አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማምጣት የሚደረገው ፍለጋ
“ልንሄድበት ወደምናልመው አዲስ ዓለም የሚመራን ምንም ካርታ የለም። ወዳለፉት ዘጠና የጦርነት፣ የጠብና የጥርጣሬ ዓመታት መለስ ብለን ስናስብ በፊታችን ያለውን የሰላም፣ የነፃነትና የብልጽግና መቶ ዓመትና ሺህ ዓመትም በጉጉት እንጠባበቅ።”
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ናቸው እነዚህን ቃላት ጥር 1, 1990 የተናገሩት። በተመሳሳይ መልእክትም የሶቪየት ፕሬዚዳንት ሚክሃይል ጐርባቼቨ “ዓለምን ከፍርሃትና ከአለመተማመን፣ አላስፈላጊ ከሆኑ የጦር መሣሪያዎች፣ ጊዜ ካለፈባቸው ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችና እምነቶች እንዲሁም በሕዝቦችና በመንግሥታት መካከል ከሚፈጠሩ ሰው ሠራሽ ልዩነቶች” ለመገላገል በ1990ዎቹ የትብብር ሐሳቦችን አቅርበው ነበር። ይህን የዘገበው የጥር 3, 1990 የጃፓኑ ሜይኒቺ ዴይሊ ኒውስ ነው።
በግልጽ እንደሚታየው ከፍተኛ ተስፋ ተፋፍሞ ነበር። አሁን አንድ ዓመት ቢያልፍም ሁኔታው ያው ነው። ጥር 29, 1991 ፕሬዚዳንት ቡሽ በተባበረው አገር መልእክታቸው ላይ የፋርሱን ባሕረሰላጤ ጦርነት በማስመልከት እንዲህ አሉ፦ “አደጋ ላይ የወደቀው አንድ ትንሽ አገር (ኩዌት) ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ትልቅ ሐሳብ አደጋ ላይ ወድቋል። ይህም ልዩ ልዩ አገሮች የሁሉም የሰው ልጆች ምኞት የሆነውን ሰላምንና ዋስትና ያለውን ሕይወት ማምጣትን የጋራ ዓላማ በማድረግ ወደ አንድ ቦታ መሰባሰብ አለባቸው የሚል ሐሳብ ነው።”
ፍለጋው ችግር አልባ አይደለም
ሰው አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማምጣት የሚያደርገውን ፍለጋ ብዙ ችግሮች ያሰናክሉበታል። የትጥቅ ፍልሚያዎች በመንገዱ ላይ ይጋረጡበታል። በወቅቱ በኢራቅና በኩዌት መካከል ይካሄድ የነበረውን ጦርነት በመጥቀስ የጥር 28, 1991 ታይም መጽሔት እንዲህ አለ፦ “ቦምቦች ሲወድቁና ሚሳይሎች ሲበርሩ አዲስ የዓለም ሥርዓት ይመጣል የሚለው ተስፋ ለተለመደው ብጥብጥ ቦታውን ለቀቀ።” መጽሔቱ በመጨመርም “ማንም ሰው ብዙ ሲለፈፍለት የነበረው አዲስ የዓለም ሥርዓት ጀምሯል ማለት ቀርቶ ቀርቧል ብሎ ማመን የለበትም” ብሏል።
ዓለም አቀፍ ትብብር ማስገኘት አልተቻለም፤ ይህ ደግሞ ሰው አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ያሰናክልበታል። ዓለምና እኔ በተባለው ጽሑፍ (ጥር 1991) ላይ በቀረበው ዘገባ መሠረት “ብቅ ማለት የጀመሩት የኃያላን መንግሥታትን የውጭ መመሪያዎችና እነዚህ መመሪያዎች አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማስፈን ባለው ተስፋ ላይ ያመጡትን ተጽእኖ” ምሁራን መርምረውታል። የጽሑፉ አዘጋጅ እንደሚከተለው በማለት ደመደሙ፦ “በጣም ጥሩ በሚባለው ጊዜ ላይ እንኳ ሰላምንና ጦርነትን የሚለያያቸው መሥመር በጣም ቀጭን መሆኑን ታሪክ ያመለክታል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ወደ አዲስ የዓለም ሥርዓት ለሚደረግ ስኬታማ ሽግግር ዓለም አቀፍ ትብብር በተለይም በዋና ዋናዎቹ የዓለም ኃያላን መካከል የሚደረገው ትብብር ወሳኝ ነው።”
የአካባቢ ችግሮችም ብዙዎቹ በዓይነ ሕሊናቸው ለሚያስቡት አዲስ የዓለም ሥርዓት እንቅፋት ነው። የዓለምን ሁኔታ የሚከታተል ኢንስቲትዩት በ1991 የዓለም ሁኔታ በሚል ርዕስ ያወጣው ዘገባ ላይ ሌስተር ብራውን እንዲህ አሉ፦ “አዲሱ ሥርዓት ምን እንደሚመስል ማንም በእርግጠኛነት መናገር አይችልም። ለተከታዩ ትውልድ ተስፋ የሚሰጥ ጊዜ ለማምጣት ከፈለግን ግን የፕላኔቷን አካባቢያዊ መበላሸት ለመቀልበስ የሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ለሚመጡት ብዙ አሥርተ ዓመታት ከፍ ብሎ የሚታይ የዓለም ጉዳዮች ክፍል ይሆናል።” የአየር መበከል “በመቶዎች በሚቆጠሩ ከተሞች ለጤንነት አስጊ የሆነ ደረጃ ላይ እንደደረሰና በብዙ አገሮች ደግሞ የሰብል አጥፊ ደረጃን በመያዝ ላይ እንዳለ” ዘገባው አስታውቋል። ጨምሮም “በፕላኔቷ ላይ የሚኖሩት ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ ሲሄድ የተክልና የእንስሳት ዘር እያነሰ በመሄድ ላይ ነው። የመኖሪያቸው መደምሰስና ብከላ የባዮሎጂያዊው ሕይወት ዓይነት ብዛት እየቀነሰው ነው። የሙቀት መጨመርና የኦዞን ንብርብር መሳሳትና መበሳትም ለጥፋት ተጨማሪ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ።”
እንግዲያው በግልጽ እንደሚታየው ሰው ለአዲስ የዓለም ሥርዓት የሚያደርገው ፍለጋ በብዙ ችግሮች የተከበበ ነው። ታዲያ ፍለጋው ይሳካለት ይሆንን? አዲስ ዓለም ቀርቧል ሊባል ይችላልን? ከሆነስ የሚመጣው እንዴት ነው?