የጥናት ርዕስ 35
መዝሙር 121 ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል
ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
“ኃጢአት ለሰውነታችሁ ምኞት ተገዢ እንድትሆኑ በማድረግ ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ።”—ሮም 6:12
ዓላማ
(1) የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ማሸነፍ እንዲሁም (2) ለፈተና እጅ ከመስጠት መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
1. ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በሙሉ የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
ይሖዋ የሚጠላውን አንድ ድርጊት የመፈጸም ከፍተኛ ምኞት አድሮብህ ያውቃል? ከሆነ እንዲህ ያለ ከባድ ፈተና ያጋጠመህ አንተ ብቻ እንደሆንክ ሊሰማህ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም” ይላል። (1 ቆሮ. 10:13) ስለዚህ አንተን የሚያታግልህ መጥፎ ምኞት ምንም ይሁን ምን ሌሎችም ከዚህ ምኞት ጋር እየታገሉ ነው ማለት ነው። ብቻህን አይደለህም፤ ደግሞም በይሖዋ እርዳታ ትግሉን ማሸነፍ ትችላለህ።
2. አንዳንድ ክርስቲያኖችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ከየትኞቹ ፈተናዎች ጋር ሊታገሉ ይችላሉ? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
2 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል” ይላል። (ያዕ. 1:14) አንድን ሰው የሚያታልለው ነገር ከሌላ ሰው የተለየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተቃራኒ ፆታ ካለው ሰው ጋር የፆታ ብልግና ለመፈጸም ሊፈተኑ ይችላሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ተመሳሳይ ፆታ ካለው ሰው ጋር የፆታ ብልግና ለመፈጸም ሊፈተኑ ይችላሉ። ፖርኖግራፊ መመልከታቸውን ያቆሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች በድጋሚ ፖርኖግራፊ የመመልከት ከፍተኛ ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል። ዕፅ መውሰድ ወይም ከመጠን በላይ መጠጣት ያቆሙ በርካታ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ፈተና ያጋጥማቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያኖችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ከሚያታግሏቸው ምኞቶች መካከል እነዚህ አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው። ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ የሆነ ወቅት ላይ የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ተሰምቶን እንደሚያውቅ ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።”—ሮም 7:21
ፈተና ሳንጠብቀው በማንኛውም ጊዜና በማንኛውም ቦታ ሊያጋጥመን ይችላል (አንቀጽ 2ን ተመልከት)c
3. አንድ ሰው ከማያባራ መጥፎ ምኞት ጋር የሚታገል ከሆነ ምን ሊሰማው ይችላል?
3 ከማያባራ መጥፎ ምኞት ጋር እየታገልክ ከሆነ አቅመ ቢስ እንደሆንክ ማለትም ፈተናውን ለማሸነፍ የሚያስችል ኃይል እንደሌለህ ሊሰማህ ይችላል። በተጨማሪም ተስፋ ቢስ እንደሆንክ ማለትም መጥፎ ምኞት ስላደረብህ ብቻ ይሖዋ እንደሚፈርድብህ ሊሰማህ ይችላል። ሁለቱም ሐሳቦች ትክክል እንዳልሆኑ እርግጠኛ ሁን። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ይህ ርዕስ ሁለት ጥያቄዎችን ይመልስልናል፦ (1) የአቅመ ቢስነትና የተስፋ ቢስነት ስሜት የሚመነጨው ከየት ነው? (2) ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምታደርገው ትግል አሸናፊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
“ክፉው” ምን እንዲሰማን ይፈልጋል?
4. (ሀ) ሰይጣን አቅመ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን የሚፈልገው ለምንድን ነው? (ለ) ከፈተና ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስ አይደለንም የምንለው ለምንድን ነው?
