የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 6/8 ገጽ 3-5
  • አዲስ ዓለም ይመጣ ይሆን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አዲስ ዓለም ይመጣ ይሆን?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አዲስ ነገር አልተነገረም
  • የሰው ልጆች ጥረት ውድቅ መሆን
  • ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ምክንያት አለን?
  • አምላክ ቃል የገባው አዲስ ዓለም
    ነቅተህ ጠብቅ!
  • አዲስ ዓለም በቅርቡ ይመጣል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማምጣት የሚደረገው ፍለጋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • አዲስ ፍጥረቶች ተወለዱ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 6/8 ገጽ 3-5

አዲስ ዓለም ይመጣ ይሆን?

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ ሚያዝያ 13 ቀን 1991 በሞንተጎሞሪ፣ አላባማ “የአዲስ ዓለም ሥርዓት ሊመጣ የሚችልበት መንገድ” በሚል ርዕስ ንግግር አድርገው ነበር። ንግግራቸውን ሲደመድሙ “አዲስ ዓለም ከፊታችን ነው . . .፤ ይህ ዓለም በጣም ድንቅ የሆነ የበርካታ ግኝቶች ዓለም ነው” ብለዋል።

ከሁለት ወራት በኋላ ዘ ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ በምሥራቅ አውሮፓ የነበረው የኮምኒስት አገዛዝ ከወደቀ ወዲህ “በሰላም፣ በፍትሕና በዲሞክራሲ ላይ የተመሠረተ የአዲስ ዓለም ሥርዓት በደጅ የቀረበ ይመስላል” ብሏል።

ስለ አዲስ ዓለም የተደረገው ይህ ልፈፋ እስከ 1993 ድረስ ቀጥሏል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በጥር ወር የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለመቀነስ ስለተደረገ ስምምነት ዘግቧል። ጋዜጣው እንዳለው “ይህ ስምምነት የፕሬዚዳንት ቡሽን ምርጥ ቃላት ብንጠቀም ‘አሜሪካንንና ሩሲያን የአዲስ ዓለም ተስፋ እውን በሚሆንበት ደፍ ላይ ያስቀምጣቸዋል።’”

ከሁለት ሳምንታት በኋላ አዲስ የተመረጡት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት፣ ቢል ክሊንተን ሥልጣናቸውን ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር “አሮጌው ሥርዓት ባከተመበት በዛሬው ቀን አዲሱ ዓለም ይበልጥ ነፃ ግን መረጋጋት የራቀው ሆኗል” ብለዋል። እንዲያውም “ይህ አዲስ ዓለም በሚልዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን ሕይወት አበልጽጓል” እስከ ማለት ደርሰዋል።

ከዚህ በፊት ከነበረው ዓለም የተለየና የተሻለ ስለሆነ አዲስ ዓለም ብዙ ተነግሯል። አንድ ቆጠራ እንዳመለከተው ጆርጅ ቡሽ በጣም ረዥም ባልሆነ ጊዜ ውስጥ ባደረጓቸው የአደባባይ ንግግሮች 42 ጊዜ ስለ “አዲስ ዓለም ሥርዓት” ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ነገር ሲነገር የመጀመሪያ ጊዜ ነውን? ከዚህ በፊት ተሰምቶ ያውቃልን?

አዲስ ነገር አልተነገረም

አንደኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ በግንቦት 1919 በአሜሪካ የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ፌዴራላዊ ጉባኤ በክሌቭላንድ ኦሃዮ ስብሰባ አድርጎ ‘አዲስና የተሻለ ዓለም ሊመጣ የተቃረበ መሆኑን’ አስታውቋል። አንድ ተናጋሪ የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥተው ነበር:- “የፉክክር ሕግጋት ለወዳጅነትና ለባልንጀርነት ሥርዓት ቦታቸውን የሚለቁበት አዲስ ዓለም ይሆናል። የመከፋፈል ሥርዓት በኅብረት ሥርዓት የሚተኩበት አዲስ ዓለም ይሆናል። . . . ከክፋት ጋር ከሚደረገው ጦርነት በቀር ማንኛውም ጥላቻና ጠብ ተወግዶ ወንድማማችነትና ወዳጅነት የሚነግሥበት አዲስ ዓለም ይሆናል።”

