ትንባሆ እና ጤንነትህ—በሁለቱ መካከል ግንኙነት ሊኖር ይችላልን?
“ባለማጨስዎ እናመሰግናለን” የዘመናችን ማስታወቂያ።
“በማጨስዎ እናመሰግናለን” በአንድ የትንባሆ ኩባንያ መጽሔት ላይ አጸፋውን ለመመለስ የወጣ ማስታወቂያ።
ሁለት ወገኖች ጎራ ለይተው በብዕርና በኮምፒዩተር በመዋጋት ላይ ናቸው። የማስታወቂያ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ማስታወቂያዎች ያወጣሉ። ይህ ጦርነት የሚካሄደው በዓለም ገበያ ነው። ይህ በትንባሆ ምክንያት የሚደረገው ጦርነት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሆኗል። በየዓመቱ በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ ይሆናል። እርስዎ ትንባሆ አጫሽ ሆኑም አልሆኑ በዚህ ጦርነት መነካትዎ አይቀርም።
ይህ ጦርነት በሁለት ዋና ዋና ጎራዎች፣ ማለትም በኢኮኖሚና በጤና መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው። ማጨስን የሚቃወሙት ወገኖች ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ለጤንነት ነው። ለትንባሆ ንግድ ቱጃሮችና ከትንባሆ ኢንዱስትሪ ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ ለሚሠሩ ደግሞ የሚታያቸው በኢኮኖሚያቸው፣ በትርፋቸውና በሥራቸው ላይ የሚመጣው አደጋ ነው። በሁለቱም መካከል ከፍተኛ የስሜት መጋጋል ይታያል። በአንድ አውሮፕላን ማረፊያ አንድ ሲጋራ አጫሽ አጠገቡ የቆመውን ሰው ሲጋራ እንዲለኩስለት ጠየቀው። ሰውዬውም “አዝናለሁ አላጨስም” በማለት በቅንነት መለሰለት። አጫሹ ግን “ታጨሳለህ ወይ? ብዬ አልጠየቅኩህም!” በማለት በቁጣ መለ ሰለት።
የዚህ ሁሉ ውዝግብ ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው? ማጨስ ይህን ያህል ከባድ ጉዳት ያስከትላል? ማጨስዎን ማቆም ይኖርብዎታልን?
መንግሥት ስለ ጤንነት የሚሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች
በዩናይትድ ስቴትስ በትንባሆና በካንሰር ጉዳይ ላይ ክርክር ሲደረግ በርካታ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። የትንባሆ ኢንዱስትሪ በ1960ዎቹ ዓመታት በካንሰርና በትንባሆ መካከል ያለውን ትክክለኛ ግንኙነት ለማወቅና ካንሰር አምጪ ከሆኑት ቅመሞች ነጻ የሆነ ሲጋራ ለማዘጋጀት የሚያስችል ዘዴ ለማግኘት ለሚደረጉ ምርምሮች በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር መድቦ ነበር። ከምርምሩ የተገኘው አንድ ውጤት ምናልባት የትንባሆ ባለ ፋብሪካዎች ከጠበቁት ውጭ ሳይሆን አልቀረም።
በ1964 የዩናይትድ ስቴትስ ጤና ጥበቃ ኃላፊ ትንባሆ ማጨስ አደገኛ መሆኑን የሚያስጠነቅቀውን የመጀመሪያ ሪፖርት አወጡ። ከ1965 ወዲህ የዩናይትድ ስቴትስ የትንባሆ ፋብሪካዎች በፓኮዎቻቸው ላይ የማስጠንቀቂያ ጽሑፍ እንዲያወጡ ሕጋዊ ግዳጅ ተጣለባቸው። መጀመሪያ ላይ ማስታወቂያው “ማስጠንቀቂያ:- የጤና ጥበቃ ኃላፊው ሲጋራ ማጨስ ለጤናችሁ አደገኛ መሆኑን አረጋግጠዋል” የሚል በጣም ጎልቶ የማይታይ ጽሑፍ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በ1985 የትንባሆ ኩባንያዎች በማስታወቂያዎቻቸውና በምርቶቻቸው ላይ አራት መልእክቶችን እያቀያየሩ እንዲያወጡ ተገደዱ። እያንዳንዱ መልእክት የሚጀምረው “የጤና ጥበቃ ኃላፊው ማስጠንቀቂያ” በሚሉ ቃላት ነው። እየተቀያየሩ የሚገቡት አራት መልእክቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው:- “ሲጋራ ማጨስ የሳንባ ካንሰር፣ የልብ በሽታ፣ ኤምፊዚማ የተባለውን በሽታ ከማምጣቱም በላይ በእርግዝና ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል።” (በገጽ 4 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ይመልከቱ።) “ነፍሰ ጡር ሴቶች ትንባሆ ካጨሱ ፅንሱ ሊሞት፣ አለ ቀኑ ሊወለድና ክብደቱ በጣም አነስተኛ ሊሆን ይችላል።” “አሁኑኑ ማጨስ ቢያቆሙ በጤንነትዎ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በእጅጉ ይቀንሳሉ።” “የሲጋራ ጭስ ካርቦን ሞኖኦክሳይድa አለው።”