4 ሰይጣን መጥፎ ነገር ለማድረግ በምንፈተንበት ጊዜ አቅመ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን ይፈልጋል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ጸሎት ባስተማራቸው ጊዜ ይህን ግልጽ አድርጓል፤ እንዲህ ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል፦ “ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።” (ማቴ. 6:13) ሰይጣን፣ የሰው ልጆች ፈተና ሲያጋጥማቸው ይሖዋን ለመታዘዝ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ተናግሯል። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን እንዲህ ማለቱ አያስገርምም? በራሱ ምኞት የተታለለውና ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ፈቃደኛ ያልሆነው ሰይጣን ራሱ ነው። እኛም ልክ እንደ እሱ እንደሆንንና ፈተና ሲያጋጥመን ይሖዋን ወዲያውኑ እንደምንተወው የሚያስብ ይመስላል። እንዲያውም ሰይጣን፣ ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ እንኳ በፈተና ሊሸነፍ እንደሚችል ተሰምቶታል። (ማቴ. 4:8, 9) እንደው ግን ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል በእርግጥ አቅመ ቢስ ነን? በጭራሽ! ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፈው በሚከተለው ሐሳብ እንስማማለን፦ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵ. 4:13
5. ይሖዋ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች መሆን እንደምንችል እንደሚተማመንብን እንዴት እናውቃለን?
5 ከሰይጣን ፍጹም በተለየ መልኩ ይሖዋ መጥፎ ምኞቶችን ማሸነፍ እንደምንችል ይተማመንብናል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም ይሖዋ ንጹሕ አቋማቸውን የጠበቁ እጅግ ብዙ ሕዝብ ከታላቁ መከራ በሕይወት እንደሚተርፉ ተናግሯል። ይህ ምን ማለት ነው? ሊዋሽ የማይችለው ይሖዋ፣ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ነጭ ያደረጉ’ እጅግ ብዙ ሕዝብ ንጹሕ አቋም ይዘው ወደ አዲሱ ዓለም እንደሚገቡ ተናግሯል። (ራእይ 7:9, 13, 14) በእርግጥም ይሖዋ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስ እንደሆንን እንደማይሰማው ግልጽ ነው።
6-7. ሰይጣን ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምንታገልበት ጊዜ ተስፋ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን የሚፈልገው ለምንድን ነው?
6 ሰይጣን አቅመ ቢስ እንደሆንን ብቻ ሳይሆን ተስፋ ቢስ እንደሆንን ማለትም መጥፎ ምኞቶች ስላደሩብን ብቻ ይሖዋ እንደሚፈርድብን እንድናስብ ይፈልጋል። ሰይጣን እንዲህ ብሎ ማሰቡስ አያስገርምም? ተስፋ ቢስ የሆነው ሰይጣን ራሱ ነው፤ የዘላለም ሕይወት አይገባውም ብሎ ይሖዋ ፈርዶበታል። (ዘፍ. 3:15፤ ራእይ 20:10) ሰይጣን እኛም የተስፋ ቢስነት ስሜት እንዲሰማን እንደሚፈልግ ጥያቄ የለውም፤ ምክንያቱም እሱ የተከለከለውን በረከት ይኸውም የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ አለን። ይሁንና ሰይጣን እንድናስብ ከሚፈልገው በተለየ መልኩ እኛ ተስፋ ቢስ አይደለንም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በእኛ ላይ ለመፍረድ ሳይሆን እኛን ለመርዳት እንደሚፈልግ ዋስትና ይሰጠናል። እሱ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።”—2 ጴጥ. 3:9
7 በመሆኑም ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስ ወይም ተስፋ ቢስ እንደሆንን የሚሰማን ከሆነ እንዲህ እንድናስብ የሚፈልገው ሰይጣን እንደሆነ እናስታውስ። ይህን መገንዘባችን እሱን ለመቃወም ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ይረዳናል።—1 ጴጥ. 5:8, 9
ኃጢአተኛ መሆናችን ምን እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል?
8. ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስና ተስፋ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን የሚያደርገው ሌላው ነገር ምንድን ነው? (መዝሙር 51:5) (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውንም ተመልከት።)
8 ከሰይጣን በተጨማሪ፣ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስና ተስፋ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን ሊያደርግ የሚችል ሌላም ነገር አለ። ምንድን ነው? ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የወረስነው ኃጢአት ነው።a—ኢዮብ 14:4፤ መዝሙር 51:5ን አንብብ።
9-10. (ሀ) አዳምና ሔዋን ኃጢአተኛ መሆናቸው ምን ስሜት አሳድሮባቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ኃጢአተኛ መሆናችን ምን ተጽዕኖ ያሳድርብናል?
9 አዳምና ሔዋን ኃጢአተኛ መሆናቸው ምን ስሜት እንዳሳደረባቸው እንመልከት። በይሖዋ ላይ ካመፁ በኋላ ተደበቁ፤ እንዲሁም ሰውነታቸውን ለመሸፈን ሞከሩ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ይህን ያደረጉበትን ምክንያት ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ኃጢአት የበደለኝነት፣ የጭንቀት፣ የስጋትና የኀፍረት ስሜት እንዲሰማቸው አደረገ።” አዳምና ሔዋን የበደለኝነት ስሜት፣ ጭንቀት፣ ስጋትና ኀፍረት የሚባሉ አራት ክፍሎች ብቻ ባሉት ቤት ውስጥ እንደተቆለፈባቸው ሊቆጠር ይችላል። አዳምና ሔዋን ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ክፍል መዘዋወር ቢችሉም ከቤቱ መውጣት አይችሉም። በሌላ አባባል፣ ከኃጢአት ነፃ መውጣት አይችሉም።
10 እርግጥ ነው፣ እኛ ያለንበት ሁኔታ ከአዳምና ከሔዋን የተለየ ነው። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከቤዛው መጠቀም አይችሉም። እኛን ግን ቤዛው ከኃጢአት ነፃ ያወጣናል፤ እንዲሁም ንጹሕ ሕሊና ይሰጠናል። (1 ቆሮ. 6:11) ያም ቢሆን የወረስነው ኃጢአት አለ። በመሆኑም እኛም የበደለኝነት፣ የጭንቀት፣ የስጋትና የኀፍረት ስሜት የሚሰማን መሆኑ አያስገርምም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች አሁንም በኃጢአት ቁጥጥር ሥር እንዳሉ ይናገራል። ‘አዳም ትእዛዝ በመተላለፍ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ያልሠሩት’ ሰዎችም እንኳ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ናቸው። (ሮም 5:14) ይህ ሐሳብ ተስፋ አስቆራጭ ሊመስል ቢችልም በዚህ የተነሳ የአቅመ ቢስነትና የተስፋ ቢስነት ስሜት ሊሰማን አይገባም። እነዚህን አፍራሽ ስሜቶች ማሸነፍ እንችላለን። እንዴት?
ኃጢአት አዳምና ሔዋን የበደለኝነት፣ የጭንቀት፣ የስጋትና የኀፍረት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል (አንቀጽ 9ን ተመልከት)
11. አቅመ ቢስ እንደሆንን ሲሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ? (ሮም 6:12)
11 ኃጢአተኛ በመሆናችን የተነሳ፣ አቅመ ቢስ እንደሆንን ማለትም መጥፎ ምኞቶችን ማሸነፍ እንደማንችል ሊሰማን ይችላል። ሆኖም እንዲህ ብሎ የሚነግረንን በውስጣችን ያለውን ድምፅ ልንሰማው አይገባም። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት በእኛ ላይ “መንገሡን” እንዲቀጥል አለመፍቀድ እንደምንችል ይናገራል። (ሮም 6:12ን አንብብ።) ይህም ሲባል፣ መጥፎ ምኞቶችን ላለመፈጸም መምረጥ እንችላለን ማለት ነው። (ገላ. 5:16) ይሖዋ ፈተናን ማሸነፍ እንደምንችል ይተማመንብናል፤ ባይተማመንብን ኖሮ እንዲህ እንድናደርግ አይጠብቅብንም ነበር። (ዘዳ. 30:11-14፤ ሮም 6:6፤ 1 ተሰ. 4:3) በእርግጥም ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስ አይደለንም።
12. የተስፋ ቢስነት ስሜት ሲሰማን ምን ልናደርግ ይገባል? ለምንስ?
