ሽማግሌዎች—ሌሎችን በየዋህነት መንፈስ አስተካክሉ
የእውነተኛ ክርስቲያን ልብ መልካም ፍሬን ከሚያፈራ መንፈሳዊ የአትክልት ሥፍራ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት በዚሁ መንፈሳዊ የአትክልት ቦታ መብቀላቸው አይቀርም። የማይበቅሉበት ምክንያትስ ሊኖር ይችላልን? እነዚህ ‘ፍሬዎች’ኮ ይሖዋ አምላክ ለውስን አገልጋዮቹ የሚሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ናቸው። (ገላትያ 5:22, 23 አዓት) ሆኖም የልቡ የአትክልት ሥፍራ ለሰማያዊ አባቱ የሚያስደስት ቦታ እንዲሆን የሚፈልግ እያንዳንዱ ክርስቲያን በተወረሰው የኃጢአት አረሞች ላይ በጣም ብርቱና የማያቋርጥ ውጊያ መዋጋት አለበት።—ሮሜ 5:5, 12
አልፎ አልፎ በአንድ አምላካዊ ሰው ፍጹም ያልሆነ ልብ ውስጥ አንድ ደስ የማይል ነገር ማደግ ይጀምራል። እርሱ ወይም እርሷ በጣም ጥሩ የመንፈሳዊነት ታሪክ የነበረው ወይም የነበራት ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ምናልባት ጤናማ ባልሆነ ቅርርብ ወይም ጥበብ በጎደለው ውሳኔ የተነሳ አንድ ችግር ይነሳል። ታዲያ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነቱን ሰው በመንፈሳዊ ሊረዱት የሚችሉት እንዴት ነው?
ሐዋርያዊ ምክር
ሽማግሌዎች አንድን የተሳሳተ ሰው ለመርዳት “ወንድሞች ሆይ፣ አንድ ሰው ሳይታወቀው የተሳሳተ እርምጃ ቢወስድ መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየዋህነት መንፈስ ልታስተካክሉት ሞክሩ፤ እናንተ ደግሞ እንዳትፈተኑ ራሳችሁን ጠብቁ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ማስታወስ ያስፈልጋቸዋል። (ገላትያ 6:1 አዓት) አንድ መሰል አማኝ “ሳይታወቀው የተሳሳተ እርምጃ ቢወስድ” ሽማግሌዎች በተቻለ ፍጥነት እርዳታ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው።
ጳውሎስ የተሳሳተ እርምጃ እንደሚወስድ የጠቀሰው “አንድ ሰው” በማለት ነው። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የተሠራበት አንትሮፖስ የተሰኘው የግሪክኛ ቃል ለወንድም ሆነ ለሴት ያገለግላል። ታዲያ አንድን ሰው “ማስተካከል” ማለት ምን ማለት ነው? ካታርቲዞ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ወደ ተገቢው መሥመር ማምጣት” ማለት ነው። ይኸው ቃል መረብ መጠገንን ለማመልከትም ተሠርቶበታል። (ማቴዎስ 4:21) የአንድን ሰው የተሰበረ እግር ወይም እጅ መጠገንን ለማመልከትም ይሠራበታል። አንድ ሐኪም ታካሚውን የማያስፈልግ ስቃይ እንዳያመጣበት ይህን ጥገና የሚያደርገው በጥንቃቄ ነው። በተመሳሳይም አንድን ወንድም ወይም እህት ወደ ተገቢው መንፈሳዊ መሥመር ለማምጣት ጥንቃቄ፣ ዘዴና ርህራኄ ያስፈልጋል።
ሽማግሌዎች አንድን ሰው ለማስተካከል በሚሞክሩበት ጊዜ የየዋህነት መንፈስ በማሳየት የራሳቸውን መንፈሳዊነት ያሳያሉ። የዋሁ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን በየዋህነት እንደሚይዛቸው የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 11:29) ሽማግሌዎችም ለአንድ የተሳሳተ እርምጃ የወሰደ የይሖዋ አገልጋይ ይህንን ባሕርይ ማሳየት ይኖርባቸዋል፤ ምክንያቱም እነርሱም ቢሆኑ ያላሰቡትን ኃጢአት ሊሠሩ የማይችሉ አይደሉም። ከዚህ ቀደም ባይደርስባቸውም እንኳን ወደፊት ሊደርስባቸው ይችላል።