አብያተ ክርስቲያናት ይህ አዲስ ዓለም ይመጣል ብለው ሊያምኑ የቻሉት እንዴት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በገባልን በአምላክ ንጉሣዊ አገዛዝ አማካኝነት ነው? አይደለም። እንዲህ ያለውን አዲስ ዓለም ያመጣል ብለው ተስፋቸውን የጣሉት በፖለቲካዊ ድርጅት ላይ ነው። አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ “ዛሬ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ድርጅት የምንለው ይህ ድርጅት ለሁሉም ክርስቲያናዊ እምነቶቻችንና ጥረቶቻችን ተፈጻሚነት ምትክና አማራጭ ሊገኝለት የማይችል መሣሪያ ነው” ብለዋል። የዚያ ዘመን የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የመንግሥታት ቃል ኪዳን ድርጅትን “የአምላክ መንግሥት ምድራዊ የፖለቲካ መግለጫ” ብለው እስከማወደስ ደርሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በጀርመን የተነሣው አዶልፍ ሂትለር የተባለ ኃያል መሪ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ድርጅትን በመቃወም በ1930ዎቹ ሦስተኛውን ራይክ አቋቋመ። ይህ ራይክ የሺህ ዓመታት ዕድሜ እንደሚኖረውና መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሚፈጽም የሚናገርላቸውን ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጽም ተናግሯል። ሂትለር “በወጣቶች እየጀመርኩ ነው። በእነዚህ ወጣቶች አማካኝነት አዲስ ዓለም ለማምጣት እችላለሁ” ብሏል።

ሂትለር የናዚን ኃያልነት ለማሳየት በኑረምበርግ በጣም ግዙፍ የሆነ ስታዲዮም አሠርቶ ነበር። ወደ 300 ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ባለው መድረክ ላይ 144 ትላልቅ ምሰሶዎች አስቆመ። ምሰሶዎቹ 144 የሆኑት ለምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ከበጉ” ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስለሚገዙና ግዛታቸውም ለአንድ ሺህ ዓመት ስለሚቆይ 144,000 ሰዎች ይናገራል። (ራእይ 14:1፤ 20:4, 6) በኑረምበርግ ስታዲዮም ላይ የቆሙት ምሰሶዎች 144 እንዲሆኑ የተመረጠው እንዲሁ በአጋጣሚ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። የናዚ ባለሥልጣኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ቃላትና ተምሳሊቶች ይጠቀሙ እንደነበረ በሚገባ ይታወቃል።

ታዲያ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሚከናወኑ የሚናገራቸውን ተስፋዎች ለመፈጸም ያደረጉት ጥረት ምን ውጤት አስገኘ?

የሰው ልጆች ጥረት ውድቅ መሆን

የመንግሥታት ቃል ኪዳን ድርጅት ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ሊያመጣ እንዳልቻለ ታሪክ በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣል። ብሔራት በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ሲዋጡ ይህ ድርጅት ተንኮታኩቶ ወደመ። ሦስተኛውም ራይክ ቢሆን 12 ዓመት ብቻ ከቆየ በኋላ ፈራርሷል። መላውን የሰው ልጅ ሃፍረት ላይ የጣለ ውድቀት ነበር።

በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሰው ልጅ ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማምጣት ያደረጋቸው ጥረቶች በሙሉ አንዳቸውም ሳይሳኩለት ቀርተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ሄንሪ ኪሲንጀር “ከዚህ በፊት የተነሱት ሥልጣኔዎች በሙሉ ከውድቀት አልዳኑም” ካሉ በኋላ “ታሪክ ሳይሳኩ የቀሩ ጥረቶች፣ እውን ሊሆኑ ያልቻሉ ሕልሞች መዝገብ ነው” ብለዋል።