ከዩናይትድ ስቴትስ ሌላ አንዳንድ አገሮችም ሲጋራ ስለሚያስከትለው ጉዳት ማስጠንቀቂያ እንዲወጣ ያዛሉ። ኢንድያ ቱደይ የተባለው መጽሔት “በሕግ አስገዳጅነት የወጣ ማስጠንቀቂያ:- ሲጋራ ማጨስ በጤንነት ላይ ጉዳት ያስከትላል” የሚሉ ቃላት የሚገኙበት ማስታወቂያ ያወጣል። በካናዳ አነስ ባሉ ጽሑፎች “ማስጠንቀቂያ:- የካናዳ የጤንነትና በጎ አድራጎት መሥሪያ ቤት የምታጨሱት ሲጋራ መጠን በጨመረ መጠን በጤንነታችሁ ላይ የሚደርሰው ጉዳትም በዚያው መጠን ይጨምራል፣ ከማጨስ ተቆጠቡ ሲል ይመክራል” የሚል ማስታወቂያ ሲያወጣ ቆይቷል። ከግንቦት 31, 1988 ጀምሮ በካናዳ የትንባሆ ማስታወቂያ እንዳይወጣ ተከልክሏል። በብሪታንያ የሚወጡ የሲጋራ ማስታወቂያዎች የሚከተሉትን ቃላት መጨመር አለባቸው:- “መካከለኛ ታር [ወይም አነስተኛ ታር] የግርማዊነታቸው መንግሥት በሚሰጠው ትርጉም መሠረት አደገኛ ነው። መንግሥታዊ የጤና አጠባበቅ ማስጠንቀቂያ:- ሲጋራ በጤናችሁ ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።” በኢጣልያ አገር ከ1962 ጀምሮ የትንባሆ ማስታወቂያ ማውጣት በሕግ ተከልክሏል። (ይሁን እንጂ የኢጣልያውያን የትንባሆ ፍጆታ ባለፉት 20 ዓመታት በእጥፍ አድጓል!) ባለፉት ዓመታት ከተደረጉ ከ50, 000 የሚበልጡ ጥናቶች በተገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ይህን የሚያህሉ ብዙ ማስጠንቀቂያዎች ካሉ ትንባሆ ማጨስ ለጤንነት ጎጂ ነው ከሚለው መደምደሚያ ለማምለጥ አይቻልም!
ትንባሆ ማጨስ በመላው ዓለም የተስፋፋ ልማድ ቢሆንም በትንባሆ ምርቶች ላይ የማስጠንቀቂያ ጽሑፎች እንዲወጡ የሚያስገድዱት ሁሉም አገሮች አይደሉም። በአንድ አካባቢ ገበያው ቀዝቀዝ ሲል ትላልቆቹ የትንባሆ ኩባንያዎች ኃይለኛ በሆኑት ማስታወቂያዎቻቸው በመጠቀም በሌሎች አገሮች አዳዲስ ገበያዎችን ይከፍታሉ። የእርስዎስ አገር ኃይለኛ በሆኑ የትንባሆ ማስታወቂያዎች የሚጠቃ ነውን? ከውጭ አገሮች የሚመጡ ሲጋራዎች በጣም ቆንጆ መስለው እንዲታዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸውን? ይህን ያህል “ከፍተኛ ሽያጭ” የተገኘበት ምሥጢር ምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሽታ አልባ የሆነው ካርቦን ሞኖኦክሳይድ የተባለ አየር ከሲጋራ ጭስ ከ1 እስከ 5 በመቶ መጠን ሲኖረው በደም ውስጥ ከሚገኘው ሂሞግሎቢን የተባለ ኦክሲጅን ተሸካሚ ሞልኪውል ጋር ጠንካራ መሳሳብ አለው። በደም ውስጥ ሊዘዋወር የሚገባውን ኦክስጂን በጣም ይቀንሳል። ይህም የልብ በሽታ ለያዘው ሰው በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሲጋራ ማጨስና ነፍሰ ጡር ሴቶች
በቅርቡ ናውካ ኢ ዢዝን (ሳይንስና ሕይወት) የተባለው የሶቪየት መጽሔት በዶክተር ቪክቶር ካዝሚን የተጻፈ አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። ዶክተሩ በዚህ ጽሑፋቸው አንዲት እናት በእርግዝናዋ ጊዜ ትንባሆ ብታጨስ በእናቲቱና በሕፃኑ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ዘርዝረዋል። “ትንባሆ ማጨስ በባዮሎጂያዊ ባሕርዩ ልዩ በመሆኑ ምክንያት በመርዛማ ነገሮች በቀላሉ ሊጎዳ በሚችለው የሴት አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። ትንባሆ ማጨስ በጤና ላይ ከባድ አደጋ የሚያስከትሉ ቅመሞች ያሉት መሆኑ የተረጋገጠ ነገር ነው።”
የሚያጨሱ እናቶች ልጆቻቸውን ሊመርዙ እንደሚችሉ ገልጸዋል። “እንደነዚህ ባሉት ሴቶች አሚኒዮቲክ ፍሉዊድ የተባለ የሽል ውኃ ውስጥ ኒኮቲንና የኒኮቲን ውጤት የሆነው ኮቲኒን የተባሉ መርዞች እንደሚገኙ የላቦራቶሪ ምርመራዎች አረጋግጠዋል። በጣም አስደንጋጭ የሆነው ግን በኤሌክትሮን ማይክሮስኮፖች ሊረጋገጥ እንደተቻለው በእርግዝና ወቅት የሚያጨሱ እናቶች እትብት ቅርጽ የተበላሸ መሆኑ ነው። ሽሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከእናቱ ማኅጸን የሚያገኘው ደግሞ በእትብት በኩል ነው። . . .