እነዚህ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሰዎች ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የአምልኮ ጓደኛቸውን ‘ሸክም መሸከም’ ይኖርባቸዋል። በእርግጥም ሽማግሌዎች አንድ ወንድም ወይም እህት ሰይጣንን፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን፣ የሥጋ ድካምንና የኃጢአትን ጥቃት እንዲዋጉ መርዳት ምኞታቸው ነው። ይህም ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች “የክርስቶስን ሕግ የሚፈጽሙበት” አንዱ መንገድ መሆኑ ጥርጥር የለውም።—ገላትያ 6:2
እውነተኛ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ‘ማንም ሰው ከሌሎች የሚሻልበት ነገር ሳይኖረው ከሌሎች እበልጣለሁ ብሎ ራሱን ቢያታልል ሁኔታውን’ ስለሚገነዘቡ ትሑቶች ናቸው። (ገላትያ 6:3) ሽማግሌዎች ትክክልና ጠቃሚ የሆነውን ለማድረግ የቱንም ያህል ቢጥሩ ፍጹም፣ አፍቃሪና ርህሩኅ የሆነውን የአምላክን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አያህሉም። ይሁን እንጂ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሊተካከሉ አለመቻላቸው የተቻላቸውን ያህል ከማድረግ ወደ ኋላ እንዲሉ ምክንያት አይሆናቸውም።
በትምክህተኝነትና ከአንተ ይልቅ እኔ ቅዱስ ነኝ በሚል መንፈስ አንድን መሰል አማኝ ማውገዝ ስህተት እንደሆነ ሽማግሌዎች ያውቃሉ! ኢየሱስ ቢሆን ኖሮ እንዲህ እንደማያደርግ የተረጋገጠ ነው። እንዲያውም ሕይወቱንም እኮ አሳልፎ የሰጠው ለወዳጆቹ ብቻ ሳይሆን ለጠላቶቹም ጭምር ነው። ሽማግሌዎች ወንድሞችን ወይም እህቶችን ከችግር አውጥተው ወደ ሰማያዊ አባታቸውና የጽድቅ ደረጃዎቹ እንዲቀርቡ ለመርዳት በሚሞክሩበት ጊዜ ተመሳሳይ ፍቅር ለማሳየት ይሞክራሉ። ታዲያ ሽማግሌዎች መሰል አምላኪዎችን ለማስተካከል የሚረዷቸው አንዳንድ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
አንዳንድ ጠቃሚ እርምጃዎች
በየዋህነት እየተናገራችሁና እየሠራችሁ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ ተደገፉ። ኢየሱስ የዋህ ነበር። አመራር ለማግኘት ወደ ሰማያዊ አባቱ ከልቡ ይጸልይና ሁልጊዜም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ያደርግ ነበር። (ማቴዎስ 21:5፤ ዮሐንስ 8:29) ሽማግሌዎች አንድን የተሳሳተ እርምጃ የወሰደ ሰው ለማስተካከል በሚሞክሩበት ጊዜ ከዚህ ያነሰ ማድረግ የለባቸውም። አንድ ሽማግሌ የዋህ የበታች እረኛ በመሆን በንግግሩ ማስፈራራት ሳይሆን የሚያጽናናና የሚያንጽ ይሆናል። በውይይቱ ወቅት እርዳታ የሚያስፈልገው ክርስቲያን ሐሳቡን በሚገልጽበት ጊዜ በተቻለ መጠን የተዝናና መንፈስ እንዲኖረው የሚያደርግ ሁኔታን ለመፍጠር ይሞክራል። ለዚህም ሲባል ልባዊ የሆነ የመክፈቻ ጸሎት በጣም ጠቃሚ ይሆናል። በየዋህነት የተሰጠውን ምክር የሚቀበለው ሰው ምክር ሰጪው እንደ ኢየሱስ አምላክን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ እንደሚፈልግ ካወቀ ለምክሩ በቀላሉ ልቡን ይከፍታል። የመዝጊያው ጸሎትም ግለሰቡ ፍቅርና የዋህነት በተሞላበት መንገድ የተሰጠውን ምክር በሥራ ላይ የማዋሉን አስፈላጊነት ሊያስገነዝበው ይችላል።