የዓለም መሪዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚለፍፉለት የአዲስ ዓለም ሥርዓትስ? በየጊዜው የሚፈነዱት የጎሣ ግጭቶች ይህን የአዲስ ዓለም ተስፋ የልጆች ጨዋታ አስመስለውታል። ለምሳሌ ያህል ዊልያም ፋፍ የተባሉት የአንድ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ መጋቢት 6, 1993 “አዲሱ ዓለም እውነትም መጥቷል። በእርግጥም ወረራ፣ ግፍና ዘር ማጥራት ተቀባይነት ያለው ዓለም አቀፍ ምግባር ሆኖ እውቅና ያገኘበት አዲስ ሥርዓት ነው” በማለት ተችተዋል።

ከኮምኒዝም ውድቀት ወዲህ የታዩት አሰቃቂ ግጭቶችና ጭፍጨፋዎች በጣም የሚዘገንኑ ናቸው። ጆርጅ ቡሽ እንኳን ሥልጣናቸውን ሊያስረክቡ ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው “አዲሱ ዓለምም ከጊዜ በኋላ የአሮጌውን ዓለም ያህል አደገኛና አስጊ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ምክንያት አለን?

ታዲያ ይህ ማለት ሁኔታው ምንም ተስፋ የለውም ማለት ነውን? የአዲስ ዓለም ተስፋ እውን የማይሆን ሕልም ነውን? የሰው ልጆች አዲስ ዓለም ለመፍጠር እንዳልቻሉ ግልጽ ነው። ፈጣሪያችን አዲስ ዓለም እንደሚፈጥር የተናገረው ተስፋስ? መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ [እንደ አምላክ ቃል] እንጠብቃለን” ይላል።—2 ጴጥሮስ 3:13

አምላክ ቃል የገባልን አዲስ ሰማይ በምድር ላይ የሚሰለጥን አዲስ አገዛዝ ነው። ይህ አዲስ አገዛዝ ኢየሱስ የሰው ልጆች እንዲጸልዩለት ያስተማረው ሰማያዊ መንግሥት፣ የአምላክ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ ሰማያዊ መንግሥት ኢየሱስ ክርስቶስንና 144,000 ተባባሪ ገዥዎችን የሚያቅፍ ይሆናል። አዲሱ ምድር ደግሞ አዲስ የሰዎች ኀብረተሰብ ነው። አዎን፣ እነዚህ ሰዎች የአምላክን አገዛዝ በታማኝነት እየደገፉ ክብራማ በሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ ይኖራሉ።

የአምላክ ንጉሣዊ መንግሥት ተስፋ የተገባልንን አዲስ ዓለም ያስተዳድራል። ስለዚህ ይህ አዲስ ዓለም የሰው ልጆች የፈጠሩት ዓለም አይሆንም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔድያ “የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆች በሚወስዱት እርምጃ ወይም ሰዎች በሚፈጥሩት ግዛት የሚገኝ አይደለም” በማለት ያረጋግጣል። “መንግሥቱ የሰው ልጆች የሚያስገኙት ክንውን ሌላው ቀርቶ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እንኳን የሚያመጡት ክንውን ሳይሆን መለኮታዊ እርምጃ ነው።”—ዘ ዞንደርቫን ፒክቶሪያል ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ዘ ባይብል

በአምላክ መንግሥት የሚተዳደረው አዲስ ዓለም መምጣቱ እንደማይቀር የተረጋገጠ ነው። ይህን ተስፋ የሰጠው ‘ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ስለሆነ’ ሙሉ ትምክህትህን ልትጥልበት ትችላለህ። (ቲቶ 1:2) የአምላክ አዲስ ዓለም ምን ዓይነት ዓለም እንደሚሆን እባክህ መርምር።

[ምንጭ]

NASA photo

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