ማጨስ እና ክርስቲያናዊ አመለካከት
ትንባሆም ሆነ ማጨስ በጥንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ የማይታወቁ ነገሮች በመሆናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳልተጠቀሱ ግልጽ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የትንባሆ ተክል ይበቅል የነበረው በደቡብ አሜሪካ፣ በሜክሲኮና በዌስት ኢንዲስ ብቻ ስለነበረ ነው። እስከ 16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ ወደ ሌሎች አገሮች አልተዛመተም ነበር።
ታዲያ እንዲህ ሲባል መጽሐፍ ቅዱስ ማጨስን የሚመለከት ምንም ነገር አይናገርም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ተፈጻሚነት ያላቸውና ስለምንኖርበት ምግባር መመሪያ የሚሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በግልጽ ያስቀምጣል። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
የአምላክና የሰው ፍቅር
አንድ ክርስቲያን ኢየሱስ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ፣ ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ” ሲል በተናገረው መሠረታዊ ሥርዓት መመራት ይኖርበታል።—ሉቃስ 10:27
አንድ ሰው አለዕድሜው እንዲታመምና እንዲሞት በሚያደርገው ልማድ በመጠመድ ሆን ብሎ በተፈጥሮ ችሎታዎቹ ላይ ጉዳት እያደረሰ አምላክን በሙሉ ልቡ፣ ነፍሱ፣ አእምሮውና ኃይሉ ሊወድ ይችላልን? እንደ ኒኮቲን ያለ ሱስ አስያዥ ዕፅ ወደ ሳንባው ስቦ እያስገባ አምላክ ለሰጠው የሕይወት ስጦታ አድናቆት ሊያሳይ ይችላልን? አምላክ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣል።” (ሥራ 17:24, 25) ታዲያ ይህን አምላክ የሰጠንን እስትንፋስ ማቆሸሽ ይገባናልን? በእርግጥም በአምላክ አመለካከት ሲታይ “ክፉ፣ ወራዳና ከጥሩ ሥነ ምግባር የራቀ ልማድ ነው።”—ዘ አሜሪካን ሄሪቴጅ ኦቭ ዘ ኢንግሊሽ ላንጉዊጅ
አንድ አጫሽ ሰው ከትንፋሹና ከጭሱ በሚወጣው መጥፎ ሽታ ልብሶችንና በአካባቢው ያለውን አየር እየበከለ ሰዎችን እወዳለሁ ሊል ይችላልን? ለአጫሹ በጣም ቅርብ የሆኑት ባልንጀሮቹ፣ ማለትም የትዳር ጓደኛውና ልጆቹስ? ቀስ በቀስ ተሠቃይቶ አለ ዕድሜው እንዲሞት በሚያደርገው አኗኗር መቀጠሉ ለእነርሱ ፍቅር እንዳለው ያሳያልን? ሌሎች ሰዎችስ ከአጫሹ አፍ የሚወጣውን መርዛም ጭስ ለመተንፈስ እንዲገደዱ ማድረግ ክርስቲያናዊ አሳቢነት ነውን? በስፔይን አገር የሚገኘው የብሌንስ አትክልት ሥፍራ ትንባሆን መርዛም ተክሎች በሚገኙበት ሥፍራ መመደቡ ተገቢ ነው።
አንድ አጫሽ ሰው ለራሱ ያለው ፍቅርስ? አንድ ሰው ለአካላዊ፣ ለአእምሮአዊና ለመንፈሳዊ ጤንነቱ እንክብካቤ በማድረግ ራሱን ቢወድ ተገቢ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና” ብሏል። ቀስ በቀስ ጤንነት በሚያመነምን ልማድ መጠመድ ራስን መውደድ ነውን?—ኤፌሶን 5:28, 29
ይሖዋ አምላክ ‘ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደሚመጣ’ ተስፋ ሰጥቷል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ዓለም ምንም ዓይነት ብክለት የሌለበት ንጹሕ ዓለም ይሆናል። በዚያ ጊዜ ማጨስ አይፈቀድም፣ የሚፈለግም ነገር አይሆንም። ታዲያ አሁን የምናጨስበት ምክንያት ምንድን ነው? በእርግጥም የሚከተለው የጳውሎስ ምክር ምክንያታዊ ነው። “እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፣ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) ኒኮቲን ቃል በቃል ሥጋን ያረክሳል። ማጨስ አንድ ክርስቲያን “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት” አድርጎ ራሱን ለአምላክ እንዳያቀርብና በትክክለኛ የማሰብ ችሎታው ቅዱስ አገልግሎት እንዳያቀርብ ያደርገዋል። (ሮሜ 12:1) የማሰብ ችሎታ ማጨስ ጎጂና ክርስቲያናዊ ሥርዓቶችን የሚቃወም እንደሆነ ያስገነዝበናል። አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ማጨስ እንድናቆም የሚገፋፋን ሌላ መሠረታዊ ምክንያትም አለ።
ለምን አቆሙ?
በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ማጨስ አቁመዋል። በእርግጥም ማቆም ይቻላል። ግን እንዴት ይቻላል? የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? ማጨስን ለማቆም የሚገፋፋ ጠንካራ ምክንያት። የብዙዎቹ ምክንያት ጤና፣ ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ያላቸው ፍላጎትና ለቤተሰባቸው ያላቸው ፍቅር ነው። የሌሎቹ ምክንያት ደግሞ ሃይማኖታዊ፣ ማለትም አምላክን ለማስደሰት ያላቸው ፍላጎት ነው።
ታዲያ በሁለተኛው ርዕስ ላይ የጠቀስናቸው ሬይ፣ ቢል፣ አሚ እና ሃርሊ ትንባሆ ማጨስ እንዲያቆሙ ያደረጋቸው ምክንያት ምንድን ነው?
ባለ ረዥም ፀጉርና ጺማም የነበረው አርቲስቱ ቢል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጠና። ከዚያ በኋላ ምን ሆነ? “አምላክን በንጹሕ አካልና አእምሮ ለማገልገል እንደምፈልግ ወሰንኩ። በአንድ ጊዜ ማጨስ አቆምኩ። ቀስ በቀስ አላቆምኩም። ጥር 1 ቀን 1975 ለመጨረሻ ጊዜ ሲጋራ ከሳብኩ በኋላ ሙሉውን ፓኮ ወረወርኩ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጤንነቴ ተሻሽሏል። አሁንም ቀለል ያለ የኤምፊዚማ በሽታ አለብኝ። ይሁን እንጂ ማጨስ ከተውኩ ወዲህ ቀለሞችን የመለየት ችሎታዬ እንኳን ተሻሽሏል።”
የቀዶ ጥገና ነርስ የሆነችው አሚ እንዲህ በማለት ታብራራለች። “በልብ ቀዶ ጥገናዎች በረዳትነት እሠራ ስለነበረ ብዙ ዓይነት ሳንባዎች፣ ጤናማና ጥሩ የተፈጥሮ ቀለም ያላቸውን እንዲሁም የጠቆሩትንና የተመረዙትን ሳንባዎች አይቻለሁ። ቁንዶ በርበሬ የተነሰነሰባቸው የሚመስሉትን በጣም የታመሙ ሳንባዎች ብመለከትም ማጨሴን አላቆምኩም ነበር። ‘አንቺ ገና ልጅ ነሽ፣ እንዲህ ያለ ነገር በአንቺ ላይ ሊደርስ አይችልም’ እያልኩ ራሴን ሳታልል ቆየሁ።”
“በ1982 ግን ሕይወቴን ማስተካከል እንደሚያስፈልገኝ ተሰምቶኝ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። በአንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤት ውስጥ የምኖር ብሆንም ቀስ ብዬ ወደ ጣሪያው እወጣና ተደብቄ አጨስ ነበር። ስለዚህ ራሴን ማሸነፍ ነበረብኝ። ደጋግሜና አምርሬ ጸለይኩ። ቁርጥ ውሳኔ ካደረግኩ በኋላ ግን ቀላል ሆነልኝ። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት በጣም ፈትነውኝ ነበር። ለማሸነፍ ቁልፍ የሆነልኝ አዘውትሬ መጸለዬ ነበር።”
የባሕር ኃይል አብራሪ የነበረው ሃርሊ ከኒኮቲን ሱስ ለመላቀቅ በጣም አስቸጋሪ ሆኖበት ነበር። “ቀስ በቀስ እየቀነስኩ ማጨስ ለማቆም ሞክሬ ነበር፣ ግን አልሆነልኝም። የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ለመጠመቅ በወሰንኩ ጊዜ ግን በአንድ ጊዜ አቆምኩ። ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት ተሠቃየሁ። ከፍተኛ ውጥረትና ጭንቀት ነበረብኝ። ሲጋራ ለማጨስ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። በዚህ ጊዜ አንድ የይሖዋ ምሥክር ጥሩ ምክር ሰጠኝ። ‘ይሖዋ እንዲረዳህ መጸለይ የሚገባህ በእጅህ ሲጋራ ለመያዝ በምትፈልግበት ጊዜ ነው’ አለኝ። ምክሩ በጣም ጠቅሞኛል። ሌላው ልቤን የነካው ሐሳብ ‘ኢየሱስ በአፉ ሲጋራ ይይዛል ብዬ ለማሰብ እችላለሁን?’ የሚለው ነው። በፍጹም የማይታሰብ ነገር ነው። አንድ አጫሽ እንዲያቆም የሚገፋፋው ጠንካራ ምክንያት ሊኖረው እንደሚያስፈልግ ተገንዝቤአለሁ። ለእናቴ ‘እማዬ፣ የምጎዳው እኮ ራሴን ብቻ ነው’ እል ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በብዙ መንገዶች እርስዋንም እየጎዳኋት ነበር።”
የባሕር ኃይል የበታች መኮንን የነበረው ሬይም ማጨስ ማቆም ቀላል ሆኖ አላገኘውም። “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከመገናኘቴ በፊት ለመተው የሞከርኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ግን አልሆነልኝም። ብዙ ሲጋራ ከሚያጨሱ ሰዎች ጋር እገናኝ ስለነበረ የሲጋራ ግብዣቸውን እምቢ ለማለት ያስቸግረኝ ነበር። እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ካወቅኩ በኋላ ግን ልክ እንደ ክርስቶስ ይሖዋን ለማገልገል ፈልግኩ። በዚህም ምክንያት በአንድ ቀን ማጨስ አቆምኩ። ለሁለት ሳምንታት በጣም መጥፎ ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። መላ ሰውነቴ ኒኮቲን አምጣ እያለ ይጮህ ነበር። ነገር ግን አቋሜ በአስደናቂ ሁኔታ ተለውጦ ነበር። ወዲያው ከፍተኛ ኃይል አገኘሁ። ስለ ራሴ ጥሩ ግምት ተሰማኝ። ራሴን በራሴ መቆጣጠር ችዬአለሁ።”
ይህን ያህል ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባ ልማድ ነውን?
ማንኛውም ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ማንኛውንም ጉዳት የሚያስከትል ልማድ መተው እንደሚኖርበት ያምናል። ማጨስ ግን ጉዳት የሚያስከትል ልማድ ብቻ አይደለም። ቀሳፊና ገዳይ ልማድ ነው። መርዝ ነው። በትንባሆ የተካበተ ከፍተኛ ሀብት የወረሱት ፓትሪክ ሬይኖልድስ ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ንዑስ ኮሚቴ በሰጡት የምሥክርነት ቃል “የሲጋራ ማስታወቂያ መርዝ የሆነ ምርት እንዲሸጥ ማግባባት እንደሆነና ማንኛውም ዓይነት የሲጋራ ማስታወቂያ እንዲከለከል ማድረግ ትክክል፣ ጥሩና ሥነ ምግባራዊ እንደሆነ አምናለሁ” ብለዋል።
አምላክን ለማስደሰት የሚመኙ ክርስቲያኖች የትንባሆ ማስታወቂያዎችን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ዓይነት የትንባሆ ውጤት ማስወገዳቸው ትክክል፣ ጥሩና ትክክለኛ ሥነ ምግባር መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ሲጋራ (“ጉዳት የሌለውም” ሆነ ጉዳት የሚያስከትል)፣ ሲጋር፣ በፒፓ የሚጨስ ትንባሆና ሱረት ሁሉም የኒኮትን ምንጭ ከሆነው ከመርዘኛው የትንባሆ ተክል የሚገኙ ናቸው። ‘ብዙ ነገር አሳልፋችሁ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችሁን’ ለማረጋገጥም ሆነ ከሕይወታችሁ ደስታ ለማግኘትና ጥሩ ጣዕም ለመቅመስ ትንባሆ መውሰድ አያስፈልጋችሁም። የበሽታና የሞት ነጋዴዎች ሊነግሯችሁ የሚሞክሩት ምንም ይሁን ምን መሠልጠናችሁን የምታሳዩት ራሳችሁን በመመረዝ አይደለም!