ከጸሎት በኋላ ልባዊ ምስጋና አቅርብ። ምስጋናው የግለሰቡን ደግነት፣ እምነት የሚጣልበት መሆን፣ ወይም ትጋት የመሳሰሉትን መልካም ባሕርያት የሚመለከት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ለብዙ ዓመታት ይሖዋን በማገልገል ያሳለፈውን ወይም ያሳለፈችውን የታማኝነት አገልግሎት ታሪክ መጥቀስ ይቻል ይሆናል። በዚህ መንገድ ለሰውየው እንደምናስብለትና የክርስቶስን የመሰለ አቀባበል እንደምናደርግለት እናሳያለን። ኢየሱስ ለትያጥሮን ጉባኤ የላከውን መልእክት “ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ” በማለት በምስጋና ጀምሯል። (ራእይ 2:19) የጉባኤው አባላት እየሠሩ የነበሩትን መልካም ሥራ ኢየሱስ እንዳወቀላቸው እነዚህ ቃላት አረጋግጠውላቸዋል። ጉባኤው የ“ኤልዛቤል”ን ዓይነት የኃጢአት ግፊት ችላ በማለቱ የራሱ ጥፋቶች ቢኖሩትም በሌሎች ዘርፎች ግን ሥራውን በሚገባ እያከናወነ ነበር፤ ኢየሱስም እነዚያ ወንድሞችና እህቶች የቀናተኛነት ሥራቸው ግንዛቤ ሳያገኝ እንዳልቀረ እንዲያውቁ ፈልጎ ነበር። (ራእይ 2:20) ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ ተገቢ በሆነበት ቦታ ሁሉ ምስጋና መስጠት ይኖርባቸዋል።
አንድን ጥፋት ሁኔታዎቹ ከሚጠይቁት በላይ አክብዳችሁ አትመልከቱት። ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ ከብከላ መከላከልና ድርጅቱንም በንጽሕና መጠበቅ አለባቸው። ሆኖም ጠንከር ያለ ምክር የሚያስፈልጋቸው አንዳንድ የተሳሳቱ መንፈሳዊ እርምጃዎች በፍርድ ኮሚቴ መሰማት ሳያስፈልጋቸው አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች እንዳስፈላጊነቱ እንዲይዟቸው ሊተውላቸው ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ክርስቲያን የተሳሳተ እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርገው ሆን ተብሎ የተደረገ ክፋት ሳይሆን በሰብአዊ ድካም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሽማግሌዎች መንጋውን በርህራኄ መያዝና “ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል” የሚለውን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ያዕቆብ 2:13፤ ሥራ 20:28-30) እንግዲያውስ ሽማግሌዎች ነገሮችን ከማጋነን ይልቅ የተጸጸቱ የእምነት ጓደኞችን ርህሩኅና መሐሪ እንደሆነው አምላካችን እንደ ይሖዋ በየዋህነት አያያዝ መያዝ አለባቸው።—ኤፌሶን 4:32
ወደተሳሳተው እርምጃ ሊያመሩ የቻሉትን ሁኔታዎች ተረዱ። ሽማግሌዎች የእምነት ጓደኛቸው ልቡን በሚያፈስበት ጊዜ በጥንቃቄ ማዳመጥ ያስፈልጋቸዋል። ‘የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አምላክ ስለማይንቅ’ ሽማግሌዎችም ቢሆኑ መናቅ የለባቸውም። (መዝሙር 51:17) ምናልባት የችግሩ መንስኤ ከትዳር ጓደኛ የስሜት ድጋፍ ማጣት ሊሆን ይችላል። ከባድ የሆነና ለረዥም ጊዜ የቆየ የአእምሮ ጭንቀት የሰውየውን አንዳንድ ጠንካራ የስሜት ብርታት አዳክሞት ወይም ጥበብ ያለበት ውሳኔ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ አድርጎበት ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ “ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው” በማለት አጥብቆ ቢያሳስባቸውም “ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” በማለትም ስለመከረ አፍቃሪ ሽማግሌዎች ግለሰቡን የገጠሙትን እንዲህ ዓይነት ችግሮች ግምት ውስጥ ያስገባሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ሽማግሌዎች የአምላክን የጽድቅ ደረጃዎች ዝቅ ማድረግ የሌለባቸው ሲሆን አምላክም እንኳን እንደሚያደርገው ሊታለፉ የማይገባቸውን የችግሩ መንስኤዎች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል።—መዝሙር 103:10-14፤ 130:3