12 በተጨማሪም ኃጢአተኛ በመሆናችን የተነሳ፣ ተስፋ ቢስ እንደሆንን ማለትም መጥፎ ምኞቶች ስላደሩብን ብቻ ይሖዋ እንደሚፈርድብን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም እንዲህ ብሎ የሚነግረንን በውስጣችን ያለውን ድምፅ ልንሰማው አይገባም። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ኃጢአተኛ መሆናችንን እንደሚረዳ ያስተምረናል። (መዝ. 103:13, 14) እሱ ስለ እኛ “ሁሉንም ነገር ያውቃል”፤ የወረስነው ኃጢአት በእያንዳንዳችን ላይ ያሳደረውን መጥፎ ተጽዕኖ በሚገባ ይገነዘባል። (1 ዮሐ. 3:19, 20) መጥፎ ምኞቶችን በመፈጸም ለኃጢአት ዝንባሌያችን እጅ እስካልሰጠን ድረስ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም መያዝ እንችላለን። ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
13-14. መጥፎ ምኞቶች ስላደሩብን ብቻ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አንችልም ማለት ነው? አብራራ።
13 መጽሐፍ ቅዱስ በመጥፎ ድርጊት እና በመጥፎ ምኞት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ይናገራል። ድርጊታችንን መቆጣጠር እንችላለን፤ ምኞት ግን ሳናስበው ሊመጣ የሚችል ነገር ነው። ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ጉባኤ ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ግብረ ሰዶም ይፈጽሙ ነበር። ጳውሎስ “[አንዳንዶቻችሁ] እንደዚህ ነበራችሁ” ሲል ጽፏል። ታዲያ ይህ ሲባል፣ እነዚህ ሰዎች ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ ግብረ ሰዶም የመፈጸም ምኞት ጨርሶ አድሮባቸው አያውቅም ማለት ነው? እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ምኞቶች ብዙውን ጊዜ ሥር የሰደዱ ናቸው። ሆኖም ራሳቸውን በመግዛት ምኞታቸውን ከመፈጸም የተቆጠቡት ክርስቲያኖች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል። ‘ታጥበው እንደነጹ’ አድርጎ ቆጥሯቸዋል። (1 ቆሮ. 6:9-11) ስለ አንተም እንዲህ ሊባል ይችላል።
14 የሚያታግልህ መጥፎ ምኞት ምንም ይሁን ምን፣ ምኞቱን በማሸነፍ ረገድ ሊሳካልህ ይችላል። ምኞቱን ከናካቴው ማስወገድ ባትችልም እንኳ ራስህን መግዛት እንዲሁም ‘የሥጋህንና የሐሳብህን ፈቃድ ከመፈጸም’ መቆጠብ ትችላለህ። (ኤፌ. 2:3) ይህን ማድረግና ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምታደርገው ትግል አሸናፊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
አሸናፊዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
15. ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች መሆን ከፈለግን ለራሳችን ሐቀኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
15 ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምታደርገው ትግል አሸናፊ መሆን ከፈለግክ ድክመቶችህን በተመለከተ ለራስህ ሐቀኛ መሆን ይኖርብሃል። “የውሸት ምክንያት” እያቀረብክ ራስህን እንዳታታልል ተጠንቀቅ። (ያዕ. 1:22) ችግሩን ማቃለል፣ ለምሳሌ ‘ከእኔ የበለጠ የሚጠጡ ሌሎች ሰዎች አሉ’ ብሎ ማሰብ ወይም ደግሞ በሌሎች ላይ ማላከክ፣ ለምሳሌ ‘ሚስቴ ፍቅር ብታሳየኝ ኖሮ ፖርኖግራፊ ለማየት አልፈተንም ነበር’ ብሎ ማሰብ ለፈተናው በቀላሉ እጅ እንድትሰጥ ከማድረግ በቀር የሚፈይድልህ ነገር የለም። እንግዲያው በአስተሳሰብህም እንኳ ለመጥፎ አካሄድ ሰበብ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። ለድርጊትህ ኃላፊነት ውሰድ።—ገላ. 6:7
16. ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ያለህን ቁርጠኝነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?
