለጸው ሲሆን ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ደግሞ ለዮሐንስ በገለጠለት ራእይ ላይ “እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን [ያኖረ]” ብሎታል። በዛሬው ጊዜ የሚገኘው ክርስቲያን ጉባኤም እንደነዚህ ካሉ የረከሱ ሰዎች እንዲጠበቅ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው ይገባል።—2 ጴጥ. 2:12-16፤ ራእይ 2:14
36 በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የሥነ ምግባር ጉድለት በተከሰተ ጊዜ ጳውሎስ የዘኁልቁ መጽሐፍን በቀጥታ በመጥቀስ ’ክፉ ነገር ስለ መመኘታቸው’ ጽፏል። “ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን” በማለት አሳስቧል። (1 ቆሮ. 10:6, 8፤ ዘኁ. 25:1-9፤ 31:16)b የአምላክን ሕግ መታዘዝ ችግር ያስከትላል በማለት ሕዝቡ ስላማረሩበት ወቅትና ይሖዋ ባወረደላቸው መና አለመደሰታቸውን በገለጹበት ወቅት ስለሆነው ነገር ምን ለማለት ይቻላል? ይህን በተመለከተ ጳውሎስ “ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን” ብሏል። (1 ቆሮ. 10:9፤ ዘኁ. 21:5, 6) ከዚያም ጳውሎስ በመቀጠል “ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጐራጐሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐራጒሩ” ብሏል። እስራኤላውያን በይሖዋ፣ እርሱ በወከላቸው ሰዎችና በዝግጅቶቹ ላይ በማማረራቸው ምክንያት የደረሰባቸው ነገር እንዴት የከፋ ነው! እነዚህ ’እንደ ምሳሌ የሆኑባቸው’ ነገሮች ይሖዋን በሙሉ እምነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል በዛሬው ጊዜ ለምንገኘውም ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሊሆኑን ይገባል።—1 ቆሮ. 10:10, 11፤ ዘኁ. 14:2, 36, 37፤ 16:1-3, 41፤ 17:5, 10
37 በተጨማሪም የዘኁልቁ መጽሐፍ ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በተመለከተ የተሻለ ማስተዋል ለማግኘት የሚረዱ ታሪኮችን ይዟል።—ዘኁ. 28:9, 10—ማቴ. 12:5፤ ዘኁ. 15:38—ማቴ. 23:5፤ ዘኁ. 6:2-4—ሉቃስ 1:15፤ ዘኁ. 4:3—ሉቃስ 3:23፤ ዘኁ. 18:31—1 ቆሮ. 9:13, 14፤ ዘኁ. 18:26—ዕብ. 7:5-9፤ ዘኁ. 17:8-10—ዕብ. 9:4
38 በዘኁልቁ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ በእርግጥም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ለይሖዋ መታዘዝና በሕዝቡ መካከል የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ለሾማቸው አክብሮት ማሳየት ያለውን አስፈላጊነት የሚያስተምረን በመሆኑ ጠቃሚ ነው። በምሳሌዎች አማካኝነት መጥፎ ድርጊትን የሚያወግዝ ሲሆን ትንቢታዊ አንደምታ ባላቸው ክስተቶች ደግሞ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሕዝቡ አዳኝና መሪ አድርጎ በሾመው አካል ላይ እንድናተኩር ያደርጋል። መካከለኛና ሊቀ ካህናት ሆኖ በተሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ ከሚመራው የይሖዋ ጽድቅ መንግሥት መቋቋም ጋር የሚዛመዱ ጠቃሚና ትምህርት ሰጪ ዘገባዎችን ይዟል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]