ክርስቲያን ጓደኛችሁ ስለራሱ ያለው ግምት እንዲወድቅ ከማድረግ ራቁ። ማንንም ወንድም ወይም እህት ክብራቸውን መንጠቅ፣ ወይም እርሱ ወይም እርሷ ዋጋ ቢስ መስሎ እንዲታየው ወይም እንዲታያት ለማድረግ ፈጽሞ አንፈልግም። በዚህ ፈንታ በሰውየው ክርስቲያናዊ ባሕርያትና ለአምላክ ስላለው ፍቅር እንደምንተማመን ማረጋገጥ ስህተቱን እንዲያስተካክል ሊያበረታታው ይችላል። በልግስና ረገድ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ስለነበራቸው ‘የአእምሮ ዝግጁነት’ እና ‘ቅንዓት’ በሌሎች ዘንድ እንደተመካባቸው በነገራቸው ጊዜ ተበረታትው ሳይሆን አይቀርም።—2 ቆሮንቶስ 9:1-3
በይሖዋ ላይ በመመካት ችግሩ ሊቃለል እንደሚችል አሳዩ። አዎን፣ በአምላክ ላይ መመካትና ቃሉን ምክር በሥራ ላይ ማዋል የሚፈለገውን መስተካከል ሊያመጣ እንደሚችል ግለሰቡ እንዲገባው ለመርዳት ከልብ ጣሩ። ለዚህም ሲባል ንግግራችሁ በቅዱሳን ጽሑፎችና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ግባችን ሁለት ነገር ነው፦ (1) እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው የይሖዋን አመለካከት እንዲገነዘብ ለመርዳትና (2) ሰውየው እነዚህን መለኮታዊ መመሪያዎች በመጠኑም ቢሆን ችላ ያላቸው ወይም ሳይከተላቸው የቀረ መሆኑን ለማሳየት።
ቅዱስ ጽሑፋዊውን ምክር በደግነት ከቀረቡ መሪ ጥያቄዎች ጋር አዋሕዳችሁ አቅርቡ። ይህ መንገድ ልብን ለመንካት በጣም ውጤታማ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ በነቢዩ በሚልክያስ በኩል ሕዝቡ ምን ያህል ከሕጉ ፈቀቅ እንዳሉ ለማስገንዘብ ሲል በጥያቄ ተጠቅሟል፦ “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን?” በማለት ጠየቀ። ጨምሮም “እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል” አላቸው። (ሚልክያስ 3:8) እስራኤላውያን የሙሴ ሕግ በሚጠይቀው መሠረት የሰብላቸውን አሥራት ሳይሰጡ መቅረታቸው ይሖዋን ከመስረቅ ጋር የሚተካከል ነበር። እስራኤላውያን ይህን ሁኔታ አስወግደው አምላክ አብዝቶ እንዲባርካቸው ለእውነተኛ አምልኮ የነበረባቸውን ግዴታ በእምነት መፈጸም አስፈልጎአቸው ነበር። ሽማግሌዎችም የማሰብ ችሎታን በሚቀሰቅሱና አሳቢነት በተሞላባቸው ጥያቄዎች አማካኝነት በዛሬው ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ በሰማያዊ አባታችን ላይ መመካትንና እርሱን መታዘዝን እንደሚጨምር አጥብቀው ሊገልጹ ይችላሉ። (ሚልክያስ 3:10) ይህን ሐሳብ የተሳሳተ እርምጃ ለወሰደው ወንድም ልብ ማስተላለፍ ‘ለእግሩ ቀና መንገድ’ እንዲያደርግ በመርዳት በኩል ብዙ ችግር ሊያቃልል ይችላል።—ዕብራውያን 12:13
ምክሩን የመቀበልን ጥቅም አጥብቃችሁ ግለጹ። ውጤታማ ምክር የተሳሳተ አካሄድ የመከተልን መዘዝ ማስጠንቀቅንና ነገሮችን ከማስተካከል የሚገኘውን ጥቅም ማሳሰብን ይጨምራል። ኢየሱስ በመንፈሳዊ ግዴለሽ ለነበረው የሎዶቅያ ጉባኤ ወቅታዊ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ከቀድሞ አካሄዳቸው ንስሐ ገብተው ቀናተኛ ደቀ መዛሙርት ከሆኑ ከእርሱ ጋር በሰማይ መግዛትን ጨምሮ ከፍ ያሉ መብቶችን እንደሚያገኙ አረጋግጦላቸዋል።—ራእይ 3:14-21