16 ድክመቶችህን በተመለከተ ለራስህ ሐቀኛ ከመሆን በተጨማሪ ለድክመቶችህ እጅ ላለመስጠት ያለህን ቁርጠኝነት ማጠናከር ይኖርብሃል። (1 ቆሮ. 9:26, 27፤ 1 ተሰ. 4:4፤ 1 ጴጥ. 1:15, 16) ይበልጥ የሚከብድህ ምን ዓይነት ፈተና እንደሆነ እንዲሁም ለፈተና ይበልጥ ተጋላጭ የምትሆነው መቼ እንደሆነ አስብ። ይበልጥ የሚፈትንህ ምንድን ነው? ለፈተና ይበልጥ ተጋላጭ የምትሆነውስ በቀኑ ውስጥ የትኛው ሰዓት ላይ ነው? ለምሳሌ ሲደክምህ ወይም ማታ ስታመሽ ፈተናውን መቋቋም ይበልጥ ይከብድሃል? ምን ዓይነት ፈተና እንደሚገጥምህ አስቀድመህ አስብ፤ ከዚያም የምትሰጠውን ምላሽ በአእምሮህ ተለማመድ። ይህን ማድረግ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ ፈተናው ከመምጣቱ በፊት ነው።—ምሳሌ 22:3
17. ከዮሴፍ ምሳሌ ምን እንማራለን? (ዘፍጥረት 39:7-9) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
17 ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት ልታማልለው በሞከረችበት ወቅት ምን ዓይነት ምላሽ እንደሰጠ እንመልከት። ምንም ሳያቅማማ በቁርጠኝነት ጥያቄዋን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጾላታል። (ዘፍጥረት 39:7-9ን አንብብ።) ይህ ምን ያሳያል? ዮሴፍ የሌላ ሰው ሚስት እንደማይወስድ የወሰነው የጶጢፋር ሚስት እሱን ለማማለል ከመሞከሯ በፊት ነው። አንተም በተመሳሳይ፣ ፈታኝ ሁኔታ ከመምጣቱ በፊት ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ያለህን ቁርጠኝነት ማጠናከር ትችላለህ። እንዲህ ካደረግክ፣ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥምህ አስቀድመህ ያደረግከውን ውሳኔ መከተል ቀላል ይሆንልሃል።
እንደ ዮሴፍ ከፈተና ወዲያውኑ ራቅ! (አንቀጽ 17ን ተመልከት)
“ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ”
18. ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምታደርገው ትግል አሸናፊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (2 ቆሮንቶስ 13:5)
18 ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምታደርገው ትግል አሸናፊ ለመሆን ‘ዘወትር ራስህን መፈተሽ’ ማለትም ያለህበትን ሁኔታ አዘውትረህ መገምገም ይኖርብሃል። (2 ቆሮንቶስ 13:5ን አንብብ።) በየጊዜው አስተሳሰብህንና ምግባርህን በመገምገም አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ። ለምሳሌ አንድን ፈተና በተሳካ ሁኔታ ብታሸንፍም እንኳ ‘እንቢ ለማለት ምን ያህል ጊዜ ወስዶብኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ምላሽ ለመስጠት እንደዘገየህ ካስተዋልክ ራስህን አትውቀስ። ከዚህ ይልቅ ጊዜ ወስደህ መከላከያህን አጠናክር። እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራስህን መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦችን ከአእምሮዬ ለማስወገድ የሚወስድብኝን ጊዜ መቀነስ እችል ይሆን? የመዝናኛ ምርጫዬ ፈተናን መቋቋም ከባድ እንዲሆንብኝ እያደረገ ነው? ሥነ ምግባር የጎደላቸው ትዕይንቶች ሲያጋጥሙኝ ወዲያውኑ ዓይኔን እመልሳለሁ? የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል ራሴን መግዛት የሚጠይቅብኝ ቢሆንም እንኳ መሥፈርቶቹ ሁልጊዜም የተሻሉ የሆኑት ለምን እንደሆነ እገነዘባለሁ?’—መዝ. 101:3
19. ትናንሽ የሚመስሉ ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎችን ማድረጋችን ከመጥፎ ምኞቶች ጋር የምናደርገውን ትግል ከባድ የሚያደርግብን እንዴት ነው?