“እናቲቱ በፀነሰች ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ትንባሆ ብታጨስ ከሁሉም በላይ የሚጎዳው የፅንሱ የማዕከላዊ ነርቭ አውታር ነው። . . . በአራተኛው ወይም በአምስተኛው የእርግዝና ሳምንት የልብና የደም ዝውውር አውታር ይዳብራል። በዚህ ጊዜ የሚመረዘው ደግሞ ይህ ክፍል ይሆናል።”
ዶክተር ካዝሚን የደረሱበት መደምደሚያ ምንድን ነው? “የትንባሆ ጭስ በእናቲቱ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በጽንሱ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ይበልጣል።” ታዲያ ይህን የሚያክል ኪሣራ ሊከፈልለት የሚገባ ልማድ ነውን? የዩናይትድ ስቴትስ ጤና ጥበቃ ኃላፊ የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ያስታውሱ:- “ማጨስ . . . በእርግዝና ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል።” ያልተጋነነ ማስጠንቀቂያ ነው።
[ምንጭ]
WHO/American Cancer Society
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማጨስ እና ኤምፊዚማ
ኤምፊዚማ የሳንባ ጡንቻዎችን የመለጠጥ ችሎታ ቀስ በቀስ ቀንሶ ሳንባችን የተቃጠለ አየር በበቂ መጠን ለማስወጣት እስከማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ የሚያደርግ በሽታ ነው። ዘ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኦቭ ፊዚሽያንስ ኤንድ ሰርጅንስ ኮምፕሊት ሆም መዲካል ጋይድ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “[በዩናይትድ ስቴትስ] የኤምፊዚማ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በአንድ ዓይነት ቡድን ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። በአብዛኛው ከ50 እስከ 70 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ ለበርካታ ዓመታት ከባድ አጫሾች ሆነው የቆዩ ወንዶች ናቸው። በቀደሙት ዓመታት የወንዶችን ያህል ብዙ ሴቶች በኤምፊዚማ በሽታ አይያዙም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ሴቶችም ከባድ አጫሾች እየሆኑ በመምጣታቸው ይህ ሁኔታ በመለወጥ ላይ ነው።”
ይኸው መጽሐፍ በመቀጠል:- “ኤምፊዚማ ለብዙ ዓመታት ተሰውሮና ሌላ በሽታ መስሎ ሳይታወቅ ሊቆይ ይችላል። ኤምፊዚማ የያዘው ሰው በየዓመቱ በክረምት ወራት ከባድ ሳልና ምናልባትም ብሮንካይትስ የታከለበት ከባድ ጉንፋን ደጋግሞ ሊይዘው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ሳሉ በቀላሉ የማይለቅና ሥር የሰደደ ይሆናል።” ሌሎች የኤምፊዚማ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
“ኤምፊዚማ ቀስ በቀስ ሥር እየሰደደ የሚሄድ በሽታ ነው። ጠዋትና ምሽት ላይ ቀላል የሆነ የመተንፈስ ችግር ሊያጋጥምና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን በሽተኛው የወትሮው ሥራውን እንዳይሠራ ሊከለክለው ይችላል። ጥቂት መንገድ መሄድ ትንፋሽ ያሳጣዋል፣ ደረጃ መውጣት አስቸጋሪ ይሆንበታል። ሳንባ ትንፋሽ ማስወጣት፣ ማስገባትና አየር መለወጥ እያቃተው ሲሄድ እያንዳንዱ ትንፋሽ ከባድ ጥረት የሚጠይቅ ሥራ ወደሚሆንበት ደረጃ ይደረሳል፤ በሽተኛውም የወትሮ ተግባሩን ለመፈጸም የማይችል አካለ ስንኩል ይሆናል።”
ይኸው የሕክምና መመሪያ መጽሐፍ ኤምፊዚማ ከባድ የልብና የደም ዝውውር ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አክሎ ይገልጻል። ታዲያ ማጨስ ይህን ያህል ኪሣራ ሊከፈልለት የሚገባ ልማድ ነውን? ኒኮቲን ለሚያስገኘው ቅጽበታዊ ደስታ ሲሉ ለምን ውድ የሆነውን የሕይወት ስጦታ በአጭሩ ይቀጫሉ?