ምክሩ ተቀባይነት አግኝቶ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ያላችሁን ፍላጎት አሳዩ። አንድ ጥሩ ሐኪም የጠገነው አጥንት አሁንም በተገቢ ቦታው ተስተካክሎ ገብቶ መግጠሙን ለማየት በተደጋጋሚ እንደሚመረምረው ሁሉ ሽማግሌዎችም የሰጡት ቅዱስ ጽሑፋዊው ምክር በሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን ለማወቅ ይሞክራሉ። ራሳቸውን፦ ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልግ ይሆን? ምክሩ ምናልባት በሌላ መንገድ መደገም ይኖርበት ይሆን? እያሉ ሊጠይቁ ይችላሉ። ኢየሱስ በትሕትና አስፈላጊነት ላይ ደቀ መዛሙርቱን በተደጋጋሚ መምከር አስፈልጎታል። ብዙ ጊዜ በምክር፣ በምሳሌዎችና በተጨባጭ ማስረጃዎች አማካኝነት በትዕግሥት አስተሳሰባቸውን ለማስተካከል ይሞክር ነበር። (ማቴዎስ 20:20-28፤ ማርቆስ 9:33-37፤ ሉቃስ 22:24-27፤ ዮሐንስ 13:5-17) ከዚህ አንፃር ሽማግሌዎች አንድን ወንድም ወይም እህት ወደተሟላ መንፈሳዊ ጤንነት እንዲሻሻሉ ታስቦ የሚደረጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶች እንዲከታተሉ ዝግጅት በማድረግ የተሟላ መስተካከል እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ።
ለተደረገው ማንኛውም መሻሻል ምስጋና አቅርቡ። የተሳሳተ እርምጃ የወሰደው ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን በሥራ ላይ ለማዋል በእርግጥ እየጣረ ካለ ከልብ አመስግኑት። ይህም መጀመሪያ ላይ የተሰጠውን ምክር ያጠናክረውና ተጨማሪ መሻሻል እንዲያደርግ ሊያበረታታው ይችላል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ በብዙ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ምክር ለመስጠት ተገዶ ነበር። ወዲያው ቲቶ መጥቶ ለደብዳቤው በጣም ጥሩ ምላሽ እንደሰጡ ለሐዋርያው ጳውሎስ በነገረው ጊዜ እነሱን ለማመስገን ደብዳቤ ጻፈ። “አሁን ግን ደስ ብሎኛል” አለ ጳውሎስ፤ “የተደሰትሁበትም ምክንያት እናንተን ስላሳዘንሁአችሁ ሳይሆን በሐዘናችሁ ምክንያት ንስሐ ገብታችሁ በመለወጣችሁ ነው፤ እንግዲህ ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ” ነው።—2 ቆሮንቶስ 7:9 የ1980 ትርጉም
ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት
አዎን፣ ጳውሎስ ምክሩ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች እንደረዳቸው በሰማ ጊዜ ተደስቷል። በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌዎች አንድ የእምነት ጓደኛቸው ለፍቅራዊ እርዳታቸው ተስማሚ ምላሽ በመስጠቱ ምክንያት ከተሳሳተ እርምጃው ሲመለስ ታላቅ ደስታ ያገኛሉ። በእርግጥም አንድ የተጸጸተ ክርስቲያን በልቡ አምላካዊ ፍሬዎች በብዛት ያፈራ ዘንድ የኃጢአትን እሾህማ አረም ለመንቀል በመርዳት ሊደሰቱ ይችላሉ።
ሽማግሌዎች አንድ ዓይነት የተሳሳተ እርምጃ ወስዶ የነበረን ክርስቲያን ለማስተካከል ከተሳካላቸው እርሱ ወይም እርሷ በመንፈሳዊ ጨርሶ ሊያጠፋ ከሚችል አካሄድ ይመለስ ወይም ትመለስ ይሆናል። (ከያዕቆብ 5:19, 20 ጋር አወዳድር።) እርዳታ ተቀባዩ ለእንዲህ ዓይነቱ እርዳታ ለይሖዋ አምላክ አመስጋኝነቱን መግለጽ አለበት። ለሽማግሌዎችም ለፍቅራዊ እርዳታቸው፣ ለርህራኄአቸውና የሰውን ችግር በመረዳታቸው ልባዊ የአድናቆት ቃላት መናገር ተገቢ ነው። መንፈሳዊ ጤንነታቸው ሙሉ በሙሉ በሚመለስበት ጊዜ በጉዳዩ ውስጥ የገቡት ሁሉ በመንፈሳዊ የዋህነት አማካኝነት መስተካከሉ ሊመጣ በመቻሉ ሊደሰቱ ይችላሉ።