19 ለድርጊቶችህ ሰበብ ከማቅረብም መቆጠብ ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም” ይላል። (ኤር. 17:9) ኢየሱስም ከልብ “ክፉ ሐሳብ” እንደሚወጣ ተናግሯል። (ማቴ. 15:19) ለምሳሌ አንድ ሰው ፖርኖግራፊ መመልከት ካቆመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ እርቃን የሚያሳዩ እስካልሆኑ ድረስ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ፎቶዎችን ቢመለከት ችግር እንደሌለው ሊሰማው ይችላል። ወይም ደግሞ ‘ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እስካልፈጸምኩ ድረስ በመጥፎ ምኞቶች ላይ ባውጠነጥን ምንም ችግር የለውም’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ከዳተኛ የሆነው የዚህ ሰው ልብ ‘የሥጋ ፍላጎቱን ለማርካት ዕቅድ እያወጣ’ ነው ሊባል ይችላል። (ሮም 13:14) እንዲህ ከማድረግ መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው? ለኃጢአት እጅ እንደመስጠት ያሉ ጥበብ የጎደላቸው ትላልቅ ውሳኔዎችን ወደማድረግ የሚመሩ ጥበብ የጎደላቸው ትናንሽ ውሳኔዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለመለየት ሞክር፤ እንዲሁም እንዲህ ያሉ ትናንሽ ውሳኔዎችን ከማድረግ ተቆጠብ።b በተጨማሪም መጥፎ ምግባር ለመፈጸም ሰበብ የሚሆኑ ‘ክፉ ሐሳቦችን’ በሙሉ አስወግድ።
20. ወደፊት ምን ይጠብቀናል? አሁንስ ምን ዓይነት እርዳታ እናገኛለን?
20 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ በይሖዋ እርዳታ ፈተናን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ይኖረናል። በተጨማሪም በይሖዋ ምሕረት የተነሳ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን። በንጹሕ ልብና አእምሮ ይሖዋን ማገልገል ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! እስከዚያው ድረስ ግን፣ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስም ሆነ ተስፋ ቢስ እንዳልሆንን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ጥረታችንን ስለሚባርክልን አሸናፊዎች መሆን እንችላለን!
መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!
a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኃጢአት” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው እንደ ስርቆት፣ ምንዝር ወይም ግድያ ያሉትን ድርጊቶች ነው። (ዘፀ. 20:13-15፤ 1 ቆሮ. 6:18) አንዳንድ ጥቅሶች ላይ ግን “ኃጢአት” የሚለው ቃል ስንወለድ ጀምሮ የወረስነውን ዝንባሌ ያመለክታል፤ ያኔ ገና ምንም የኃጢአት ድርጊት ባንፈጽምም እንኳ የኃጢአት ዝንባሌን ወርሰናል።
b በምሳሌ 7:7-23 ላይ የተጠቀሰው ወጣት ለፆታ ብልግና እጅ በመስጠት ጥበብ የጎደለው ትልቅ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ጥበብ የጎደላቸው ትናንሽ ውሳኔዎችን እንዳደረገ ልብ በል።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ በስተ ግራ፦ አንድ ወጣት ወንድም ሻይ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ሁለት ወንዶች ፍቅራቸውን ሲገላለጹ ይመለከታል። በስተ ቀኝ፦ አንዲት እህት ሁለት ሰዎች ሲያጨሱ ትመለከታለች።