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከትንባሆ ንግድ አፈንግጠው የወጡ ሰዎች
አር ጄ ሬይኖልድስ በ1875 በሰሜን ካሮላይና አንድ የሚታኘክ ትንባሆ የሚያመርት ኩባንያ አቋቋሙ። በ1913 ካሜል የተባለ የንግድ ምልክት የተሰጠውን የመጀመሪያ ሲጋራቸውን ማምረት ጀመሩ። ንግዳቸው ከዚህ ደረጃ ተነስቶ በዩናይትድ ስቴትስ በሲጋራ ሽያጭና በገቢ መጠን ከፊልፕ ሞሪስ ቀጥሎ ሁለተኛ እስከመሆን ደረጃ ደረሰ። በአሁኑ ጊዜ በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ፓትሪክ ሬይኖልድስ የዚህ ኩባንያ መሥራች የልጅ ልጅ ልጅ ናቸው። ለ15 ዓመታት ትንባሆ አጫሽ የነበሩት እኚህ ሰው በትንባሆ ዓለም ላይ ትልቅ ፈንጂ ጥለዋል።
በ1986 በመንግሥት ምክር ቤት ንዑስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ትንባሆን የሚቃወም የምሥክርነት ቃል ሰጥተዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምረው የትንባሆ አጠቃቀምን የሚቃወም ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ለቤተሰባቸው ከፍተኛ ብልጽግና ያስገኘውን ይህን ምርት እንዲጠሉ ያደረጋቸው ምክንያት ምን ነበር? ከባድ አጫሽ የነበሩት አባታቸው በኤምፊዚማ በሽታ ተይዘው እንዴት ተሠቃይተው እንደሞቱ በልጅነት ዕድሜያቸው ያዩትን ማስታወሳቸው ነበር። ፓትሪክ “ትዝ የሚለኝ አባቴ ሁልጊዜ ትንፋሹ የሚቆራረጥና ለመኖር የቀረውን አጭር ጊዜ የሚቆጥር ሰው እንደነበረ ነው” ብለዋል።
ፓትሪክ በሕይወታቸው አንድ ዓይነት በጎ ተግባር ለማከናወን ወሰኑ። “በሕይወቴ አንድ ዓይነት ለውጥ የሚያስገኝ ሥራ ለመሥራት እንደምችል ተገነዘብኩ።” “ነፍሰ ገዳይ መሆኑ የተረጋገጠለትን ምርት” በማስፋፋት መቀጠል “ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ግልጽ ነው” ብለዋል።
“ሲያጎርሰኝ የነበረው እጅ የትንባሆ ኢንዱስትሪ ቢሆንም ይኸው እጅ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል፣ ወደፊትም ሰዎች ሲጋራ ከሚያስከትለው አደጋ ካልተጠነቀቁ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ይገድላል።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ጥቅምት 25, 1986
ዴቪድ ገርሊዝ በዊንስተን ሲጋራ ማስታወቂያዎች ላይ ዊንስተን ሲጋራ አጫሽ ሆነው በመታየት ከፍተኛ ዝና ያተረፉ ሰው ናቸው። አሁን ግን በሲጋራ አስተዋዋቂነት መሥራታቸውን አቁመው የአሜሪካ ካንሰር ሶሳይቲ ቃል አቀባይ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። ይህን ለውጥ እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ምንድን ነው? ታኅሣሥ 29, 1988 ለአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዲህ ብለዋል:- ‘በቦስተን በሚገኝ ሆስፔታል በካንሰር ክፍል ውስጥ የተኛውን ወንድሜን ለመጠየቅ ሄጄ ነበር። በዚህ ጊዜ ሥራዬ ያስከተለውን ውጤት ፊት ለፊት ተመለከትኩ። ትንባሆ በማጨሳቸው ምክንያት ካንሰር ተይዘው የሚሠቃዩ ሰዎችን አየሁ። በትንባሆ ሰለባዎችና የትንባሆ ሰላባዎች ሰለባ በሆኑት አጫሽ ቤተሰቦች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማየት ቻልኩ። በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ፀጉራቸው በሙሉ አልቆ፣ በጉሮሮአቸውና በሆዳቸው ላይ የፕላስቲክ ቱቦ ተሰክቶ አየሁ። የወንጀለኛነት ስሜት ስለተሰማኝ ትንባሆ ማስተዋወቄን ለመተው ወሰንኩ።’
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በልብ ቀዶ ሕክምና በረዳትነት ስለ ሠራሁ ብዙ ዓይነት ሳንባ አይቻለሁ”